የሚመጣው አንተ ነኽን ወይስ ሌላውን እንጠብቅ ፧ ብሎ ወደ ኢየሱስ ላከ ።

የሚመጣው አንተ ነኽን ወይስ ሌላውን እንጠብቅ ፧ ብሎ ወደ ኢየሱስ ላከ ።

ሚያዚያ~8~2013 ዓ.ም

ሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፯

« ፲፰፤ ደቀ ፡ መዛሙርቱም ፡ ለዮሐንስ ፡ እነዚህን ፡ ዅሉ ፡ አወሩ ። (ክርስቶስ የሚሰራውን...) 

 ፲፱፤ ዮሐንስም ፡ ከደቀ ፡ መዛሙርቱ ፡ ኹለት ፡ ወደ ፡ ርሱ ፡ ጠርቶ ፦ የሚመጣው ፡ አንተ ፡ ነኽን ፡ ወይስ ፡ ሌላውን ፡ እንጠብቅ ፧ ብሎ ፡ ወደ ፡ ኢየሱስ ፡ ላከ ። » (ለዛሬው ምክራችን ምስጢሩ ያለ ከዚህ ነው!...)

...እጅግ ግሩም ነው ወገኖቼ ! እንዴት አድርጎ ለመናገር የሚጥም ለመስማትም ጣፋጭ ቃል ተናገረ ቅዱስ ዮሐንስ !? 

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን ! በእሳት መሃል የሚጠብቀን ፡ በውርጭም መሃል የሚያሞቀን ሁሉን የፈጠረ ሁሉንም አሳልፎ በማያልፍ ህልውና የነበረ ያለና የሚኖር አልፋና ዖሜጋ መጀመሪያና መጨረሻ ልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ ስሙ ከአጽናፈዓለም እስከ አጽናፈዓለም ከዘላለም እስከ ዘላለም ከቅድስት እናቱ ጋር የተመሰገነ ይሁን ! አሜን !

... ከላይ በመግቢያችን የሰፈረውን ጥያቄ የጠየቀ መጥምቁ ዮሐንስ ነው ። መጥምቀ መለኮት የተባለ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ያጠመቀ ቅዱስ ። ተስፋ የምናደርገው ፣ የምንጠብቀውና የሚመጣው መሲሕ ክርስቶስ ማለት አንተ ኢየሱስ ነህን ወይስ ከአንተ ውጭ ሌላ የሚመጣ እንዳለ በተስፋ እንጠብቅ ? ብሎ መልዕክተኞችን ጥያቄ አስይዞ ወደመድኃኒታችንና አምላካችን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ላከ። መልዕክተኞችም መልዕክቱን ይዘው ክርስቶስን ሲጠይቁት በሕዝቡ ሁሉ ፊት የእውሮችን ዓይን አብርቶ ፡ አንካሶችን ፈውሶ ፡ የሌሎችንም ቋጠሮ ሁሉ ፈትቶ ፡ ሙታንን አስነስቶ ሌላም ሌላም ብዙ አምላካዊ ታምራትን በሁሉም ፊት አድርጎ ለታሰሩት መፈታትን ሊሰጥ እንደመጣ በምስክር አሳያቸውና ለመልዕክተኞች እንዲህ አላቸው፦

"እላችዃለኹ ፥ ከሴቶች ፡ ከተወለዱት ፡ መካከል ፡ ከመጥምቁ ፡ ዮሐንስ ፡ የሚበልጥ ፡ ማንም ፡ የለም ፤ በእግዚአብሔር ፡ መንግሥት ፡ ግን ፡ ከዅሉ ፡ የሚያንሰው ፡ ይበልጠዋል ።" አለ። ይህንን ሲናገርም «የሰሙትም ፡ ሕዝብ ፡ ዅሉ ፡ ቀራጮች ፡ እንኳ ፡ ሳይቀሩ ፡ በዮሐንስ ፡ ጥምቀት ፡ ተጠምቀው ፡ እግዚአብሔርን ፡ አጸደቁ...» ይላል ቃሉ ሉቃስ ፯ ፥ ፳፰—፳፱።

አዎን! ወገኖቼ አስተውሉ! መጥምቁ ዮሐንስ ከጌታችን መምጣት ቀድሞ የቆሸሸውን መንገድን ይጠርግና የጠመመውንም ሁሉ ያቃና ዘንድ የተላከ የእግዚአብሔር ባርያ ነው ።

