ADDIS ABABA
#ADDIS_ABABA

በአዲስ አበባ ከተማ ካሉ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ጋር በተያያዘ ባለፈው ዓመት ከኦሮሚያ ክልላዊ ባንዲራ እና መዝሙር ጋር ተያይዞ የነበረው ሁኔታ ዘንድሮ በተለይም ደግሞ ከሰሞኑን ተባብሶ ነበር።
ይኸውም ችግር በተለያዩ ወገኖች እና በመንግስት አካላት የተለያየ ማባራሪያ እየተሰጠበት ነው። ወላጆችም የሚሉት አላችሁ።
ነዋሪዎች ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ያሉ ግለሰቦች፣ የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚፅፉ ግለሰቦች ፦
- የከተማው አስተዳደር ምንም በማያውቁ ተማሪዎች ላይ ያለፍላጎታቸው ጫና በማድረግ የኦሮሚያ ክልል መዝሙር እንዲዘምሩ፣ ባንዲራም እንዲሰቀል እና የበላይነትን ለማስፈን እየሰራ ነው ፤
-በአዲስ አበባ የሁሉም መቀመጫ ከሆነች ለምን የሌላው ቋንቋ አይሰጥም ? የሌላው ባንዲራ አይሰቀልም ?
- መንግስት በተለይም የኦሮሚያ ክልል ብልፅግና ሆን ብሎ አቅዶ የሚሰራው ስራ ዛሬ በግልፅ ካልተቃወምን ነገ መዘዙ አደገኛ ነው የሚል ሀሳብ ይሰነዝራሉ።
ለሚፈጠረው ቀውስ ሁሉ መንግስትን ተጠያቂ በማድረግም ከድርጊቱ እንዲታቀብ ተማሪዎችን እንዲዘምሩ እና የክልል ባንዲራ ያለፍላጎት እንዲሰቀል ማስገደድ መቆም አለበት ይላሉ።
በሌላ በኩል ፤ የከተማው አስተዳደር ፣ አስተዳደሩንም የሚደግፉ አካላት ፦
- ይኸው በአ/አ ትምህርት ቤቶች በአፋን ኦሮሞ የማስተማር ስራ አዲስ እንዳልሆነ ፣ በኢህአዴግ ጊዜ እንደጀመረ ፣ በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ተጀምሮ ፍላጎት በመጨመሩ መስፋፋቱን
- ባንዲራው እና መዝሙሩ የአ/አ ከተማ አስተዳደር የራሱ የአፋን ኦሮሞ ማስተማሪያ ስርዓተ ትምህርት ስለሌለው ከኦሮሚያ ክልል እንደተዋሰና እሱኑ እያስፈፀመ እንደሆነ፣
- አሁን ለመፅደቅ በሂደት ላይ ባለ ስርዓተ ትምህርት ውስጥ ሌሎችም ቋንቋዎች እንዲሰጡ እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ።
ይህ እየታወቀ፣ በቀጣይም ሌሎች ቋንቋዎችን ፣ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ለማድረግ ስራ እየተሰራ እንዳለ እየታወቀ ሆን ብሎ አጀንዳ በመፍጠር ከተማውን ለመበጥበጥ፣ በግጭት ገንዘብ ለማግኘት የሚፈልጉ አካላት ተማሪዎችን እያነሳሱ ፣ በብሄር እየከፋፈሉ ፣ እንደሆነ በዚህም ጉዳት እየደረሰ እንደሚገኝ ይገልጻሉ።
የከተማው ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፦

" በነገሮች ላይ ግልፅ መሆን አስፈላጊ ነው። ግልፅ ለመሆን ለእናተ የሚደበቅ ነገር የለም። ... ምንድነው እንደ አጀንዳ ፊት ለፊት የመጣው " የኦሮሚያ ባንዲራ እና መዝሙር በየትምህርት ቤቱ ተዘመረ ሁለተኛ ተሰቀለ ነው " ፊት ለፊት የሰማችሁት መቼ ነው ይሄ የጀመረው ከ5 ዓመት በፊት ነው ይሄ የለውጥ አመራር አልጀመረውም።
ያኔ ከማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ አዲስ አበባ ዙሪያ በጣም ከፍተኛ ውጥረት ሲሆን አንዱ የሚጠየቀው ፣ ለዘመናት ሲጠየቅም የቆየ ጥያቄ በመሆኑ ምክንያት መመለስ እንዳለበት ያውቅ ስለነበር ኢህአዴግ በወቅቱ አስጀመረው በአራት ትምህርት ቤቶች ላይ።
