BBC

BBC

ቲክቫህ ኢትዮጲያ

በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ ከ4 ያላነሱ ነባር ጋዜጠኞች ባለፉት ጥቂት ወራት በተለያዩ አጋጣሚዎች ባቀኑባቸው ምዕራባውያን ሃገራት ጥገኝነት ጠይቀዋል።

ከእነዚህም መካከል አንዱ ለ9 ዓመታት በኢቢሲ ከሪፖርተርነት እስከ ዜና ክፍል ምክትል ዋና አዘጋጅነት ያገለገለው ጋዜጠኛ ቢላል ወርቁ ይገኝበታል።

ጋዜጠኛው ቢላል በዚህ ሳምንት ሰኞ የተካሄደውን የዩኬ-አፍሪካ የኢንቨስትመንት ፎረም ለመዘገብ በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ከሚመራ ልዑክ ጋር ወደ ለንደን የተጓዘ ሲሆን ጥገኝነት መጠየቁን ለቢቢሲ አረጋግጧል::

ከቢላል በተጨማሪ ሌሎች ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የኢቢሲ ነባር ጋዜጠኞች በተለያዩ አጋጣሚዎች በሄዱባቸው ምዕራባውያን ሃገራት ጥገኝነት ለመጠየቅ የተገደዱት ከጋዜጠኝነት ሥራቸው ጋር በተያያዘ በሚደርሱባቸው ጫናዎች እንደሆነ ተናግረዋል።

"ጋዜጠኞች የኤዲቶሪያል ነጻነት የላቸውም"

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት እና በውጪ አገራት የሚገኙት የቀድሞ የኢቢሲ ጋዜጠኞች ለቢቢሲ በላኩት የጽሑፍ መልዕክት በጋዜጠኝነት ሥራቸው የኤዲቶሪያ ነጻነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።

"ጉዳዮች እየተመረጡ ነው የሚዘገቡት" ያሉት ጋዜጠኞቹ እንደምሳሌ፤ በጅግጅጋ አብያት ክርስቲያናት ሲቀጣሉ በፍጥነት ሳይዘገብ መቆየቱን፣ የሃይማኖት ተቋማት መግለጫዎች ለምሳሌ ሲኖዶሱ የኦሮሚያ ቤተክነት መቋቋምን አወግዛለሁ ማለቱ አለመዘገቡ፣ በሞጣ የተፈፀመው ጥቃት ሰፊ ሽፋን ሳይሰጠው እንደቀረ፣ የትግራይ ክልል እና የህውሃት መግለጫዎች አለመዘገባቸው፣ የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ የተዘገበበት መንገድ እና ሌሎችን ጉዳዮችን በመጥቀስ የዜና ሽፋን የሚሰጣቸው ጉዳዮች የተመረጡት ብቻ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ጋዜጠኛ ቢላል ወርቁም፤ ኢቢሲ "እንደ ከዚህ ቀደሙ እኔን ብቻ አገልግሉ የሚልና ሌላውን ሰምቶ እንዳልሰማ የሚሆን መገናኛ ብዙኃን በመሆኑ የድርጅቱ አገልጋይ ሆኖ ላለመቀጠል ወስኛለሁ" ብሏል።

እሱ እንደሚለው ከሆነ፤ ኢቢሲ የሚዘገቡ ጉዳዮችን ከመምረጡም ባሻገር ጋዜጠኞች በጉዳዮቹ ላይ ዘገባ ለመስራት ሲጠይቁ ይሁንታ እንደማይሰጣቸው ይናገራል።

የኢቢሲ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ እና የቴሌቪዥን ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ አብዱልጀሊል ሃሚድ ግን በተቋሙ የኢዲቶሪያል ነጻነት የለም የሚሉ ክሶችን ሙሉ በሙሉ ያጣጥላሉ።

