ፍቅር♥አይቀናም ይነበብ!

ፍቅር♥አይቀናም ይነበብ!

UTOPIA ☜ ለአስተያየት
Share and like

ፍቅር❤️ አይቀናም!


(አጭር ታሪክ)


 ©ዘ-ፍቅር™


በህይወት ጉዞ ላይ…

ቢሰፋ ጎዳናው- ቢተልቅ መንገዱ

ፍቅርና ቅናት አንድ ላይ አይሄዱ!

“…ወይኔ!...” ትላለች ቤቲ “…ወይኔ!...”

ክብ ቀይ ፊቷ ላይ ያሉት ጎንጮች የቲማቲም ድልህ

መስለው፣ በሊፒስቲክ በቀለሙት ስስ ከንፈሮቿ መሃል የሌባ

ጣቷን ከታ፣ በጥርሶቿ ጥፍሯን በንዴት እየቀረጠፈች፣ ህዝበ

አዳም በሞላው ሰፊ ካፌ ውስጥ አሻግራ ጥግ ላይ ዳኒና አፍ

ለአፍ ገጥሞ የሚያወራት ቆንጅዬ ልጅ ላይ አይኖቿን ተክላ

እያየች … በቅናት ዛር ውስጥ እየተንዘፈዘፈች “…ወይኔ!..”

ትላለች።

ዳኒ ፊት ለፊት ያለችው ቆንጆ …. ትከሻዋ ላይ ተዘናፍሎ

የተኛውን ረጅም ጸጉሯን ወደ ኋላ እየመለሰች በሳቅ

ስትፍነከነክ ዳኒም አብሯት እንዲሁ ሲስቅ፣ ከሩቅ የምታየው

የሁለቱ ሳቅ ውስጧን በንዴትና በቁጣ እያንቀጠቀጣት

ታስባለች “…ምን አድርጌው ነው? ድሮም ሰውን ማመን!....