ሲጀመር አዲስ አበባ አፋን ኦሮሞ የምታስተምርበት ስርዓተ ትምህርት አልነበራትም መምህራኖች ታውቃላችሁ ይሄንን እውነት ያኔ ቀርቶ እስካሁንም አፋን ኦሮሞ / ቋንቋዎች የምናስተምርበት ስርዓተ ትምህርት አልጨረስንም አላፀደቅንም። ስርዓተ ትምህርት ከኦሮሚያ ተዋስን አፋን ኦሮሞ የሚሰጠው ኦሮሚያ ነው በዘመነ ኢህአዴግ ነው ።እዛ ላይ ስርዓተ ትምህርቱ ላይ ምን አለ ትምህርት ክፍል ከመጀመሩ በፊት የክልሉ መዝሙር ይዘመራል፤ የክልሉ ባንዲራ ይሰቀላል የሚል አለ።

ሙሉ ስርዓተ ትምህርቱን በመተግበር ነው እኚህ አራት ትምህርት ቤቶች የጀመሩት። አጀንዳ ያደረገውም የለም። በዚህ ምክንያት በተለየ ሁኔራ ኦሮሞ ይጠቀማል ተብሎ የታሰበ ነገር አልነበረም። ከዛ ተማሪዎች እያደር እየሰፉ መጡ ፣ ከየአካባቢው ፍላጎት ያላቸው ፣ በየአካባቢው ተመዝጋቢ እየበዛ መጣ ኦሮሞም የሆነ ያልሆነ መማር የሚፈልግ እየተመዘገበ መጣ።
እና እንዴት አድርገን ነው የካ ላይ የተመዘገበን ሄደህ ኮልፌ ነው የምትማረው የምንለው ? ለምን በአካባቢው ላይ ባለ ትምህርት ቤት ክፍል የማንከፍትለት ? በአካባቢው ትምህርት ቤት ላይ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር እንዲችሉ ትምህርት ቤት እየተከፈተ (በ403 ት/ቤት ውስጥ) በአፋን ኦሮሞ መማር ተጀመረ ሲጀመር ይኸው ካሪኩለም / ስርዓተ ትምህርት ነው አብሮ እየሄደ ያለው።
መማህራኖች፣ ትምህርት ቤቶች እጃቸው ላይ ያለው ስርዓተ ትምህርት እሱ ነው ስርዓተ ትምህርቱን ተግብሩ ተብሎ ስለተሰጣቸው ስርዓተ ትምህርቱ ላይ ያለውን ሙሉ ነገር እየተገበሩ መጡ ይኸው ነው።
ባለፈው ዓመት አንድ ትምህርት ቤት ላይ አጀንዳ ተነሳ ፤ ሰማንና ምንድነው ስንል ትምህርት ቢሮ አሁን የምንለውን መረጃ ሰጠን ወዲያው ምክር ቤት ስብሰባ ነበረን በምክር ቤት ስብሰባ ላይም ተነሳ ም/ቤት ላይ ሲነሳ በዚህ ምክንያት የኦሮሞ ህዝብ በተለየ ሁኔታ የሚያጋኘው ጥቅም የለም የኦሮሚያ ባንዲራ እዚህ ስለተውለበለበ ፣ በክልል ደረጃ እንዲውለበለብ የፀደቀ ባንዲራ ነው። መዝሙሩም የኦሮሚያ ክልል ክልላዊ መዝሙር ነው በክልሉ የተዘጋጀ ነው፤ እኛ ነን ሄደን ተውሰን ያመጣነው ስርዓተ ትምህርት ስላልነበረን እኛ ተውሰን ያመጣነው ነው እባካችሁ አዲስ አበባ ላይ ይህን አድርጉልን ብሎ የኦሮሞ ህዝብ የተለየ ጥቅም ጠይቆ እዚህ ውስጥ ጥቅም አገኛለሁ ብሎ ያመጣው አይደለም እና የራሳችንን የአዲስ አበባ ስርዓተ ትምህርት የተለያዩ ቋንቋዎችን ምናስተምርበት እንዲጠና ሰጥተናል ይሄ ይመልሰዋል። ከዛ ውጭ ይሄን ቀጥለው ይሄን አቀጣጥለው የሚመጡ አስተሳሰቦች እና ጥርጣሬዎች ስህተት ናቸው እናተ ባሰባችሁበት መንገድ ያደረገ የለም ብለን ለመረጠን ምክር ቤት በይፋ ተናግረናል።

እንግዲህ ስለ ኦሮሚኛ ቋንቋ ብቻና ከዛ ጋር ተያይዞ ተነሳ እንጂ የሶማልኛም እየሰጠን ነው አሁን የጀመርነው ፤ በጋሞን እየተሰጠ ነው። ሌሎችም አሉ ሰልፍ ላይ የገቡ። ብዙ ቋንቋ ማወቃችን ሃብት ስለሆነ። ኢትዮጵያውያኖች እሷን ስለምንመስል። ብዝሃ ቋንቋ ፣ ብዝሃ ባህል ፣ ብዝሃ እምነት ያለን ህዝቦች ስለሆን እንዴት ነው ኢትዮጵያውኒነትን የሚያጠፋው ይሄ ? እንዴት ነው ኢትዮጵያዊነትን ዝቅ አድርጎ የአንድ አካባቢን ወይም ሌላውን ከፍ አድረገ ተብሎ የሚታየው ?
