ብርሃን ባንክ የትምርት ቤቶችን ክፍያ በዲጂታል ሥርዓት ማስተናገድ ጀመረ

ብርሃን ባንክ የትምርት ቤቶችን ክፍያ በዲጂታል ሥርዓት ማስተናገድ ጀመረ

Ethiopian Business daily

Join - Ethiopian Business Daily


የክፍያ መንገዶች በማዘመን ሒደት ትምህርት ቤቶችን በዲጂታል የክፍያ አገልግሎት ተካታች የሚያደርግ ሥርዓት መዘርጋቱን ብርሃን ባንክ አስታወቀ፡፡ ትምህርት ሚኒስቴርም በሥርዓቱ አብሮ መሥራት ጀምሯል፡፡

 ብርሃን ባንክ ሰኞ ጳጉሜን 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በይፋ ያስጀመረው የትምህርት ቤቶች የዲጂታል ክፍያ አገልግሎት ‹‹ብርሃን ስኩል ፔይ›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ወላጆች በሚያመቻቸው የክፍያ አማራጭ የትምህርት ቤት ክፍያዎችን ካሉበት ሆነው እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

ከስማርት ስልኮች በተጓዳኝ በማንኛውም ዓይነት የሞባይል ስልክ አገልግሎት የሚሰጥበት ይህ አሠራር፣ የትምህርት ቤት ክፍያዎች ከሞባይል በተጨማሪ በኢንተርኔትም መፈጸም ያስችላል፡፡ ባንኩ ከትምህርት ቤቶች ጋር ውል በመግባት እያንዳንዱ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ተማሪ የራሱ ሚስጥራዊ መለያ ቁጥር ተሰጥቶት በዚሁ መለያ ቁጥር ወይም ኮድ አማካይነት ክፍያ የሚፈጽምበት ዘመናዊ የክፍያ ዘዴ ለወላጆችና ተማሪዎች ማቅረቡን ባንኩ አስታውቋል፡፡

ስለ አገልግሎቱ ገለጻ ያደረጉት የብርሃን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አብርሃም አላሮ እንዳሉት፣ ችግር የሚፈቱና በጥናት ላይ የተመሠረቱ አገልግሎቶችን ወደ ሥራ የማስገባት ሥራ ባንኩ እያከናወነ ይገኛል፡፡ የብርሃን ባንክ የትምህርት ቤት የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ለትምህርት ቤቶችና ለተማሪ ወላጆች ስለሚሰጣቸው ጥቅሞች አብራርተዋል፡፡ ለትምርት ቤት የሚከፈለው ክፍያ በምን አግባብ ወደ ትምህርት ተቋሙ እንደተላለፈ ለማወቅ፣ ሒደቱ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ፣ የትኛው ተማሪ እንደከፈለና እንዳልከፈለ በቀላሉ ለማወቅ የሚያስችል ሥርዓት ሲሆን፣ ከተለመደው መደበኛ የክፍያ አገልግሎት ለየት ተደርጎ እንደቀበረ አብራርተዋል፡፡

 የአገልግሎቱ መጀመር ወላጆች ወደ ትምህርት ቤትና ወደ ባንክ ቅርንጫፍ በመሄድ የሚያባክኑትን ጊዜና ገንዘብ ይቀንስላቸዋል ያሉት አቶ አብርሃም፣ የተዘረጋው የክፍያ ሥርዓት ማናቸውንም ግንኙነቶች በአጭር ጽሑፍ መልክቶች አማይነት መለዋወጥ እንዲችሉ የሚያስችላቸው በመሆኑም አጠቃላይ ተግባቦቱን በተሻለ ለማቀራረብና ፈጣን የመረጃ ልውውጥ እንዲፈጠር ያስችላል ብለዋል፡፡

