Adawa

Adawa


የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ለንቅናቄያችን አባላትና ደጋፊዎች፣ ለአማራ እና መላ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ለ124ኛው የአድዋ የድል በዓል በሰላም አደረሳችሁ ይላል፤


አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ ለመከፋፈል የአውሮጳ ሃያላን በጀርመን በርሊን ኮንፈረንስ ከተሰባሰቡና ስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ ጣሊያን ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛት ለማድረግና ሀብቷን ለመመዝበር፣ በሂደትም ኮሎኒያሊስት ሰፋሪዎችን አየሩ ተስማሚ በሆነው በኢትዮጵያ ደጋማ መሬቶች ለማስፈር ቋመጠች። ኢትዮጵያን አንበርክካ የቅኝ ግዛትን ኅልሟን ለማሳካት የጦር ክተት ዘመቻዋን አወጀች፡፡

ጠንቃቃና ብልህ የነበሩት የወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት ግርማዊ ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ (እምየ ምኒሊክ) የፋሽስት ጣሊያንን ኅልም ለማምከን መስከረም 17 ቀን 1888 ዓ.ም ሕዝባቸው ለአገሩ ነፃነትና ለማንነቱ እንዲፋለም ብሔራዊ የክተት ዘመቻ ጥሪ አወጁ፡፡

የመሪያቸውን የክተት አዋጅ የሰሙት ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን እናትና አባቶቻችንም ብሔርና ሃይማኖት ልዩነት ሳይገድባቸው ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ እምቢኝ ለባርነት በሚል በአንድነት ወደ አድዋ ተመሙ፡፡ ከ124 ዓመት በፊት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ/ም ጣሊያን ብቻ ሳይሆን የአውሮፓ ኢምፔሪያሊዝም ህልም ጭምር በኢትዮጵያውያን ጀግንነት በአድዋ ጦርነት ሽንፈትን ተከናነቡ፡፡

አድዋ ጀግኖች እናትና አባቶቻችን በነፍጣቸው የወራሪ ጠላትን ቅስም የሰበሩበትና የአውሮጳውያን የቅኝ ግዛት በጥቁር ሕዝቦች ተጋድሎ የተሸነፈበት፣በመላው ዓለም ለሚኖሩ ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ጎህ የቀደደ ታሪካዊ ድል ነው፡፡ በእናትና አባቶቻችን ደም ነፃነታችን በአድዋ በደማቁ ተፃፈ፤ አድዋም የትላንት ማንነታችንና የዛሬ እኛነታችን ሁሌም የማይደለዝ ግንባር-ቀደም የታሪክ አምድ ሆኖ የሚኖር ታላቅ ድልና ገድል ሆነ፡፡ የአድዋ ድል የወቅቱ የአውሮጳውያን ቅኝ ገዢዎች ጭምር የኢትዮጵያን ሉአላዊነት አምነው የተቀበሉበት፣ ሌሎች የበባርነት ይኖሩ የነበሩ ጥቁር ህዝቦችም የነፃነት የተስፋ ጭላንጭል እንዲያዩና የሞራል ስንቅ እንዲሰንቁ ያስቻለ፣ ቅኝ ግዛትም በጥቁሮች ተጋድሎ መሸነፍ እንደሚችል ያስቻለና የአለምን ታሪክ የቀየረ የሰው ልጆች ታሪክ ነው።

124ኛውን ታላቁን የአድዋ ድል በዓል ስናከብር ትላንት በአባቶቻችን ነፍጥና ገድል ክብሯንና ነፃነቷን ያላስደፈረች ታፍራና ተከብራ የኖረች አገር እንዳስረከቡን ሁሉ እኛም የእምዬ ምኒልክን ጀግንነትና ወኔ ሱሪ ታጥቀን የጣይቱን ብልኅነትና አስተዋይነት ተክነን ታሪክ ወቃሽና ነቃሽ ሳንሆን ታሪክ ወራሽና ዳግም ታሪክ ሰሪዎች ሆነን፤ የአባቶቻችን ልጆች መሆናችንን ለልጆቻችን ነፃነትና ፍትኅ የሰፈነባት፣ እኩልነትና አንድነት የነገሰባት አገር ለማስረከብ በተግባር በመነሳት ሊሆን ይገባል።

አብን በድጋሚ እንኳን አደረሳችሁ ይላል!

Report Page