በጉራጌ ዞን ጉንችሬ ከተማ በግጭት ሳቢያ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ

በጉራጌ ዞን ጉንችሬ ከተማ በግጭት ሳቢያ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ

ሁሌ አዲስ ሚዲያ

የሙስሊም ሴት ተማሪዎች የተሟላ ሒጃብ (ኒቃብ) በሚማሩባቸዉ ትምህርት ቤቶች መልበስ አለብን በሚለው ጥያቄ ተነስቷል በተባለው ግጭት ከተማው ውጥረት ውስጥ ገብቶ ነበር።

በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ጉንችሬ ከተማ ላይ ያለፈው እሁድ ከምሽት ሁለትሁለት ሰዓት ጀምሮ እምነትን መሰረት አድርጓል በተባለዉ ጥቃት የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ተቋማት ሲወድሙ በሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን ሁሌ አዲስ ሚዲያ አረጋግጧል። 

በከተማዋ በዋናነት ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ ይዘቱን እያሰፋ መጥቷል በተባለዉ ዉጥረት “በሙስሊም እና በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ በሃይማኖታዊ ስርዓቱ ላይ የተፈጠረው አለመግባባት ሳቢያ ትላንት እሁድ ለተከሰተዉ ግጭት መነሻ” መሆኑን ምንጮች ገልፀዋል።  

ለሁሌ አዲስ ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸዉ እንንዳይጠቀስ የፈለጉና የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ምንጫችን ነዋሪነታቸዉን በጉንችሬ ካደረጉ ከ15 ዓመታት በላይ እንደሆናቸዉ ተናግረዉ በትላንትናው ግጭት ማንነታቸው የሚታወቁ ናቸዉ ያሏቸዉ ወደ አስር የሚጠጉ ሰዎች በዱላ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸዉን እንዲሁም በቤት ንብረታቸዉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አስረድተዋል። 

"ምሽት ሁለት ሰዓት ገደማ በአካባቢዉ በተሰማዉ የተኩስ ድምፅ ተደናግጠን  ከቤታችን ወጣን የሚሉት ምንጫችን የእስልምና እምነት ተከታዮች ናቸዉ ያሏቸዉ ሰዎች በዱላ ጥቃት ካደረሱባቸዉ በኋላ ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን” ተናግረዋል። የሞባይል ስልክ መሸጫ መደብራቸዉ እንዲሁም የመኖሪያ ቤታቸዉ መዉደሙን ተናግረዋል።

የግጭቱ መነሻ ምክንያት እንደሆነ የተነገረው በ2014 ዓ.ም. የሙስሊም ሴት ተማሪዎች የተሟላ ሒጃብ (ኒቃብ) በሚማሩባቸዉ ትምህርት ቤቶች መልበስ አለብን በሚል በተነሳዉ ጥያቄ ሲሆን ይሄም ጭቅጭቅ ማስነሳቱ ተነግሯል።

በዞኑ እኖር ወረዳ ጉንችሬን ጨምሮ በአጠቃላይ አራት የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ የትምህርት ተቋማት ሲኖሩ ለሁሌ አዲስ ሚዲያ መረጃ የሰጡት ተማሪዎች በእምነታችን ጫና በመድረሱ ምክንያት ለስነልