Afar-Somali

Afar-Somali


በሱማሊ እና አፋር ክልል መካከል ያለው ውጥረት !

ዛሬ የሱማሌ ክልል መንግስት የአፋር ክልላዊ መንግስት በክልሉ ነዋሪዎች ላይ እያደረሰ ያለውን ግድያና ማፈናቀል አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫው ሲጀምር ፥ "ባለፈዉ አርብ መጋቢት 24 - 2013 ዓ.ም ደአዋዲ እና ቀረፋ በተበሉ ቀበሌዎች ላይ እንዲሁም ዛሬ መጋቢት 28 ጠዋት በደዋዲድ ፣ በገውረአን ፣ በቀላሌና በደንለሄላይ በሚባሉ አራት የክልላችን ቀበሌዎች በሚኖሩ ንፁሃን ነዋሪዎች ላይ በአፋር ክልል ልዩ ሀይል በተፈፀመው ግድያ፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እንገልፃለን" ይላል።

መግለጫው ቀጥሎም፥ "በአንድ በኩል የውስጥና የውጪ ፀረ ኢትዮጵያ ሀይሎች ተቀናጅተው የአገራችንን ህልውና እየፈተኑ ባሉበት ፤ በሌላ በኩል አገር ወዳድ ሀይሎች ሰላማዊና ፍትሀዊ ምርጫ በማድረግ አገር ለማሻገር ጥረት እያደረጉ ባለበት በዚህ ወሳኝ ወቅት የአፋር ክልል መንግስት በየእለቱ እያደረገ ያለው የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ የክልሉ መንግስት አሰላለፍ ከየትኛው ወገን እንደሆነ እንድንጠራጠርና እንድንጠይቅ የሚያስገድድ ሆኖ አግኝተነዋል" ብሏል።

የአፋር ክልል መንግስት በሰመራ እና በአዋሽ መካከል ሱማሌ መኖር የለበትም በሚል ከንቱ ፍላጎት እየተመራ ነዋሪዎችን በመግደል፣ ንብረታቸውን በማውደምና በማፈናቀል ለአመታት አካባቢው ሀዘን የማይለየው የሰቆቃ ምድር እንዲሆን ሲያደርግ ቆይቷል የሚለው የሱማሊ ክልል መንግስት መግለጫ ፥ ባለፈው አርብ መጋቢት 24-2013 ዓ.ም በአፋር ክልል ልዩ ፖሊስ እና በክልሉ መንግስት በሚደገፈው ኡጉጉማ በሚባለው ቡድን የተቀናጀ ጥምረት በንፁሃን የአካባቢው ነዋሪ ዜጎች ላይ ጉዳት መድረሱን አሳውቋል።

ይህን ጉዳይ የሱማሊ ክልላዊ መንግስት ለሰላምና ለአገር አንድነት ሲባል ጉዳዩ በትእግስትና በሰከነ መንገድ መያዝ እንዳለበት በማመን ስለተፈጠረው ሁኔታ መግለጫ ከማውጣትና ወደሚዲያ ከመውሰድ ተቆጥቦ መቆየቱን ገልጿል።

የሱማሊ ክልል ፥ "በኛ በኩል በአስተዋይነትና በአርቆ አሳቢነት ያለንበትን አገራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት የተወሰደውን የዝምታ አማራጭ የአፋር ክልል መንግሥት እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ መግደልና ማፈናቀሉ ሳያንስ ስግብግብ ፍላጎቱን ለማሳካት የፈፀመውን አስነዋሪ ተግባር እኛ እንደፈፀምነው አድርጎ በሚዲያ በማቅረብና ቀድሞ በማልቀስ የማሳሳት ሙከራ አድርጓል" ሲል ወንጅሏል።

ይሁን እንጂ ይላል መግለጫው፥ የአፋር ክልል መንግስት ለአመታት ሲያደርግ እንደቆየው ሁሉ በተለይም ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ጣቢያዎችን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በእቅድ የተመራ አካባቢውን የማተራመስ የጥፋት ተግባሩን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን በዚህም ባለፋው አርብ መጋቢት 24-2013 ዓም ደአዋዲ እና ቀረፋ በተባሉ ቀበሌዎች በኑፁሃን ዜጎች ላይ ጥቃት በመፍፀም ከ 25 በላይ አርብቶ አደሮች ሲገደሉ ከ 30 በላይ የሚሆኑት ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ንብረትም ወድሟል ሲል አስታውሷል።

