የፀሐይግርዶሽ እና ዓይናችን

የፀሐይግርዶሽ እና ዓይናችን

Dr. Tena - Bethel


🖐🖐🖐 ሰላም የዶክተር ጤና ቤተሰቦች!! 🖐🖐🖐

በነገው እለት የየፀሐይ ግርዶሽ በ ኢትዮጵያ እንደሚታይ ከመዘገቡ ጋር ተያይዞ የፀሐይ ግርዶሹን ለማየት ሲባል ቀጥታ ወደ ፀሐይ ማየት ስለሚያስከትለው ጕዳትና እንዴት መከላከል እንደሚቻል በአይን ስፔሻሊስት ሐኪም የተሰጠ ማብራሪያ ቀጥሎ እናቀርባለን፡፡

 

 የፀሐይ ግርዶሽ እና ዓይናችን


በፀሐይ ጨረር የሚመጣ የ ሬቲና (የብርሃን መቀበያ) ጉዳት ይባላል። ይኽ ጉዳት የሚከሰተው በቀጥታ ፀሐይን ወይም የፀሐይ ግርዶሽን ለማየት ሲሞከር የሚከሰት ችግር ሲሆን የብርሃን መቀበያችን(ሬቲና) ላይ ጉዳት በማድረስ ዕይታችንን ይቀንሳል፡፡

ጨረሩን ለአንድ ደቂቃ እንኳን ያዩ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በዚህ ምክኒያት የሚከሰተው ጉዳት ለመዳን ከ3-6 ወር ሊፈጅ ይችላል። እንደዛም ሆኖ ግን ወደቀድሞው የዕይታ አቅም ሳይመለስ ዘለቄታዊ የዕይታ መቀነስ ሊያስከትል ይችላል።

የዚህ ችግር ዋና መንስዔ ከፀሐይ የሚወጣው ጨረር ቢሆንም በብረት ብየዳ ጊዜ ከሚወጣ ጨረር፣ ከትክክለኛው ኃይል በላይ የሚለቀቁ ሌሎች የብርሃንና የሌዘር ምንጮችም ሊከሰት ይችላል። ጨረሩን (በተለይ ልዕለሐምራዊ-ለ Ultraviolet -B )በቀጥታ የብርሃን መቀበያና መጋቢ ህዋሳት ላይ ኬማካዊ ለውጥ በመፍጠር ጉዳት ያስከትላል።

አጋላጭ ሁኔታዎች

·        ህጻናትና ወጣቶች የተፈጥሮ ሌንሳቸው ሞራ ያልጀመረው ስለሚሆን በቀጥታ ፀሐይን ሲያዩ ሊጐዱ ይችላሉ፡፡

 

·        ባንጻራዊነት እድሜያቸው የገፋ ሰዎች ላይ ሞራ ስለሚጀምር ወደ ዓይን የሚገባው ጨረር ይቀንሳል፡፡

 

·        ሆኖም የሞራ ቀዶ ጥገና አድርገው አርቲፊሻል ሌንስ የገባላቸው ሰዎች ወደ ፀሐይ ቀጥታ ማየት የለባቸውም፡፡

 

·        የአዕምሮ ህመም ወይም ውስንነት ያላቸው ሰዎች በብዛት ወደፀሐይ ቀጥታ ሊያዩ ስለሚችሉ ጥንቃቄና እርዳታ ያሻቸዋል፡፡

 

·        ወንዶች ከሴቶች የበለጠ ተጋላጭ ናቸው

 

·        ነጮች ከጥቁሮች የበለጠ ተጋላጭ ናቸው

 

·        በብየዳ ጊዜ ተገቢውን መነጽርና የፊት ጋሻ አለመጠቀም ለተመሳሳይ ጉዳት ይደርጋል።

ምልክቶች

 

·        በዚህ ችግር የተጠቁ ሰዎች ለጨረሩ በተጋለጡ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ብዙ ጊዜ በሁለቱም ዓይን ላይ፦