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ሁሉን እያወቀ አንዲት ምስጢር አምላኩን እስከሚጠይቅ ድረስ ቢሸሸግበት ይጠይቅ ዘንድ ግድ ሆነበትና "የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላውን እንጠብቅ" ብሎ እስር ቤት በግዞት ሳለ ወደጌታችን መልዕክተኛ ላከበት። ወገኖቼ ልብ አድርጉ ! ያ ሁሉ ጸጋ ፡ ያ ሁሉ ቅድስና ያለው ሀብተ ትንቢት ሀብተ ትምህርት ሁሉ የበዛለት የእምነት ባለጸጋ ፡ ከሴቶች ከተወለዱት ከእሱ የሚበልጥ የለም እስከመባል በአምላካችን አንደበት የተመሰከረለት ባሕታዊ መምህር ነው ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ማለት ጌታችንንም ያጠመቀ ብቸኛ ሰው ግን ደግሞ ስለኢየሱስ ስራ ሰዎች በነገሩትና ባወሩለት ጊዜ መሲሑ አንተ ነህን ወይስ ሌላ ተስፋ እናድርግ ብሎ የጠየቀ ድንቅ መምህር ! በጊዜው ያልተገለጠለትን ጥያቄ ይዞ ሁሉን አዋቂ ወደሆነው እግዚአብሔር የቀረበ ሊቅ ! በቀደመ እውቀቴ ልመራመር ልፈላሰፍና ልወቀው ሳይል ያልተገለጠለትን ምስጢር ሁሉን ወደሚገልጥና ወደሚሰውር አምላክ ጥያቄውን በትህትናና በፍጹም እምነት ይዞ የቀረበ ጀግና ባሕታዊ ! "ሊቃውንት" እስኪ ከዚህ ድንቅ ጻድቅ ሊቅነትን ተማሩ ! ፤ "ባሕታውያን" እስኪ ከዚህ የባሕታዊነትን ጥግ ከሆነው ድንግል ሁሉን አውቃለሁ ካላለው ቅዱስ ብሕትውናን ካስመሰከረው ጻድቅ ተማሩ ! ፤ "መምህራን" እስኪ ከዚህ ታላቅ የእምነት መምህር ቅዱስ ዮሐንስ ጌታየን ብጠይቀው እውነትን ይነግረኛል የሚለውን የእምነት መሠረት ተማሩ ! ፤ ምዕመናን ወገኖቼም ታውቁት ዘንድ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ የምትጠይቁትን አካል ከዚህ ጭብጥ አስተውሉ ! መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስኮ ጥያቄውን በዘመኑ ወደነበሩ መምህራን ፣ ካህናት ፣ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ፣ የአይሁድ ሊቃውንት ወደሚባሉት የጥፋት መሠረቶች ሁሉ አላደረሰም ! አዎን ! ወደኢየሱስ መልዕክተኞችን ላከ ነው የሚለን ቅዱስ ቃሉ ። ጥያቄውን ይዞ ወደክርስቶስ ቀረበ መልስንም በድንቅ ከጌታው ተቀበለ ፡ አመነ ነው ምስጢሩ ።

