BBC

BBC


ለረዥም ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በግል እና በፓርቲ ደረጃ ተሳታፊ የነበሩት አቶ በቀለ ገርባ ከፓርቲያቸው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) በመልቀቅ በአሜሪካ ጥገኝነት መጠየቃቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።

አቶ በቀለ ለቢቢሲ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ “በሰላማዊ መንገድ ለመታገልም ሆነ በግል በነጻነት መኖር” አሳሳቢ በመሆኑ በሄዱበት በአሜሪካ ለመኖር ጥገኝነት መጠየቃቸውን ገልጸዋል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል የሆኑት አቶ በቀለ፣ በውጭ አገር ሆነው ሥልጣኑን ይዘው መቀጠለቸው ጠቃሚ ስላልሆነ እራሳቸውን ከፓርቲው ለማግለል መወሰናቸውንም ተናግረዋል።

አቶ በቀለ ገርባ ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ ተፈጥሮ የነበረውን ሁከት ተከትሎ በቁጥጥር ሥር ውለው ለ18 ወራት በእስር ላይ ቆይተው ከተለቀቁ በኋላ ወደ አሜሪካ ተጉዘዋል።

አቶ በቀለ ከእስር ከወጡ በኋላ ወደ አሜሪካ ሲጓዙ ዓላማቸው የእርሳቸውን ከእስር መለቀቅ ሲጠይቅ ለነበረው የዳያስፖራ ማኅብረሰብ ምስጋና ለማቅረብ እንጂ በዚያው የመቅረት ዕቅድ እንዳልነበራቸው ጨምረው ተናግረዋል።

“ወደዚህ አገር ከመጣሁ አንድ ዓመት ከሦስት ወር ሆኖኛል። መጀመሪያ ስንመጣ የነበረኝ ዕቅድ በውጭ ከሚኖረው ሕዝባችን ጋር ተገናኝተን፣ አንደኛ ከእስር እንድንለቀቅ ላደረጉት ትግል ለማመስገን ሁለተኛ ደግሞ ወደፊት ምን ማድረግ አለብን የሚለው ላይ ለመወያየት ነበር” ብለዋል።

አቶ በቀለ አሜሪካ በቆዩባቸው 15 ወራት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በመቀየሩ “ወደዚያ አገር መመለሱ አስፈላጊ መስሎ አልታየኝም” ብለዋል።

ወደ አገር እንዳይመለሱ ያደረገቸው በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ሁኔታን ሲያስረዱም “በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ ከመጣበት ወዲህ በተለይ ደግሞ ያለፈው ዓመት እጅግ አደገኛ ነው” ብለዋል።

“ከአንድ ዓመት ወዲህ ያለው በጣም የሚያሳዝን ነው። ሰዎች ከእስር ቤት እየተወሰዱ ይገደላሉ፣ የፈለገ አካል ሰው ይዞ ያስራል፣ የሰዎች አድራሻ ይጠፋል፣ ሰው ከመሬቱ ይፈናቀላል፣ ኦሮሞ ድንበሩ ተሰብሮ ቤቱ ይቃጠላል፣ በሕይወት እያለ በቁሙ በእሳት ይቃጠላል፣ እራሱ በቆፈረው ጉድጓድ ውስጥ ተገድሎ እንዲቀበር የሚደረግም አለ።”

የፖለቲካ ፓርቲዎች ጽሕፈት ቤት ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚባልበት መልኩ ተዘግተዋል የሚሉት አቶ በቀለ፤ በዚህ ምክንያት በአገሪቱ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማድረግ አይቻልም ብለዋል።

“በዚህ ሁኔታ ውስጥ በሕይወት እንኳ መቆየት አሳሳቢ የሆነ ደረጃ ላይ ተደርሷል። ሁለተኛ ደግሞ ወደዚያ አገር በመመለስ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ስለማይቻል እና የማመጣው ውጤት ስለማይኖር እዚሁ ለመቆየት ወስኛለሁ።”

አቶ በቀለ ከዚህ ቀደም ወደ አገር ቤት በተመለሱበት ጊዜ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደነበራቸው የመምህርነት ሥራ መመለስ እንዳልቻሉ ሲያስረዱ፣ “ከእስር ቤት እንደወጣሁ ዩኒቨርሲቲው እድሜህ 60 ዓመት ሞልቷል በማለት ጡረታ አስወጥቶኛል” ብለዋል።

“ከእስር ቤት እንደወጣሁ ደብዳቤ ላኩልኝ። 60 ዓመት ስለሞላህ ጡረታ ወጥተሃል አሉኝ። ጡረታዬን ለማስከበር ያደረኩት ጥረትም ሳይሳካ ቀርቷል። ዕድሜ ልኬን ስለፋበት የነበረውን ሳላገኝ ቀርቻለሁ። በዚህም ባዶ እጄን በሰው አገር ለመቅረት ተገድጃለሁ።”

