#AA

#AA


“አረና” የመገንጠል አላማ ያላቸውን ሃይሎች አጥብቄ እታገላለሁ አለ!

በትግራይ የተለየ አስተሳሰብን የማፈን እንቅስቃሴ እንዲቆም ጠይቋል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየተቀነቀኑ ያሉ ፀረ አንድነት ዘመቻዎችን እቃወማለሁ ያለው አረና ትግራይ ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ፤ በትግራይ የመገንጠል አላማ ያነገቡ አደረጃጀቶች መበራከታቸው አሳሳቢ ነው ብሏል፡፡ 

ፓርቲው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ባወጣው መግለጫ፤ የትግራይ ክልል ህዝብን ከሌሎች ክልል ህዝቦች ጋር ለማጋጨት በመንግስታዊ ሚዲያዎችና በማህበራዊ ድረ ገፆች ጥረት እየተደረገ መሆኑን በመጠቆም፤ በማንኛውም መልኩ ህዝቦችን ለማጋጨት የሚደረጉ ጥረቶችን በጥብቅ እንደሚያወግዝ አስታውቋል፡፡ 

በጥላቻና ባልተገቡ ዘመቻዎች መፈናቀል የደረሰባቸው የትግራይ ተወላጆች እርቅ ተፈጽሞ ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ የጠየቀው አረና፤ የወሰን ጥያቄዎችም በውይይትና መግባባት መፈታት እንዳለባቸው ገልጿል፡፡ 

አሁን በተፈጠረው ቀውስና እሱን መነሻ በማድረግ በተከሰተው ጽንፈኝነት የመገንጠልና የመበታተን አጀንዳ እንደ ዋነኛ መፍትሔ የሚያቀርቡ ልሂቃን የተሳሳቱና ህዝቡን ለከፋ ችግር የሚዳርጉ መሆናቸውን በመግለጫው የጠቆመው አረና፤ ይህን አስተሳሰብ አጥብቆ እንደሚታገል አስታውቆ፤ የብሔር ብሔረሰቦች መብትን የማያከብሩትንም በእኩል እታገላለሁ ብሏል። በትግራይ ክልል እየተነሱ ያሉ የወረዳ እንሁን ጥያቄዎችም ተገቢው ምላሽ እንዲሰጣቸው የጠየቀው ፓርቲው፤ በክልሉ የተለየ አስተሳሰብን የማፈን እንቅስቃሴም እንዲቆም አሳስቧል፡፡ 

ኢህአዴግ በለውጡ መጀመሪያ ላይ ያደረጋቸው ማሻሻያዎችን ያደነቀው አረና፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የለውጡን ዘላቂነት አጠራጣሪ ያደረጉ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ጠቁሞ ለውጡ ዘላቂነት እንዲኖረውም ፍኖተ ካርታው በግልጽ ሊታወቅ እንደሚገባ አረና አስገንዝቧል። ቀጣዩን አገራዊ ምርጫ አስመልክቶም በትግራይ ያለው አፈና ምርጫ ለማድረግ የማያስችል በመሆኑ አፈናው እስካልቆመ ድረስ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ሁኔታ አለ ብሎ እንደማያምን አስታውቋል፡፡ 

Via አዲስ አድማስ

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page