የማሕሌተ ጽጌ ፍጻሜ የተፈጸመ ናሁ ትርጓሜ
November 6, 2020 by @YeBiruk ዲያቆን ቡሩክ ይርጋ ዘውብ✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
አሜን
✍"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
ቀናችንን በጸሎት እንጀምር
✥••┈┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈┈••✥
የማሕሌተ ጽጌ ፍጻሜ የተፈጸመ ናሁ ትርጓሜ
✥••┈┈┈••●◉ ✞ ◉●••┈┈┈••✥
❖ በመጨረሻዋ የጽጌ እሑድ የቤተክርስቲያን ሊቃውንት፣ በእናት ቤተክርስቲያን የተሰበሰቡ ምእመናን ኅሊናቸው በወላዲተ አምላክ ፍቅር ነድዶ፣ በምስጋናዋ ጣዕም ልቡናቸው ረክቶ ይልቁኑ በማሕሌተ ጽጌ ፍጻሜ ላይ የመጨረሻዋን የማሕሌተ ጽጌ ውዳሴ በመፈጸሟ አመስግኖ በቃኝ የማይል ልቡናቸውን ቅር ቢለውም ደግሞም የእመቤታችን በረከቷን የምትሰጥበት ምሽት ነውና መንፈሳቸው በደስታ ተመልቶ ይኽቺን ውዳሴ በማሕሌት ያደርሳሉና፤ ልዩ ምስጢሯን ንባቧንና ትርጓሜዋን እነሆ
✍“ሕብረ ሐመልሚል ቀይሕ ወጸአድዒድ አርአያ ኰሰኰስ ዘብሩር ተአምርኪ ንጹሕ በአምሳለ ወርቅ ግቡር ተፈጸመ ናሁ ማሕሌተ ጽጌ ሥሙር አስምኪ ቦቱ ንግሥተ ሰማያት ወምድር ከመ በሕጽንኪ ያሰምክ ፍቁር”
👉የሚያብረቀርቅ ቀይና ነጭ ቀለም ያለው አርአያው የብር ዝንጒርጒር የኾነ ንጹሕ ተአምርሽ በወርቅ አምሳል የተሠራ ነው፤ እነሆ የተወደደ (መልካም) ማሕሌተ ጽጌ ደረሰ ተፈጸመ፤ የሰማይና የምድር ንግሥት ማርያም ሆይ የተወደደ ልጅሽ በጒያሽ (በዕቅፍሽ) እንዲጠጋ (እንዲደገፍ፣ እንዲንተራስ) በርሱ አማጥኚ) ሊቁ አባ ጽጌ ድንግል ይኽነን ልዩ ምስጋና የተናገረው ከሙሴ ቃል ተነሥቶ ሲኾን ይኸውም ላይ
✍“ስሙ ለአሐዱ ፈለግ ኤፌሶን ውእቱ ዘየዐውድ ውስተ ኲሉ ምድረ ኤውላጦን ወህየ ሀሎ ወርቅ፤ ወወርቃ ለይእቲ ምድር ሠናይ ወህየ ሀሎ ዕንቊ ዘየኀቱ ወዕንቊ ሐመልሚል”
👉የአንዱ ወንዝ ስሙ ኤፌሶን ነው፤ ርሱ የኤውላጦንን ምድር ኹሉ የሚያጠጣ ነው በዚያም ወርቅ አለ፤ የዚያችም ምድር ወርቅ ጥሩ ነው፤ ከዚያ የሚያበራ ዕንቊ፤ ዝንጒርጒር ዕንቊም ነበር ከሚለው ኀይለ ቃል ነው።
📖ዘፍ 2፥11-12
❖ ይኸውም ገነት የእመቤታችን፤ ወርቅ የንጽሕናዋ የቅድስናዋ ምሳሌ ነው፤ የዚያች ሀገር ወርቅ የጠራ እንደኾነ የእመቤታችንም ምግባር እና ሃይማኖት የጠራ ነውና፡፡
❖ ዕንቊ የንጽሕናዋ፤ ያ የሚያበራ እንደኾነ ቅድስት ድንግል ማርያምም በአዳማዊ ኀጢአት ያልተያዘች በቅድስና በንጽሕና የምታበራ ናትና
✍“ማርያምሰ ተሐቱ እምትካት ውስተ ከርሡ ለአዳም ከመ ባሕርይ ጸዐዳ”
👉ማርያምስ ከጥንት ዠምሮ በአዳም ባሕርይ ውስጥ እንደ ነጭ ዕንቊ ታበራለች እንዲል ቅዱስ ያሬድ፤ “ዝንጒርጒር ዕንቊ” የጌታችንም ምሳሌ ያ ሐመልሚል እንደኾነ ጌታም አምላክ ወሰብእ (አምላክም ሰውም) ነውና፡፡
❖ ዳግመኛም ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በምድረ ርስት በኢየሩሳሌም ላይ የተገኘች በየዋህነቷ በርግብ የምትመሰል ቅድስት ድንግልን ክንፎቿ በብር በተሠሩ ጐኖቿም በወርቅ
በተሸለሙ በርግብ አምሳል በመንፈሰ እግዚአብሔር ተመልክቶ
✍“እመኒ ቤትክሙ ማዕከለ መዋርስት”
