BBC HardTalk

BBC HardTalk


የኢትዮጵያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከቢቢሲ ሀርድቶክ ፕሮግራም ጋር ሰኞ ዕለት ቆይታ አድርገው በትግራይ ክልል ከተከሰተው ጦርነት ጋር በተያያዘ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ትግራይ ውስጥ ተጀምሮ ወደ ሌሎች ክልሎች ስለተስፋፋው ጦርነት፣ በትግራይ ስለተቋረጡት መሰረታዊ አገልግሎቶች፣ ሰለሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ ስለእርዳታ አቅርቦት እና ተያያዥ ጉዳዮች ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ከስቴፈን ሳከር ተወያይተዋል።

• ስለመሠረታዊ አገልግሎቶች

የተቋረጡትን መሠረታዊ አገልግሎቶች መልሶ ለማስጀመር አሁን ባለው አለመረጋጋት የመብራት ኃይል እና የኢትዮ-ቴሌኮም ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን ወደ ትግራይ ለመላክ አስቸጋሪ እንደሆነ አመልክተዋል።

ከወራት በፊት የፌደራል መንግሥት የትግራይ መዲና መቀለን መቆጣጠሩን ካስታወቀ በኋላ የመብራት፣ የስልክ እና የኢንተርኔት መስመር ለመቀጠል ወደ ክልሉ ያቀኑ ሠራተኞች በሥራ ላይ ሳሉ እንደተገደሉ ገልጸው፤ "አሁን ባለው አለመረጋጋት እነዚህ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን ወደ ትግራይ መላክ አይችሉም" ብለዋል።

የሰብዓዊ እርዳታ ሰጪዎች የባንክ፣ የመብራት፣ የስልክና ሌሎችም መሠረታዊ አገልግሎቶች መቋረጥ ከፍተኛ መሰናክል እንደሆነባቸው በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ሌሎችም ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድርጅቶች መሠረታዊ አገልግሎቶች መቋረጣቸው "በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ችግር ውስጥ ይከታል" ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የትግራይ አማጽያን "ትግራይ ከበባ ውስጥ ናት። ከበባው እስኪነሳም ትግሉን እንቀጥላለን" ማለታቸው አይዘነጋም። ቢቢሲም ይህንን ንግግር ጠቅሶ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለምን ከበባውን አያነሳም? የሚል ጥያቄ ሰንዝሯል።

ዶ/ር ጌዲዮን በበኩላቸው፤ የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም ያወጀው "ለሰላም እድል ለመስጠት እና ሰብዓዊ እርዳታ ያለ መሰናክል ወደ ትግራይ እንዲደርስ በማሰብ ነው። ህወሓት የተኩስ አቁሙን ቢቀበል ነገሮች ይቀየራሉ" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የፌደራል መንግሥት ትግራይን ከተቆጣጠ በኋላ "ክልሉን መልሶ ለማልማት ገንዘብ አውጥቷል። ህወሓት ግን ንጹሀን ዜጎችን በብዛት ወደ ጦርነት እየላከ ስለነበር ሰብዓዊ ዋጋውን ለመቀነስ በተናጠል ተኩስ አቁመን ከመቀለ ወጥተናል" ሲሉ የመንግሥትን አቋም አንጸባርቀዋል።

ጦርነቱ አሁን ላይ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ ቀጥሏል። የህወሓት አማጽያን በትግራይ ላይ የተጣለው ከበባ እንዲነሳ ጫና ለማሳደር እንደሚጥሩ ገልጸዋል።

የፌደራል መንግሥት እና የአማራ ክልልም እንዲሁ የትግራይ አማጽያንን ለመመከት የክተት አዋጅ ጠርተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአሜሪካ መንግሥት እንዲሁም ሌሎችም አገራት ሁሉም ወገኖች በአፋጣኝ የቱኩስ አቁም አድርገው ወደ ውይይት እና ድርድር እንዲመጡ መጠየቃቸውን ገፍተውበታል።

• የሰብዓዊ መብት ጥሰት ክሶች

ቢቢሲ ሀርድቶክ ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ጋር ባደረገው ቆይታ ካነሳቸው ነጥቦች መካከል የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የመብት ጥሰትን በተመለከተ ያወጧቸውን ሪፖርቶች ይመለከታል።

ቤልጄም የሚገኘው የጌንት ዩኒቨርስቲ ባደረገው ምርመራ አማካይነት ባለፉት ወራት በ232 አጋጣሚዎች የተገደሉ ያላቸውን 2562 ንጹሀን ዜጎች ስም ዝርዝር አውጥቷል። የዩኒቨርስቲው አጥኚዎች ግድያውን የገለጹት "ጭፍጨፋ" በማለት ነው።

በሌላ በኩል አምነስቲ የዓይን እማኞችን አጣቅሶ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት መሠረት በሴቶች ላይ መዋቅራዊ ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰ፣ በርካቶች እንደተደፈሩ፣ ለወሲብ ባርነት የተጋለጡ ሴቶች እንዳሉም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚህን ሪፖርቶች በተመለከተ ምን እርምጃ እንደወሰደ እና ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችን ተጠያቂ አድርጎ እንደሆነ ቢቢሲ ዶ/ር ጌዲዮንን ጠይቋል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ "መንግሥት ሪፖርቶቹን ቀላል አድርጎ አይወስዳቸውም" ብለው የሲቪል እና ወታደራዊም ምርመራዎች እንደተደረጉና እየተደረጉ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

