ባሕር ተከፈለ

ባሕር ተከፈለ

ዲያቆን አሸናፊ መኮንን

ባሕር ተከፈለ


ቍጥር የሌለው ኃጢአታችንን ቍጥር በሌለው ፍቅርህ ደምስሰህ ይኸው ባሕር ተከፈለ ። መውለድ መሐን መሆን ሁለቱም ሲያስፈራን ፣ ፍቅር ጥላቻ ሁለቱም ሲያውከን ፣ የምንመርጠውን ለማናውቅ ለእኛ ባሕር ተከፈለ ። ገነትን አጥተን ግዞት ለወረድነው ፣ ንገሡ ብንባል በሌብነት ቅጠል ሥር ለተሸሸግነው ፣ ልጆቻችን ሲጋደሉ ላየነው ፣ ሞትን በልጅ ለጀመርነው ለእኛ ለትኩዛን ደስ ይበለን ባሕር ተከፈለ ።


ውኃ ተሸክመን ፣ ውኃ ሆነን ውኃ ለምንፈራ ፣ በውኃ ጅራፍ ልክ የሌለው መከራ ለደረሰብን ፣ ሞገድ የማይቀርበው መርከብ ኢየሱስ ክርስቶስ ፣ ልብሱን ውኃ እንዳይነካው ዕርቃኑን ተሰቅሎ ባሕር ከፈለልን ። በእውነት ደስ ይበለን ። የባለጠጋው አብ ልጅ ፣ ባለጠጋው ኢየሱስ ድሀ መሆን ምን ያስቀናዋል ! ብርዝና ጠጁ ሳለ ሀብታም ሁሉ በድሀ እየቀና ውኃ ፣ ውኃ አለ ። ድሀ የያዘው ሁሉ ሀብታም ያስቀናዋል ። ድሀ መሬት ሲተኛ ፣ መሬት መተኛት ለጤና ጥሩ ነው እያለ ሀብታም በድሀ ቀና ። ባለጠጋው ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ከድሀ ቤት ማደርህ ፣ እንደ ድሀ መኖርህ ፣ በአንዲት ጨርቅ ዕድሜ ልክህን መታየትህ ፣ ምንም እንደሌለው ዕርቃንህን መሰቀልህ ፣ መሬት ላይ ለሦስት ቀን መተኛትህ ፣ ስለ እኛ ብትቀና ነውና ድሀ ሆነህ ባለጠጋ ያደረግኸን የሰማይና የምድር ውበት ፣ የቁንጅና ዳርቻ አማኑኤል ተመስገን ።


ባሕር ተከፈለ ሰዎች እልል በሉ ። በባሕር ላይ መሻገር ሳይሆን በተከፈለ ባሕር ውስጥ ማለፍ ለእኛ ሆነ ። በባሕር ላይ መሻገር ብልጠት ፣ በባሕር ውስጥ ማለፍ የእምነት ኃይል ነው ። የትላንት ገዥ ፣ የጣለኝ ድጥ መልሶ ሊይዘኝ ፣ ወጣሁ ስል ሲያስቀረኝ እየገሰገሰ ነው ። ትላንትናዬ ነገ ላይ ተሻግሮ መንገድ ሊዘጋብኝ ነው ። የትላንት ታሪክ ፣ የዛሬ ሕይወት ፣ የነገ ተስፋ የሌለኝ ሊያደርገኝ ነው ። ምስጋና ለአማናዊው ሙሴ ይሁን ባሕር ተከፈለ ። በእምነት የተሻገሩትን ፣ የሚሞክሩ የተዋጡበት የቀይ ባሕር ምሥጢር ድንቅ ነው ። እምነት ያሻግራል ፣ ሙከራ ያሰጥማል።


ባሕር ተከፈለ በአማናዊው ሙሴ በክርስቶስ ሞት የጀርባ ታሪክ ሆነ ። ልጆቻችንን የበላ ፣ በውዶቻችን ደም ጡብ የሠራ ፣ ኖረንለት የገደለን ፈርዖን ዲያብሎስ ድል ተነሣ ። ላንገናኝ ከሰይጣን ተለያየን ። በሕልማችን እንዳያውከን የፈርዖን ሬሳ በቀይ ባሕር ታየን ። እባቡ እንዳያስደነግጠን ራሱ ተቀጠቀጠልን ። በደምመላሽ ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ በጠላት ራስ ላይ ቆመን ዘመርን ። የወይራው ቀንበጥ መንፈስ ቅዱስ መዳናችንን አረጋገጠልን ። እውነትን በእውነት ተቀበልን ። መንፈሱ ለመንፈሳችን መሰከረልን ። ስለነገሩን ሳይሆን ስለተሰማን በእውነት በእርሱ ዐረፍን ። ባሕር ተከፈለ ሰዎች ደስ ይበለን !!!


ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሚያዝያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም.

Report Page