BBC AMAHRIC

BBC AMAHRIC


ዘንድሮ የኢትዮጵያ የ“ኬጂ” ተማሪዎች እና እንግሊዝኛ ተቆራርጠዋል። በእንግሊዝኛ ቃላት ወደተሰየሙት የግል ትምህርት ቤቶች የሚሄዱት ህጻናት እንደወትሮው ስማቸውን በእንግሊዘኛ መጻፍ አይለማመዱም።

የመዋዕለ ህጻናት ተማሪዎች “ኤ፣ ቢ፣ ሲ፣ ዲ…”ን በዜማ መቁጠር፣ “ኤ ፎር አፕል፣ ቢ ፎር ቦል…” እያሉ ቃላት መመሥረት አቁመዋል። ከዚህ ዓመት ጀምሮ “ስፖክን ኢንግሊሽ” እና “ኢንግሊሽ ሊትሬቸር” ከ“ኬጂ” ተማሪዎች የትምህርት ዓይነቶች ውስጥ ተሰርዘዋል።

እንደ ቀድሞው በአማርኛ ሂሳብ፤ በእንግሊዝኛ “ማትስ” እያሉ የቁጥሮችን አጠራር በሁለት ቋንቋ መሸምደድም ቀርቷል። የዘንድሮ የ“ኬጂ” ተማሪዎች ለአካባቢ ሳይንስ እና ለ“ጄኔራል ሳይንስ” ሁለት ደብተር አይዙም።j

በአራት ዓመታቸው “ነርሰሪ” የሚገቡት ህጻናት፣ በስድስት ዓመታቸው ከ“ዩ ኬጂ” ሲመረቁ የሚያውቁት ብቸኛ የፊደል ገበታ “ሀ፣ ለ፣ ሐ፣ መ…” የሚል ብቻ ይሆናል።

ልጆችን እንግሊዝኛ በማስተማር ተመራጭ የሆኑት የግል መዋለ ህጻናት ከዚህ ዓመት ጀምሮ ሁሉንም ትምህርት የሚሰጡት በአካባቢው የአፍ መፍቻ ቋንቋ ብቻ ነው። በአዲሱ የትምህርት ሚኒስቴር አሠራር መሠረት ተማሪዎች እንግሊዝኛ ቋንቋን እንደ አንድ ትምህርት መማር የሚጀምሩት አንደኛ ክፍል ሲደርሱ ነው።

“ጊብሰን አካዳሚ” ትምህርት ቤት ከአንድ ወር ገደማ በፊት የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት (ኬጂ) የመስጠት ፈቃዱ እንዲሰረዝበት ካደረጉ ምክንያቶች ውስጥ በቀዳሚነት የተጠቀሰው ይህ የእንግሊዝኛ ትምህርት ጉዳይ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት እና ሥልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለሥልጣን ለ“ጊብሰን” በጻፈው ደብዳቤ “ትምህርት ቤቱ ከከተማ አስተዳደሩ የማስተማሪያ ቋንቋ ውጪ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በትምህርት ዓይነት እየሰጠ” መሆኑን ከጥፋቶቹ አንዱ አድርጎ ጠቅሷል።

ቢቢሲ የተመለከተው በአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ የተዘጋጀ የጀማሪ እንዲሁም አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ “የኬጂ” ተማሪዎች የመማሪያ መጽሐፍ (መለማመጃ ደብተር) በውስጡ የያዘው የአማርኛ የፊደል ገበታን ብቻ ነው።

በአዲሱ ካሪኩለም መሠረት ህጻናቱ የሚማሩበት መጽሐፍ ይህ ብቻ ሲሆን፣ በውስጡ የአማርኛ፣ የሂሳብ እንዲሁም አካባቢ ትምህርቶች ተቀላቅለው ቀርበውበታል።

ህጻናት ልጆቻቸውን ቦርሳ አስነግበው እና ምሳ ዕቃ አስይዘው ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት የሚልኩት ወላጆች ግን የእንግሊዝኛ ትምህርትን ያስቀረው አዲስ ሥርዓተ ትምህርት የተዋጠላቸው አይመስልም።