እንዲህ ያለው አገልግሎት የትምህርት ቤት ክፍያዎችን በቀላሉ ከመፈጸም ባሻገር የዲጂታል ክፍያ ሥርዓትን ለማስፋፋት የሚደረገውን ጥረት ለማጠናከር አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የብርሃን ባንክ ፕሬዚዳንት ይጠቅሳሉ፡፡

ባንኩ ትምህርት ቤቶችን ወደ ዲጂታል ሥርዓቱ ለማስገባት ባደረገው ጥረት እስካሁን 13 ትምህርት ቤቶች እንደተቀላቀሉት አስታውቋል፡፡ እስካሁንም ከ91 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ መሰብሰብ ችሏል፡፡ በርካታ ትምህርት ቤቶችን ወደ ዲጂታል ክፍያ የማስገባቱ ሥራ እየተካሄደ ሲሆን፣ በተለይ ትምህርት ሚኒስቴር ምዝገባ እንዲጀመር ካስታወቀ ወዲህ በርካታ ትምህርት ቤቶች ይህንኑ አገልግሎት ፍለጋ እየመጡ እንደሚገኙ ብርሃን ባንክ አስታውቋል፡፡

የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቱ ወደ ባንክ በመሄድ የትምህርት ክፍያዎችን መፈጸም ለሚፈልጉም የተመቻቸ ሥርዓት እንዳለው ሲገለጽ፣ ወላጆች የብርሃን የሞባይል ሒሳብ አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑም የልጆቻቸው ወርኃዊ ክፍያ በዚያው አግባብ እንዲደርሳቸውና ክፍያውን እንዲፈጽሙ ያስችላቸዋል ያሉት አቶ አብርሃም፣ የክፍያ ሥርዓቱ ትምህርት ቤቶች በሚያስቀምጡት መሥፈርትና ፈቃድ ላይ ተመሥርቶ ወላጆች ቅድሚያ ክፍያ እንዲከፍሉ የሚያስችል ጭምር እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡ በተለያየ ጊዜ ቆራርጠው መክፈል የሚችሉበት አሠራርም እንዲኖረው በመደረጉ ትምህርት ቤቶች እንዲህ ያለው አገልግሎት ለወላጆች እንዲቀርብ ሲፈቅዱ ይተገበራል ተብሏል፡፡ 

አገልግሎቱን በይፋ ያስጀመሩት የትምህርት ሚኒስትሩ ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር)፣ ብርሃን ባንክ ትምህርትን ከዲጂታል ሲስተም ጋር በማገናኘት አገልግት መስጠት መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ዓለማችን ዲጂታል እየሆነ ነው፡፡ ብዙ ነገር ወደ ቴክኖሎጂና ወደ ዲጂታል ያጋደለ እየሆነ ነው፡፡ ምናልባትም በኮሮና ምክንያት ቴክኖሎጂ ምን ያህል ጠቃሚና አስፈላጊ እንደሆነ ያየንበት ወቅት ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ የትምህርት ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት ከደረሰባቸውና ከተመቱ ዘርፎች መካከል አንዱ እንደሆነ በመጥቀስ ከጠቅላላ ኢኮኖሚው በመከተል በሁለተኛ ደረጃ የተጎዳ ዘርፍ ስለመሆኑም አስታውቀዋል፡፡

ሚኒስትር ጌታሁን እንዳሉት በተመድ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) መረጃ መሠረት 195 አገሮች በሚያዝያና ግንቦት ወር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ትምህርት ቤቶቻቸውን ዘግተው 1.6 ቢሊዮን ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታ ተለያይተው በቤታቸው እንዲቀመጡ ያስገደደ ወረርሽኝ በመከሰቱ ከፍተኛ ጫና ተፈጥሯል ብለዋል፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮችም በቴክኖሎጂ ለመጠቀም እምብዛም ዝግጁ ስላልነበሩ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ገብተዋል፡፡ በኢትዮጵያ በትምህርት ላይ የነበሩ 26 ሚሊዮን ያህል ተማሪዎች ከትምህርት ተስተጓጉለዋል ያሉት የትምህርት ሚኒስትሩ፣ ከ26 ሚሊዮን ተማሪዎች ውስጥ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ከመቶ ሺሕ የማይበልጡ በኢንተርኔት፣ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ትምህርታቸውን ለመከታተል እንደቻሉ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ስለዚህ ኮቪድ ያስተማረን ነገር ቴከኖሎጂ ቅንጦት እንዳልሆነና ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ነው፤›› በማለት ቴክኖሎጂ ተኮር አገልግሎት መስፋፋት እንዳለበት አመላክተዋል፡፡

