BBC
BBC AMHARICየታጣቂዎች ግድያ በኦሮሚያ ምዕራብ ሸዋ ዞን :
• 10 ሰዎች ተገድለዋል።
• የሟቾች አስክሬን ዛሬ አርብ ለቤተሰቦቻቸው ይሰጣል።
ከቀናት በፊት በአማሮ አካባቢ ታጣቂዎች የሁለት ወጣት ኢንጂነሮችን ህይወት በግፍ ማጥፋታቸውን ከሰማን በኃላ ዛሬ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት በመንገድ ግንባታ ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ 10 ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸውን ሰምተናል።
ይህን መረጃ ይፋ ያደረገው ቢቢሲ የአማርኛው ክፍል ነው።
ጥቃት ተፈፅም የሰዎች ህይወት መጥፋቱን የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዲሪርሳ ዋቁማ ያረጋገጡ ሲሆን ጥቃቱ በዞኑ ሜታ ወልቂጤ ወረዳ ሎያ ጎዳኔ ቀበሌ ውስጥ ረቡዕ ሰኔ 09/2013 ዓ.ም አመሻሽ 12 ሰዓት አካባቢ መፈፁም ገልፀዋል።
በታጣቂዎች የተገደሉት የፌደራልና የኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣን ባለሙያ የሆኑ 9 ሰዎች እና የቀበሌው ነዋሪ የሆነች አንዲት ሴት ናቸው ብለዋል።
ጥቃቱ በተፈጸመበት መኪና ውስጥ ከነበሩ 11 የመንገድ ሥራ ባለሙያዎች በሕይወት የተረፉ መኖራቸውንም አክለዋል።
በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች አስከሬን አዲስ አበባ ወደሚገኘው ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል መላኩንና ለቤተሰቦቻቸው መርዶ መነገሩን ጠቅሰው አስከሬናቸው ዛሬ አርብ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
አቶ ዲሪርሳ ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው አስራ አንድ የመንገድ ግንባታ ባለሙያዎች መካከል ከግድያው ያመለጡት ሁለቱ "በአካላቸው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም፤ ደህና ናቸው" ብለዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ተገኝ ጥቃቱ መፈፀሙን አረጋግጠው፤ የባለሥልጣኑ ባልደረቦች የሆኑ አስር ሰዎች በታጣቂዎቹ በተተኮሰ ጥይት መገደላቸው ተናግረዋል።
አቶ ሃብታሙ ፥ "ችግሩ ተከስቷል፤ ገና ዝርዝር መረጃ የለንም። ነገር ግን ጥቃቱ የተፈጸመው ምዕራብ ሸዋ አካባቢ፣ ሜታ ወልቂጤ በተባለ ቦታ ላይ ነው" ብለዋል።
ቢቢሲ ከባለስልጣኑ አንድ ባልደረባ አገኘሁኝ ባለው መረጃው በታጣቂዎቹ ከተገደሉት ሰዎች መካከል መሃንዲስ፣ ሾፌር፣ የቡል ዶዘር ቴክኒሺያንና በተለያዩ ሙያዎች የመንገድ ግባታ ባለሙያዎች ይገኙበታል።
ጥቃቱ በተፈፀመበት ወቅት አንድ ሰው ለማምለጥ ባደረገው ሙከራ በአቅራቢያው ወዳለ ገደል ዘሎ መግባቱን እና በህይወት ስለመትረፉ የታወቀ ነገር እንደሌለ እኚሁ የባለስልጣኑ ባልደረባ ገልፀዋል።
በምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ ጥቃቱን የፈጸመው "ኦነግ-ሸኔ" የተባለው ቡድን እንደሆነ ገልፀዋል። ስለተፈጸመው ግድያ ከቡድኑ በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ይህ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተለይቶ የወጣውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተሰየመ ሲሆን፤ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከሚፈጸሙ ግድያዎችና ጥቃቶች ጋር ስሙ በተደጋጋሚ ይነሳል።
@tikvahethiopia