BBC

BBC

ቲክቫህ ኢትዮጵያ

የለማ ጉያ ድንቅ የቆዳ ላይ ሥዕሎች

ለማ ጉያ ይህን ሥዕል ከሠሩት 42 ዓመታት ተቆጥረዋል። የአፍሪካ መሪዎችን በድመቶቹ መስለው የሀገራቸውን ሃብት በሙስና ሲመዘብሩ፣ በአልጋው ሥር የሚታዩት የአህጉሪቷ ጠላት አይጦች ደግሞ የአፍሪካን ሃብት ሲቀራመቱ ይታያሉ፤ እየፈሰሰ ያለው ወተትም ያለጥቅም ለዘመናት የሚፈሱት የአፍሪካ ወንዞች ምሳሌ ነው።

'እናት ኦሮምያ' የሚል ስያሜ ያለው ይህ ስዕል በክልሉ ያለውን የሀይማኖቶች መቻቻል፣ ኢሬቻ፣ የተፈጥሮ ሃብትና የሕዝቡን አኗኗር ያሳያል። ከፍ ብላ ከፊት የምትታየው ሴትም 'እግዚአብሔር ሆይ አንተ አሳድገን' ብሎ ከመለመን ጋር ይመሳሰላል። ያሰረችው ነጭ ሻሽም ነፃነትን የሚያሳይ ሲሆን መቀነቷ ላይ ያለው ቀይ ጥለት ደግሞ ኦሮምያ ያሳለፈችው ውጣ ውረድ ተምሳሌት ነው።

ለማ ጉያ በዚህኛው ሥራቸው ኦዳ የኦሮሞ ህዝቦች መለያ መሆኑንና ያለውን ክብር ያሳያሉ። ከዚህም በተጨማሪ ባህላዊ የኢሬቻ ጨዋታዎችና ከክብረ በዓሉ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሌሎች ባህላዊ ተግባራትን ያሳያል። ከፊት ለከፊት ጎልተው የሚታዩት አዛውንት ሴት 'አደ ነፍሶ' የሚባሉ የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪ የነበሩና በ120 ዓመታቸው ያረፉ ባልቴት ናቸው።

ይህኛው ስዕል ደግሞ አርቲስቱ የተወለዱበትና ያደጉበትን የገጠር አካባቢ የሚያሳይ መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህም በተጨማሪ የግብርና ሥራ የገጠሩና የከተማው ማኅበረሰብ የኑሮ መሰረት መሆኑንም ያሳያል ይላሉ።

ይህን የቢሾፍቱን ሀይቅ ስዕል የሳሉት የአየር ኃይል አባል በነበሩበት ወቅት የሃይቁን ዙሪያ ከአየር ላይ ሙሉ ለሙሉ ለመመልከት በመቻላቸው ነው። በሥዕሉ ላይ የሚታየውን በሃይቁ ዙሪያ ያለውን መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥን በዘመናዊ የፎቶ ካሜራ ሙሉውን ለማንሳት በጣም አስቸጋሪ እንደሚሆን ይናገራሉ።

(ሁሉም ፎቶግራፎች በቢቢሲ የተነሱ ሲሆኑ ዘገባው ከሦስት አመት በፊት የቀረበ  ነው )

Report Page