አበባ፡- ክርስቶስ

አበባ፡- ክርስቶስ

ዳረጎት ሚዲያ

ወርኀ ጽጌ ምስጢረ ጽጌ ...የአበባ ወር የአበባ ምስጢር

፪ኛ አበባ፡- ክርስቶስ



አበባ የኢየሱስ ክርስቶስ ምሣሌ ነው፡፡ ለዚህም ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎችን በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በዘኁልቊ ፲፮፥ ፩ ጀምሮ የተጻፈውን ታሪክ ይመለከቷል፡፡ እስራኤል ዘሥጋ ምድረ ከነዓን ለመድረስ፣ የተስፋይቱን ሀገር ለመውረስ በጉዞ ላይ ሳሉ በአንድ ወቅት ቆሬ፣ ዳታንና አቤሮን የተባሉ ፫ ሰዎች

‹‹መንግሥቱን ሙሴ፤ ክህነቱን አሮን ተቀራምተውት እግዚአብሔር ሰው እንዳጣ ኹለት ወንድማማቾች ብቻ በማኅበሩ ላይ ታበዩ፤ ከበሩ!›› ብለው በእግዚአብሔር አመጹ፤ በሙሴና በአሮን ላይ በምቀኝነት ተነሱባቸው፡፡

በተለይ የአሮን ክህነት ላይ ከፍተኛ ቅንዓት ስለነበራቸው ‹‹እኛስ ከማን አንሰን!›› በማለት ልብሰ ተክህኖ ለብሰው፣ ማዕጠንት ይዘው ከመገናኛው ድንኳን ገብተው ለማጠን ሲሞክሩ ከመላ ቤተሰቦቻቸው ጋር ምድር ተከፍታ ውጣቸው ከነሕይወታቸው ሲኦል ወርደዋል፡፡

ከዚህ መቅሠፍት በኋላ እግዚአብሔር ምንም እንኳ ‹‹ወንድምህ አሮንም ነቢይ፣ ካህን ይሁንህ›› ብሎ ፣ሙሴን እማኝ አድርጎ፣ አስቀድሞ የመረጠው አገልጋዩ ቢኾንም አሮንን ለክህነት የመምረጡን ቃልኪዳን ለማጽናት፣ በ ፫ቱ አማጽያን ምክንያት በሕዝቡ የተፈጠረውን ውዥንብር ለማጽዳት ታላቅ ምልክት በሕዝቡ ፊት ለማሳየት ፈለገ፡፡

ሙሴንም ጠራውና፦፲፪ አብትር(በትሮች) ከ፲፪ቱ ነገድ አለቆች እንዲሰበስብና በመጀመርያው ሰዓተ ሌሊት ከመቅደስ እንዲያኖረው፤ በማግሥቱም በመጀመርያው ሰዓተ መዓልት በሕዝብ ኹሉ ፊት እንዲያያቸው ነገረው፡፡ ሙሴም እንደታዘዘው አደረገ፡፡

በበነጋው አብትሩ ሲታዩ ከነገደ ሌዊ የአሮን በትር ሳይተክሏት፣ ውኃም ሳያጠጧት አብባ፤ አበባዋም የበሰለ የለውዝ ፍሬን አፍርታ ተገኘች፡፡ በትሯ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን ድርሰቱ እንዳብራራው የእመቤታችን ምሣሌ ናት፡፡ ስለኹለት ነገር፡፡

አንደኛው፦በትረ አሮን እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት መጀመርያ በደብተራ ኦሪት፣ ኋላም በቤተመቅደሱ ቅድስተ ቅዱሳን ከሚቀመጡ ከ፭ቱ የብሉይ ንዋያት አንዷኾና ትጠበቅ እንደነበር ኹሉ (ዕብ.፱፥፫-፬ ፣ዘኁልቊ ፲፯፥፲ ድንግል ማርያምም ፲፪ ዓመት በቤተመቅደስ መላእክት እየጠበቋት እያገለገሏት በንጽሕና በቅድስና ስለኖረች ነው፡፡