የስድስት ዓመት ልጅ ያላት የአዲስ አበባ ነዋሪ ማኅሌት ታምሩ ከእነዚህ ወላጆች መካከል ነች። “አብዛኛው ቦታ የሚነገረው ዓለም አቀፍ ቋንቋ እንግሊዝኛ ነው። እንግሊዝኛ መጻፍ፣ ማውራት መቻል፤ ተናጋሪ መሆን አለባቸው። የትምህርት ሥርዓታችን እዚህ ላይ ተጽእኖ ባያደርግ” ስትል ቅሬታዋን ትገልጻለች።

ልጇን በምታስተምርበት መዋለ ህጻናት ውስጥ የወላጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆነችው ማኅሌት እንደምትናገረው ይህ ቅሬታ ከሌሎች ወላጆችም ይነሳል። ወላጆች ለልጆቻቸው ይሰጥ የነበረው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ለምን እንደቀረ ጥያቄዎችን እያነሱ መሆኑን ለቢቢሲ ገልጻለች።

የትምህርት ዓይነቶቹን የተካው “ጭብጥ” ምንድነው?

በመዋዕለ ህጻናት ትምህርት ላይ ከወላጆች በኩል ቅሬታ ያስነሳው የትምህርት ለውጥን ያመጣው አዲሱ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት (ካሪኩለም) ነው። ከዚህ ዓመት ጀምሮ መተግበር የጀመረው ሥርዓተ ትምህርቱ ህጻናት የሚማሩትን ትምህርት በተለያዩ የትምህርት ዓይነቶች (ሰብጀክት) አይከፋፍልም።

የኬጂ ተማሪዎች እንደ ቀድሞው ሂሳብ፣ አማርኛ ወይም አካባቢ ሳይንስ የሚባሉ የትምህርት ዓይነቶች አይኖሯቸውም። በትምህርት አይነቶች ፋንታ ህጻናቱ የሚማሩት “ጭብጦችን” ነው።

ለምሳሌ፤ የመጀመሪያ ዓመት የመዋለ ህጻናት ተማሪዎች ስድስት ጭብጦችን ይማራሉ። ከእነዚህ ጭብጦች ውስጥ “ስለ እኔ”፣ “ቤቴ እና ቤተሰቦቼ” እንዲሁም “ትምህርት ቤቴ እና አካባቢዬ” የሚሉት ይገኙበታል። የኬጂ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከሚማሯቸው ጭብጦች ውስጥ ደግሞ “ዋሊያ”፣ “ህዋ”፣ “ተክሎች” እና “መጓጓዣ” ተጠቃሽ ናቸው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቀዳማይ ልጅነት እንክብካቤ እና ትምህርት ማዕከል (Center for Early Childhood Care and Education) መምህር እና ከካሪኩለሙ አዘጋጆች ውስጥ አንዱ የሆኑት ዶ/ር ታደሰ ጃለታ እንደሚያስረዱት “ጭብጦች” በራሳቸው የትምህርት ዓይነት አይደሉም።

ዶ/ር ታደሰ፤ “ጭብጥ (context) ማለት ህጻናት በአካባቢያቸው የሚያውቁትን ነገር ተጠቅሞ፤ ማወቅ አለባቸው የሚባሉትን ነገሮች ውስጡ በማዋሃድ የሚቀርብበት ነው። በራሱ ትምህርት ሳይሆን ለትምህርቱ [የሚያገለግል] አውድ ማለት ነው” ሲሉ ያብራራሉ።

“ሰብጀክት የሚባል ነገር የለም፤ ሁሉም ነገር የተዋሃደ ነው” ሲሉም ያክላሉ። እንደ ዶ/ር ታደሰ ገለጻ አንድ ጭብጥ ህጻናቱ እንዲማሩ የሚፈለጓቸውን ቋንቋ፣ ቁጥር እና ሌሎች ጉዳዮች በውስጥ ይይዛል።

“ስለ እኔ” የሚባለውን ጭብጥ በምሳሌነት የሚያነሱት ዶ/ር ታደሰ፤ “በዚህ ውስጥ ተማሪው ስለራሱ፣ ስለ አካላቱ ያወራል። ይህንን ሲያወራ የማኅበራዊ ተግባቦት ክኅሎት፣ የአዕምሮ እድገት፣ በራስ መተማመን፣ ኢሞሽናል ቋንቋ ያዳብራል” ይላሉ።

ታዲያ ህጻናት እነዚህን ጭብጦች የሚማሩት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ብቻ ነው።