...በዘመናችን ከጥቂቶች እውነትን ካነገሡት በቀር በሙሉ በሚባል መልኩ በቤተክርስቲያን ያሉ "አገልጋዮችን" (ነን ስለሚሉ አገልጋዮች እንበላቸው) ያሰናከለውና የጣለው ምስጢር ያለው ከዚህ ላይ ነው ። ❞እኔ ሁሉንም አውቃለሁ ፤ ከእኔ በላይ ሊቅ ከወዴት ይመጣል ፤ እኔ ከሌለኹ ቤተክርስቲያንም አገርም የለችም ፤ እኔ ነኝ የሁሉ ቋጠሮ ፈች ፤ እኔ ያልተረዳሁት ነገር የለም ካለም ስህተት ነው ፤ እናንተ ብቻ በድላችኋል እኔ ንጹሕ ነኝ ፤ እኔ ብቻ ነኝ መናገርም መሰማትም ያለብኝ... እኔ... እኔ... እኔ...!❞ ወዘተ። ይሄ አይደል ወይ ያጠፋን ? ይሄንን አይደለም ወይ በጆሯችን ዕለት ተዕለት የምንሰማው በዓይናችን የምንመለከተው ጥፋት በዚህ የመጣ አይደለም ወይ??? አዎን ! በወቅቱ ምስጢሩ ባይገለጥለት ጥያቄ ወደፈጣሪው ያቀረበውን መጥምቁ ዮሐንስን ጌታችን መድኃኔዓለም በእውነት ቅድስናውን በአደባባይ ሲገልጸው ከሴቶች ከተወለዱት ሁሉ ከእርሱ የሚበልጥ የለም ብሎ ነበር ። ለምን ? እውንነቱን ማወቅና ማረጋገጥ የፈለገውን ነገር ወደ እግዚአብሔር አቅርቦ ስለጠየቀና ስላረጋገጠ !! ዛሬስ ፤ ኢትዮጵያ የዓለም ብርሃን የሚል መልዕክት ወደትውልዳችን ባለመታከት እያስተላለፉ ያሉትን አባት ምንነትና ማንነት ለማወቅ የምትደክሙ ሁላችሁ ለምን ጌታችንን አምላካችንን አትጠይቁም ? ለምንድን ነው ከእምነት ጎድላችሁ እገሌ መምህር ይነግሩኛል ፡ እገሌ አባት ይህ አይጠፋቸውም ፡ ከእገሌ መምህር ከእገሌ ሊቅ ከእገሌ መጋቢ ከእገሌ ባሕታዊ የተሰወረ ምስጢር የለም እሳቸው አይጠፋቸውምና ይነግሩኛል ... እያላችሁ ሁሉም ሰው ሁሉን ያውቃል ብላችሁ ለምን ትደክማላችሁ ? ለምንስ ተጠያቂዎቻችሁን በከንቱ ታደክሟቸዋላችሁ?? ፡ ለምንስ ባልተገለጠላቸው መስክረው እንዲጠፉ ታሰነካክሏቸዋላችሁ ?? ፤ እነሱም የሚያውቁትኮ የተገለጠላቸውን ያህል ብቻ ነው ። እናንተስ በእነሱ የተዛባ መልስ ለምን ትጠፋላችሁ ፡ ለምን እውነትን ትከሷታላችሁ ?! በእኔ የማይሰናከለው ምንኛ ብጹዕ ነው እንዳለ ጌታችን ! እናንተስ ለምን በሰዎች ማንነት ባልተረዳችሁት ጉዳይ ትሰናከላላችሁ ? ለምን በሰዎች ምንነት እንሰነካከላለን? ለምን ውሸት ከባሕሪው የሌለበትን ሁሉን አዋቂ የሆነውን ልዑል እግዚአብሔር አትጠይቁትም ? እሱ መቼ ነው ማወቅ ያለባችሁን ሁሉ አትጠይቁኝ ያለን ? ፡ እኔን ሳይሆን ሰዎችን ጠይቁ ያለ መቼ ነው?? ኢትዮጵያ የዓለም ብርሃንን መጀመሪያ በቅን ልቦና አዳምጡትና ስለጸሐፊውም ይሁን የመልዕክታቸውን ይዘትና እውንነት ለማረጋገጥ ፡ ስለእሳቸውም ስልጣን ለመረዳት (አስፈላጊ ከሆነ!) ምስጢሩ ካልተገለጠልንና የሰማነውም እውነት ካልተዋጠልን ለምን ወደአጋዕዝተዓለም ሥላሴ ጥያቄ አናቀርብም ?? ከእሱ የተሰወረ ምን ነገር ሊኖር ይችላል !? ስለዚህ እንቅረብ እንዲህም ብለን ጌታችንን እንጠይቅ ፦ "ለዘመናት ሣልሳዊ ቴዎድሮስ በመባል ሲጠበቁ የነበሩትና አሁን ዘመኑ ደርሶ እንደመጡ የሚነገርላቸው *ኢትዮጵያ የዓለም ብርሃን* የሚል የንስሐና የፍርድ አዘል መልዕክት ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት ባለመሰልቸት ያስተላለፉት ሰው እነሱ እንደሚናገሩት እውን አንተ ያዘዝኻቸውና የላክኻቸው ናቸው ወይ ? ንጉሡ እሳቸው ናቸው ወይ ? መልዕክታቱ ያንተ ነው ይላሉ እውነታቸውን ነው ወይ ? እንዲህ አድርጉ እንዲያ አታድርጉ ይሉናል እንስማቸው ወይ ? የቤተክርስቲያን