እንደ ትምህርት ሚኒስትሩ ገለጻ፣ የንግድና የፋይናንስ ሥርዓቱ ቴክኖሎጂን ያማከለ እንዲሆን ተደርጎና የዲጂታል ስትራቴጂም ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ እንዲሸጋገር ሥራዎች መጀመራቸውን አስታውቀዋል፡፡ የትምህርት፣ የግብርና፣ የኢንዱትሪ ዘርፉ በተለይም የማኑፋክቸር ዘርፉን ጨምሮ ሁሉም የኢኮኖሚ ዘርፎች ቴክኖሎጂን እንዲጠቀሙ መንግሥት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ለዚህ አጋዥ የሆኑ ሕጎችና ሥርዓቶች እንደተዘረጉ፣ ከዚህ በኋላም በሁሉም ዘርፎች ቴክኖሎጂ እንዲተገበር መንግሥት መወሰኑን ገልጸዋል፡፡

ከዲጂታል ቴክኖሎጂ አኳያ ትምህርት ሚኒስቴር ስለሚያከናውናቸው ተግባራት የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ በአሁኑ ወቅት 450 ሺሕ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን በዚሁ አግባብ ብሔራዊ ፈተና እንዲወስዱ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ፣ ለተማሪዎችም ልዩ የመለያ ቁጥር እንደሚዘጋጅላቸው አብራርተዋል፡፡ በ2013 ዓ.ም. የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚከታተሉ ተማሪዎች ቁጥር 4.6 ሚሊዮን እንደሚሆን ተጠቅሶ፣ የእዚህ ተማሪዎች የጣት አሻራ ተወስዶ በሚካሄድ ምዝገባ አማካይነት ልዩ መለያ ቁጥር ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ አሠራር የክፍያ ሥርዓቱን ጨምሮ የተማሪዎችን የትምህርት ውጤት በኦላይን ለመላክና እንዲያውቁት ለማድረግ ይረዳል ተብሏል፡፡

በመጪው ዓመት ትምህርት ሚኒስቴር ሁሉም ተማሪዎች ልዩ የመለያ ቁጥርና መታወቂያ እንዲኖራቸው የማድረግና ከባንኮች ጋር የማገናኘት ዕቅድ እንዳለ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ያለውን ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት ከትምህርት ዘርፍ ጋር በማስተሳሰር ሌሎች ባንኮችም እንዲሳተፉበት ጠይቀዋል፡፡

ብርሃን ባንክ ይህንን አገልግሎት በተለያዩ አማራጮች ማቅረቡ ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓቱን ከማጎልበት ባሻገር፣ ወደ ባንክ አገልግሎት የሚመጡ ዜጎችን ቁጥር ለማበራከት አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ባንኩ ለትምህርት ቤቶች ላቀረበው የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት እስካሁን የአገልግሎት ክፍያ ሳይጠይቅ በነፃ እያቀረበ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ትምህርት ቤቶችም ሆኑ ወላጆች ለአገልግሎት ክፍያ ባይጠየቁም ወደፊ ግን የአገልግሎት ክፍያ እንደሚኖረው ታውቋል፡፡ ብርሃን ባንክ ከተመሠረተ አሥር ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከ17 ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖችን ያካተተ የግል ባንክ ነው፡፡ 

#Reporter

Report Page