👉በርስቶች መኻከል ብታድሩ በማለት ቀድሞ ኖኅ ለልጁ ለሴም ባወረሰው ኋላም ለአብርሃም ወደ ተሰጠው ወደ ሴም ዕፃ ብትደርሱ
✍“ክነፈ ርግብ በብሩር ዘግቡር”
👉ከብር እንደተሠሩ እንደ ርግብ ክንፎች በማለት በዚያች የሴም ርስት ውስጥ በየዋህነቷ በርግብ የተመሰለችው ቅድስት ድንግል ማርያምን ክንፎቿ በብር በተሠሩ ርግብ አምሳል ማለት የሥጋዋን የነፍሷንና የሕሊናዋ ንጽሕናን በብር በተሠሩ ክንፎች አምሳል ማየቱን ከገለጸ በኋላ
✍“ወገበዋቲሃኒ በሐመልማለ ወርቅ”
👉ወገቦቿም በሚያብረቀርቅ በወርቅ ቅጠል የተሠሩ በማለት በወርቅ የተመሰለ ወገበ ልቡናዋ “እንደ ቃልኽ ይኹንልኝ” በሚል የቅዱስ ገብርኤልን ብሥራት በማመን የጸና መኾኑን በምስጢር ከገለጸ በኋላ እናቱን እንዲያበሥር ባዘዘው በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ሰማያዊ ንጉሥ ጌታ በየዋህነቷ በርግብ ከተመሰለችው ከቅድስት ድንግል ተወልዶ ድኅነትን እንደሚያደርግ።
✍“አመ አዘዘ ሰማያዊ ንጉሥ ላዕሌሃ”
👉ሰማያዊ ንጉሥ በላይዋ ባዘዘ ጊዜ በማለት
የተናገረው ትንቢታዊ ኀይለ ቃል ተፈጽሞባታልና
✍️ “የሚያብረቀርቅ ቀይና ነጭ ቀለም አርአያው የብር ዝንጒርጒር የኾነ ንጹሕ ተአምርሽ በወርቅ አምሳል የተሠራ ነው” ይላታል፡፡
❖ ሊቁ አባ ጽጌ ድንግል በመጨረሻ ይኽ መልካም፣ ያማረ፣ የተወደደ እስከ ዕለተ ምጽአት ድረስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከመስከረም 26 ዠምሮ እስከ ኅዳር 6 መድረሻ የመጨረሻዋ ሰንበት የሚደረሰው ይኽ ድንቅ ማሕሌተ ጽጌ መፈጸሙን “እነሆ የተወደደ (መልካም) ማሕሌተ ጽጌ ደረሰ ተፈጸመ” ብሎ ተናገረ፡፡
❖ በመቀጠልም ሕፃናት ናላ ይወርዳቸዋል ብለው ወላጆች በመኻል እጃቸው እንዲይዟቸው ዓለምን የሚደግፈውን፣ የያዘውን ፍቁር ጌታን የያዙ ጒያዎቿን ያደንቃል፤ በተመሳሳይ መልኩ የመልክአ ማርያም ደራሲም
✍ “ሰላም ለሕፅንኪ ለጥበበ ሰማይ ምዕራፋ ዘኢይትረከብ ሱታፋ”
👉መጋጠሚያዋ (ግጥሚያዋ) ለማይመረመር (ለማይገኝ) ለሰማይ ጥበብ ማረፊያዋ ለኾነ ጒያሽ ሰላምታ ይገባል) ይላታል፡፡
❖ ደራሲው አባ ጽጌ ብርሃን ቅድስት ድንግል ማርያምን “ንግሥተ ሰማያት ወምድር” ይላታል፤ ይኽ ንግሥትነቷ በነቢያት በሐዋርያት ተመስክሮላታል፤ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመንፈሰ እግዚአብሔር ተቃኝቶ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ክብር፣ ቅድስና፣ ንግሥትነት፣ አማላጅነትና በንጉሠ ሰማይ ወምድር በጌታ ስለመመረጧ “አዋልደ ንግሥት ለክብርከ” (የእቴጌ (የንግሥት) ሴት ልጆች ለክብርኽ ናቸው) በማለት ሰማያዊ ንጉሥን የወለደች የንጉሣችን የክርስቶስ እናቱ የንግሥተ ሰማይ ወምድር የቅድስት ድንግል ማርያም የአደራ፣ የቃል ኪዳን ልጆች ለጌትነቱ እንደሚገዙና ለክብሩ ለመንግሥተ ሰማያት የመመረጣቸው ነገር ተገልጾለት አስቀድሞ በመዝሙሩ
አመስግኗል።
📖መዝ 44፥9-17
❖ በእውነት ቅድስት ድንግል ማርያም ንግሥት መኾኗን ንግሥት መባሏን ነቢዩ ዳዊት ብቻ ሳይኾን ነቢያት ሐዋርያት ባንድ መንፈስ ቅዱስ ገላጪነት ሲጽፉ፤ ከዐበይት ነቢያት አንዱ ኢሳይያስ በትንቢቱ ላይ