አሁን የምናፀድቀው ስርዓተ ትምህርት ሁሉንም ቋንቋዎች እንዴት እናስተምር ነው ፤ እንኳን የራሳችንን የውጭዎችን እየተማርን ነው። የኛን ደግሞ እርስ በእርሳችን ለመተዋወቅ እና ለመቀራረብ እንጠቀምበታለን እንጂ አንጎዳም።
አሁን ደግማ ትምህርት ሚኒስቴርም ብዝሃን ልሳን ት/ቤት ውስጥ ያስፈልጋል ተማሪዎች ቢያንስ 3 ቋንቋ የሀገር ውስጥ መማር አለባቸው የሚል ፀድቋል መላው ክልል ላይ እየተተገበረ ነው።
አዲስ አበባ ይህን ስርዓተ ትምህርት እንዳፀደቀች ትሄድበታለች። ለማንኛውም 3 ጀምረናል። ከሶስት በላይም አለን። በዛ አይነት ሁኔታ ተጀመረ እንጂ አንድን ብሄር ተጠቃሚ ለማድረግ ፣ የሌላውን ብሄር ሳናነሳ ስለኦሮሞ ብቻ አንስተን ይሄኛውን በደንብ አድርጋችሁ ከፍ አድርጋችሁ ዘምሩት ተጠቀሙበት ለማለት አይደለም ስርዓተ ትምህርቱን ተውሰን ስላመጣን ብቻ አብሮ የመጣ ነው። ከዛ አንፃር ሌላ ጥርጣሬ ውስጥ መግባት ትክክል አይደለም።

...እዚህ ምክር ቤት ማብራሪያ የሰጠናቸው እየተሰራ ያለ የቤት ስራ መሆኑን ስለሚያውቁ አጀንዳ ስለሚፈልጉ አጀንዳ አድርገው ነገሩ ውሳኔ አግኝቶ ነገሩ ከእጃቸው ሳይወጣና ነገ አጀንዳ እንዲያጡ እንዳይሆኑ ዛሬ በየማህበራዊ ሚዲያው በተለያየ መገናኛ ብዙሃን ዘምተዋል።
ብዬ ነበር ፣ እኔ ጀግናው ፣ ይሄ ነው አሁን ሀገርን መከራ ያሳየው ፤ እኔ ነኝ የታገልኩልህ እኔ ነኝ ድምፅ ያሰማውልህ ... እየሰራን እንደሆነ ያውቃሉ እውነት ለመናገር ፤ ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ አጠናቆት ለውሳኔ እንድናየው እንዳቀረበልን በደንብ ያውቁታል ውስጥ አዋቂዎች አሉ፤ ውሳኔ ላይ ስንድረስ ሊያመልጣቸው ስለሆነ በምን ይግቡ አዲስ አበባ ፣በምን አጀንዳ ይጉበበት ? ስለዚህ ጀግኖች ለመሆን፣ ድምፅ ሆነንላችሁ ነበር ለማለት ፣ እንትን አድርገንላችሁ ነበር ለማለት ገንዝብ ከየት ይገኛል ግጭት ከሌለ እነሱ ስለልጆቹ ምን አገባቸው ስለገንዘባቸው እንጂ ... ስለዚህ መነገጃ ነው የሆነው። "
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ደግሞ ህፃናት በአፍ መፍቻ ቋንቋ ይማሩ በሚለው ዓለም አቀፍ ህግ በአዲስ አበባ በ2009 የአፋን ኦሮሞ ትምህርት በአራት ትምህርት ቤቶች መሰጠት የተጀመረው ብሏል።

በከተማው ካሉ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የአፋን አሮሞ ቋንቋ በብዛት በሚነገርባቸው 403 ትምህርት ቤቶች ከ120 ሺህ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በአፋን ኦሮሞ ይማራሉ።
