“ዓለም እና ጊዜ”

“ዓለም እና ጊዜ”

The poet፦ for any comment @Theauthorofmystery

በከበደ ሚካኤል

❖❖❖❖❖❖❖

እኔማ አቶ ጊዜ፥ ከጥንት ዠምሬ፣

ለፍጥረት ታዛቢ፥ ሆኜ በመኖሬ፣

እጅግ በረዘመው፥ በራቀው መንገዴ፣

ቸኩዬ በፍጥነት፥ ሳልፍ እንደ ልማዴ፣

መቼም አይቀርና፥ አይቶ መመልከት፣

ትልቅ ግቢ አይቼ፥ ባለ ብዙ ቤት፣

ከደጅ ሲተራመስ፥ ሰዉ ከቤት ተርፎ፣

ይመስል ነበረ፥ ንብ ያለበት ቀፎ።

ያጥሮቹ አሠራር፥ የግቢውም መድመቅ፣

የቤቶቹም ብዛት፥ በጣም የሚደነቅ፣

እንደዚህ ግቢውን፥ ሠርቶ ያሳመረ፣

ማን ይሆን? አልኩና፥ ከዚህ የሰፈረ፣

ደንቆኝ ስመለከት፥ በጣም ተገርሜ፣

ሰው አገኘሁና፥ አልኩት “በል ወንድሜ፣

የዚህ የውብ ግቢ፥ ባለቤቱ ማነው?”

“ያባት ያያቱ ርስት፥ ያንድ ከበርቴ ነው፣

ርስቱም ዘላለም፥ አለ ሳይነካ”፣

ብሎ መለሰልኝ፥ ኰርቶ እየተመካ።

ብዙ ትውልድ አልፎ፥ ለትውልድ ደርሼ፣

ደግሞ በዚያው መንገድ፥ መጣሁ ተመልሼ።

ከዚያ ካጥር ግቢ፥ ከዚያ ሁሉ ቤት፣

ከቁመቱ ርዝመት፥ ከጐኑ ስፋት፣

አንድ ድንጋይ እንኳን፥ ጠፍቶ ምልክት፣

ያ ያየሁት ሁሉ፥ እንዳልነበር ሆኖ፣

ከግቢው ቦታ ላይ፥ አየሁ ትልቅ መስኖ።

የለመለመበት፥ አንድ ትልቅ ጨፌ፣

ተመለከትኩና፥ ልሄድ ስል አልፌ፣

አንድ ትልቅ ዛፍ ሥር፥ ተጠግቶ ጥላ፣

አንድ እረኛ አገኘሁ፥ ከብቶች ሣር ሲያበላ።

“እንደዚህ ያለ ሣር፥ የበቀለበት፣

ከመቼ ወዲህ ነው?” ብዬ ጠየቅሁት፤

እሱም ቁጭ እንዳለ፥ ቀና ብሎ አይቶኝ፣

“ዘለዓለም ለከብቶች፥ ግጦሽ የሚገኝ፣

ከዚሁ መስኖ ነው” ሲል መለሰልኝ።

ብዙ ትውልድ አልፎ፥ ለትውልድ ደርሼ፣

ደግሞ በዚያው መንገድ፥ መጣሁ ተመልሼ።

መስኖውም ጠፋና፥ ጨፌነቱ ቀርቶ፣

ከመስኩ ቦታ ላይ፥ ከተማ ተሠርቶ፣

የቤቱ መበርከት፥ የመንገዱ ማማር፣

የከተማው ጥዳት፥ የግንቡም አሠራር፣

የሕዝቡ አበዛዝ፥ የገበያው መድመቅ፣

ታይቶ እማይጠገብ፥ እጅግ የሚደነቅ።

ያማረች ከተማ፥ የጥበብ መዝገብ፣

ጠንተው የቆሙባት፥ ዐዋጅና ደንብ፣

ውበቷን አድንቄ፥ ስመለከታት፣

ዕድሜው የጠና ሰው፥ አግኝቼ ድንገት፣

“መች ነው የተሠራች?” ብዬ ጠየቅሁት።

እሱም መለሰልኝ፥ በጣቱ አመልክቶ፣

“ይች ትልቅ ከተማ፥ ከጥንትም አንሥቶ፣

መልኳ እየታደሰ፥ ውበቷ እያበራ፣

ይኖራል ዘለዓለም፥ ሥልጣኗ እንደ ኰራ”።

ብዙ ትውልድ አልፎ፥ ለትውልድ ደርሼ፣

ደግሞ በዚያው መንገድ፥ መጣሁ ተመልሼ።

ከዚያች ከከተማ፥ ጠፍቶ ምልክት፣

አየሁ ከዚያ ቦታ፥ ጫካ በቅሎበት፤

ሲተራመሱበት፥ ዥብ ነበር አንበሳ፣

በያይነቱ አውሬ፥ አዕዋፍ እንስሳ፣

ሁሉም በየቋንቋው፥ ድምፁን እያሰማ፣

ለጫካው ሲሰጡት፥ የሚያስፈራ ግርማ፣

የዛፉ አበዛዝ፥ ያውሬው መበርከት፣

እጅግ አስደናቂ፥ ሆኖ አገኘሁት።

ደኑን ተመልክቼ፥ እያየሁ ስሄድ፣

አገኘሁ ያገር ሰው፥ ድንገት በመንገድ፤

“ዛፍ እንጨቱ፥ በቅሎ ጫካው የደመቀው፣

ከመቼ ወዲህ ነው?” ብዬ ብጠይቀው፣

ትክ ብሎ እያየ፥ ጫካ ጫካውን፣

እንዲህ መለሰልኝ፥ እሱም ተራውን፤

“ይህን መጠየቅህ፥ እንግዳ ነህ ለካ፣

ጥድ የሚበቅልበት፥ ግራርና ወርካ፣

ጥንቱንም ደን ነው፥ የዘላለም ጫካ”።

አንዱ ስፍራ ሲለቅ፥ አንዱ እየተተካ፣

ሁሉም ርስቴ ነች፥ እያለ ሲመካ፣

ሞኝነት አድሮብን፥ ሳናስበው እኛ፣

ዓለም ሰፈር ሆና፥ ሕዝቡ መንገደኛ፣

ትውልድ ፈሳሽ ውሃ፥ መሬቷም ዥረት፣

መሆኑን ዘንግቶ፥ ይህ ሁሉ ፍጥረት፣

ስትመለከቱት፥ በሰልፍ ተጉዞ፣

ሁሉም በየተራው፥ ያልፋል ተያይዞ።

.

ከበደ ሚካኤል


(1936 እና 1956 ዓ.ም)


.


[ምንጭ] – “የቅኔ አዝመራ”። ፲፱፻፶፮። ገጽ 4-8።


join☞ @yetebibanelifign

Report Page