ይህም ብቻ አይደለም። በአዲሱ ካሪኩለም መሠረት ህጻናቱ እንደ ቀድሞው አብዛኛውን ጊዜያቸውን ክፍል ውስጥ ቁጭ ብለው ከሰሌዳ እና ከደብተር ጋር እንዲፋጠጡ አይፈለግም።

ዘንድሮ የኬጂ ተማሪዎች የሚማሩባቸው ዋነኛ መንገዶች ጨዋታ፣ መዝሙር እና ተረት ናቸው። የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ለካሪኩለሙ ትግበራ ያዘጋጀው የመምህራን መምሪያ “ህጻናት የሚማሩት በጨዋታ ነው” ይላል። ጨዋታ “አማራጭ የሌለውና በሁለም ትምህርቶች ውስጥ በማዋሃድ ለማስተማር የሚያገለግል አይነተኛ ስልት ነው” ሲል የጨዋታን አይተኬነት ለመምህራን ያስረዳል።

ህጻናት በአንድ ቀን የትምህርት ቤት ቆይታቸው ውስጥ የክፍል ውስጥ እና የውጭ የጨዋታ ጊዜ እንዲሁም የተረት እና የመዝሙር ጊዜ ሊኖራቸው እንደሚገባ የመምህራን መምሪያው ሰፍሯል። የመጻፊያ እና የማንበቢያ ጊዜ በአንጻሩ “መጠነኛ” መሆን እንዳለበት ያስገነዝባል።

“ከአቅማቸው በታች እንዲማሩ እያደረገ ነው”

በአዲሱ ሥርዓት ምክንያት ከአሁን በኋላ አብዛኛውን የትምህርት ቤት ጊዜያቸውን በጨዋታ የሚሳልፉት የኬጂ ተማሪዎች፤ የሚማሩት የትምህርት ይዘትም ቀንሷል።

በአዲስ አበባ አድዋ ድልድይ አካባቢ የሚገኘው “ብሩህ ኪንደርጋርተን” ባለቤት የሆኑት ወ/ሮ ገነት መንገሻ፤ “እኛ ከዚህ በፊት የምናስተምራቸው እና አሁን የሚማሩት የእውቀቱ ደረጃ በጣም አንሷል” ሲሉ አዲሱ ካሪኩለም ላይ ያላቸውን ግምገማ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ወ/ሮ ገነት፤ ላለፉት 15 ዓመታት በቆየው መዋዕለ ህጻናታቸው ውስጥ የሚገቡ ተማሪዎች ሲመረቁ አማርኛ እና እንግሊዝኛ ማንበብ እንዲሁም በሁለቱም ቋንቋዎች “ትናንሽ” ዓረፍተ ነገሮችን መመሥረት ይችሉ እንደነበር ያስታውሳሉ።

“ቁጥርን በተመለከተ አማርኛውንም እንግሊዝኛውንም እስከ መቶ ድረስ ያውቃሉ። መደመር መቀነስን ያውቃሉ” ሲሉም ህጻናቱ በአማርኛ እና እንግሊዝኛ ሂሳብ ይማሩ እንደነበር ያነሳሉ።

በዚህ ዓመት ግን ይህ ቀርቷል። የትምህርት ቤት ባለቤቷ፤ “አዲሱ ካሪኩለም ሁሉም ትምህርት [እንዲሰጥ የሚያዘው] በአማርኛ ነው፤ እንግሊዝኛ አይማሩም። በእንግሊዝኛ ምንም ነገር የለም። ሁሉም ትምህርት በአማርኛ ነው” ስለ አዲሱ አሰራር ይናገራሉ።

በአዲሱ ካሪኩለም መሠረት ህጻናቱ በሦስት ዓመት ቆይታቸው ቁጥር የሚማሩት እስከ 20 ድረስ እንደሆነ በመምህራን መምሪያ መጽሀፉ ላይ ሰፍሯል። የቀድሞው የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት መጽሐፍ “ከባድ እና ብዙ ይዘቶችን” የያዘ እንደነበር የሚያስረዳው የመምህራን መምሪያው፤ ማሻሻያ የተደረገበት አንዱ ምክንያት ይህ መሆኑንም ያስረዳል።