የትምህርት ቢሮው ኃላፊ ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ ፦
" የሆኑ ት/ቤቶች ላይ ይሄንን ቋንቋ አንሰማም የሚል ይህ መዝሙር መዘመር የለበትም የሚል ጥያቄ ያነሳ አለ። ሌላ ትምህርት ቤቶች ላይ በተለይ አፋን ኦሮሞ ተማሪዎች የሚበዙበት ላይ ሌላ ጥያቄ። በአማርኛ የሚማሩ/ የአፋን ኦሮሞ ተማሪዎች ቁጥር ባነሰበት በባንዲራ መዝሙር አላማው አንድ ያደረገ ግን በተለያየ ስትራቴጂ መጥቶ የከተማውን ሰላማዊ መማር ማስተማር ማደፍረስ ነው። ይሄ ብቻ ሳይሆን ሌላ ትምህርት ቤት እርስ በእርስ ግጭት ወደ ትምህርት ቤት ማውደም የመቀየር ፣ አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ላይ የውጭ ኃሎች ገብተው የሚማሩ ተማሪዎችን ውዥንብር ውስጥ መክተት ከውጭ ነው ድንጋይ የሚወረወረው ተማሪ ደንግጦ ሲወጣ ከውሥጥ የሚወረውር ኃይል ይመጣል። "
#ፖሊስ

የአዲስ አበባ ፖሊስ በየትምህርት ቤቱ ከባንዲራ ጋር በተያያዘ ትምህርት እንዲስተጓጎል የሚመሩት አጅንዳ ተቀርፆ በቴሌግራም፣ በዋትስአፕ፣ ሌላ ሀገር ባሉ ሰዎች ጭምር የሚመራ ነው ብሏል።
ይህን የሚመሩትም ምሁራን እንደሆነ የገለፀው ፖሊስ በሂደቱ ጥቅማችንን እናስከብራለን ብለው አድሚን ግሩፕ በመክፈት በየትምህርት ቤቶቹ ቴሌግራም አለ ይሄ እጃችን ላይ ነው ተማሪዎችን የማነሳሳት ስራ ነው እየተሰራ ያለው ብሏል።
በአንድ በኩል የኦሮሚያን ባንዲራ አውርደው መሬት የጎተቱ አሉ፣ በአንድ በኩል ማንነቴ ተነካ በሚል የኢትዮጵያን ብሄራዊ ባንዲራን አውርደው ጎተተዋልን የሚለው ፖሊስ አንዳንድ ተማሪዎች ድርጊቱን እንዲቀርፁ ስማርት ስልክ ጭምር ተገዝቶ እንደሚሰጣቸው ድርሼበታለሁ ብሏል።
ከባንዲራ በተጨማሪ " የወልቃይት እና አዲስ አበባ ጉዳይ አንድ ነው " በሚል አጀንዳ ተቀርፆም ተሰጥቷል ይሄ ከተማውን የማተራመስ አጀንዳ ያለውና እና ወደ አደባባይ እስከመውጣትም የደረሰ ነው ሲል ገልጿል።

ተማሪዎች የእነሱ ጉዳይ እንዳልሆነ ይገባናል ነገር ግን ተልዕኮ ተቆጥሮ ነው የተሰጣቸው ብሏል። ይህ የሚሰጣቸው ትምህርት ቤት ውስጥ ረብሻ እንዲነሳ መሆኑን ገልጿል።
የፓርቲ ተልዕኮ ተሸክመው የሚሰሩ / ምርጫ ውስጥ ጭምር የተሳተፉ መምህራንም መኖራቸውን የሚያነሳው ፖሊስ እንደዚህ አይነት መምህራን መያዛቸውን አሳውቋል።
ወላጆች እና ተማሪዎች የቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባላት ምን ይላሉ ?