-         የዕይታ መቀነስ

-         በዕይታ አድማስ ውስጥ የሚታይ ጥላ

-         የዕይታ ቅርጽ መዛባት (የሚያዩት ነገር የተጣመመ ፣ በመጠን ያነሰ ወይም የተለቀ መምሰል)

-         በተጨማሪም በግንባርና በጭንቅላት ጐን አካባቢ ራስ ምታት ሊከሰት ይችላል፡፡

ይህን ችግር መከሰቱን ለማወቅ የዓይን ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በማይክሮስኮፕ በማየት ወይም ሬቲናውን ፎቶ በማንሳት ወይም OCT በሚባል መሳሪያ በማየት ችግሩ መከሰቱን ማረጋገጥ ይቻላል።

ህክምናው

ምንም እንኳን ይህን ችግር ለማከም የተለያዩ መድኃኒቶች (ስቴሮይድን ጨምሮ) ቢሞክሩም አጥጋቢ ውጤት አላመጡም፡፡ ስለዚህ ዋነኛው ነገር ችግሩ እንዳይከሰት አስቀድሞ መከላከል ነው ።

 

መከላከያ መንገዶች

 -         ፀሐይን ፣ ፀሐይ ግርዶሽን ፣ የብየዳ ጨረርና ሌሎች ኃይለኛ ብርሃን የሚረጩ ነገሮችን በቀጥታ አለማየት፣

 

-         በፀሐይ ግርዶሽ በዓመታት አንዴ የሚታይ በመሆኑና ብርሃኑም የቀነሰ ስለሚመስለን ለማየት ሊያጓጓን ይችላል... ሆኖም በፍጹም በቀጥታ ማየት የለብንም

 

-         ህጻናት፣ የአዕምሮ ህመምና ውስንነት ያለባቸውን ሰዎች ወደ ፀሐይ እንዳያዩ መከላከል፣ ጥንቃቄ ማድረግ፣ መርዳት

 

-         የፀሐይ ግርዶሽን ለማየት ዓላማ የተሰሩ ISO እና CE ሰርቲፊኬት ያላቸው ልዕለሐምራዊ (UV) ንዑሰ - ቀይ (Infrared) ጨረሮችን 99 - 1ዐዐ% የሚከላከሉ ጥቁረታቸው (shade no 12) የሆኑ መነጽሮችን ብቻ መጠቀም ይቻላል።

 

-         ሆኖም እንደነዚህ ዓይነት መነጽሮች በሀገራችን ስለመግባታቸው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ቱሪስቶች ወደእኛ ሀገር ሲመጡ ይዘው ይመጡ ይሆናል፡፡

የተለመዱትን የፀሐይ መነጽሮች ማድረግ ይቻላል ?

 

·        በፍጹም! ምንም እንኳን የፀሐይ መነጽሮች ጐጂ ጨረሮችን መቀነስ ቢችሉም በቀጥታ ወደ ፀሐይ ለማየት ተብሎ ስላልተሰሩ ተጨማሪ ጨረሮችን ወደ ዓይን ያስተላልፋሉና በፍጹም እነዚህን መነጽሮች ተማምነው ወደ ፀሐይ/ ፀሐይ ግርዶሽ ማየት የለብዎትም፡፡

 

·        ጥቁር መነጽር መሆኑ ብቻ ጨረሮቹን ይከላከላል ማለት አይደለም።

-         መንግስት ይኽን አጋጣሚ ተጠቅመው ጥራታቸው ያልተረጋገጠ መነጽሮች እንዳይሸጡ ቁጥጥር ማድረግ ይገባዋል።

 

ምንጭ:- ዶ/ር ጸደቀ አሳምነው

(የዓይን ሐኪም፣ የቪትሮ-ሬቲና ድህረ-ስፔሻሊስት)

 

ይህንን መረጃ ሼር በማድረግ ለሌሎች ያጋሩ!!

                            

            ተጨማሪ የጤና መረጃ እንዲደርሶ፦

        የዶክተር ጤና ቴሌግራም ገፅ

                          t.me/DoctorTena

        የዶክተር ጤና ፌስቡክ ገፅ፦

                        fb.com/DoctorTenaEthiopia

 

Report Page