የኬጂ ትምህርት ይዘት ግን መቀነስ ወላጆችን አላስደሰተም። ከእነዚህ ወላጆች ውስጥ የሆነችው ወ/ሮ ማኅሌት፤ በአሁኑ ጊዜ ህጻናት ለቴክኖሎጂ ካላቸው ቅርበት አንጻር ትምህርት ቤት ሳይገቡ ብዙ እንደሚያውቁ ትናገራለች።

“ካሪኩለሙ መቀነሱ ልጆቹ ፍላጎት እንዳይኖራቸው አድርጓል። የእኔ ልጅ ኬጂ 3 ነች። ‘ይሄንን አምና ተምሬዋለሁ’ ብላኛለች” ስትል ትምህርቱ ከልጆቹ አቅም በታች ነው የሚል እምነት እንዳላት ገልጻለች።

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች ይህንን አይነት ቅሬታ ከወላጆች እየተቀበሉ መሆኑን የአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች አሠሪዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ አበራ ጣሰው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ አበራ፤ “በአጥኚዎች ዘንድ [ያለው አመለካከት] ሌላ ሊሆን ይችላል። በእኛ፣ መሬት ላይ ባለነው ሰዎች እምነት ግን ልጆቹ እየተጎዱ ነው። ከአቅማቸው በታች እንዲማሩ እየተደረጉ ነው የሚል አቋም ነው ያለን። ወላጆችም በጣም እየጮኹብን ነው። ወላጆች ብዙ ስም ነው የሚሰጡት። ‘አውቃችሁ ነው፣ አስተማሪ ለመቀነስ ብላችሁ ነው’ ይሉናል” ሲሉ ትምህርት ቤቶቹ እያስተናገዱ ያሉትን ቅሬታ ይጠቅሳሉ።

የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ካሪኩለሙ በዝግጅት ላይ በነበረበት ወቅት የትምህርት ይዘቱ መቀነሱን እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት መውጣቱን በተመለከተ ማኅበሩ ተቃውሞ አስተያየት መስጠቱንም አቶ አበራ ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ፤ “በአገሪቱ ካለው ተጨባጭ የኑሮ ሁኔታ አንጻር ሲታይ የግል ትምህርት ቤቶች ብዙ ነው የምናስከፍለው። [ወላጆች] ለኬጂ 3500፣ 4000 [ብር] ይከፍላሉ። ይሄንን እየከፈሉ ያሉት ልጆቻቸው ተጫውተው እንዲመጡ ነው ወይ?” ሲሉም ይጠይቃሉ።

የ“ብሩህ ኪንደርጋርተን” ባለቤት ወ/ሮ ገነት፤ አዲሱን የኬጂ ሥርዓተ ትምህርት በተመለከተ ከወላጆች ጋር ስብሰባ አድርገው እንደነበር ይጠቅሳሉ። “አብዛኛው ወላጅ ‘እንደዚህ ከሆነ ለምን እመጣለሁ ለምን ከፍዬ አስተምራለሁ። እዚህ ከምታስተምሩት በላይ ልጄ ቤት ውስጥ ብዙ ያውቃል’ ይላል” ሲሉ ወላጆች በስብሰባው ላይ የተናገሩትን አስታውሰዋል።

የዚህ ለውጥ ምክንያቱ ምንድን ነው?

የቅድመ አንደኛ ሥርዓተ ትምህርትን ካዘጋጁ ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ታደሰ፤ “ቤተሰብ ልጁ እንግሊዝኛ ከቻለ፣ ፊደል ከቆጠረ ወይም መደመር ከቻለ ተምሯል፣ አድጓል ብሎ ያስባል። በህጻናት ደረጃ ትምህርት እርሱ አይደለም” ይላሉ። እንደ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህሩ ገለጻ የህጻናት ትምህርት ከመደበኛው ትምህርት የተለየ መሆን አለበት።

ህጻናት ኬጂ የሚማሩበት አምስት እና ስድስት ዓመት የሰው አዕምሮ የሚያድግበት መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር ታደሰ፤ የህጻናት ትምህርት ማተኮር ያለበት የአዕምሮ እድገት ላይ መሆኑን ያስረዳሉ።