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰቦቹ በአዲስ አበባ ስላለው ሁኔታ እንዲነጋገሩና ሀሳብ እንዲለዋወጡ ባመቻቸው የኦንላይን መድረክ በርካታ ሀሳብ የተሰጠ ሲሆን ይኸውም እንደማከተለው ቀርቧል።
ቤዛ ሽፈራው ፦
" ሁለት የወንድሞቼ ልጆች የመንግስት ትምህርት ቤት ይማሩ። ከዳይሬክቱ በሚደረግ ጫና እንዲዘምሩ እንደሚገደዱና በተማሪዎች መካከል ደግሞ ኦሮሞ የሆነ ያልሆነ የሚል ክፍልል እንዳመጣ ይነግሩኛ ገና የ7ኛ እና 8ኛ ክፋ ተማሪዎች ናቸው ግን የሚያወሩትን መስማት ያስደነግጣል "
ጆን ዳሎል ፦
" የ12ኛ ክፍል ተማሪ ልጅ አለችኝ። በምንም ተዓምር ከኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊ መዝሙር ውጪ ሌላ መዝሙር እንድትዘምርም ሆነ ከፌዴራሉ ባንዲራ ውጪ ሌላ ባንዲራ እንድትሰቅል እኔ፣ እሷም፣ መላ ቤተሰቤም ፍላጎት የለንም።
ልጄ ብሔር ተኮር አስተሳሰብ እንዳይኖራት የቻልኩትን ያህል ደክሜያለሁ። አዲስ አበባ ውስጥ መወለዷን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ የክልሎች የብሔርተኝነት ጣጣ ሳይገጥማት በመኖሯ ደስተኛ ዜጋ ነበረች። ዛሬ ግን ብሔርተኝነት ት/ቤቷ ድረስ መጣ። በጣም አዝኛለሁ።
ብሔሬን ሳልጠቅስ በኢትዮጵያዊ ዜግነቴ ብቻ ከቤተሰቤ ጋር በደስታ ለመኖር ያለኝ ተስፋ በእጅጉ ተሸርሽሯል። ድህነት ይዞኝ እንጂ ልጆቼን ሰብስቤ ጥርግ ባልኩ። በአገሬ ሁለተኛ ዜጋ መሆን ካልቀረልኝ ለልጆቼ መልካም ሕይወት መስጠት ወደምችልበት ሌላ አገር በሔድኩ። "
ደስ ታቲሌስ ፦
" ትምህርቱን በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር እና የአንድ ክልልን ባንዲራን መስቀልና መዝሙር ማዘመር በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው።
ለምሳሌ አብዛኛዎችን የትምህርት አይነቶች የምንማረው በእንግሊዘኛ ነው። ነገር ግን የእንግሊዝን መዝሙር አልዘመርንም፣ ባንዲራቸውም በትምህርት ቤቶቻችን ላይ አልተሰቀለም።
ይህንን ያልኩት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወይንም በመንግስት የተገነቡት ትምህርት ቤቶች ላይ ነው።
የግል ትምህርት ቤትን አይጨምርም። አሁን ግን የኦሮሚያ ክልል መዝሙር እየተዘመረ እና ባንዲራው እየተሰቀለ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በራሱ ወጪ በሰራቸው ትምህርት ቤቶች ላይ ነው።
ሲቀጥል ቋንቋውን ማስተማርም ካስፈለገ የሌላውን ክልል መዝሙር እንዲዘምሩ በማስደረግ መሆን የለበትም።
አማርኛ ተናጋሪ የሆኑ ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሲማሩ እኮ የአማራ ክልል ባንዲራ አልተሰቀለም የአማራ ክልልን መዝሙርም አልተዘመረም።
አሁን እየታየ ያለው ነገር እና ለድርጊቱ የከተማ አስተዳደር እየሰጠ ያለው መልስ ፍፁም የተለያየ ነው። በአጭሩ የከተማ አስተዳደሩ የከተማው ተወካይ አይደለም። "
ሞላ ግዣቸው ፦
" የሰፍር ወገንተኝነትን ትተን እደ ሀገር ብናስብ ለልጆቻችንም ለሀገርም ይጠቅማል።
ትምህርቱ እደ ትምህርት ጉዳት የለውም ነገር ግን በመዝሙርና ባንዲራ ምክንያት አንድ ለትምህርት የወጣ ተማሪ ምንም በማያውት ይገላታሉ።
ከንቲባዋ እንደ ከንቲባነታቸው የሁሉም ቤሄር ተወካይ ናቸው ለሁሉም ቢስቡ ጥሩ ነው በተረፍ ሀገራዊ ፀሎት ያስፈልጋ እሱፈጣሪ ከልደረሰልን ለዜጋው የሚያስ ባለስልጣን ጠፍቷል። "
ነመር ሶን ፦
