ክረምትን ምን አስበናል?

ክረምትን ምን አስበናል?

Awaqi' ያንስ


“ለካ ብዙ ብዙ የሚታሰበው በክረምት ነበር!”


“ ለክረምት ምን አስባችኋል? በምንስ ጊዜያችሁን ልታሳልፉ ነው?” በሚል ርዕስ Awaqi telegram live chat ላይ ሲያወሩ ሰማኋቸው! ህ! . . .አይገርምም ለካ ብዙ ብዙ የሚታሰበው ክረምት ነበር። ያ-ደጉ ዘመን..... ልጅነቴን አስታወሱኝ። ታስታውሱ ከሆነ ልጆች እያለን ትምህርት ቤት ተዘግቶ ከጓደኞቻችን ጋር የምንሯሯጥበትን እምንፈነድቅበትን ጊዜ ነበር። የምንናፍቀው።


ጭቃ አቡክተን ፣ ብይ ሰርተን፣ በዛው ጭቃ እንጀራ ጋግረን፣ ብሉልኝ ዳቦ ነው ብለን አቅርበን። ሲኒ ሰርተን፤ በልጅ አይምሯችን ቡና ተጠራርተን፣ ቤተሰብ ሳያየን አፈር በልተን ክረምቱን ቦርቀን ለማሳለፍ እንጓጓ ነበር። በተለይ ዝናብ ሲዘንብ እኛን አለማየት ነው!!! ቤት ስንት ተመክረን ተዘክረን ካበቃን በኋላ፤እኛ እንደለመድነው ገና ለመዝነብ ሲያስብ ከቤት ወተን ፤ ዝናቡ ላይ ስንሯሯጥ፣ ስንደባደብ፤ በታቆረ ውሃ ስንረጫጭ፣ የታቆረ ውሃ ውስጥ ጓደኛችንን ስንጥላቸው፤ አቤት ደስታችን!!! ቤተሰብ እሚባለውን ነገር ከናካቴው ከአይምሯችን አውጥተን ነው ታዲያስ እንዲ እምንደሰተው ።


ከዛስ ቤት ለመግባት ጭንቅ!! ልብሳችን አልደርቅ ይለናል፤ ቤት ስንገባ ከታወቀብን እራት ይሰጠንና እንደለመድነው " ይሄ ዱላማ ምግብህ ነው" ተብለን እንደሁልጊዜው ተመተን እያለቀስን እንቅልፍ ይዞን ይሄዳል። ከፍ ስንል ደግሞ በብዙ የሆሊዎድ እና የቦሊውድ ፊልሞች ታጅበን ክረምታችንን እናጣጥም ነበር። ትርጉም በስለሺ አንድ አንድ ብር እምንከራያቸው የ ህንድ ፊልሞች አንዱ የ3 ሰዓት ርዝማኔ ያለው ስለሆነ ግማሹን ቀን ያገባድድልናል።


የበቆሎውስ ድባብ!!! ቤት ውስጥ ሰብሰብ ብለው በቆሎ እየተጠበሰ የድሮ ታሪክ ሲያወሩ መስማት ሲያስደስት። የእነሱን ልጅነት ያለፉበትን ይነግሩን ነበር። አባቴ ስለድሮው ሲነግረን " እኛ ልጆች እያለን ጉም ሳይለቅ በጠዋት፤ የሰፈሩ ልጆች ሰብሰብ ብለን እንጨት ለቀማ ጫካ እንወጣ ነበር። ልጅነት ደጉ እጃችንን ቆፈን ይዞት፤ ብርዱ እያንዘፈዘፈንም ቢሆን ጓደኞቻችን አብረውን ስላሉ ዝም ብለን እንሄድ ነበር።