እስካሁን ከ30 በላይ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከጾታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ በሕግ ተጠያቂ እንደተደረጉ ጠቅሰዋል። የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመሆን ምርመራውን እንደቀጠለም አያይዘው ጠቅሰዋል።

የሚታመኑ ሪፖርቶች በሚኖሩበት ጊዜ ተጠያቂነትን ለማረጋጋጥ እርምጃ እንደሚወስዱ ነገር ግን "ስሜትን ለመኮርኮር የሚወጡ የተጋነኑ እና ደካማ ድምዳሜ ያላችው ሪፖርቶች" እንዳሉ ነገር ግን ተጠቂዎችን በቀላሉ አንደማይለከቱ ተናግረዋል።

በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ተጠያቂ ከተደጉት መካከል የኤርትራ ወታደሮች ይገኙበታል። በኤርትራ ወታደሮች ላይ ሥልጣን የሌለው የኢትዮጵያ መንግሥት በምን መንገድ ፍትሕ ያሰፍናል? በሚልም ተጠይቀዋል።

ዶ/ር ጌዲዮን "ከእኛ ሥልጣን ውጪ ያሉትን ተጠያቂ ለማድረግ በጎረቤት አገሮች ጉዳይ ሥልጣን ካላቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር አብረን እንሠራለን። ምርመራችንን ስንጨርስ ለዓለም አቀፍ አካል አሳልፈን እንሰጣለን" ብለዋል።

• የትግራይ ተወላጆች እስር

ህወሓት በሕጋዊ መንገድ ሽብረተኛ ተብሎ በአገሪቱ ምክር ቤት መሰየሙን ያስታወሱት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ በመሆኑም ለዚህ ቡድን ቁሳቁስ በመስጠት አሊያም በመደገፍ የሚሳተፍ ማንኛውም ሰው ተጠያቂ መሆኑ እንደማይቀር ገልጸዋል።

ጨምረው "ህወሓት ከትግራይ ብሔር ጋር የተያያዘ ድርጅት ስለሆነ ሁሉም ሳይሆኑ፤ አብዛኞቹ ተባባሪዎቻቸው፣ ደጋፊዎቻቸውና በገንዘብ የሚረዷቸው ከአንድ ብሔር ናቸው" ብለዋል።

አንዳንዴ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህንን አውድ ላይረዳውና መንግሥት እየገጠመው ያለውን ተግዳሮት እንደማይገነዘቡት አመልክተው "በመሆኑም ይህንን ሊረዱት ይገባል" ሲሉ ጠቅሰዋል።

• ሰላማዊ መፍትሔ

መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ሲያውጅ ለሰላም ዕድል መስጠቱን አመልክተው "ህወሓት ግን የተኩስ አቁሙን በማክበር ፋንታ ግጭቱን ወደ አፋርና ወደ አማራ ክልሎች በማስፋት ጥቃት ፈፅሟል፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አፈናቅሏል። በመቶዎች የሚቆጠሩትን ገድሏል። በዚህ ሁኔታ ምን እንድናደርግ ይጠበቃል?!" ሲሉ ጠይቀዋል።

አክለውም "በተደጋጋሚ በሚፈጽመው ጥቃትና ጠብ አጫሪ ባህሪው በሽብርተኛ የተሰየመው ህወሓት የተኩስ አቁሙን እውን እንዳይሆን አድርጓል። በዚህ ሁኔታ ሕዝባችንን የመጠበቅ መብትና ኃላፊነት አለብን። እያደረግን ያለው ይህንን ነው።"

የሰብዓዊ እርዳታ ጉዳይ

ዓለም አቀፍ ሰብዓዊ እርዳታ ሰጪዎች በትግራይ በርካቶች ለረሃብ አደጋ እንደተጋለጡና አስፈላጊው የእርዳታ አቅርቦት እየደረሰ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

የፌደራል መንግሥት እርዳታ በአግባቡ እንዳይደርስ እያስተጓጎለ ነው ብለው የሚከሱ አካላት ያሉ ሲሆን፤ መንግሥት ደግሞ በምላሹ የህወሓት አማጽያንን ለችግሩ ተጠያቂ ያደርጋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለምን የእርዳታ ድርጅቶችን ያግዳል? ለምንስ እርዳታ የሚደርስበትን መንገድ ይዘጋል? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር ጌዲዮን "የተናጠል ተኩስ አቁም ስናደርግ በአፋር በኩል ሰብዓዊ እርዳታ መተላለፊያ አዘጋጅተናል። ከአዲስ አበባ መቀለ ሰብዓዊ በረራ እንዲደረግ ፈቅደናል። የህወሓት ትንኮሳ መቀጠል ግን ነገሮችን ውስብስን አድርጓል" ብለዋል።

መንግሥት የአገሪቱን ሕግና ደንብ ተከትለው ከሚሠሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የእርዳታ ድርጅቶች ጋር በጥምረት እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ እንደ ኤምኤስኤፍ እና ኖርዌጅያን ሬፍዩጂ ካውንስል ያሉት የእርዳታ ድርጅቶች በመርኅ መሠረት የሚንቀሳቀሱ ከሆነ ፍቃዳቸው እንደሚመለስላቸው አክለዋል።

(BBC AMHARIC)


Report Page