አቶ በቀለ ገርባ ወደ ኢትዮጵያ ቢመለሱ ለሕይወታቸው አስጊ መሆኑን አሁን ባሉበት አገር ማሳወቃቸውን እና የጥገኝነት ማመልከቻቸውን ማስገባታቸውንም ገልጸዋል።

ተስፋ መቁረጥ

አቶ በቀለ ገርባ ከዚህ ቀደም ከአንድም ሁለት ጊዜ ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ሰላማዊ የፖለቲካ ተሳትፎን ተስፋ በማድረግ መሆኑን አስታውሰው፣ “አሁን ግን ምንም አይነት ተስፋ የለም” ብለዋል።

እውቁ ፖለቲከኛ እአአ 2015 ላይ ለጉብኝት ወደ አሜሪካ በሄዱበት ወቅት ‘ስኮላርስ አት ሪስክ’ የተባለ ተቋም ወደ አገራቸው ቢመሰሉ ሕይወታቸው አደጋ ላይ ሊወድቅ ለሚችሉ ባለሙያዎች በአሜሪካ በቋሚነት የሚኖሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ፍቃድ ቢሰጣቸውም የቀረበላቸውን ጥያቄ ውድቅ አድርገው ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን ተናግረዋል።

አቶ በቀለ ከዚህ ጉብኝታቸው መልስ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ለእስር መዳረጋቸውን በመግለጽ፣ እአአ 2018 ላይም ከእስር ወጥተው ወደ አሜሪካ በተጓዙበት ወቅት የተጠቀሰው ድርጅት በአሜሪካ በቋሚነት የሚኖሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥያቄ ቢያቀርብላቸውም በፓርቲያቸው በኩል የጀመሩትን ትግል ለማስቀጠል ዳግም ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸውን ይገልጻሉ።

አቶ በቀለ የቀረበላቸውን ዳግም ጥያቄ ውድቅ አድርገው ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ ለእስር ተዳርገዋል። ከእስር በኋላም ባለፈው ዓመት ወደ አሜሪካ ተጉዘው ሁለት ጊዜ የመኖሪያ ፈቃድ ለማመቻቸት ጥያቄ አቀርቦላቸው የነበረውን ድርጅት ጠይቀው ሦስተኛ ዕድል አልሰጠም የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው ግልጸዋል።

“ማሸነፍ የምንችል ከሆነ ሕዝብ ሊጠቅም የሚችል ፖሊሲ ቀርጸን አገር የማስተዳደር ተስፋ አለን ብለን ነበር ለሁለተኛ ጊዜ የቀረበልኝን ዕድል ትቼ ወደ አገር ቤት የተመለስኩት። አሁን ግን በጭራሽ ምንም አይነት ተስፋ የለም” ብለዋል።

“እንደ ኦፌኮ አመራር የመጨረሻ ቃሌ ነው”

አቶ በቀለ ረዥም የፖለቲካ ሕይወት ካሳለፉባት የትውልድ አገራቸው ተሰደው በውጭ አገር በስደት ለመኖር የወሰኑት ከእስር ለመውጣት ከመንግሥት ጋር የደረሱት አንዳች የስምምነት አካል ይሆን ወይ? ተብለው የቀረበላቸውን ጥያቄ አስተባብለዋል።

አቶ በቀለ ከበርካታ ፖለቲከኞች ጋር ለእስር ከተዳረጉ በኋላ “ከእስር ለመውጣት የቀረበልኝ አንዳችም ቅድመ ሁኔታ የለም ብለዋል፤ ከአገር እስከወጣ ድረስ የደረሰብኝ አንዳችም ማስጠንቀቂያ የለም” በማለት የተለቀቁበት ሁኔታ ገልጸዋል።

ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ በፖለቲካ ቀጥተኛ ተሳትፎ ውስጥ የቆዩት አቶ በቀለ ገርባ “ይህ ቃለ መጠይቅ እንደ የኦሮሞ ፌደራሊስ ኮንግረስ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር ሆኜ የምሰጠው ቃሌ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ በቀለ የፖለቲካ ፓርቲ አስፈላጊ የሚሆነው ሕዝብን የሚጠቅም ፖሊሲ ሲያወጣ ዕድሉን ካገኘ ደግሞ መንግሥት መመሥረት፣ ካልሆነም ለመንግሥት ምክረ ሃሳቦችን መለገስ ነው የሚሉት አቶ በቀለ “አሁን ባለው ሁኔታ ግን እነዚህ አማራጮች ሙሉ በሙሉ ዝግ ናቸው” ይላሉ።

“ስለዚህ እኔ አሁን ላይ የፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ መቆየቱ አያስፈልገኝም። ለፖለቲካዊ ሥልጣን እየተንቀሳቀስኩም አይደለም። በፖለቲካ ፓርቲ ስም በዚያ አገር ሕዝብ እያንቀሳቀስኩ አይደለም። ለዚያ ሕዝብ እየሠራሁ አይደለም። ይህን ለማድረግ ዕድሉ የለኝም።”