ለወንድ ልብን መስጠት!....” በዳኒና በማታውቃት ባላንጣዋ፣

የፍቅሯ ተናጣቂ መሃል ከምታየው የክህደት ክብ ተነስታ

ሰውን ሁሉ፣ የአዳም ዘርን ባለማመን መስቀል ላይ፣

በጥርጣሬ መስማሮች ትቸነክራለች “…ድሮም ሰውን ማመን፣

በተለይ ደግሞ ወንድን!...” ትላለች።

ቀጥላም … እሷ አሳቻ ስፍራ ላይ ሆና ተደብቃ የምታያቸውን

እነሱ የማያይዋትን የክህደት ደቀ መዝሙሮች መመልከቷን

ትቀጥላለች።

“….አይደረግም፣ አታዳርገውም ዳኒ…” ድንገት ጮኸች፦

በዙርያዋ ያሉት ሁሉ ዞር ብለው እስኪያዯት ድረስ። በቁጣ

ያስጮሃት ዳኒ በፈገግታ ለቁንጅዬዋ ልጅ በሹካ ከኬኩ ቆርሶ

ሲያጎርሳት፣እሷም ምላሹን ለዳኒ ስታደርስ አይታ ነው።

ቤቲ ከዚህ በላይ የምትታገስበት አቅም አልነበራትም። የቅናት

ዛሩ አእምሮዋን ሲቆጣጠራት፣ ደረቷ ላይ በእልህ አንዳች

ነገር መጥቶ ሲሰነቀር፣ አይኖቿ በሃዘን ያቆሩትን የእንባ

እንክብሎች ማዘል ሲያቅታቸው…. የእንባዋ ክብልሎች

ከማዘያው ላይ እየወረዱ ጉንጮቿ ላይ ሲንከባለሉ፣ ካፌው

ውስጥ መቆየት አልቻለችም። ከንፈሯን በንዴት ነክሳ…

እንባዋን እያዘራች “….ድሮም ሰውን ማመን!....” ለእራሷ

ከራሷ ጋር እንደ ታመመ ሰው እያወራች መንገዷን ጀመረች፦

ዳኒና እሷ ተከራይተው ወደሚኖሩበት ኮንደሚንዬም።

*

*

*

ቤቲ ብቸኛ ነበረች። ፍቅሮችን፣ ትዳሮችን፣ ቤተሰቦችንና

ሌሎችንም ሁሉ አቅፋ በያዘች ህይወት በምትባል ሰፊ አዳራሽ

ውስጥ አንድ ራሷን ይዛ የምትኖር፣ ብቻዋን የምትወጣ

የምትገባ ቀይ፣ የደስ ደስ ያላት፣ አጠር ያለች፣ ሁሉ ነገሯ

በልኳ ተመጥኖ የተሰራ ወጣት ነበረች። ከሰባት ቢሊዬን

ህዝብ በላይ በሚርመሰመስባት ምድር ላይ ቤቲ አንድ

ነጠላዋን ብቸኝነት በሚባል ካባ ውስጥ ከትታ ስትመላለስ

ኖረች፦ ዳኒ እስኪመጣ ድረስ።

ህይወትን አታምናትም። ለምን?...ገና የአፍላ ህጻን ሳለች

ከእሷና ከወንድሟ ዮኒ ወላጆቿን የፍቅርና የእንክብካባያቸውን

ማር ሰፈፍ በቅጡ እንኳን አጣጥማ ሳትጨርስ አከታትላ

ቀምታታለች።

ህይወትን በጥርጣሬ ታያለች? ምክንያት? ሌሎች እኮዮቿ

በሚቦርቁበት ዘመን ላይ እሷና ወንድሟን ግን ካ’ንዱ የገጠር

ከተማ ወደ ሌላው የቅርብና የሩቅ ዘመዶቿ እንደ ኳስ

ሲቀባበሏቸው አመታት አልፈው በመጨረሻም እንደ አይኗ

ብሌን የምት ሳሳለት ወንድሟ የት እንኳን እንደደረሰ ሳታውቅ

ላይገናኙ ተለያይተዋል። ቤቲ ወንድሟን ፈልጋ አስፈልጋ

ስታጣው ተሰፋ ቆርጣ ከተወች አመታት አለፉ።እንደ ልጅ

የሮጠችበት፣ ገመድ የዘለለችበት፣ ‘…ጭንና ወገብ…’ እያለች

ሱዚ ያጠላለፈችበት፣ አዋራው እስኪጨስ ድረስ ተጫውታ

የዋለችበት ቀን ትዝ አይላትም። ህይወት ከምትባል መራር

የጉዞ ኡደት ትዝ የሚላት ወላጃቿን የቀማት አውሬው ሞት

ነው፣ የምታስታውሰው በ’ርሃብና እርዛት ያደረችባቸው ረጅም

ሌሊቶች፣ የሰዎች የቁጣና “ስለቸሺን” ብለው የሚነግሯት

አይኖች ነው ። ለቤቲ ይህቺ ሕይወት የምትባል ነገር የሆነች

በሴት የተመሰለች የአስቆሮቱ ይሁዳ አይነት ነገር ነበረች።

ይህ ሁሉ ነገር ግን ነበር ነው። በዳኒ መምጣት ወደ ኃላ

የተረሳና ነበር የሆነ ታሪክ ነው።

ከጥቂት አመታት በፊት አንድ ቀን አንድ ጠቆር ያለ፣ ረጅምና

የወንዳወድ ሰውነት ያለው፣ ተጫዋች ልጅ ቤቲ በመስተንግዶ

ተቀጥራ የምትሰራበት ትንሽዬ ካፌ ውስጥ መጣ። ነገር ግን

ካፌው ውስጥ ብቻ አልነበረም የመጣው፦ የቤቲ ህይወት

ውስጥም እንጂ። ልጁ ዳኒ ወደ ቤቲ የጥርጣሬና የፍርሃት

ህይወት ውስጥ መጣና ጭል ጭል የምትል አነስተኛ የፍቅር

ብርሃን ረጨባት። በማግስቱም ሌላ ብርሃን… በሶስተኛው

ቀንም ሌላ… ከዛም ሌላ….የቤቲ ህይወት በዝግመተ ሂደት፣

ቀስ እያለ በፍቅር ብርሃኑ ይወረስ ጀመር። የዳኒ ፍቅር ብርሃን

ሲጨምር ቤቲም በደስታና እምነት ሙቀት ልቧ ይቀልጥ

ጀመር። ሙቀቱ ሲበዛ ቀስ ብላ ለአመታት የተጀቦነችበትን

የብቸኝነትን ካባ አወልቃ አርቃ ሰቀለችው። አሁንም ሙቀቱ

ከፍ ሲል የጥርጣሬ ስካርፏንና፣ የአለማመን ሹራብን

ከህይወቷ ላይ “ሂዱልኝ!” ብላ አወላልቃ ወረወረች።

“…እመኚኝ ብስኩት… (ዳኒ ለቤቲ የሰጣት የቤት ስሟ ነው)

…. እመኚኝ ብስኩትዬ...” አላት።

ቤቲ አመነችው።

“….ብስኩት ላልተውሽ፣ በዘመኔ ሁሉ ፍቅሬን ልሰጥሽ ቃሌ

ነው!...” ብሎ እጇን ይዞ ማለላት።

ቤቲ ቃሉን በደስታ ተቀበለችው።

ተጋቡ።

እንደ ቃሉም እንዲሁ ዳኒ ፍቅሩን እንደ ሃምሌ ዝናብ የቤቲ

ልብ ላይ አንዴ በስሱ፣ ሌላ ጊዜ በዶፉ ያወርደው ጀመር፦

በየቀኑ ሳያቋርጥ። ቤቲ በዚህ አለም ላይ አይታ በማታውቀው

ሁኔታ በዳኒ ተወደደች። ሲወጣ ሲገባ ‘…ብስኩትዬ ማር!...”

