#A
ጋዜጠኛውን ለማስፈታት የቀረበው አቤቱታ ውድቅ ሲደረግ በሽብር ተጠርጣሪዎች ላይ 28 ቀናት ተፈቀደ፦
በሕግ ሥልጣን ያልተሰጠው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሽብር ተግባር ወንጀል ተጠርጣሪን በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ሕገወጥ መሆኑ ተጠቅሶ፣ ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩን ነፃ ለማውጣት (Habeaus Corpus) ለፍርድ ቤት የቀረበው አቤቱታ ውድቅ ተደረገ፡፡ በሽብር ወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩት የአብን የሕዝብ ግንኙነትና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ በአራት ተጠርጣሪዎች ላይ የተጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ 28 ቀናት ተፈቀደ፡፡
ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ምሽት 2፡40 ሰዓት ላይ በማይታወቅ ግብር ኃይል በቁጥጥር ሥር ውሎ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ታስሮ የሚገኘው ጋዜጠኛው እስር ሕገወጥ በመሆኑ፣ ከእስር እንዲለቀቅ በጠበቃው አቶ ተማም አባቡልጉ አማካይነት ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ስምንተኛው ፍትሐ ብሔር ችሎት የቀረበው አቤቱታ ውድቅ ተደረገ፡፡
ፍርድ ቤቱ አቤቱታው በቀረበለት ወቅት የአዲስ አበባ ፖሊስ ጋዜጠኛውን ለምን እንዳሰረው? ወይም ለምን እንደማይለቀው? ሐምሌ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠዋት ጋዜጠኛውን ይዞ በመቅረብ እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር፡፡ ሐምሌ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ሁለት የፖሊሶች አባላት ጋዜጠኛውን ሳይዙ የጽሑፍ ምላሽ ለፍርድ ቤቱ ሰጥተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በጽሕፈት ቤቱ የተቀበለውን የፖሊስ ምላሽ፣ ‹‹አዲስ አበባ ፖሊስ ስለታሰረው ግለሰብ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ የያዘው የፌዴራል ፖሊስ በመሆኑ የሚመረምረው እሱ ነው፤›› የሚል መሆኑን ገልጿል፡፡
ፍርድ ቤቱም፣ ‹‹የማይመለከታችሁ ከሆነ ለምን መጣችሁ?›› የሚል ጥያቄ ቢያነሳም፣ ፖሊሶቹ ምንም የሚያውቁት ነገር እንዳልነበረ ጠቁመው፣ ታሳሪውን እንዲያቀርቡ ከታዘዙ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡
የጋዜጠኛው ጠበቃ ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹት፣ ያመለከቱት በሕግ ሥልጣን ያልተሰጠው የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ በሕገወጥ መንገድ ደንበኛቸውን ማሰሩን መሆኑን አስታውሰው፣ ደብዳቤ እንዲያደርሱ የቀረቡት ፖሊሶችም እነሱን እንደማይመለከት ማረጋገጣቸውንና በደብዳቤም በመግለጻቸው፣ ደንበኛቸው በዕለቱ እንዲፈታላቸው ወይም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ታስረው ቀርበው እንዲጠየቁላቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም ሐምሌ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ፖሊስ ጋዜጠኛውን ይዞ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ፖሊስ በቀጠሮ ቀንና ሰዓት ጋዜጠኛውን ይዞ ቀርቧል፡፡ ታስሮ የሚገኘው በአዲስ አበባ ፖሊስ መሆኑንና ምርመራ እያደረገበት የሚገኘው ግን የፌዴራል ፖሊስ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ጋዜጠኛው ስለአያያዙ ተጠይቆ የያዘውም፣ እየመረመረውና ፍርድ ቤት ያቀረበውም የአዲስ አበባ ፖሊስ መሆኑን ተናግሯል፡፡ የጋዜጠኛው ጠበቃ ለፍርድ ቤቱ እንደተናገሩት፣ አዲስ አበባ ፖሊስ የማይመረምረውን ተጠርጣሪ ለምን ያስራል? ብለው ይኼ በሕግ ሥልጣን እንዳልተሰጠው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሰው በአደራ አይቀመጥም፡፡ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ በአደራ እንዲቀመጥ ተደንግጎ የሚገኘው ዕቃ ብቻ በመሆኑ ደንበኛዬ እዚሁ በችሎት ይለቀቅልኝ፤›› በማለት ተከራክረዋል፡፡
ይዘውት የቀረቡት አዲስ አበባ ፖሊስ አባላት፣ በተጠርጣሪ ላይ ምርመራ እያደረገ የሚገኘውና ለተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ቀጠሮ የጠየቀው ፌዴራል ፖሊስ መሆኑን አስረድተው ራሱ ቀርቦ እንዲያስረዳ እንዲታዘዝ ጠይቀዋል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ የፌዴራል ፖሊስ ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ ቀርቦ እንዲያስረዳ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡
ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. የፌዴራል ፖሊስና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ፍርድ ቤት ቀርበው እንዳስረዱት፣ ታሳሪውን ግለሰብ በሽብር ድርጊት ወንጀል እንደጠረጠሩትና ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ እንደጠየቁበት አስረድተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በብይኑ ጋዜጠኛ ኤልያስ ፍርድ ቤት መቅረቡን በራሱ ቃል ስላረጋገጠ፣ አካልን ነፃ ለማውጣት የቀረበውን አቤቱታ እንዳልተቀበለው በመግለጽ ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል፡፡
የጋዜጠኛው ጠበቃ ግን ባቀረቡት የመከራከሪያ ሐሳብ እንደተናገሩት፣ በማመልቻቸው በዋናነት ያመለከቱት የደንበኛቸው እስር ሕገወጥ መሆኑን ነው፡፡ ‹‹ሕገወጥ እስራት ሕገወጥ ነው፡፡ መርዛማ ፍሬም መርዛማ ነው፤›› ስለሚባል፣ ፍርድ ቤቱ እንዲወስንላቸው የጠየቁት ደንበኛቸው ‹‹ፍርድ ቤት ቀርቧል? ወይስ አልቀረበም?›› ሳይሆን፣ ሕገወጥ እስራት መኖሩ እንዲረጋገጥላቸው መሆኑንና ሌሎች ፍሬ ጉዳዮች ቀጥለው የሚመጡ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በብይኑ ላይ ይግባኝ ስለማለታቸው ጠበቃ ተማምን ሪፖርተር አነጋግሯቸው፣ ‹‹ይግባኝ እንላለን፡፡ ሕገወጥ እስር መሆኑን ፖሊስ ጭምር አረጋግጦት እያለ ዝም አንልም፤›› ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከተሞች ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ከተፈጸመው ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ግድያ ጋር በተያያዘ፣ የሽብር ተግባር ወንጀል በመፈጸም በተጠረጠሩት የአብን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ክርስቲያን ታደለና የአማራ ዴሞክራሲያን ኃይሎች ንቅናቄ (ኢዴአን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ላይ ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ 28 ቀናት ተፈቅዶለታል፡፡
አቶ ክርስቲያን ወጣቶችን በሕገወጥ መንገድ እንደሚያደራጁ፣ ከአዴፓ ኃላፊዎች ጋር እንደሚገናኙና ከተፈጸመው ግድያ ጋር በተያያዘ እንደጠረጠራቸው ፖሊስ አስረድቷል፡፡
አቶ ክርስቲያንም ወጣቱን ማደራጀት ሥራቸው መሆኑንና ከእስርም ሲለቀቁም እንደሚቀጥሉበት አስረድተው፣ ከአዴፓ አመራሮችም ጋር አብረው በጋራ ለመሥራት ስምምነት እንዳላቸውና መግለጫም አብረው እንደሚሰጡ አስረድተዋል፡፡ እሳቸው ፖሊስ እንዳለው ሳይሆን የህሊና እስረኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
የኢዴአን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችን በሚመለከት ፖሊስ መሣሪያ ታጥቀው ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ እንደያዛቸው ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ለፍርድ ቤቱ በሰጡት ምላሽ፣ ወደ አዲስ አበባ የመጡት በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሊሰጡ መሆኑንና የታጠቁት ሽጉጥም ሕጋዊ ፈቃድ ያለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝን ክርክር ከሰማና የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ካየ በኋላ ፖሊስ ያመለከተው በአግባቡ መሆኑን በመጠቆም፣ ከሐምሌ 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ የሚቆጠር 28 ቀናት ለተጨማሪ ምርመራ በመፍቀድ ለነሐሴ 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ዓርብ ሐምሌ 19 ቀን 2011 ዓ.ም. የአብን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በለጠ ካሳ ፖሊስ ‹‹ትፈለጋለህ›› ብሏቸው ከሄዱ በኋላ፣ መታሰራቸውን አብን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ስለተጠረጠሩበት ጉዳይ ግን ያለው ነገር የለም፡፡ በተመሳሳይ ጥርጣሬ ታስረው የነበሩት የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ባልደረባ የነበሩት አቶ የወግሰው በቀለን ጨምሮ ስምንት ተጠርጣሪዎች ሐምሌ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ አቶ የወግሰው የተጠረጠሩበት ጉዳይ ሽብር መሆኑ ቀርቶ፣ የአዲስ አበባ ባላደራ ምክር ቤት (ባልደራስ) የሚባለው አባል መሆናቸውን ፖሊስ መግለጹን ጠበቃቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ሌሎቹ ሰባት ተጠርጣሪዎች ላይ ግን የተለወጠ ነገር አለመኖሩንም ጠቁመዋል፡፡ ፖሊስ ተጨማሪ ጊዜ የጠየቀ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ አምስት ቀናት ብቻ በመፍቀድ ለሐምሌ 23 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
Via ሪፖርተር