#ABH

#ABH


የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ከፍተኛ ባለስልጣናት የ174.6 ሚሊዮን ብር ክስ ቀረበባቸው

ኤቢኤች ሰርቪስስ ኃ/የተ/የግል ማህበር የተባለው የማማከርና የምርምር ተቋም በከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ እና በኤጀንሲው አምስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ የብር 174.6 ሚሊዮን የካሣ ክስ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 241863 ከሰውና ከሰነድ ማስረጃዎች ጋር አቅርቧል፡፡ 

ካሣውን ከኤጀንሲው ጋር በአንድነትና በነጠላ ይከፍሉ ዘንድ የተከሰሱት ባለስልጣናት የቀድሞው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ የነበሩትና አሁን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አንዱአለም አድማሴ፤ የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት ሞታ፤ የኤጀንሲው የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ታረቀኝ ገረሱ፤ የኤጀንሲው የእውቅና አሰጣጥ ዳይሬክተር አቶ አብይ ደባይ እና የኤጀንሲው የህግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ታደሰ ናቸው፡፡

ክሱ እንደሚያሳየው ጅማ ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢው ጅማ ከተማ ሆኖ በሌሎች ቦታዎች ካምፓስ የመክፈት መብት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 240/2003 ተሰጥቶት እያለ፣ እንዲሁም ከሌሎች አገልግሎት አቅራቢዎች የድጋፍ አገልግሎት የማግኘት መብቱ በአዋጅ ቁጥር 650/2001 ተጠብቆለት እያለ ኤጀንሲውና የኤጀንሲው ከፍተኛ ባለስልጣናት የዩኒቨርሲቲውንና የኤቢኤችን ግንኙነት በፌስቡክና በጋዜጣዊ መግለጫ ለመሻር ሞክረዋል፡፡ ጅማ ዩኒቨርሲቲና ኤቢኤች ነሐሴ 13 ቀን 2011 ዓ.ም በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተከሳሾቹ ይህንኑ ተግባራቸውን እንዲያርሙና ህዝብና መንግስትን ይቅርታ እንዲጠይቁ ማሳሰባቸው ይታወቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኤቢኤች ለተከሳሾች የሰጠውን የመጨረሻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ወደ ጎን በመተው ዩኒቨርሲቲውና ኤቢኤች ለዘመናት ያካበቱትን መልካም ስምና ዝና የሚያጎድፉ የሐሰት መግለጫዎችን በመስጠት የተቋማቱን ስም የማጥፋት ተግባር በይፋ ፈፅመዋል፡፡

ተከሳሾቹ የኤጀንሲውን የፌስቡክ ድረ-ገፅ ጨምሮ በልዩ ልዩ የመገናኛ ብዙኃን ባሰራጩት መረጃ እንዲሁም ነሐሴ 16 ቀን 2011 ዓ.ም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ኤቢኤች ሰርቪስስ ኃ/የተ/የግል ማህበር የተባለው ድርጅት መንግስት የማያውቀው ድርጅት ነው ከማለት አልፈው ዩኒቨርሲቲው በአዲስ አበባ በከፈተውና ከኤቢኤች የድጋፍ አገልግሎት በሚያገኝበት ካምፓስ የሚማሩትን ተማሪዎች መንግስት እንደማያውቃቸው፣ አንድ ተማሪ ለትምህርት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚከፍል ጭምር ገልፀዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር አንጋፋው ጅማ ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ በሚሰጠው የትምህርት ፕሮግራም ተማሪዎችንና ወላጆችን የሚያጭበረብር አስመስለው ዩኒቨርሲቲውና ኤቢኤች ማስታወቂያ ለሚያስነግሩባቸው የመገናኛ ብዙኃን የማስፈራሪያ ደብዳቤ በመፃፍ ፕሮግራሙ እዲቋረጥ ሙከራ አድርገዋል፡፡

ኤቢኤች በክሱ እንዳመለከተው ተከሳሾቹ በዚህ የስም ማጥፋት ተግባራቸው ተማሪዎችና ወላጆች በሁኔታው እንዲደናገጡና በአዲስ አበባ በሚሰጠው የትምህርት ፕሮግራም ላይ አመኔታ እንዲያጡ፣ አዲስ ተማሪዎችም ስጋትና ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው አድርገዋል፡፡ ተከሳሾቹ የዩኒቨርሲቲውንና የኤቢኤችን ስም በማጥፋት በኤቢኤች ሌሎች ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ አድርገዋል፡፡ 

ስለሆነም ኤጀንሲው በአዋጅ ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ ትክክለኛ ባልሆነ መረጃ፣ በኤቢኤች መልካም ስም እና ዝና ላይ ጉዳት በማድረሱ የህግ ኃላፊነት አለበት፤ የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች የሆኑት ቀሪዎቹ ተከሳሾች ደግሞ የመንግስት ሥልጣናቸውን ከህግ ውጪ (ያለአግባብ) በመጠቀም በተለያዩ ማህበራዊና መደበኛ የመገናኛ ብዙኃን የኤቢኤችን መልካም ስም እና ዝና በማጉደፋቸው ጥፋተኛ ናቸው፡፡ 

ኤቤኤች በክሱ ተከሳሾቹ በፈፀሙበት የስም ማጥፋት ተግባር የደረሰበትንና የሚደርስበትን በድምሩ የብር 174,636,893.40 /አንድ መቶ ሰባ አራት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሠላሳ ስድስት ሺህ ስምንት መቶ ዘጠና ሦስት ብር ከአርባ ሣንቲም/ የጉዳት ካሣ ተከሳሾቹ በአንድነትና በነጠላ እንዲከፍሉት፣ እንዲሁም ጉዳቱ ከዚህም እንዳይከፋ ተከሳሾቹ ስሙን ባጠፉበት የመገናኛ ዘዴ መልካም ስሙን እንዲያድሱና ሌሎች አስፈላጊ የእርምት እርምጃዎችን እንዲወሰዱ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡

#ABH

Report Page