በፓስፖርት ማጭበርበርና በህገ- ወጥ ሰነድ የተጠረጠሩ ግለሰቦች የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደረገ

በፓስፖርት ማጭበርበርና በህገ- ወጥ ሰነድ የተጠረጠሩ ግለሰቦች የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደረገ

Brook Genene

ፓስፖርት በህገ- ወጥ መንገድ በመስጠት እና በሐሰተኛ ሰነዶች ግለሰቦች ወደ ሀገር ውስጥ እንዲወጡ እና እንዲገቡ በማድረግ ተጠርጥረው ፍርድ ቤት የቀረቡየተከሰሱ የ10 ግለሰቦችን የዋስትና መብት ጥያቄ ውድቅ ተደረገ። 


ከተከሳሾቹ መካካል ሁለቱ የውጭ ሀገር ዜጎች፣ ሁለቱ ደላሎች ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ በኢሚግሬሽን ዜግነት ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ እና በቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት የሚሰሩ ሰራተኞች ናቸው:: 

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት በ ጥቅምት 26 2016 በዋለው ችሎት ተከሳሾች የጠየቁትን የዋስትና መብት መከበር ጥያቄን ከምስክሮች የሚወሰደው ቃል እና የምርመራ ሂደት ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ጫና ምክንያት በማድረግ ጥያቄያቸውን ውድቅ አድርጓል።

በችሎቱ ውሎ ፖሊስ ያደረጋቸውን የምርመራ ሂደቶች  ለፍርድ  ቤቱ አስረድቷል። የጣት አሻራ መውሰድን ጨምሮ የተጠርጣሪዎችን የመኖሪያ ቤት ብርበራ ማድረግ እና የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ለምርመራ መውሰዳቸውን ፖሊስ አስረድቷል:: 

ለተጨማሪም ምርመራም ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበት ድርጊት ያደረሰው የጉዳት መጠንም በገንዘብ እና በአይነት ኦዲት ተደርጎ እንዲቀርብ መጠየቁንም ፖሊስ አስረድቷል። የገንዘቦች ዝውውርን በተመለከተ የባንክ መረጃ በመመልከት ከየት አካውንት ዝውውሩ እንደ ተደረገ ለማጣራት ምርመራ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ፖሊስ ዳኞቹ ገጿል::

የተጀመሩ ምርመራዎች ለማጠናቀቅና ተጨማሪ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ፖሊስ ተጨማሪ 14 ቀናትን ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። 

የተጠርጣሪ ጠበቆችም በተናጠል ደምበኞቻቸው ላይ በቂ ምርመራ ሳይደረግ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን፤ ማንኛቸው፣ የትኛውን ወንጀል መቼ እንደሰሩ በፖሊስ የክስ ማመልከቻ በግልጽ እንዳልተመለሰ፤ የደንበኞቻቸው የስራ ኃላፊነት ተራ የሚባል እንደሆነ እና የተጠረጠሩበትን ወንጀል ለመፈፀም በቂ ምክንያት እንደሌለ፤ ደንበኞቻቸው የውጭ ሀገር ዜጋ እንደሆኑ እና ከኢምግሬሽን ጋር የሚያገናኛቸው ምንም ነገር እንደሌለ፤ ደንበኛቸው ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸው እና በንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰብ መሆናቸውን እና ተጠርጣሪዎች የቤተሰብ ሃላፊዎች እንደሆኑ በመጥቀስ ክሱን ከውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስም በምላሹ ከ2010 ዓ.ም በኃላ ከደህንነት ኤጀንሲ ወደ ኢሚግሬሽን የመጡ ግለሰቦች እንዳሉ እና ሰነዶች በቀላሉ እንዲጠፉ የማድረግ አቅም እንዳላቸው በመግለጽ የዋስትና መብት ጥያቄያቸው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል።

የመርማሪ ፖሊስን ጥያቄ ተቀብለው ዳኞቹ ፖሊስን ምርመራውን አጠናቆ ክስ ለመመስረት ለህዳር 7፣ 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተስጥቷል::


Report Page