ጉሙ አልገልጥ ካለ ደግሞ በመንገዳችን ላይ የነጋበት ጅብ እናገኛለን። ጫካ ውስጥ ኮሽም እንበላለን፣ ቤት ስንመለስ ደግሞ እንጨት ለቅሞ የመጣ ሰው የተለየ እንክብካቤ ስለሚደረግለት እንጀራ ይሰጠን ነበር..... አቤት የነበር ደስታ... እንጀራ በጣም የሚናፈቅ ምግብ ነበር.... ደግሞ እኛ ልጆች እያለን ለመስከረማችን ጫማ፣ ደብተር፣ ልብስ ለመግዛት የግዴታ ክረምትን መስራት ነበረብን" ይለናል።  እናቴ ደግሞ " እኛ ደግሞ ለቀማ የወጣው ሰው ሲመጣ ምግብ አቅርበን እንጠብቀዋለን፤ ቤቱን እናሳምራለን። ማሳመር ማለት መጥረግ ወይንም መወልወል አይደለም፤ እበት አምጥተን ቤቱን ለቅልቀን፣ ጋዜጣውን በአብሲት ግርግዳ ላይ ለጥፈን፤ ስንለጥፈው ደግሞ ማታ ስንተኛ እንዲነበብ አድርገን ነው የምንለጥፈው።


እንደናንተ ጊዜ ስልክ ቲቪ ስለሌለ ማታ ከመተኛታችን በፊት ከ ጋዜጣው ላይ ቃል ስንጠያየቅ ነው የምናመሸው፤ በዛው እንቅልፍ ይዞን ይሄዳል። የእኛ ጊዜ ጨዋታችን ደግሞ ጭቃ ላይ ሸርተቴ፣ በኮባ ሽጉጥ፣ ወንዝ ወርደን እንዋኛለን፣ ከዛ ያው ቤት ስንገባ 'እስኪ ገላችሁ' ተብለን ነጭ ከሆነ አበቃልን፣ እንገረፍ ነበር " እያሉ ያሳለፉትን ክረምት የነበረውን የልጅነት ጊዜ ሲነግሩን ያመሻሉ። ከልቤ ነው ደስ የሚለኝ ግን እነሱ ያሳለፉት የልጅነት ጊዜ እውነት ለመናገር ከእኛ በላይ አስቸጋሪውች ነበሩ። በዛላይ ሁሉንም ያቁታል፣ ደስታውንም ፤ ያለውን ድባብ፤ ቢሆንም እኛ በስብሰን ስንመጣ ከመምታት ወደኋላ አይሉም? ለምን ይሆን!

በርግጥ በአሁኑ ወቅት ያለው አኗኗር ድሮው ከነበረው የአኗኗር ዘዴ በጣም የተለየ ነው። ልጆች ዝናብ ላይ ከመሯሯጥ ይልቅ በዝናቡ ቤታቸው ቁጭ ብለው tiktok ቢያዩ ይቀላቸዋል። በርግጥ ቤተሰብም ልጁ ከቤት ክከሚወጣበት ስልኩን ሰቶ ቤት እርፍ ቢልለት ይመርጣል። አንዳንድ ት/ቤቶች ክረምቱን ተማሪዎቹ እንዲማሩ ያስገድዳል።


የተማሪዎችን ስሜት ደስታ ወይንም ድብርት ጠዋት ትምህርት ቤት ሲሄዱ በኮፍያቸው ውስጥ የተደበቀው ፊታቸው ያሳብቅባቸዋል። ክረምት ትምህርት እማይማሩ ተማሪዎች ደግሞ ጊዜያቸውን በተለያየ ነገር ያሳልፉሉ። ስራ በመስራት ፣ ተከታታይ ፊልም በማየት፣ ቤተሰቦቻቸውን በማገዝ፣ በዘመድ ጥየቃ ኢትዮጵያን በመዞር፣ እንዲሁም አቅዶ ባለማሳካትም ሊሆን ይችላል። በተለየ መልኩ የዘንድሮ ተማሪዎች የስራ እና አዳዲስ ነገር የማወቅ ፍላጎት ይታይባቸዋል። ክረምታቸውን አዳዲስ ነገር በመሞከር፤ አጫጭር ኮርሶችን በመማር፤ ስራዎችን በመስራት ያሳልፋሉ። ይሄንን ሳላደንቅ አላልፍም። በአሁን ጊዜ በአብዛኛው ሰው ኢንተርነት ይጠቀማል፤ ብዙ ምርጫዎችም አሉት።