" በመጀመርያ ደረጃ እንዴት ነው የአንድ ሀገር ሰንደቅ አላማ ከክልል መለያ ጋር እኩል የሚያረገው ሁለተኛ የሚዘመረው መዝሙር(የክልሉ )ምንን ነው መሰረት አርጎ የተቀረጸው ስንል በዛ የክልል አስተሳሰብ ታጥረን እንደሀገር እንዳናስብ የሚያረግ ከትውልድ ላይ የሀገር ፍቅርን ስለሀገር ማሰብን የሚያጠፋ ለተወሰነ ግሩብ ብቻ መኖርን የሚሰብክ ነው ይህም ማለት የምናፈራው ትውልድ በመንደር የተጠረ አመለካከት ብቻ የያዘ የሀገር ትርጉምን ምንነት ግድ የማይሰጠው ይሆናል ከዚ ሁሉ ጊዜው አረፈደም ቆም ብለን ማሰብ አለብን ለማይረባ የጊዜ ፖለቲካ ብለን መጥፎ ነገር አንስራ። "
ሜሮን ታደሰ ፦
" እኔ እንደወላጅነቴ የምለው ይሄ በግድ የሚደረግ ነገር መቆም አለበት።
አአ የሁሉም ዜጎች መኖሪያ ሆና ሳለ የአንድ ብሄር የበላይነት ሊነግስባት አይገባም።
ደሞ ይሁን ቢባል እንኳን በፍቅር እና በሀሳብ የበላይነት ነው እንጂ አንዴት ሲቀጥል።
የመንግስት ባለስልጣናት የሚሰጡት መግለጫም በማን አለብኝነት እና በንቀት ሰለሆነ ልክ አይደለም።
ህዝብ ለጠየቀው ጥያቄ አግባብ ባለው መልኩ መልስ ማግኘት አለበት ከዚህ ጋር ተያይዞ ባልተረጋጋ ሀገር ፣ ለቅሶ ግድያ መፈናቀል የዜጎች በሰላም የመኖር መብት ተገፎ ሰቆቃ በሰፈነበት ሀገር ላይ ህዝብን የማረጋጋት እና ሰላም ማስከበር ስራ እንደመስራት ለህዝብ ሌላ አጀንዳ መስጠት እና ተማሪዎች ላይ ግፍ መፈፀም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያወግዘው ይገባል። "
ታምር አድማሱ ፦
" የመንግስት ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው አገር የሚረከቡት? እስቲ የግል ትምህርት ቤቶች ያዘምሩ። አንድም ባለሥልጣን ልጁን የመንግስት ት/ቤት አያስተምርም ስለዚህ የሚደበደቡትም ሆነ መከራ የሚያዩት የእኛ የድሆች ልጆች ናቸው ። ብልፅግና ለኢትዮጵያውያን unfit ነው። "
ደረጃ ለማ ፦
" እኔ የተማሪ ወላጅ ነኝ እሁድ እለት ት/ቤት ስብሰባ ጠርተውን ወደዳችሁም ጠላችሁም ባንዲራው ይሰቀላል መዝሙሩም ይዘመራል ብለው ነው ያስፈራሩን።
በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው ልጆቼን የማስተምረው?ይሄ ጉዳይ ከትምህርት ጋር ምን አገናኘው?
ትምህርት ቤት እኮ የዕውቀት ማዕከል እንጂ የፓርቲ ጽ/ቤት አይደለም።
እኛ እያበላናቸው እያለበስናቸው እንዴት የነሱብናል ብለዋል ነገር ግን ቢያበሉቸው እና ቢያለብሱአቸው በህዝብ ገንዘብ እና በዕርዳታ ገንዘብ እንጂ የትኛውም ባለስልጣን ከኪሱ አውጥቶ አይደለም ይሄ ማስፈራሪያ ሊሆን አይገባም። "
ባሚ ባም ፦
" አዎ እንደተባለው ለገንዘብና ፖለቲካን ብቻ ዓላማ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ብዙ አካላት አሉ፡፡ ግን ይኸ እንዲፈጠር ያደረገው ዋናው መንግስት የተባለው አካል ነው፡፡
የዚህም ማሳያ፡-
1. ህዝቡም ተማሪዎችም እያሉ ያሉት አንድ ሀገር አንድ ባንዲራ ነው ያለን ለእሱ እንዘምራለን እንገዛለን ነው ያልነው እንጂ በቋንቋ አይማሩ ያለ ማንም የለም እንዲሁም አንማርምም አላልንም፤ መንግስት ሆን ብሎ ለፖለቲካው ሲል የአዲስ አበባ ልጅ የኦሮሚያን እህትና ወንድሞችን እንደምንጠላ እንደማንወዳቸው አድርጎ ይናገራል፤ ለዚህም ማሳያ ከዚህ በፊት ጠ/ሚ አብይ አህመድ ፓርላማ ላይ የተናገረው ንግግር ማየት እንዲሁም ሰሞኑን ከንተብዋ የምትናገረው፡፡ 2. ት/ት ፖሊሳቸው ከኦሮሚያ ነው የተወሰደው አሉ የአ/አ ስለሌለው ይኸ ማለት እኮ እኛ ባለሥለጣናት እንተኛ ከዚህ በፊት የተሠራውን ከሌላ ቦታ አምጥተን እንጠቀም መን ማለት ነው የመረጥናቸው እኮ ሊያገለግሉን እንጂ ለቀልዱብን አይደለም፡እሺ እንበልና ሲያመጡ እንኳን ለአ/አ ህዝብ በሚሆን መልኩ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ኮፒ ነው። አፈጻጸሙ በጉልበትና በጥይት አይደለም መሆን ያለበት እንዴት አንድ መንግስት ነኝ ከሚል አካል ከ5-20 ዓመት ዕድሜ ያሉ ልጆች ላይ ያን ያክል ዱላ ይውርድባቸዋል፡፡
