BBC

BBC

BBC NewsAmharic

በአድዋ የኤርትራ ወታደሮች ተኩስ ከፍተው የሰው ህይወት ማጥፋታቸው ተገልጿል :

ሚያዚያ 4 (ሰኞ) ረፋድ ላይ የኤርትራ ወታደሮች የከፈቱት ተኩስ ነዋሪዎችን ገድሏል ፤ ቁስለኛ አድርጓል።

በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የአክሱምና የማዕከላዊ ዞን ጸጥታ ጽህፈት ቤት ፥ ተኩሱ በኤርትራ ወታደሮች መከፈቱን አሳውቆ ፥ ቢያንስ አንድ ሰው ሞቷል ብሏል።

ነዋሪዎች ግን በተኩሱ 8 ሰዎች መሞታቸውን ነው የተናግሩት።

የአክሱም ሆስፒታል ዶክተር ከትናንት ረፋድ ጀምሮ እስከ ከሰዓት በኋላ ድረስ 20 የቆሰሉ ሰዎች ከአድዋ እንደመጡ ተናግሯል።

ዓለም አቀፉ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ማኅበር (MSF) ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን ከአድዋ ሆስፒታል እንዳመጣቸው የሚናገረው ይህ ዶክተር "2 ሴቶች የሚገኙባቸው 20 ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እያከምን ነው" ብሏል።

MSF ትናንት በትዊተር እንደገለጸው ፥ ሰኞ እለት 18 ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ወደ አድዋ ኪዳነምህረት ሆስፒታል እንደመጡና እርዳታ እንደተደረገላቸው በመጥቀስ፤ 11 ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ለከፍተኛ ህክምና ወደ አክሱም ሆስፒታል ተልከዋል ብሏል።

"ወታደሮቹ ጥቃት በደረሰባቸው ሰዎች ላይ መተኮሳቸው ነግረውኛል" ብሏል።

የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው ስድስቱ ከፍተኛ ጉዳት ስለ ደረሰባቸው በጽኑ የህክምና ክትትል ውስጥ ሲሆኑ፤ ከእነዚህ አንዷ ሴት እንደሆነች ቃሉን ቢቢሲ የሰጠው ሐኪም ገልጿል።

የህክምና ባለሙያው እንደሚለው አንዳንዶቹ ሆዳቸው ላይ፤ የተቀሩት ደግሞ በተለያየ የሰውነታቸው ክፍል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

እነዚህ በ20ዎቹ መጀመሪያ የእድሜ ክልል የሚገኙ ሲሆን አንድ በ60ዎቹ የሚገኙ ግለሰብ እንደሆኑ ለማወቅ ችለናል።

በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የአክሱምና የማዕከላዊ ዞን ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስገዶም ስዩም፤ ጥቃቱ በአድዋ መናኽሪያ በመባል በሚታወቀው አካባቢ እንደሆነ ገልፀው በመኪና ተጭነው ሲሄዱ የነበሩት የኤርትራ ወታደሮች "አንድ የባጃጅ አሽከርካሪ መንገድ ዘጋብን" በሚል ጥቃት እንደፈጸሙ ተናግረዋል።

"ባለ ባጃጁ ጉዳት ደርሶበታል፤ 1 ሰው እንደሞተም መረጃው ደርሶኛል። ሌሎች 5 ሰዎች ደግሞ ተመትተው አክሱም ሪፈራል ሆስፒታል ይገኛሉ" ብለዋል።

በተጨማሪም "የአክሱም ሕዝብም ሲሮጥ ነው የዋለው፤ የኤርትራ ወታደሮች ያገኙትን ሰው እየገደሉ እየመጡ ነው የሚል ስልክ ወደ አክሱም ተደወለ። ሕዝቡም ንብረቱን ትቶ፣ የከፈተው ሱቅ ሳይዘጋ ሸሸ" ሲሉ አቶ አስገዶም ተናግረዋል።

በዚህ ጉዳይ የኤርትራ መንግሥት የሰጠው ማብራሪያ የለም።

ባለፈው ሳምንት ግን የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው የገቡት የኤርትራ ወታደሮች መውጣት እንደጀመሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ገልጾ ነበር።

ቃላቸውን ለቢቢሲ የሰጡ ተጠቂዎችና ኗሪዎች እንደሚሉት የኤርትራ ወታደራዊ ልብስ የለበሱ ታጣቂዎች ጥቃት እንደፈፀሙ ነው።

የአካል ጉዳት ደርሶበት አክሱም ሆስፒታል ላይ ከሚገኙት ታካሚዎች አንዱ የሆነው በጸጉር ሥራ ላይ የተሰማራው ወጣት፤ ሰኞ ጠዋት ወደ ሥራ እየሄደ ዲጋዲግ ተብሎ በሚጠራው የአውቶብሶች መናኽሪያ መኪና ላይ ሆነው የሚተኩሱ የኤርትራ ወታደር ልብስ የለበሱ ወታደሮች በጥይት እንደመቱት ገልጿል።

"ሁለት የኤርትራ ሠራዊት የጫኑ የጭነት መኪኖች አንበሳ ባንክ አካባቢ ሲደርሱ መተኮስ ጀመሩ። አጋጣሚ አጠገቤ አንድ ሱቅ ነበርና ወደ እዚያ ልገባ ስሮጥ ሦስት ጊዜ ተኮሱብኝ። ሁለት ከጀርባዬ አንድ ደግሞ ሆዴ ላይ መታኝ።"

ተመሳሳይ ቆስሎ ሆስፒታል ውስጥ የሚገኘው ሌላ ታካሚ አምስት ጥይት እንደተተኮሰበት በመግለጽ "አንዱ አንገቴ አካባቢ፣ ሦስት ከጀርባዬ፣ አንድ ደግሞ እጄን መቶኛል" ብሏል።

ሰኞ እለት ጥቃቱ ሲፈጸም አካባቢው ላይ ማን ነበር ብሎ የጠየቀው ሌላ የአድዋ ከተማ ኗሪ በበኩሉ" ወታደሮቹ ወደ ከተማዋ ሲገቡ፣ ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት አድዋ ላይ ምንም አይነት ጦርነት አልነበረም" ብሏል።

ምንጭ፦ [ www.bbc.com ]

@tikvahethiopiaBOT

Report Page