"የራሳችን ኤዲቶሪያል ፖሊሲ አለን። በዛ መሠረት ነው በነጻነት የሚሰሩት። ምንም የተቀየረ ነገር የለም። ማንም ጣልቃ አይገባም። ሁሉም ነገር የሚሰራው በጋዜጠኝነት ሥነ-ምግባር ነው። አቶ ቢላል በራሱ ፍቃድ ለኑሮ ይሻለኛል ብሎ ነው የቀረው እንጂ የኤዲቶሪያል ነጻነት የለም የሚለው አያስኬድም" በማለት ጉዳዩን ለማብራራት ይሞክራሉ።

ጋዜጠኞቹ እንደምሳሌ የጠቀሱትን በማንሳት ዜናዎች እየተመረጡ ነው የሚሰሩት ለሚለው ቅሬታ ምላሽ የተጠየቁት አቶ አብዱልጀሊል፤ "እኛ አገርን በማይንድ ፣ ሕዝብን በማያራርቅ መልኩ ነው ዜናዎችን የምንመርጠው። እንደውም የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጉዳይ ቀድመን የዘገብነው እኛ ነን" ይላሉ።

የጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ፕሬስ ሴክረታሪያት በኢቢሲ ቀርበው ስለታገቱት ተማሪዎች ከሰጡት መግለጫ ውጪ ኢቢሲ ተከታታይ ዘገባ አለመስራቱን እና ጋዜጠኞች በጉዳዩ ዝርዝር ዘገባዎችን ለመስራት ጠይቀው መከልከላቸውን የቀድሞ የኢቢሲ ጋዜጠኞች ይናገራሉ።

አቶ አብዱልጀሊል ግን፤ "ይሄ ዘበት ነው። ዛሬ ጠዋት በነበረው ስብሰባ ላይ እንኳን ተከታታይ ዘገባዎች ለምን አይሰሩም ብለን ጥያቄ አቅርበን ነበር። አቶ ቢላልም እራሱ ቡድን መሪ ስለሆነ ይህን ሃሳብ አቅርቦ በኤዲቶሪያሉ ጸድቆለት ነበር። እሱ የቤቱን ስም ለማጠልሸት ካልሆነ በቀር ከዚህ ጋር የተገናኘ ነገር የለም" ይላሉ።

Image copyrightBILAL WORKU
አጭር የምስል መግለጫጋዜጠኛ ቢላል ወርቁ
"ተቋሙ ብቃት በሌላቸው ሰዎች ነው የሚመራው"

ጋዜጠኛ ቢላል ተቋሙን የሚመሩት "ምንም ዓይነት የሚዲያ ልምድ እና በቂ የትምህርት ዝግጅት የሌላቸው እንደ ፌደሬሽን ምክር ቤት በብሔር ውክልና የተቀመጡ ናቸው፤ ሃሳቦችም ሲነሱ በብሔር ነው የሚቃኙት" ይላል።

ለቢቢሲ በጽሁፍ ሃሳባቸውን የላኩ ጋዜጠኞችም በተመሳሳይ መልኩ ከአርታኢዎቻቸው መካከል ጥቂት የማይባሉት በቂ ልምድ እና የትምህርት ዝግጅት እንደሌላቸው ጠቁመዋል።

አቶ አብዱልጀሊል በበኩላቸው "ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች አገር ነች። ይሄ ሚዲያም የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ነው ብለን ነው የምናምነው። እየተሰራ ያለውም በዚሁ መልክ ነው። ሰዎቹ አቅም የላቸውም ለሚባለው፤ አቅሙን ማነው የሚወስነው? ዩኒቨርሲቲዎች አስተምረው ሰርተፊኬት ስጥተዋል። እስከ ሁለት ማስተርስ ዲግሪ ያላቸው ጋዜጠኞች አሉ" ሲሉ መልሰዋል።

