BBC

BBC


በኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ የተከሰከሰው የቦይንግ 737 ማክስ 9 አውሮፕላን ከአደጋው በፊት የኤሌክትሪክ ችግሮች እንዳሉበት የሚያሳየውን መረጃ መደበቁን የቀድሞ የቦይንግ ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ።

ፋውንዴሽን ፎር አቪየሽን ሴፍቲ የተባለ ቡድን የሚመሩት የቦይንግ የቀድሞ ሥራ አስኪያጅ ለ157 ሰዎች እልቂት የሆነው እና ከስድስት ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የተከሰከሰው 737 ማክስ 9 አውሮፕላን የኤሌክትሪክ ችግሮች እንዳሉበት በኩባንያው ይታወቅ ነበር ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በዝቅተኛ ከፍታ ላይ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን እንደሚችል እና በርካታ እክሎች እንደነበሩበት ይፋ አድርገዋል።

ፋውንዴሽኑ በአሁኑ ወቅት እየበረሩ ያሉ ከ1000 በላይ የቦይንግ አውሮፕላኖች በሚመረቱበት ወቅት በነበሩ ችግሮች ምክንያት የኤሌክትሪክ ብልሽት ስጋት እንደተጋረጠባቸው ገልጿል።

ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተነስቶ ጉዞውን በጀመረ በስድስት ደቂቃዎች ውስጥ የተከሰከሰው አውሮፕላን የኤሌክትሪክ ብልሽቶች ነበሩበት ብለዋል።

አውሮፕላኑ በተከሰከሰበት ወቅት አዲስ ሞዴል 737 ማክስ 9 ነበር። ከዚያ ቀደም ብሎ ተመሳሳይ 737 ማክስ 9 አውሮፕላን በኢንዶኔዥያው አየር መንገድ አደጋ ተከስክሶ የ189 ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር 302 አደጋን ተከትሎ “ሙሉ በሙሉ ትብብር በማድረግ ለምርመራው ጠቃሚ መረጃ ሰጥቷል” ሲሉ የቦይንግ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

አክለውም “ለበለጠ መረጃ የመርማሪ ኤጀንሲዎችን እንጠብቃለን” ብለዋል።

ለሁለቱም አደጋዎች ምክንያት የቦይንግ የበረራ መቆጣጠሪያ ሥርዓት (ኤምካስ) ችግር እንደሆነም ተገልጿል።

ቦይንግ የገጠመው ኤምካስ (ማኑቨሪንግ ካራክተርስቲክስ ኦግመንቴሽን ሲስተም) የተሰኘው የበረራ መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ችግር መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ይህም አውሮፕላኑን በተደጋጋሚ ለመቆጣጠር ቢሞከርም ሳይታዘዝ ቀርቶ ወደ ምድር ተምዘግዝጎ እንደተከሰከሰ ተገልጿል።

ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያ አደጋ የተከሰከሰው አውሮፕላን ምርትን በተመለከተ በቦይንግ ሰራተኞች ሾልኮ የወጣ በርካታ ሰነዶችን በድረ ገጹ አሳትሟል።

ከፍተኛ የቴክኒካል ዝርዝሮችን የያዙት ሰነዶች አውሮፕላኑ በአመራረቱ ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችን አስፍረዋል።

ሰነዶቹ “የ737 አውሮፕላኑ በሚመረትበት ወቅት በፋብሪካው ውስጥ የነበረውን ግራ የሚያጋባ እና የተመሰቃቃለ የምርት ክንውኖችን ፍንትው አድርገው ያሳዩ ናቸው” ብሏል።

በሰነዶቹ ላይ በግልጽ ከሰፈሩት መካከል የኤሌክትሪክ ቁሶች እጥረት፣ በአግባቡ ያልተገጠሙ የኤሌክትሪክ ሽቦዎች እንዲሁም በአውሮፕላኑ ያልተገጠሙ ሽቦዎች እንዲሁም ጉድለት ያለባቸው ቁሶችን እንደገና እንዲገጥሙ ሰራተኞች ላይ የደረሰው ከፍተኛ ጫና ተዘርዝሯል።

ይህ አደጋ ከመከሰቱ በፊት ባሉት ሳምንታት እና ወራት ውስጥ አውሮፕላኑ እነዚህ የኤሌክትሪክ ብልሽቶች ገጥመውት እንደነበርም ሰፍሯል።

አውሮፕላኑ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ከደረሰ ከሦስት ሳምንታት በኋላ ይሄው ተመሳሳይ ችግር እንደነበረበት ሰነዱ በተጨማሪ ገልጿል።