ተማሪዎችም ሰራተኞችም ራሳቸውን ማሳደግ ቢፈልጉ ከድሮ በተሻለ እንደውም ለውድድር ማቅረብ እንኳን በሚያዳግት መልኩ ብዙ ቀላል ቴክኖሎጂዎች ወደሃገራችን መተዋል። በ 2000 ዓ.ም ጠቅ'ጠቅ. . . በ-ተች(Blackberry). . . ) የያዘ ሰው ጉድ የተባለበት ጊዜ ነበር።

blackberry mobile

አሁን ላይ በአብዛኛው ሰው ‘Smart Phone’ ተጠቃሚ ነው። ያንን በመጠቀም የተለያዩ ‘Online’ ትምህርቶች፣ ስራዎችን፣ ስልጠናዎችን፣ ልምዶችን መውሰድ ራሱን ማሳደግ ይችላል። ጊዜው እያደገ መምጣቱ ደግሞ ለታዳጊ ተማሪዎች እና ወደ ስራ አለም ለተቀላቀሉ ሰዎች የተለያዩ ‘InternShip’ እድሎችን በተለያዩ ድርጅቶች ይሰጣሉ። እውቀት ባላቸው ሰዎች እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች 'Workshop' በነጻ እና በክፍያ ይዘጋጃሉ። ብዙ እድሎች እንደዚያውም ብዙ የሚያሰናክሉ ነገር! ምርጫው የእኛ ነው።

ክረምትን ለካ ብዙ እምናቅድበት እምንሰራበት ጊዜ ነበር ያስባለኝ አሁን ያለሁበትን የስራ ጊዜ ሳስበው ነው። ክረምት ይሁን በጋ፤ ልዩነቱ በዝናብ እና በጸሃይ ስራ መሄዳችን፤ በዝናብ እና በጸሃይ ታክሲ መጠበቃችን፤ በጋ ላይ ተማሪዎች ስለሚኖሩ ጠዋት እና ማታ ብዙም ታክሲ አለማግኘታችን፤ ክረምትን ግን ታክሲ እንደልብ ባይባልም በተሻለ መልኩ መሳፈራችን፤ እንዚህን እና የመሳሰሉ ልዩነቶች በስተቀር የጎላ ልዩነት አይታይበትም። ነገርግን ለተማሪውች ብዙ እጅግ በጣም ብዙ ልዩነቶች አሉዋቸው። ምርጫው የእናንተ ነው።    

በነገራችን ላይ ምንም አረግን ምንም ከእነዚህ ሶስት ነገሮች አያልፍም፦ መስራት፣ መማር አልያም መተኛት። በምርጫ የተከበበ አለም ወስጥ ነው የምንኖረው። ሁሉም ነገር ምርጫ ነው። ዝናብ እየዘነበ መተኛት እና ማለም፤ ወይንም በዝናብ ተነስቶ በመስራት ህልማችንን መኖር መጀመር። በሚገርም ሁኔታ በዝናብ ቤት ተኝተን በተመሳሳይ ሰዓት በመነሳት ህልሞቻችንን መኖር መጀመር እንችላለን። እንዴት ማለት ጥሩ የ 'Online' ስራዎችን እና ትምህርቶችን በማሰብ። አዋቂ ኢትዮጵያ ደግሞ መማር ለሚፈልግ ለማንኛውም ሰው በነጻ የሚሰጣቸው ኮርሶች አሉት ” courses.awaqi.org “ በዚህ link ያገኙታል። እንዲሁም Telegram Channel ላይ የተለያዩ የትምህርት እና የስራ እድል ያጋራል።


እንዳልኳችሁ ነው ሁሉም ነገር የምርጫ ጉዳይ ነው!!! “CHOOSE THE BEST ANSWER” ተብለን እንዳደግነው ነው። ህይወትም እንዲ ነች ሁሉም ምርጫዎች መልስ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገርግን ትዕዛዙ “THE BEST” ነው የሚለው!!! ምርጫችን ላይ ጠንቀቅ፣ አሰብ ማድረግ ይኖርብናል።


ብቻ! እንደዚም እንደዚያም፤ ሰርተንበትም ተኝተንበትም ቢሆን ጊዜው አይጠብቀንም፤ ይዞን ወይንም ትቶን ይሄዳል። ይህ ደግሞ የራሳችን፣ የግላችን ምርጫ ነው!!!

“CHOOSE THE BEST ANSWER”, as they say.


ሰናይ ክረምት ተመኘው !!✍️


Report Page