የቀድሞ የኢቢሲ ጋዜጠኞች ከሚያነሷቸው ቅሬታዎች መካከል የጋዜጠኝነት ሙያን እና ልምድን በሚጠይቁ የኤዲቶሪያል ስብሰባዎች ላይ እንደ ጠቅላላ አገልግሎት እና የሹፌሮች ስምሪት ኃላፊዎች ያሉ በኤዲቶሪያል ስብሰባዎች ላይ ተገኝተው በዜናዎች አዘጋጋብ እና ይዘት ዙሪያ አስተያየት ይሰጣሉ ይህም በሥራችን ላይ አሉታዊ ጫና ያሳድራል የሚለው ይገኝበታል።

አቶ አብዱልጀሊል ለዚህ ምላሽ ሲሰጡ፤ "በኤዲቶሪያል ፖሊሲያችን ላይ የኤዲቶሪያል አባላት እነማናቸው ተብሎ ተጽፎ ተቀምጧል። የሹፌሮች ስምሪት ኃላፊዎችም ሆኑ ጠቅላላ አገልግሎት እንዲሳተፉ የሚደረገው ከሎጂስቲኩ በተጨማሪ በሚዲያው ላይ ብዙ ዓመት ስለቆዩ በዜናዎች ላይ ሃሳብ ይሰጣሉ፤ ሃሳባቸው ተቀባይነት ካገኘ ይወሰዳል"።

የመንግሥት ባለሥልጣናት ጣልቃ ገብነት

በጋዜጠኝነት ሥራችን ላይ የመንግሥት ኃላፊዎች እና መሥሪያ ቤቶች ጣልቃ ገብነት ሥራችንን በገለልተኛነት እንዳናከናውን ጫና ያሳድራል የሚለው ሌላው የጋዜጠኞቹ ቅሬታ ነው።

የኢቢሲ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የቴሌቪዥን ዘርፍ ኃላፊው ለዚህ ቅሬታ ምላሽ ሲሰጡ፤ "ጫና የሚያሳድሩ የሉም ማለት ባይቻልም ይህ ገፍቶ የመጣ ጉዳይ አይደለም" ይላሉ። አቶ አብዱልጀሊል እንደሚሉት ከሆነ ከዚህ ቀደም አንዳንድ ዜናዎች እና ፕሮግራሞች 'አይተላለፉ' እያሉ የሚደውሉ ኃላፊዎች አሉ። እሳቸው እንደሚሉት ግን የተቋሙ ኤዲቶሪያ ፖሊሲ ላይ በመመርኮዝ የውጪ ጫና በተቋሙ ሥራዎች እና በጋዜጠኞች ላይ እንዳይደረግ ያደርጋሉ።

አሁን ለምን?

ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፤ በርካታ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ከእስር ተለቀዋል። እግድ ተጥሎባቸው የነበሩ መገናኛ ብዙኃን ወደ ሃገር ገብተዋል። በኢትዮጵያም የተሻለ የመናገር ነጻነት ሰፍኗል ተብሏል።

ይህ አዎንታዊ ለውጥ አለ በሚባልበት ወቅት ጋዜጠኞቹ ለምን በሄዱባቸው አገራት መቅረትን መረጡ?

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጠን ጋዜጠኛ ቢላል፤ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለውጡ ሲመጣ ትልቅ ተስፋ እንደነበረው እና ደስተኛ እንደነበር ይናገራል።

ቢላል ከዚህ ቀደም ወደ ምዕራብ አፍሪካ እና መካካለኛው ምስራቅ አገራት ለዘገባ መጓዙን በማስታወስ በለውጡ ትልቅ ተስፋ ስለነበረው ከዚህ በፊት ባደረጋቸው ጉዞዎች በዚያው ለመቅረት እንዳላሰበ ይናገራል።

"አሁን ላይ ግን 'እኛ ያልንህን ብቻ ሥራ። ባዘዝንህ መልኩ አገልግል።' የሚለውን እንደ ጋዜጠኛ መሸከም ስላልቻልኩ ለመወሰን ተገድጃለሁ" ይላል።

በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ ከ4 ያላነሱ ነባር ጋዜጠኞች ባለፉት ጥቂት ወራት በተለያዩ አጋጣሚዎች ባቀኑባቸው አገራት ጥገኝነት ጠይቀዋል።

Report Page