3. እየተወሰደ ያለው መፍትሔ ከልብና ትክክለኛ አይደለም ምክንያቱም እየተሰበሰቡና ሀሳብ እየሰጡ ህዝቡንና ተማሪውን የሚያሳጡ ዝም ብለው ጥቅም ፈላጊዎች ናቸው እንጂ ትክክለኛ ወላጆች አይደሉም ምክንያቱም የሽሮሜዳ ህዝብ ተሰብስቦ የሰጠውን ሀሰብ ምንግስት አልተቀበሉም እነሱ የሚፈለ‹ጉት የእነሱን ሀሳብ ብቻ የሚደግፍ ነው፡፡ በዛ ላይ የሚናጉሩት ከእነሱ የማይጠበቅ ነው እንዴት ሰው እኛ እየመገብናቸው ነው እንደዚህ የጠገቡት ይባላል ከኪሳቸው አውጥተው ነው ወይስ በጀቱ ከኦሮሚያ ክልል ነው የአ/አ ህዝብ ግብር አይከፍልም ማለት ነው፡፡ "
ስንዱ ፦
" ኦሮምኛ ቋንቋን ቢማሩ ችግር የለውም። ባንዲራና መዝሙሩ ግን በፍፁም አይቻልም ይሰቀል ከተባለ አዲስ አበባ የሁሉም ነውና የሁሉም ክልል ባንዲራ ይሰቀል።
የሁሉም ክልል መዝሙር እስቲ እዩት የሚካሰስ ና የሚገፋፋ እከሌ ገደለኝ የሚል ነው።
ይህንን ለቀጣይ ትውልድ ማስተማርና ማስተላለፍ ሲቀጥል በቤቴ ልጆቼ ከኦሮሞ የተወለዱ እኔ አማራ ነኝ ማን ማንን ገደለ ነው የምል ልጆቻችንን በፍቅር እናሳድግ ተውንማ መርዝ በትዳር በቤተሰብ በሰፈር በብሄር አትዝሩ። "
Hila G. ፦
" I really hope the next generation is smarter than all of us. Learning a second language is actually good for kids; it will make them smarter.
While foreigners come here and learn our language, we don't want to learn each others language and despise one another. If the Italian Government showed interest to teach kids Italic, everyone would be happy and accept it.
Learning another language is a blessing, not a curse. we should stop putting fire to everything we hear.
It is sad how if each and everyone of us get ask about Ethiopia, we say we are all about acceptance, tolerance and love. But we cover our face with social media and show the hate we feel for one another. "
ኤስ ኤም ፦
" በአፍ ብቻ ኢትዮጲያ አትበታተንም አንድ ትሆናለች እያሉ እያወሩ በተግባር ግን የሚከፋፍል ስራ እየተሰራ እንደሆነ ዋናው ማሳያ ነው።
ቋንቋ መማሩና ማወቁ ጥሩ ነው ግን የ አንድ ክልል ባንድራ ካልሰቀላችሁ የ አንድ ክልል መዝሙር ካልዘመራችሁ ማለት የ ባለስልጣኖቻችን የ ብሄርተኝነት ጥግ የት ላይ እንዳለ ማሳያ ነው።
አላማው ቋንቋ ማስተማር ከሆነ ፦
1, የ ክልል ባንድራ መስቀሉን ምን አመጣው
2, የ ኢትዮጲያ ቢሄራዊ መዝሙርን በ ኦሮመኛ ቋንቋ ተርጉሞ ዘምሩ ማለት ይቻል ነብር የ አንድ ክልል መዝሙር ዘምሩ ከማለት። "
ሀብታሟ ከበደ ፦
" ት/ቤቶችን የፖለቲካ ታርጌት መምቻ ለምን እንደሚደረግ አይገባኝም፡፡
ኦሮሚኛ ቋንቋ በት/ቤቶች ውስጥ መሰጠቱ ምንም ችግር የለውም ባይ ነኝ፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ ህዝብ ከተለያየ ቦታ የመጣና እዛው ተወልዶ ያደገ እርስበርሱ ደግሞ ተቻችሎ የሚኖር ህዝብ በመሆኑ ተማሪዎችም የቤተሰቦቻቸውና የአካባቢያቸው ነፀብራቅ ስለሆኑ የሚያውቁትን የለመዱትን የኢትዮጵያ ባንዲራ መስቀል በቂ ነው፡፡