እያለ ግንባሯን እንደ ታዳጊ ህጻን በከንፈሩ ሲስም፣ በማለዳ

ተነስቶ ቁርስ ሰርቶ ሲመግባት፣ በቀን አራት አምስት ጊዜ

እየደወለ በፍቅሩ ሲያፍለቀልቃት፣በሚሄድበት ሁሉ ውብ

ሚስቴን ብስኩትን ተዋወቁ እያለ ኮርቶባት ሲያኮራት፣

ደስታዋን አባዝቶ ሲሰጣት፣ ሃዘኗን እየሸራረፈ ሲጥልላት …

ሌላም ብዙ ብዙ ነገር ሲያደርግ ....ዳኒን ከልቧ ከማፍቀር

ውጪም አማራጭ አልነበራትም። ቤቲ ዳኒን በሚያስፈራ

ሁኔታ አፈቀረችው። ሁሉ ነገር ሰላምሰላምና ፍቅርፍቅር ብቻ

እያለ ያለፉት አመታት ነጎዱ።

*

*

*

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ግን ቤቲን የያኔ የድሮውን

ያለማመንና የጥርጣሬ ልጅ በልቧ ውስጥ የሚቀስቀስ ነገር

መሆን ጀመረ። ይህም ዳኒ ያለወትሮው ከሷ ደበቅ እያለ

የሚለዋወጠው ቴክስት ነው። እያደር ቤቲ እንደገና ህይወትን

መጠርጠር ጀመረች። ወላጆችን የቀማችው፣ ከወንድሟ ዮኒ

ጋር የለየቻት፣ በመከራ ደራሽ ውሃ ከዚህ እዚያ እያላጋች

ስትጫወትባት የኖረችው ህይወት እንደገና ዳኒን ልትቀማት

እያደባች አሾልቃ የምታያት መሰላት። ቤቲ ጥርጣሬዋ ከፍ

ሲል በጥንቃቄ ዳኒን መከታተል ጀመራ...መረጃ ብታነፈፍም

ምንም ማግኘት አልቻለችም። ከሶስት ቀናት በፊት ግን ስልኩ

ላይ አንድ ቴክስት አየች። እዚሁ የዛሬው ካፌ ውስጥ

እንዲገናኙ የሚጋብዝ ቴከስት ነው፦ ከሆነ ሰው የተላከ።

በድንጋጤ የምትለውና የምታደርገው ቢጠፋትም ወዲያውኑ

ግን ለዳኒ ምንም አላለችውም። እውነቱን ለማወቅ ክትትሏን

ቀጠለች። በማግስቱ አሳቻ ጊዜ ጠብቃ የዳኒን ስልክ እንደገና

ቼክ ስታደርግ ቴክስቱ delete ተደርጏል። አሁን በትክክል የሆነ

የተደበቀ ነገር እንዳለ ገባት። ጥርጣሬዋን በአይኗ

ለማረጋገጥም ዛሬ ተደብቃ መጣች። ካፌው ውስጥም

ያየችው ባላንጣዋን፣ የፍቅሯን ቀማኛና ዳኒን ነው።

የተመለከተችው ሁለመናዋን በቅናት ዛር የሚያንዘፈዝፍ

ይህንን ጉድ ነው።

*

*

*

ማታ ላይ ሁልጊዜ ቤት በሚገባበት ሰዐት ላይ ዳኒ መጣ። “…

ብስኩትዬ ማር!...” የኮንዶሚንዩሙን በር እጁ ላይ ባሉት

ቁልፎች ባንዱ እየዘጋ


ተጣራ።

ቤቲ ኪቺኑ ውስጥ እራት ለማዘጋጀት ሽንኩርት እየከታተፈች

ነው። መልስ አልሰጠችውም።

“…ብስኩትዬ ሰላም ነሽ?...” ዳኒ ያለወትሮዋ ዝም ማለቷ

አስደንግጦት ፈጠን ፈጠን እያለ ተጠጋትና ግንባሯን ሊስማት

ሲል ቀስ ብላ ፊቷን አዞረች።

“…የኔ ቆንጆ ፍቅር ምነው?... ሰላም ነው?...” ሁኔታዋ

የበለጠ አስደንብሮት

ቤቲ በንዴት እሳት በሚተፉ አይኖቿ ቀና ብላ አየችው። ፊቱ

ላይ ምንም አይታይም። ያው ዳኒ ነው። ‘…ምን አይነት ጉድ

ነው? ምንድን ነው ይሄ? እንዴት ነው ማስመሰል

የሚችልበት?...’