“ለህጻናት ዋናው የመማሪያ እና የእድገት ምንጭ ጨዋታ ነው። ህጻናት ትምህርት ቤት ሄደው መጫወት አለባቸው። እንደ [መደበኛ] ትምህርት ቤት ቁጭ ብለው መማር የለባቸውም” ሲሉም ያክላሉ። የእንግሊዘኛ ትምህርት ከትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ወጥቶ ሁሉም ትምህርት በህጻናቱ የአፍ መፍቻ ቋንቋ እንዲሰጥ የተደረገውም በዚህ ምክንያት መሆኑን ያነሳሉ።

“[ህጻናት] በደንብ መጫወት የሚችሉት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ነው። ህጻናቱ ሜዳ ላይ ሲወጡ፣ ተረት ተረት ሲጫወቱ፣ መዝሙር ሲዘምሩ፣ እነዚህን ጨዋታዎች ሲጫወቱ በእንግሊዝኛ ሊጫወቱ አይችሉም” ሲሉ ውሳኔው የመጣበትን መነሻ ሀሳብ ይጠቅሳሉ።

“ይሄ የኢትዮጵያ መንግሥት ያመጣው አይደለም። ዓለም አቀፍ ስምምነት ነው” ሲሉም የህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማራቸውን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚደገፍ ጉዳይ መሆኑን በማንሳት ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

በዚህ ደረጃ የሚኖር የህጻናት የትምህርት ቤት ቆይታ “አዕምሮ አድጎ ኋላ ለሚመጣው ትምህርት ዝግጁ መሆን” እንዳለበት የሚናገሩት ዶ/ር ታደሰ፤ ይህ የሚለካው “ህጻናቱ ምን ያህል ሶሻሊ አክቲቭ ናቸው? ምን ያህል ይጫወታሉ? ምን ያህል ከሰው ጋር መግባባት ይችላሉ? ምን ያህል ራሳቸውን መግለጽ ይችላሉ?” የሚሉት ከግምት ውስጥ ገብተው መሆኑን ያስረዳሉ።

“ቤተሰብ የህጻናትን ትምህርት የሚለካው እንግሊዝኛ በማውራት ነው። ኤ፣ቢ፣ሲ፣ዲ፤ ስፖክን እንግሊሽ በደንብ ካወቁ ተምረዋል ብሎ ያስባል። ቁጥሮችን መደመር ከቻሉ ‘በደንብ አውቀዋል’ ብሎ ነው የሚያስበው። ከዚህ አንጻር ስለሚሰፍሩት ነው እንጂ ቤተሰብ የአዕምሯቸውን እድገት መለካት አይችልም። የአዕምሮ እድገትን ማወቅ የሚችለው ዕለታዊ ምዘና የሚሠራው መምህር ነው” ሲሉም ያክላሉ።

ቢቢሲ የቅድመ አንደኛ ሥርዓተ ትምህርት ትግበራን አስመልክቶ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ማብራሪያ በስልክ ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረገው ጥረት ምላሽ አላገኘም።

የ“ብሩህ ኪንደርጋርተን” ባለቤቷ ወ/ሮ ገነት፤ ወላጆች በሥርዓተ ትምህርቱ የተዋወቀውን አዲስ አሠራር እንዲቀበሉት ይህ ዓመት ተጠናቆ በልጆቻቸው ላይ ለውጥ ማየት አለባቸው የሚል እምነት እንዳላቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“[ለወላጆች] እንደዚህ ነው ብለን አስረድተናል፤ ግን በመናገር ብቻ አሆንም። ወላጆች የሚያምኑት በተግባር ሆኖ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የሆነ ለውጥ ሲያዩ ነው፤ ጊዜ ይፈልጋል። አዲስ የተቀበልናቸው ልጆችን በሥርዓተ ትምህርቱ አስተምረን ሦስተኛ ዓመት ላይ ሲመረቁ ነው ውጤቱ የሚታየው” ሲሉ ሀሳባቸውን ያብራራሉ።

“[አዲሱ] የኬጂ ካሪኩለም ከአቅማቸው በታች ነው። [ህጻናቱ] ብዙ ማወቅ መሥራት ሲገባቸው እንዳይሠሩ ነው የተደረገው” የሚሉት የግል ትምህርት ቤቶች አሠሪዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት አቶ አበራ በበኩላቸው “ጥቅም እና ጉዳቱን መልሰው ያዩታል ብለን እናስባለን” ሲሉ ሥርዓተ ትምህርቱ ይሻሻል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

(ቢቢሲ)

Report Page