የወቅቱ አገልጋዮች በብዙ መንገድ ይከሷቸዋል ማንኛው እውነት ላይ የቆመ ?? ጌታ ሆይ አንተስ ለማን ትፈርዳለህ ? በማንስ ላይ ትፈርድበታለህ? ፤ ወይስ ይመጣል የተባለው የኢትዮጵያ ትንሣኤ መሪ ንጉሥ ሌላ ናቸው ወይ ? ሌላ ከሆኑ ሌላውን የኢትዮጵያ ትንሣኤና ሌሎችን ነገሥታትንም እንጠብቅ ዘንድ ምን ትለናለህ ??" ብላችሁ ለምን ልዑል እግዚአብሔርን በትህትናና በቅድስና ራሳችሁን በማዋረድ (ሁሉን አውቃለሁ ባለማለት) ቀርባችሁ አትጠይቁም ? ለምን በሁለት ዐሳብ ታነክሳላችሁ? እኛ እውነቱ ይሄ ነው ፡ መልዕክታቱም የእግዚአብሔር ድምጽ ናቸው ስንል በስጋና ደም ስሜት ገንፍላችሁ በመውጣት መልዕክቱንም ምንም ከምን ሳታውቁ ፡ ጌታንም ሳትጠይቁ እንዲ ነው እንዲያ ነው እያላችሁ ለምን በሐሰት ክስ ትመሰርታላችሁ ? እናንተው ተሰናክላችሁ ለምን ሌሎችንም በተጣመመ ሐሳብ ታሰነካክላላችሁ ? እናንተ ከመጥምቁ ዮሐንስ በልጣችሁ ነው ሁሉንም ነገር ያወቃችሁ ??? ከሆነማ ከሴት ከተወለዱት ሁሉ ከእናንተ የሚበልጥ እንደሌለ ነው የሚሰማችሁ ማለት ነው!? ወይ የጉድ ዘመን !። በቃ እግዚአብሔርን መጠየቅ እንደውርደት ተቆጠረ አይደል ?? በቃ እግዚአብሔር ሆይ ይህ ነገር እውነት ነው ወይስ ስህተት ብሎ መጠየቅ የሚያስነቅፍ ፥ የሚያስተች ተብሎ ተወሰነ አይደል ? ፤ መምህራን ተብዬዎች ፡ ሊቃውንት ተብዬዎች ደግሞ ሁሉንም አዋቂ ስለተባሉ እነሱን መጠየቅ ብልህነትና አስተዋይነት ነው ተባለ አይደል ?? ይሁን ። እኛ ግን መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ በወቅቱ ሊቃውንትና መምህራን የተባሉትን የአይሁድ የጥፋት ካህናት እውነቱን ያስረዱኛል ብሎ ስለኢየሱስ ማንነት እንዳልጠየቃቸው ሁሉ አሁንም ከጥፋት ሰዎች የምናገኘው እውነት እንዳለ አናምንምና ማንንም ስለሚመጣው የኢትዮጵያ ትንሣኤም ሆነ ስለንጉሥታቱ ማንነት ሰውን ታምነን ባንጠይቅ መልካም ነው ። ይልቅስ ወደእግዚአብሔር ጥያቄያችንን ፡ ወደድንግል ጥያቄያችንን ስለሚሆነው ሁሉ መረዳት እንዲኖረን ወደእነሱ ቀርበን ቋጠሯችንን በጾም በጸሎት በስግደት በሱባኤ አጅበን እናቀርባለን በድንቅ ይመልስልናል ቃሉ እውነት ነውና እናምናለን ። በዚህም ስራችን እውነት እላችኋለሁ በዚህ ዘመን ከተነሱት ሰዎች ከወገኖቻችሁ እኔን አምናችሁና ታምናችሁ እንደጠየቃችሁኝ እንደእናንተ የሆነልኝ የለም ይለናል ። ለምን ? ግራ በሚገባን ፡ በማይገለጥልን ምስጢር ሁሉ አምላካችንን ታምነን እሱን አምነን እንጠይቃለንና በዚህ ከምንም በላይ ስለሚደሰት ነው። ለእናንተ ለመልዕክታቱ ተከታታዮችም የዘወትር ምክራችን ይኸው ነው ። ሰውን እንዳታመልኩ ! እግዚአብሔርን እንድትታመኑ ነው የምንለምናችሁ ።

ወለወላዲቱ ድንግል ፤

ወለመስቀሉ ክብር ።


የራዕይ ዮሐንስ~20 ትክክለኛ ገጾችን ለምትፈልጉ

ራዕይ ዮሐንስ 20 ዋናው ግሩፕ-https://t.me/rayeyohanes20

ራዕይ ዮሐንስ 20 ቻናል - https://t.me/rayyohanes20 ኢትዮጽያ የዓለም ብርሃን መልዕክቶቹን በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ለማግኘት ወደ ቻናሉን ይቀላቀሉ::

ራዕይ ዩሐንስ 20 የንፅፅር ቻናል-https://t.me/ethiopialightoftheworld 

ራዕይ ዮሐንስ 20 የመማማሪያ ግሩፕ-https://t.me/ethiopiayealembrehan

Report Page