ዛሬ መጋቢት 28-2013 ዓ.ም ጠዋት የአፋር ክልል ልዩ ፖሊስ ኡጉጉማ ከሚባለው ቡድን ጋር በመቀናጀት በ4 የክልሉ ቀበሌዎች ማለትም በደዋዲድ፣ በገውረአን ፣ በቀላሌና በደንለሄ ላይ መጠን ስፊ ጥቃት በመፈፀም ለጊዜው ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ ንፁሀንን ገድለዋል ሲል ከሷል። 

የአፋር ክልላዊ መንግስት ከውስጥና ከውጪ ሆነው የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማወክ እንደሚሰሩ ሀይሎች ሁሉ የአካባቢው ነዋሪዎች አንድነትና ትብብር እንዳይጠናከር በየጊዜው ጥቃት በመፈጸም አካባቢው የሁከት ቀጠና እንዲሆን የማድረጉን ተግባር አጠናክሮ ቀጥሎበታል ብሏል።

መግለጫው በመጨረሻ ፥ "የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ለአገር ሰላም ዋጋ በመስጠትና ለህዝቦች አንድነት በማሰብ እስካሁን ህዝባችን እየሞተና እየተሰቃየም ቢሆን ጉዳዩን በትእግስትና በማስተዋል ሲከታተለው ቆይቷል። ይሁን እንጂ ያንድ ወገን ጥረት ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ ስለማይችል በቀጣይ በክልላችን ነዋሪዎች ላይ የሚደርሰውን ሞት፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት ለመከላከል ማንኛውንም አስፈላጊ እርምጃ ለመውሰድ የምንገደድ መሆኑን እያሳወቅን ጉዳዩ ወደለየለት ግጭት ከማምራቱ በፊት የአፋር ክልል መንግስት ቆም ብሎ ማሰብ እንዲጀምርና የፌደራል መንግስትም የመፍትሔው አካል ለመሆን እንዲሰራ በጥብቅ ለማሳሰብ እንወዳለን" ብሏል።


በአፋር በኩል ፦

በአፋር ክልል ሀሩቃ በተባለ ቦታ ባለፈው አርብ በተሰነዘረ ጥቃት በትንሹ 30 ሰዎች መገደላቸውን እና ከ50 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች መቁሰላቸውን የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

ጥቃቱን ፈጸሙ የተባሉት የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት በዚያኑ ዕለት ምሽት ገዋኔ በተባለ ቦታ በከፈቱት ተኩስ ሁለት የክልሉ መንግስት ሰራተኞች መገደላቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።

የአፋር ክልል የፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እና የወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ አቶ አህመድ ሁመድ ለ 'ኢትዮጵያ ኢንሳይደር' ድረገፅ እንደተናገሩት፥ ወደ ክልላቸው ዘልቆ የገባው የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል፣ በሀሩቃ ቀበሌ ጥቃቱን የፈጸመው መጋቢት 25፤ ከቀኑ 9 ሰዓት ገደማ ነው።

የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ወደ ቀበሌዋ ገብተው ተኩስ መክፈታቸውን የሚገልጹት ምክትል የፖሊስ ኮሚሽነሩ፣ በጥቃቱም “ከ30 በላይ ንጹሃን ዜጎች ተረሽነዋል” ብለዋል።

በአርቡ ጥቃት ከተገደሉት ውስጥ ሴቶች እና ህጻናት እንደሚገኙበት የጠቀሱት አቶ አህመድ፤ ከ50 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች መቁሰላቸውንም አስረድተዋል።

በጥቃቱ የተጎዱት ሰዎች በሎጊያ እና ዱብቲ በሚገኙ ሆስፒታሎች በአሁኑ ወቅት የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን አመልክተዋል። 

