የመስቀሉ ክብር በአባ ጊዮርጊስ ብዕር

የመስቀሉ ክብር በአባ ጊዮርጊስ ብዕር

ዳረጎት ዘተዋሕዶ


በአምላኩ ደም የተቀደሰ ፣ ከፈጣሪው ጎን በወጣ ውኃም የተጠመቀ ዕፅ እንዴት ያለ ነው?

ለገነት ዛፎች አክሊል ፣ ለገዳም ዛፎችም ክብር የሆናቸው ዕፅ እንዴት ያለ ነው?

ለአሸናፊ የእግዚአብሔር በግ መሠዊያ የሆነው ዕፅ እንዴት ያለ ነው?

ከእርሱ ምዕመናንን ለማተም የሚሆን የሕግና የሥርዓት ደምን ያንጠባጠበ ዕፅ ምን ዓይነት ነው?

የተከሉትን የበተናቸው ፣ ያመኑትንም የሰበሰባቸው ዕፅ እንዴት ያለ ነው?

ምድርን የቀደሳት፣ ሰማይንም ያማተበበት፣ ዓለምንም ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ በረከት የባረከ ዕፅ እንዴት ያለ ነው?

                               ❖❖❖❖

መስቀል ዕፀ ሕይወት ነው። መስቀል ዕፀ መድኃኒት ነው። መስቀል ዕፀ ትንቢት ነው። መስቀል ዕፀ እረፍት ነው። መስቀል ሰይጣንን ገዝግዞ የሚገነድስ ምሳር ነው። የአጋንንትንም ራሶች የሚቆርጥ ሰይፍ ነው። መስቀል ርኩሳን መናፍስትን የሚወጋቸው የእሳት ዘገር ነው። የአመስቴማውያንንም ሠራዊት የሚመታ የመብረቅ ጦር ነው።

                                 ❖❖❖❖

ኦ እጅግ የሚደንቅ ነው። የተሰቀለው ድል አደረገ። የሰቀሉትም ድል ሆኑ።

ኦ እጅግ ያስገርማል የሞተው ያሳፍራቸዋል። የገደሉትም ያፍራሉ።

ኦ እጅግ ያስደምማል፤ የታመመው መከራን አመጣ ፤ ሕማሙንም ያመጡት መከራው ደረሰባቸው።

ዕፀ መስቀሉን የተከሉት ተሰደዱ፤ እርሱን የሰቀሉት በዓለም ተበተኑ።...በመስቀል ስም በሰው ልጅ አንደበት ሊነገር የማይችል ምሥጢር አለ።

በመስቀል ስም የሰቃልያንን ማኅበር የሚበትን ምሥጢር አለ። በመስቀል ስም የእባቡን ራስ የሚቀጠቅጥ ምሥጢር አለ።

                                 ❖❖❖❖

የመስቀልህ ምስጋና ለሚያምንብህ መሰንቆው ፣ ለሚክድህም ተግሣጹ ነው።

የመስቀልህ ምስጋና ለሚያፈቅርህ እንዚራው ፣ ለሚጠላህ ግን ስድቡ ነው።

የመስቀልህ ምስጋና የከረመ ወይን እንደጠጣ ሁሉ ልብን ደስ ያሰኘዋል።

የመስቀልህ ምስጋና ያበራልናል። የእስራኤልን ልጆች ከሴይር በረሃ እስከ ቃዴስ ምድረ በዳ እንዳበራላቸው ዓምደ እሳት መሪ ይሁነን።

                                  ❖❖❖❖

መስቀልህን ለዕሌኒ ልጅ ቆስጠንጢኖስ አይሁድ በጎልጎታ ከቀበሩት በኋላ የገለጥከውን፣ በጨለማ ማኅተም እንዲታተም ያልተውከውን አንተን አቤቱ አመሰግንሃለሁ።

መስቀልን በመፈለግ የደከመችውን የአገልጋይህ የዕሌኒን መሻትዋን የፈጸምህላትን አንተን አቤቱ አመሰግንሃለሁ።

ቅዱስ መስቀልህን ለማግኘት ምልክት ይሆናት ዘንድ የዕጣኑን ጢስ የሰጠሃት አንተን አቤቱ አመሰግንሃለሁ።

ከልመናዋ ፊትህን ያልመለስህ የተመኘችውንም ከማግኘት ያላሳፈርካት ብርሃኑንም ለዓለም እንድትገልጥ ያደረግካት አቤቱ አመሰግንሃለሁ።

በመስቀልህ መገኘት በአፏ እልል እስክትል፣ በእጆቿም እስክታጨበጭብ በእግሮቿም እስክታሸበሽብ ድረስ በደስታ የመላሃት አቤቱ አንተን አመሰግንሃለሁ።

Report Page