BBC

BBC


የኤርትራ ሠራዊት ከትግራይ የመውጣቱ ሂደት በጣም አዝጋሚ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አስታወቀ።

በፕሪቶሪያ ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት እና በናይሮቢ የትግበራ ሰነድ መሰረት ኤርትራ ጦሯን ከትግራይ ማስወጣት እንዳለባት ቢያትትም ጦሯ ጠቅልሎ አለመውጣቱን የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ምክትል ኮሚሽነር ናዳ አል ናሺፍ ገለጹ።

በጄኔቫ እየተካሄደ ባለው 52ኛው ዓመታዊው የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ላይም ኮሚሽነሯ የኤርትራ ጦር ከትግራይ የመውጣት ሂደት “በጣም አዝጋሚ እና ገና ያላለቀ” ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ቀጣይነት ያለው ክትትል እንዲደረግም የድርጅቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን አሳስበዋል።

በተመሳሳይ ኤርትራ ወታደሮቿን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከትግራይ እንድታስወጣ የአውሮፓ ኅብረት በዚሁ ጉባኤ ላይ ጥሪ አቅርቧል።

በተጨማሪም በኤርትራ ጦር የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እንዲመረምርም ኅብረቱ ጠይቋል።

በፕሪቶሪያ እና በናይሮቢ የተፈረመው የሰላም ስምምነት እና የመተግበሪያ ሰነድ መሠረት የትግራይ ኃይሎች ከባድ መሳሪያ የሚፈቱት የውጭ ኃይል እና ከአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ውጪ ያሉ ኃይሎች ሲወጡ በተመሳሳይ ወቅት መሆኑን ማስቀመጡ ይታወሳል።

ሆኖም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላም የኤርትራ ሠራዊት ያልወጣባቸው አንዳንድ አካባቢዎች እንዳሉ የትግራይ ተደራዳሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በነበራቸው ቆይታ የኤርትራ ጦር ከትግራይ ስለመውጣቱ ጉዳይ መነሳቱን አውስተው ነበር።

“በተደራጀ መልኩ የሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች እንዳሉ እናውቃለን። በነበረንም ውይይት ይህንኑ አቅርበናል። በኢትዮጵያ መንግሥት እንዲወጡ ተጠይቀዋል። ሲወጡ ‘በሰላም እንዲወጡ ዝግጅት አድርገን ነው የሸኘናቸው የሚል ነው የተነገረን” ሲሉ አስረድተዋል።

የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ ከወራት በኋላ የኤርትራ ወታደሮች ግድያዎችን መፈጸማቸውን እንዲሁም የመድፈር ወንጀል ክሶች እየቀረበባቸው ይገኛል።

ቢቢሲ በኤርትራ ጦር አባላት የተደፈሩ ነዋሪዎችን ያናገረ ሲሆን የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞችም ይህ ተግባር መቀጠሉን ተናግረዋል።

የኤርትራ ሰብዓዊ መብት አያያዝ አሳሳቢ እና በአሁንም ወቅት መሻሻል አለማሳየቱን በተመለከተበት በዚህ ጉባኤ ላይ፣ ጦሯ በትግራይ ውስጥ በፈጸመው መጠነ ሰፊ ጥሰትም ተጠያቂነት ለማስፈን ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰዷም ተገልጿል።

የኤርትራ ጦር በትግራይ ግድያዎች፣ መድፈር፣ ሰላማዊ ዜጎችን ማሰቃየት ጨምሮ በአስከፊ መጠነ ሰፊ ጥሰቶች በመፈጸም በተለያዩ ወገኖች ሲከሰስ ቆይቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ ባደረጉት ምርመራ እነዚህ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይፋ ቢሆኑም፣ በኤርትራ በኩል ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ምንም አይነት ሥርዓት አለመዘርጋቱን ምክትል ኃላፊዋ አንስተዋል።

“ኤርትራ የጋራ የምርመራ ሪፖርቱን ውድቅ አድርጋ በጦሩ ውስጥ ያሉ ወንጀለኞች ያለ ምንም ቅጣት እንዲቀጥሉ ፈቅዳለች። የአገር ውስጥ የፍትህ ሥርዓቱ ወንጀለኞችን ተጠያቂ የሚያደርግበት ሁኔታም የለም” ሲሉም ተናግረዋል።

