“የምትመከር ወንድሜ ኾይ! እድለኛ ነኽ!”

“የምትመከር ወንድሜ ኾይ! እድለኛ ነኽ!”

ቴዎፍሎሳውያን ፡ ሚዲያ
“የምትመከር ወንድሜ ኾይ! እድለኛ ነኽ!”
ቴዎፍሎሳውያን ሚዲያ | ግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም.        
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ እንደተናገሩት


"ድክመትኽን እና ጥፋትኽን የሚነግሩኽን ሰዎች ቃላት እንደ ስድብ ወይም እንደ ጸያፍ ቃል ለምን ትቆጥራለኽ? እንዲኽ የተግሣጽ ቃላት አንተነትኽን ለማስተካከል የተሰነዘሩ ገንቢ ቃላት እንደሆኑ አድርገኽ ለምን አትቆጥራቸውም?

ስለነዚኽ ቃላት ብለኽ የምትቆጣና የምትበሳጭ ከሆንኽ ግን ውዳሴን የምትሻና ሰዎች ኹሌ ስለ አንተ መልካም የኾነውን ብቻ እንዲናገሩልኽ የምትወድ ሰው ነኽ ማለት ነው። ወንድሜ ኾይ! ሰዎች ሲገስጹኽ ደስ ሊልኽ ይገባል። ይኽ ለአንተ መልካም ነውና። ለምትጠባበቀው የዘለዓለም ሕይወት ያነጥርሃል ያበቃሃልም።

አንድ ሰው በወቀሰኽ ጊዜ ምናልባት የዚያ ሰው ወቀሳ የእግዚአብሔር ወቀሳ ሊኾን ስለሚችል አመስግነው። ለማለት የፈለኩት የሚወድኽ እግዚአብሔር ያን ሰው ወደአንተ ልኮ ሊመራኽና ክፉ ሥራኽን በመግለጥ ዳግመኛ እንዳታደርገው ሊከለክልኽ ወዶ ይሆናልና። ምናልባትም እግዚአብሔር በቅርቡ ወይም ከብዙ ጊዜ በፊት ስለፈጸምካቸው ኃጢአቶች በእነዚኽ የዘለፋ ቃላት ሊቀጣኽ ፈልጎ ይኾናል። ነቢዩ ዳዊት የስድብ ቃላትን በሰማ ጊዜ በትሕትና በመኾን እንዲኽ ነበር ያለው። "እግዚአብሔር ዳዊትን ስደበው ብሎ አዝዞታልና ይርገመኝ።..." (2ኛ ሳሙ 16፥10)

ስለዚኽ ውድ ወንድሜ ሆይ!

አንድ ሰው ሲገሥጽኽ የቀደመ ኃጢአትኽን በማስታወስ ከተግሣጽ በላይ መኾን የማትችልና ብቃት የሚጎድልኽ ሰው መሆንኽን አስብ። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር በአንተ አድሮ የተዋጣለት ሥራ ይሠራል አንተ ግን ይኽን ራስኽን ለማመጻደቅና ለማጽደቅ ዓይነተኛ መሣሪያ አድርገኽ ትጠቀምበታለኽ። በዚኽ ጊዜ ይኽ ትዕቢትኽ እና ኩራትኽ ለውድቀት እንዳይዳርግኽ እግዚአብሔር እርሱ በፈቀደ አንድ የሚዘልፍህ ሰው ይልክብኻል። ይኽ ኩራት እና ትዕቢትኽን በመጠኑም ቢኾን በመቅረፍ በቆይታ ሊያስተካክልኽ ይችላል። እንዲኽ ያሉት የተግሣጽ ቃላት ፍቅር እና መታገስን ስለሚያስተምሩኽ ለአንተ ትምህርት ነውና ደስ ይበልኽ።"


“ለነገዋ ፡ ቤተ ፡ ክርስቲያን ፡ ዘመኑን ፡ የቀደሙ ፡ አገልጋዮች ፡ ማፍራት”
ብፁዕ ፡ ወቅዱስ ፡ አቡነ ፡ ቴዎፍሎስ ፡ ፓትርያርክ ፡ ዘኢትዮጵያ


Report Page