በዚህም የተነሳ አቶ በቀለ አሁን ካሉበት ሁኔታ አንጻር በኦፌኮ ፓርቲ ውስጥ ባላቸው ተሳትፎ መቀጠሉ አስፈላጊ ሆኖ ስላልታያቸው ፓርቲውን መልቀቃቸውን ተናግረዋል።

“ይህ ቃለ መጠይቅ ምናልባት እንደ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ተቀዳሚ ሊቀ-መንበር ሆኜ የምሰጠው ቃሌ ነው። ከአሁን በኋላ እንደማንኛውም ለኦሮሞ ሕዝብ እንደሚቆረቆር ሰው፣ እንደ አንድ ኦሮሞ እንጂ እንደ ፓርቲ አመራር የምቀጥል አይሆንም።”

አቶ በቀለ እራሳቸውን ከኦሮሞ ፌደራሊስት ፓርቲ የማግለላቸውን ውሳኔ እስካሁን ድረስ ለፓርቲያቸውም ሆነ ለየትኛውም ሰው አለመናገራቸውን ገልጸዋል።

“በዚህ ጉዳይ ብዙ ሳስብ ቆይቻለሁ። ጥቅሙ [ፓርቲው ውስጥ መቆየቴ] ስላልታየኝ በቅርቡ ከውሳኔ ላይ ደርሻለሁ” በማለት በኦፌኮ ውስጥ የነበራቸው ኃላፊነት እና ተሳትፎ ማብቃቱን ተናግረዋል።

አቶ በቀለ የኦሮሞ ፌደራሊስት ፓርቲ ለሚታገልለት ሕዝብ ከፍተኛ ተቆርቋሪ ድርጅት መሆኑን እራሳቸው እስከ መስዋትነት አሳልፈው ከሚሰጡ የፓርቲ አመራሮች ጋር በርካታ መራር ጊዜያትን ማሳለፋቸውን አስታውሰው፤ “እንደከዚህ ቀደሙ ከእነርሱ ጋር አብሬ መታገል አለመቻሌ፣ መሥራት አለመቻሌን ሳስብ ትልቅ ሐዘን ነው የሚሰማኝ” ብለዋል።

አቶ በቀለ ገርባ እራሳቸው ከኦፌኮ ፓርቲ አግልያለሁ ይበሉ እንጂ “ፓርቲው እና የኦሮሞ ሕዝብ በሚያደርገው ትግል በምፈለግበት ጊዜ ሁሉ ለመገኘት ዝግጁ ነኝ” ብለዋል።

“ፖለቲካ አቆምኩ ማለት አይደለም። ስለ ኦሮሞ ሕዝብ መናገር አቆማለሁ ማለት አይደለም። ኦሮሞ በሚፈልገኝ ወቅት የኦሮሞ ተቋም በሚፈልግበት ወቅት እና ጊዜ አቅሜ በፈቀደ ሁሉ ለመዘገኝ ዝግጁ ነኝ።”

አቶ በቀለ ከፓርቲያቸው ምንም አይነት ጫና በየትኛውም መልኩ እንዳልደረሰባቸው እና ከፓርቲው አመራሮች ጋር ተከባብረው መሥራታቸውን እንዲሁም በይፋ ከፓርቲው ቢለያዩ ደስታቸው ይሆን እንደነበር ገልጸዋል።

አቶ በቃለ ከፓርቲው መለየታቸው በፖለቲካ ፓርቲው ላይ ምንም አይነት አሉታዊ ተጽእኖ ሊፈጠር ይችላል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ተናግረዋል።

የአርቲስ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ በቀለ ገርባ፣ ጃዋር መሐመድ እና ሌሎች እስረኞችን ጨምሮ በርካቶች ለቀናት የረሃብ አድማ ማድረጋቸው ይታወሳል።

እነ አቶ በቀለ ፖለቲከኞች ላይ የሚደርሰውን እንግልት እና እስር እንዲሁም በሌሎች ላይ የሚፈጸም እስር እና ወከባ እንዲቆም ለመጠየቅ ነበር የረሃብ አድማ ሲያደርጉ የቆዩት።

አቶ በቀለን ጨምሮ ፖለቲከኞቹ በረሃብ አድማ ለረዥም ቀናት በመቆየታቸው ከፍተኛ የሆነ የጤና መቃወስ አጋጥሟቸው እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል።

አቶ በቀለ በአሁኑ ወቅት ጤናቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ “አሁን ላይ ሙሉ ጤና አለኝ። ከዚህ ቀደም አደርገው የነበረውን ነገር በሙሉ እያደረግኩ ነው። ከየትኛውም ጊዜ በላይ ጤንነት እየተሰማኝ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

(ቢቢሲ)

Report Page