ኢትዮጵያ ሁለት ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኦፕሬተሮችን በጨረታ ወደ ቴሌኮም ገበያ ልታስገባ ነው፦

ኢትዮጵያ ሁለት ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኦፕሬተሮችን በጨረታ ወደ ቴሌኮም ገበያ ልታስገባ ነው፦


የኢትዮ-ቴሌኮም እና የስኳር ፋብሪካዎች ፕራይቬታይዜሽን ሂደትን በተመለከተ የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው ላይ እንዳመለከቱትም የቴሌኮም ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የፓይቬታይዜሽን ሂደቱን በተመለከተ መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ከኢትዮ ቴሌኮም በተጨማሪ ሌሎች ሁለት ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ወደ ገበያ እንዲገቡ ያደርጋል። በተጨማሪም የኢትዮ-ቴሌኮምን አብላጫ ድርሻ እና የቦርድ አስተዳደርን መንግሥት ይዞ 49 በመቶ ድርሻውን ወደ ግል እንደሚያዘዋውርም ተመልክቷል። ኩባንያው በመሠረተ ልማት ወይም በመስመር ዘርጋታ እና በአገልግሎት ዘርፍ ለሁለት መከፈሉንም አስታውቀዋል። በመሠረተ ልማት ዘርፍ የተከፈለው አካሉ ዓለም አቀፍ መስመረን፣ ሀገር አቀፍ የፋይበር ኦፕቲክስ፣ ለኔትወርክ ጠቃሚ የሆኑ እንደ ሞባይል ኔትወርክ ማማ የመትከል ድርሻ ይኖረዋል።

የአገልግሎት አቅርቦት ዘርፉ ደግሞ ሁሉንም የሞባይል፣ የኢንተርኔት እና የመደበኛ ስልክ ችርቻሮ ሥራን ያከናውናል። ሁለቱም ዘርፎች ለግል ባለሀብቶች ክፍት ይሆናሉም ብለዋል። ሚኒስትር ዴኤታው ይህን ጨምሮ ሁለት ዓለም አቀፍ የቴሌኮም ኦፕሬተሮችን ወደ ገበያው የማስገባቱ ሂደት በ2012 ዓ.ም ሦስተኛ ሩብ ዓመት ድረስ እንደሚጠናቀቅም አስታውቀዋል። ዶክተር ኢዮብ በመግለጫቸው እየተተገበሩ ያሉት የቅድመ ፕራይቬታይዜሽን እርምጃዎች በዓለም ላይ ግንባር ቀደም የሚባሉ ኩባንያዎችን እየሳቡ መሆኑንም ተናግርዋል።

እርምጃው ጥሩ የገበያ ውድድር በመፍጠር የተሻለ የቴሌኮም አገልግሎት ማግኘት ያችላል መባሉን የዘገበው ኤፍ.ቢ.ሲ ነው። በተጨማሪም የቴሌኮም አገልግሎት ክፍያን ለመቀነስ እና ተደራሽነትን ለማስፋት በመንግሥት የተቀመጠውን ግብ የሚያሳካም ይሆናል። እንደዚሁም ወደ ሀገሪቱ ተጨማሪ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት በመሳብም በኩል ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል። የስኳር ፋብሪካዎችን በተመለከተም በአሁኑ ወቅት የስኳር ፋብሪካዎች አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።

አዋጁም ስኳር የማምረት እና የመሸጥ እንዲሁም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባና ወደ ውጭ የሚላክ የስኳር ምርትን ለማስተዳደር የሚረዳ ነው ተብሏል። እስካሁን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ኩባንያዎች መጠይቁን በመውሰድ ሞልተው መመለሳቸውን እና በርካታ ኩባንያዎች ፍላጎት ማሳየታቸውን ዶክተር ኢዮብ ተናግረዋል። የተመረጡ የስኳር ፋብሪካዎች ጠቅላላ የይዞታ ጥናት እየተጠናቀቀም መሆኑን ገልፀዋል። ሀገሪቱ ካሏት የስኳር ፋብሪካዎች መካከል አምስት ወይም ስድስት የሚሆኑትን ከስድስት እስከ 12 ወራት ውስጥ ባለው ጊዜ ወደ ግል እንደሚዘዋወሩም አስታውቀዋል።

ምንጭ፦ አብመድ

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page