ኹለተኛና ዋናው ግን፦ በትሯ ሳትተከል፣ ውኃ ሳትጠጣ እንዳበበችና እንዳፈራች፤ ድንግል ማርያምም እንዲሁ ያለ ወንድ ዘር መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወልዳለችና ነው፡፡ እንግዲህ በትር እመቤታችን ከሆነች፤ የበቀለው አበባ ከርሷ የተወለደው የማኅፀኗ ፍሬ ክርስቶስ እንደኾነ ግልጽ ነው፡፡

አበባው ያፈራው የለውዝ ፍሬ ደግሞ ልጇ የዘለዓለም ሕይወት ይኾነን ዘንድ እንካችሁ ብሎ የሰጠን ፍሬ ሕይወት ሥጋ ወደሙ ነው፡፡ ይኼን ታላቅ ምስጢር በመንፈስ ቅዱስ የተረዳው ነቢይ፣ ልዑለ ቃል ኢሳይያስም ደረቅ ሐዲስ በተባለ የትንቢት መጽሐፉ ላይ ‹‹ትወጽእ በትር እምሥርወ እሤይ፤ ወየዐርግ ጽጌ እምጉንዱ…ከእሤይ ሥር በትር ትወጣለች፤ ከግንዱም አበባ ያቊጠቁጣል፡፡›› (ት.ኢሳ.፲፩፥፩) በማለት ያለማወላወል የእሤይ ልጅ የዳዊት ዘር የኾነች እመቤታችን በትር፤ አበባ ደግሞ ክርስቶስ እንደኾነ ነግሮናል፡፡

በተጨማሪ ክርስቶስ በአበባ የሚመሰልባቸው ሌሎችም ምክንያቶች አሉ፡፡ የአበባ መልኩ ውበቱ እንደሚማርክ ኹሉ፦ ክርስቶስም መልኩ የከበረ፣ ደምግባቱ ያማረ ስለነበር በአበባ ተመሰለ፡፡ ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም ‹‹ይሴንይ ላህይከ እምውሉደ እጓለ እምሕያው... ከሰው ልጆች ይልቅ መልክህ ደምግባትህ ያማረ ነው፡፡›› (መዝ.፵፭፥፪) ብሎ መሥክሮለታል፡፡ በመዋዕለ ትምህርቱም ከተከተሉት ከ፭ ገበያው ሕዝብ አንድ ገበያ ያኽሉ ይኽን የተወደደ ደምግባቱን ለመመልከት ብቻ የመጣ ነበር፡፡

የአበባ መልሶ እንዲረግፍ እንዲሁ የከርስቶስም ያማረ ደምግባት ስለሁላችን መከራን በተቀበለ ጊዜ በግርፋት ብዛት ጎስቊሏል፣ ጠፍቷልና አበባ ተባለ፡፡ ‹‹ባየነው ጊዜ እንወደው ዘንድ ደምግባት የለውም፡፡›› (ኢሳ. ፶፫፥፪) እንዲል፡፡ የአበባ ለአፍንጫችን መልካም የኾነ መዓዛ እንዳለው ኹሉ ክርስቶስም አሠረ ፍኖቱን አብነቱን የተከተሉ፣ ትምህርተ ወንጌሉን የተቀበሉ፣ ለስሙ የተጋደሉ ቢሎም ሰማዕትነትን የተቀበሉ ቅዱሳንና ምዕመናን መዓዛዎቹ ናቸውና በአበባ ተመስሏል፡፡

ክርስቶስ መዓዛ ቅዱሳን፣ መዓዛ ምዕመናን ተብሎይጠራል፡፡ ማኅቶተ ቤተክርስትያን፣ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው መልዕክቱ ላይ ‹‹በሚድኑቱና በሚጠፉቱ ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና›› (፪ቆሮ.፪፥፲፭) በማለት የተናገረው ይኽንኑ ነው፡፡

አማን በአማን ክርስቶስ አበባ እኛ ክርስትያኖች መዓዛዎቹ፣ ክርስቶስ የወይን ግንድ እኛ ቅርንጫፎቹ (ዮሐ.፲፭፥፭)፣ ክርስቶስ አካል እኛ ብልቶቹ (፪ቆሮ.፲፪፥፲፪) እንደኾንን ቅዱስ መጽሐፍ ይመሠክራልና ክርስቶስ በአበባ መመሰሉ ትክክል ነው፡፡

ይቆየን!

#DaregoMedia

Report Page