የኤርትራ መንግሥት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሠረት በማድረግ ለሚነሱ የምርመራ ተጠያቂነት እና የሽግግር ፍትህ ሂደቶች እንዲተባበርም ተጠይቋል።

ኤርትራ ጦሯ በትግራይ ውስጥ በፈጸመው ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ውስጥ በተፈጸሙ ጥሰቶችም ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ምንም እርምጃ አልወሰደችም ተብሏል።

የተመድ የሰብዓዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን ኤርትራ በዜጎቿ ላይ ባርነት፣ በግዳጅ መሰወር፣ እስር፣ ስቃይ፣ ግድያ፣ መድፈር እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች መፈጸሟን ሪፖርት ቢያደርግም አንድም ሰው ተጠያቂ አልሆነም ተብሏል።

በጄኔቫው ጉባኤ የተመድ ልዩ ራፖርተር ሞሃመድ አብዱልሰላም ባቢከር በኤርትራ የሰዎችን መሠረታዊ ነጻነቶች መገርሰስ መቀጠሉና ምንም የመሻሻል ምልክት አልታየም ብለዋል።

በአገሪቱ ለዘመናት የዘለቀው ዜጎችን ለጦርነት መመልመል በትግራይ ጦርነት ተባብሶ እንደቀጠለም ያየው ይህ ጉባኤ በግዳጅ ተመልምለዋልም ብሏል።

በትግራይ ጦርነት ተጠባባቂ የተባሉ ዕድሜያቸው ከ40-66 የሚደርሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎችም እንዲዋጉ መደረጉ አሳሳቢ ነው ተብሏል።

ሞሃመድ አብዱልሰላም የግዳጅ ምልመላዎች “ጊፋ” በከፍተኛ ሁኔታ ተጠናክረው መቀጠላቸውን ለዚህም አዳዲስ አካባቢዎች መኖራቸውን ነው የተናገሩት።

የግዳጅ ምልመላውን አምልጠው የጠፉ ወይም የተደበቁ ቤተሰቦቻቸውን አሳልፈው ያልሰጡ ቤተሰቦችም ከቤታቸው እንዲወጡ ተደርገዋል።

በዚህም ጉባኤ ለሁለት አስርት ዓመታት በድብቅ የታሰሩ እና የጠፉ ዜጎችንም ጉዳይ ከፍተኛ ስጋት እንዳሳደረበት ገልጿል።

በኤርትራ የሰብአዊ መብት ማሻሻያዎች እንዲመጣ ምክር ቤቱ የበለጠ ግፊት እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡት ልዩ ራፖርተሩ አገሪቱ “የሕግ የበላይነት፣ ሕገ መንግሥት፣ ብሔራዊ ጉባኤ፣ ነፃ የዳኝነት ሥርዓት እና ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ የላትም” ብለዋል።

በኤርትራ ያለው የሲቪል ምህዳር የተገደበ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ምንም አይነት ገለልተኛ ሚዲያ የለም እንዲሁም በመንግሥት ላይ የሚደረግ ተቃውሞ እስር ወይም ሞት ይደርስበታል ብሏል።

በተመድ የኤርትራ ቋሚ ተወካይ አደም ኦስማን ኢድሪስ በበኩላቸው አገራቸው የማያባራ ጠላትነትና ማዋከብ ቢቀጥልባትም ለማኅበራዊ ፍትህ ቁርጠኛ ናት ብለዋል። ሁሉንም ሰብዓዊ መብቶች እና ነፃነቶች ለሁሉም ዜጋ ተጠቃሚ ታደርጋለች ብለዋል።

የልዩ ራፖርተሩ ዓላማው ፖለቲካዊ ነው ያሉት አደም ኦስማን ሰብዓዊ መብቶችን እንደ መሳሪያ የመጠቀምና አገሪቱን በተንኮል በመንወጀል የማዋከቢያ መንገድ ነው ብለዋል።

(BBC)


Report Page