Addis Ababa

Addis Ababa

Tikvah Magazine

አዲስ አበባ ከያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ጀምሮ ተማሪዎቿን ወደ ትምህርት ቤት ጠርታለች። በዚህ ምክንያት በክረምቱ ወቅት የነበረው የትራንስፖርት ፍሰት ይበልጥ ተጨናንቆ እና የታክሲ እጥረት ተስተውሎ ተገልጋዮችን ወደ ማጉላላት እየደረሰ ነው።

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ለዚህ ወቅታዊ የትራንስፖርት እጥረት በምክንያትነት ካነሳው ጉዳይ አንዱ ከተሰጣቸው ፍቃድ ውጪ ለተማሪዎች ሰርቪስ የሚሰጡ ባለታክሲዎች መበራከታቸው እንደሆነ ገልጿል። እየሰጡ ያሉትን አገልግሎትም ወዲያው እንዲያቆሙ አስጠንቅቋል።

በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን ያካፈሉን በርካታ የቲክቫህ ቤተሰቦች የአዲስ አበባ ትራንስፓርት ቢሮን ዉሳኔ የተሳሳተና ፍታዊነት የጎደለዉ ሲሉ ገልጸውታል። ''ዛሬ አይደለም የተጀመረዉ የተማሪ ሰርቪስ ጥንትም የነበረ ነዉ። ይህ ዉሳኔ ቀላሉን ችግር በከባድ ችግር መተካት ማለት ነዉ።'' ሲሉም ነው የገለጹት።

''እንዲህ እንደዛሬው ያለ ከፋተኛ የህዝብ ጥቅም የሚነካ ጉዳይ ላይ የሚሰጥ ውሳኔ ከፋተኛ ጥንቃቄ ይጠየቃል።'' ሲሉ ውሳኔውን ነባራዊ ሁኔታውን ያላገናዘበ ነው ሲሉ በውይይቱ ጠቅሰዋል።

ለተማሪዎች ትራንስፖርት ለማቅረብ 100 ያህል የተማሪ ሰርቪስ ተሽከርካሪዎችን መሰማራታቸው ቢገለጽም ''ሸገር ተመዝገቡ ብሎ ባወጣው መሰረት በመጀመሪያው ቀን ቦታ የለንም ብሎ በተጠባባቂ ቢይዘንም በተደጋጋሚ ስንጠይቀው ምንም ቦታ የለም ተብለናል'' በማለት ቅሬታቸውን አቅርበዋል።

ይህንኑ ጉዳይ ይዘን ወደ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ጥያቄዎችን አቅርበናል። የቢሮው የኮሚውኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አረጋዊ ይመሩ ባለፉት ቀናት የትራንስፖርት ፍሰቱ መጨናነቅ ተከትሎ ቢሯቸው ቅኝት ማድረጉን የገለጹ ሲሆን በዚህም ቁጥራቸው በርካታ የትራንስፖርት ሰጪ መኪኖች(ታክሲ) ወደ ሰርቪስነት መቀየራቸውና ይህም ከህግ ውጪ በመሆኑ ከፍተኛ ችግርም በመፍጠሩ የተወሰነ ውሳኔ መሆኑን አስረድተዋል።

የቢሮው ኃላፊነት እንደዚህ አይነት ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር እንደሆነ ያነሱት ኃላፊው አማራጭ የትራንስፖርት አቅርቦትን በተመለከተ ትምሀርት ቤቶች ከወላጆች ጋር ምክክር ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸው ህብረተሰቡን ከመጉላላት ለመታደግ ህግ ማስከበር ይቀድማል ብለዋል።

100 ያህል የተማሪ ሰርቪስ ተሽከርካሪዎች ብቻ ይበቃሉ ወይ ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ

''ቁጥሩ አነስተኛ እንደሆነ እናቃለን ነገር ግን ጫና እየፈጠርን ከተማ አስተዳደሩ አማራጭ እንዲወስድ በማድረግ እንጂ ህገወጥነትን በማበረታታት መፍትሔ አናመጣም'' ሲሉ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ''የሰው ጉልበትና ጊዜ መንገድ ላይ ነው እያለቀ ያለው'' ሲሉም በዚኛው ወገን ያለውንም ችግር ጠቁመዋል።

ለዚህ ጉዳይ ፈቃድ የተሰጣቸው ባለታክሲዎች ስለመኖራቸው የጠየቅናቸው ኃላፊው ለየትኛውም የታክሲ ፈቃድ ላለው አካል የሰርቪስ ሥራ እንዲሰራ ፈቃድ አልተሰጠውም።

ከዚህ ቀደም የተወሰኑ ታክሲዎች ብቻ በዚህ ሥራ መሰማራታቸው ጉዳዩ የታለፈ እንደሆነና ዘንድሮ ግን ቁጥሩ የተጋነነ የታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች ሰርቪስ መሆናቸው አፋጣኝ እርምጃ እንድንወስድ አስገድዶናል ሲሉ ገልጸዋል።

በከተማዋ ያለው የትራንስፖርት አቅርቦት እንዲሁም የሰረተ ልማት ዝርጋታ ከአጠቃቀም ችግሮችና የተለያዩ ጉዳዮች ታክለውበት እስካሁን የከተማዋ የራስ ምታት ሆነዋል። መንግስት ከህብረተሰቡና ከአገልግሎት ሰጪው ጋር ቀርቦ መወያየት ለችግሮች የተሻለ መፍትሔ ለመስጠት ያግዛል።

Report Page