#AMN

#AMN


ዓለምዓቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ በኢትዮጵያ የጋዜጠኞች መታሰር እንዳሳሰበው ትላንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደ መንበሩ ከመጡ ወዲህ በሚዲያ ነጻነት ድንቅ እምርታን እየታየ የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሁኔታዎች የመቀልበስ አደጋ ተጋርጦባቸዋል ብሏል።

በባለፈው አመት በብዙዎች ዘንድ ጨቋኝ የተባለውን የበጎ አድራጎትና የሲቪል ማህበራት ህግ መሻሻሉን እንዲሁም በእስር ላይ የነበሩ ጋዜጠኞችና ጦማሪዎች ተፈትተዋል ብሏል።

አለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ሲፒጄ ባወጣውም መረጃ አንድም ጋዜጠኛ በእስር የለለበት ሁኔታ መፈጠሩንና በአለም አቀፉ የፕሬስ ነፃነት ደረጃም (ወርልድ ፕሬስ ፍሪደም ኢንዴክስ) መሰረት አርባኛ ሆናም ነበር በማለት መግለጫው አስታውሷል።

ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሁኔታዎች ወደነበሩበት መለወጣቸው አሳሳቢ ሆኗል ይላል አምነስቲ።

በነዚህ ሳምንታት በአዲስ መልኩ ጋዜጠኞችን የማሸማቀቅና የማሰር ዘመቻ እንዳለ የገለፀው መግለጫው ተከትሎም በትናንትናው ዕለት የመከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የተቋሙንና የሰራዊቱን ስም እያጠፉ ያሉ የመገናኛ ብዙኃን ላይ ክስ ሊመሰርትም መሆኑንም አስታውቋል።

"የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አስተዳደር በፕሬስ ነፃነት ላይ በታየው እመርታ ከፍተኛ ሙገሳን የተቀበሉ ሲሆን ኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት ቀንን ለማስተናገድም በቅታ ነበር።" በማለት በአፍሪካ ቀንድ፣ በምስራቅና የግሬት ሌክስ የአምነስቲ ዳይሬክተር ጆዋን ናንዩኪ ተናግረዋል።

"ይህ በአዲስ መልኩ የተጀመረው ጋዜጠኞችን የማሰር ዘመቻ የታየውን የፕሬስ ነፃነት ወደ ኋላ የሚመልስ እርምጃ ነው።የኢትዮጵያ መንግሥት የታሰሩ ጋዜጠኞችን በቶሎ ይፍታ፤ ክሳቸውም አሁኑኑ ውደቅ ይደረግ" ብሏል አምነስቲ

የአስራት ቴሌቪዥን ዋና አዘጋጅ በሪሁ አዳነ እንዲሁም ከህትመት የወጣችው የዕንቁ መጽሔት የቀድሞ ዋና አዘጋጅ ኤሊያስ ገብሩ በመግለጫው ከተጠቀሱ ጋዜጠኞች መካከል ይገኙበታል።

ጋዜጠኞቹ የጸረ ሽብር ሕግ ተጠቅሶ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል። ይህ ሕግ ቀደም ያለው አስተዳደር የተቃውሞ ድምጽን ለማፈን ሲጠቀምበት የነበረ እንደሆነ መግለጫው አክሎ አትቷል።

መግለጫው የሰኔ 15ቱን ክስተት ተከትሎ የአብን አባላትና ሌሎች የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች መታሰራቸውንም ነቅፏል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

Report Page