ANRSAG
ቲክቫህ ኢትዮጵያከሰኔ 15ቱ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ግድያ ወንጀል በተከሰሱ በእነ ሻምበል ማማር ጌትነት መዝገብ የሚገኙ 49 ተከሳሾች በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ክስ ቀርቦ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሽታ ምክኒያት ከሰኔ 22 ቀን 2012ዓ.ም ጀምሮ አስከ ሐምሌ 17 ቀን 2012ዓ.ም በተለያዩ የስራ ቀናት በመነጣጠል ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡
ሃምሌ 17 ቀን 2012ዓ.ም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በዋለው ችሎት የምስክር አሰማምን በተመለከተ ዐቃቤ ሕግን ጠይቆ ዐቃቤ ሕግም በትዕዛዙ መሰረት
1ኛ.የቀረቡት ክሶች አንደኛው ከሌላኛው ክስ ጋር ተያያዥነትና ቀጥተኛ ትስስር ያላቸው ከመሆናቸው ባሻገር የማስረጃዎች ይዘትም አንዱ ከሌላኛው ጋር በቀጥታ የተሳሰረ በመሆኑ የምስክሮች ተነጣጥሎ መስማት እንዲሁም የተከሳሾች ተነጣጥሎ መቅረብ የፍትህ መጓደልን የሚያስከትል በመሆኑ የማስረጃ የመሰማት ሂደቱ ሁሉም ባሉበት እንዲስተናገዱ፣
2ኛ.በአሁኑ ወቅት ሁሉም ተከሳሾች እና ምስክሮች በአንድነት ቀርበው ይሰሙ ቢባል እንኳን የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሽታን ተከትሎ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በግልፅ የሚጥስና በዚሁ ሳቢያ ምስክሮቻችንን ለማቅብ በእጅጉ የምንቸገር ስለሆነ ክቡር ፍርድ ቤቱ ይሄን ተረድቶ ወደፊት ሁኔታው በተሻሻለ ጊዜ የማስረጃው መሠማት ሂደት እንዲቀጥል እንዲታዘዝ፣
3ኛ.የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከመሠማቱ በፊት በወ/መ/ሥ/ህ ቁጥር 124/1 መሠረት የተከሳሾች የመከላከያ ምስክሮቻቸው ዝርዝር እና የመከራከሪያ ጭብጣቸውን እንዲያቀርቡ እንዲታዘዝለት አስተያየቱን አቅርቧል፡፡
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም ዐቃቤ ሕግ በሰጠው ምላሽ መሠረት ከተከሳሾች ጠበቆች የቀረበውን ማሳሰቢያ ካዳመጠ በኋላ ዐቃቤ ሕግ የምስክሮችን ዝርዝር በቁጥር የትኛው ምስክር በየትኛው ተከሳሽ ላይ እንደሚመሰክር በመለየት ለፍርድ ቤቱ ለሐምሌ 24 ቀን 2012ዓ.ም እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
በእነ ሻምበል ማማር ጌትነት መዝገብ የሚገኙ አጠቃላይ ተከሳሾች 55 ሲሆኑ ከስድስቱ ተከሳሾች ወስጥ አራቱ ተከሳሾች ላይ የጋዜጣ ጥሪ ተደርጓል፡፡በሁለቱ ተከሳሾች ላይ ሐምሌ 24 ቀን 2012ዓ.ም የጋዜጣው ጥሪ እንዲቀርብ የተቀጠሩ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