አውሮፕላኑ በዝቅተኛ ከፍታ እየበረረ ለማረፍ በሚዘጋጅበት ወቅት ከቁጥጥር ውጭ እንደሚሆን የአውሮፕላን አምራቹ እና አየር መንገዱ ተነጋግረው ነበር።

ይህም በኋላ በአመራረቱ ወቅት በአውሮፕላኑ በተገጠሙ የኤሌክትሪክ ሽቦዎች በተፈጠረ መሰረታዊ ስህተት ምክንያት እንደሆነ ይኸው ፋውንዴሽን አስፍሯል።

እነዚህ ሰነዶች “ከመንግሥት ባለስልጣናት፣ ከሕግ አስከባሪዎች፣ ከአየር መንገዶች፣ ከተጎጂ ቤተሰቦች እና ከሕዝብ የተደበቁ ነበሩ” ሲል የአቪዬሽን ደኅንነት ፋውንዴሽኑ ገልጿል።

በዚህም ምክንያት የአውሮፕላን አምራቹ መሰረታዊ የጥራት እክሎች ባሉበት የአሰራር ሁኔታ ምርቱን እንዲቀጥል ተደርጓል ብሏል።

በዚህም ምክንያት በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው አሰቃቂ ከሚባሉት አደጋዎች በተጨማሪ ከጥቂት ወራት በፊት የአላስካው አየር መንገድ የቦይንግ ማክስ 9 በር በአየር ላይ ተገንጥሎ መውደቁ በምርቶቹ ደኅንነት እና ጥረት ላይ ያሉ ችግሮች መቀጠላቸው ማሳያ እንደሆነ ጠቅሷል።

ፋውንዴሽኑ የሚመራው በዋሽንግተን ግዛት፣ ሬንተን የቦይንግ 737 ፋብሪካ የቀድሞ ሥራ አስኪያጅ በሆኑት ኤድ ፒርሰን ነው።

ኤድ የሁለቱ የ737 ማክስ አደጋዎች ተከትሎ በአሜሪካ የሕግ አውጭዎች ፊት በተደጋጋሚ ምስክርነት በመስጠት ስመ ጥር ሆነዋል።

በፋብሪካው ውስጥ ያሉ የአመራረት የደኅንነት እና የጥራት ችግሮች ለሁለቱም አደጋዎች ቁልፍ ሚና መጫወታቸውን በተደጋጋሚ የሚናገሩ ሲሆን ቦይንግ በበኩሉ ይህንን ክስ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጓል።

የአሜሪካ የአደጋ ምርመራ ቢሮ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ ላይ ያደረገው ምርመራ ይህንኑ ያረጋግጣል።

ቢሮው ከምርት ጋር የተገናኙ ጉድለቶች በአውሮፕላኑ የተገጠመው ቃኚ (ሴንሰር) እንዳይሰራ እክል ፈጥሮ ለአደጋው መንስዔ እንደሆነ ጠቁሟል።

የአሜሪካ ብሔራዊ የትራንስፖርት እና ደኅንነት ቦርድ በበኩሉ ይህንን ውድቅ አድርጎ ለዚህ ምንም አይነት ማስረጃ የለም ብሏል።

የአውሮፕላኑ ቃኚ (ሴንሰር) ሳይሰራ የቀረው ከባዕድ ነገር ምናልባትም በወፍ ምክንያት ሊሆን ይችላል ብሏል።

በቦይንግ ውስጥ ያሉ የኩባንያው ባለሙያዎች በበኩላቸው ሰነዶች ተደብቀዋል የሚለውን የፋውንዴሽኑን ክስ ውድቅ አድርገው በርካታ ምርመራዎች እነዚህ ትክክል እንዳልሆኑ ያሳያሉ ብለዋል።

የቦይንግ አዲሱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኬሊ ኦርትበግ በኩባንያው ላይ ያለውን እምነት ወደነበረበት መመለስ ላይ ለማተኮር ማቀዳቸውን ገልጸዋል።

አውሮፕላን አምራቹ የደኅንነት እና የጥራት ቁጥጥርን ለማሻሻል "የማስተካከያ የድርጊት መርሃ ግብር" እንዲያከናውን በአሜሪካ የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር ታዟል።

ነገር ግን በፋብሪካው ውስጥ ያሉ ሰዎችን ዋቢ አድርገው ለጋዜጠኞች የተናገሩት ኤዲ በአመራረቶቹ ላይ አሁንም በቂ የሆኑ ማሻሻያዎች የሉም ብለዋል።

ለዚህም የአቪዬሽኑ ባለስልጣናት በሥፍራው መጥተው የሚያደርጉት ምርመራ ቀደም ብለው ስለሚታወቅ እና ዝግጁ ሆነው ስለሚጠብቁ መሆኑን አክለዋል።

(ቢቢሲ)


Report Page