ልጆቻችን የማያውቁትን ዘረኝነትና የዘረኝነት ጥላቻ እንዲፈጠርባቸው ለምን እናደርጋለን፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር የመንግስት ት/ቤቶችን የሚያስተዳድረው የአዲስ አበባ ህዝብ ስለመረጠው መሆኑንና ከአዲስ አበባ ህዝብ በሚሰበሰብ ግብር የሚያስተዳድሩ መሆኑን መረሳት የለበትም፡፡
የአዲስ አበባ ህዝብ ደግሞ የአፍ መፍቻ ቋንቋው አማርኛ ሆኖ ሳለ ተማሪዎች የማያውቁትን የኦሮሚያ ህብረ መዘመር እና ባንዲራ እንዲሰቀል ማድረግ ስሜት የማይሰጥ ነገር ነው፡፡
እዛ ውስጥ የኦሮሚኛ ተማሪዎች አሉም ከተባለ ከኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር አይበቃንም ካሉ ለብቻቸው እንዲዘምሩ ይደረግ፡፡ ስለሆነም ለተማሪዎቻችን እንደ አንድ ሰብጀክት የኦሮሚኛ ቋንቋ ለሁሉም ት/ቤት ቢሰጥ መጥፎ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ነገር ግን አግባብ ያልሆኑ ፖለቲካዊ ነገሮች መስተዳድሩ ከማድረግ ቢቆጠብና ልጆቻችን በተረጋጋ መንፈስ ትምህርታቸውን እንዲከታተው ሰላማዊ የሆነ አካባቢ መፈጠር የመስተዳድሩ ሀላፊነት ነው የሚል አስተያየት አለኝ፡፡ "
በዳኔ ደሬሳ ፦
" እኔ ሁለት ልጆች አሉኝ ፊንፊኔ ነው የማስተምረው ፤ ለዚህ ችግር ብቸኛው ምክንያት በከተማው ያለው የኦሮሞ ፎቢያ እና በሀገሪቱ ውስጥ ያለ የአንድ ብሔር (አማራ) ፓርቲዎች ድብቅ አጀንዳ የማዘጋጀት ፍላጎት ነው።
እመኑኝ ነገሮች በዚህ መንገድ ከቀጠሉ ሁላችንም በተለይ የፊንፊኔ ነዋሪዎች ትልቅ ችግር ይገጥመናል። በነገራችን ላይ ፊንፊኔ የፌደራል መንግስት መቀመጫ ብትሆንም የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማም ነች። መቻቻል ለሁላችንም ይበጃል። "
አሳልፈው ነጋሽ ፦
" አንድ ክልል የራሱን ባዲራ በራሱ ክልል ነው ማስቀጠል ያለበት አዲስ አበባ የሁሉም እደመሆኗ ከፌደራል ማንዲራ ውጪ ሌላ ማንዲራ መስቀል ለምን አስፈለገ ? "
ሰለሞን ዱሬሳ ፦
" ብዙ ሰዎችን ያልተረዱት ነገር አዲስ አበባ ፊንፊኔ በሚል የኦሮሚያ ክልል መቀመጫም መሆኗን ነው። ከተማዋ የፌዴራልም የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ ናት ይሄ ደግሞ ዛሬ ሳይሆን ከኢህአዴግ ጊዜም የነበረ ነው።
የኦሮሞ ህዝብ ብዙ ጥያቄ በጠየቀበት ወቅት ነው ኢህአዴግ ትም/ቤት ውስጥ ይህን ያስጀመረው በእርግጥም ጥያቄ የኛ የወላጆች ጥያቄ ነው ልጆቻችን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር አለባቸው። በተለያዩ ፖለቲከኞች ይህን ጉዳይ በማራገብ ጥላቻ መዝራቱ ችግሩን ያባብሰዋል እንጂ አይቀርፈውም።
የኦሮሞ ህዝብ በአዲስ አበባ ጉዳይ ብዙ ጥያቄ እንዳለው በገሃድ የሚታወቅ ነው። በዚህ ጉዳይ ተማሪዎችን ማነካከት ተገቢ ስላልሆነ የአፋን ኦሮሞ ተማሪዎችን ባሉባቸው ግቢዎች ቢዘመር ቢሰቀል ክፋት የለውም። "
ጊፍቲ ደምሴ ፦
" አንዳንድ ሰዎች ያላቸው ጥላቻ የከፋ ነው። እና ልጆቻችን በአፍ መቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ እንፈልጋለን። መዝሙር መዘመር እና ባንደራ መሰቀልን እያገናኙ በህዝብ ላይ ጥላቻ የሚዘሩ እና ነገ እልቂት የሚጠሩ የሀገር ጠላቶች ናቸው። ሁሉንም ነገር በተነሳ ቁጥር ተረኛ፣... ምናምን እያሉ ህዝብን መፈረጅ ትክክል አይደለም ፤ አደገኛም ነው። በተለይ ፖለቲከኞች ህዝቡን ፍቅር ቢያስተምሩት ጥሩ ነው። "
@tikvahethiopia