✍“ነገሥታትም አሳዳጊ አባቶችሽ ይኾናሉ፤ እቴጌዎቻቸውም ሞግዚቶችሽ ይኾናሉ፤ ግምባራቸውንም ወደ ምድር ዝቅ አድርገው ይሰግዱልሻል፤ የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ” በማለት የእቴጌዎች እመቤት፣ የንግሥታት ንግሥት መኾኗን ተናግሮላታል።
📖ኢሳ 49፥23
❖ ዳግመኛም ሰማያዊ ንጉሥን በመውለዷ ምክንያት ፍጥረት ኹሉ ንግሥት እመቤታችንን እንደሚያመሰግናት ጠቢቡ ሰሎሞንም በመሓልዩ ላይ
✍“ርግቤ መደምደሚያዬ አንዲት ናት፤ ለእናትዋ አንዲት ናት፤ ለወለደቻትም የተመረጠች ናት፤ ቈነዣዥትም አይተው አሞገሱአት፤ ንግሥታትና ቁባቶችም አመሰገኑአት፤ ይኽቺ እንደ ማለዳ ብርሃን የምትጎበኝ፤ እንደ ጨረቃ የተዋበች እንደ ፀሓይም የጠራች፤ ዐላማ ይዞ እንደተሰለፈ ሰራዊት የምታስፈራ ማን ናት?” በማለት በትንቢት መነጽርነት የተገለጸለትን የንግሥትነቷን ክብር ጽፏል።
📖መኃ 6፥9‐10
❖ ይኽነን የንግሥትነት ክብሯን በዐይኑ የተመለከተ ከሐዋርያት አንዱ ዮሐንስም፤ በዚኽ ዓለም ያሉ ምድራውያን ንግሥታት የወርቅ ካባ ሲለብሱ፤ የወርቅ ጫማ ሲጫሙ፤ የወርቅ የዕንቊ አክሊል ሲደፉ፤ የምድርና የሰማይ ንግሥት አማናዊ ፀሐይ ክርስቶስን የወለደች ቅድስት ድንግል ግን የቀን ጌጥ ፀሓይን ተጐናጽፋ የሌሊት ጌጦች የኾኑትን ጨረቃን ተጫምታ፤ ከዋክብትን በራሷ ደፍታ እንደምትገኝ በራእዩ ላይ “ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ፤ ፀሓይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት፣ በራስዋም ላይ የዐሥራ ኹለት ከዋክብት አክሊል የኾነላት” በማለት ልክ እንደ ዳዊት የንግ መጠናቀቁን ተናገረ፡፡
❖ አባ ጽጌ ድንግል ይኽነን ያማረ የተወደደ ምስጋና እንዲያመሰግንሽ የባረክሽው የአምላክ እናት ሆይ በእጅጉ የምንወድሽ እኛንም ልጆችሽን ዘወትር እናወድስሽ ዘንድ ትባርኪን ዘንድ እንማፀንሻለን፡፡
የእናታች የቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት ምልጃዋ አይለየን፤ አስራት አገሯን ሰላም ፍቅር ታድርግልን
📌ምንጭ
✍በመጋቤ ሐዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ
✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝
✍"ልብህን በእርጋታ አኑረው፤ የሁሉም መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ለመሆን በጣም ትጋ ለከንቱ ንግግር ዘገምተኛና ሰነፍ ሁን፤ ነገር ግን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል በማወቅ በመስማት ድኅነትን የሚሰጡ ናቸውና ብልህ ሁን"
📚ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ይቆየን
Channel
🧲 https://telegram.me/Tewahedo12
FB Like Page (የፌስቡክ ፔጅ)
🧲 http://facebook.com/Tewahedo12
YouTube Subscribe (ሰብስክራይብ)
🧲 https://www.youtube.com/channel/UCvYxUdv1D-5juH_P6iE7XXw
───────────