“…ብስኩትዬ … ማሬ ምን ሆንሽብኝ?...” አስተያየቷና

የአይኖቿ ማፍጠጥ ግራ ያጋባው ዳኒ

“….የት ነበርክ ዛሬ?...” ባፍንጫዋ አየር በሃይል እየሳበች፣

በዛው በቁጣ አይኖች እያየችው።

“….ምን ማለት ነው የት ነበርክ ብስኩትዬ? …ስራ ነዋ…ሌላ

የት…”

“…ዝጋ!...” አቋረጠችው “…ቅድም ስምንት ሰዐት ላይ ካፌው

ውስጥ ከማን ጋር ነበርክ?...” ቤቲ አሁንም አፍጥጣ።

ዳኒ በድንጋጤና በገረሜታ አይኖቹ ተከፍተው ለአፍታ

የሚለው ጠፍቶት ሲያያት።

“…ተናገር!...” ከንፈሯ እየተንቀጠቀጠ፣ ፊቷ የቲማቲም ድልህ

መስሎ

ዳኒ ፈገግ አለ። “…ብስኩትዬ ተረጋጊና ሁሉንም ነገር ልንገርሽ

እሺ…”

ቤቲ ፈገግታው የበለጠ ደሟን አንተከተከው። “….ውሻ…

ከሃዲ ውሻ ነህ …አትረባም…” በንዴት ቀኝ እጇን አወናጭፋ

ልትመታው ስታነሳ ሽንኩርት ስትከትፍበት የነበረው ቢላዋ

እስካሁን በእጇ ላይ መሆኑን ፈጽሞ ረስታዋለች። ዳኒም

ፈጽሞ አልተዘጋጀም። አልጠበቀውም። ወደ ግራ አንገቱን ዞር

ሲያደርግ ስሉ ቢላዋ አንገቱን ላይ ያለውን ትልቅ የደም ስር

አገኘው። ከዛ ቡሃላ የሆነው ሁሉ እጅግ የሚዘገንን ነበር።

ደም እንደዚህ በሃይልና በቁጣ እየገነፈለ ይፈሳል። አንገቱ

ላይ ወደ ላይ የሚቡልቀለቀው ደም ከምድር በሃይል ተነድሎ

እንደሚወጣ ምንጭ ነበር።

በሰከንዶች ውስጥ በቅናት ዛር ፈረሶችና፣ በቅጽበታዊ ቁጣ

ሳታስበውና ሳትጠብቀው ያደረገችው ነገር ቤቲን በድንጋጤ

በድን አድርጓት አንገቱን በሁለት እጆቹ ይዞ የሚፈሰውን ደም

ለማቆም የሚታገለውን ዳኒን አፍጥጣ ታየው ጀመር። ዳኒ

የሚፈሰውን ደም ለማቆም የሚያደርገው ትግል የሚረዳው

አልነበረም። ደሙ የለበሰውን ነጭ ሸሚዝ በደማቅ ቀይ

እያቀለመ በብዛት ይወርዳል። ቀስ ብሎ ግድግዳውን ተደገፎ

ቁጭ አለና እየደከመ በሚሄድ ትንፋሹ ለዘላለም ከውስጧ

የማይወጡ ቃላትን ይነግራት ጀመር።

“…የል…ጅቷ ስም ሄ…ዊ ነው። የወ …ን ድም …ሽ የ..ዮ…. ኒ

ሚ….ስት ናት። ለ..ል…ደትሽ ቀን ሁ..ለ…ታችሁን አገናኝ…ተን

ሰርፕራ…ይዝ ልናደር…ጋችሁ ነበር። ብስ ኩትዬ ማ ር …እ …

ወ ድ ሻ….” መጨረስ ግን አልቻለም። አንገቱ ዘንበል አለ።

የቤቲ ልደት መቼ ነው?

ከነገ ወዲያ ነው።

እሷ ያላስታወሰችውን ልደቷን አስቦ፣ በህይወቷ ትልቁን ስጦታ

ሊሰጣት የነበረው ልጅ ማን ነው?

ይህን ሊሰጣት የነበረው ፍቅሯ ዳኒ ብቻ ነው።😭😭😭😭😭😭😭


አስተያየታችሁን @yohanes02 ላይ ፃፉልኝ እንዲሁም ሼር በማድረግ ሌሎች እንዲማሩበት የበኩሎትን ይወጡ🙏

@zeelove @zeelove @zeelove