የአፋር ክልል ልዩ ኃይል ጥቃት ሲፈጽም ነበር ያሉትን አንድ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባል “እጅ ከፍንጅ” መያዛቸውን የሚናገሩት አቶ አህመድ፤ ግለሰቡ በአሁኑ ወቅት “በፖሊስ ቁጥጥር ስር” እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የአካባቢው ህብረተሰብ በወሰደው የመከላከል እርምጃ ሌሎች የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት መገደላቸውን አክለዋል። 

መሰል ጥቃቶች ከዚህ ቀደምም በአካባቢው በተደጋጋሚ ይከሰቱ እንደነበር የሚናገሩት ምክትል የፖሊስ ኮሚሽነሩ፤ መንስኤውም “ከሶማሌ ክልል የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ጋር የተያያዘ ነው” ይላሉ።

“በአፋር ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሶስት የኢሳ ቀበሌዎች አሉ። ‘የእኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ስላሉ ቦታውን እንወስዳለን’ የሚል የሶማሌ ክልል ግልፅ የሆነ አቋም አለ” ሲሉ ይወነጅላሉ።

የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት አርብ ከምሽቱ 5 ሰዓት አካባቢ ገዋኔ በምትባለው ከተማ አካባቢ በከፈቱት ተኩስ ሁለት የአፋር ክልል የመንገድ ልማት እና ትራንስፖርት ቢሮ ሠራተኞች መገደላቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ በተጨማሪነት ገልጸዋል።

አብዱልቃድር ሁመር እና መሀመድ ሰይድ የተባሉት ሁለቱ ሰራተኞች የተገደሉት ለስራ ከአዋሽ ወደ ሰመራ በመኪና በመጓዝ ላይ ሳሉ ነበር ተብሏል። 

በሀሩቃ እና በገዋኔ ተፈጸሙ ስለ ተባሉ ጥቃቶች የተጠየቁ የሶማሌ ክልል የመንግስት ሰራተኛ፤ የአፋር ክልል ላደረሰው ጥቃት ምላሽ ከመስጠት በዘለለ “የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በነዋሪዎች ላይ ጥቃት አልፈጸመም” ሲሉ አስተባብለዋል።

በሶማሌ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በቡድን አስተባባሪነት የሚሰሩት አቶ አብዶ ሂሎው እንዳሉት፥ በሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ላይ ጥቃት የተፈጸመው አርብ ከቀኑ 11 ሰዐት አካባቢ ነው። 

ጥቃቱ የተፈጸመበት ቦታ በአፋር ክልል ባለስልጣናት “ሀሩቃ” ተብሎ ቢጠራም ትክክለኛ ስያሜው ግን “ገረብኢሴ” የሚባል እንደሆነና በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን ስር ይተዳደር እንደነበር ያስረዳሉ።

የሶማሌ ክልል በ“ሀሩቃ” ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ሰዓት በአፋር ክልል ስር የተጠቃለሉ ሌሎች ሁለት ቀበሌዎች ላይም “የይገባኛል ጥያቄ” እንዳለው ገልፀዋል።

በ “ገረብኢሴ” አካባቢ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ካምፕ እንደሚገኝ የሚናገሩት አቶ አብዶ፤ የአፋር ክልል ልዩ ኃይል አባላት ጥቃቱን የሰነዘሩት በዚሁ “ካምፕ ላይ ነው” ባይ ናቸው።

ጥቃቱ የተሰነዘረባቸው የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል አባላት፤ ለጥቃቱ ምላሽ ከመስጠት ባለፈ ያጠፉት ነገር እንደሌለ አስረድተዋል። 

በገዋኔ አካባቢ በጥይት ተመትተው ስለሞቱት የአፋር ክልል የመንግስት ሠራተኞች የተጠየቁት አቶ አብዶ፤ በአካባቢው በተፈጠረው አለመረጋጋት ሳቢያ የሁለቱም ክልል ኃይሎች የተኩስ ልውውጥ ያደርጉ ስለነበር፤ ጥቃቱን ማን እንደፈጸመው ለመግለጽ ያስቸግራል ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። “በራሪው ጥይት ከየትኛው አካል እንደመታቸው አይታወቅም” ሲሉም ተናግረዋል።


የሱማሊ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን

የአፈር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

Ethiopia Insider

Compiled By ; Tikvah

@tikavhethiopiaBOT @tikvahethiopia

Report Page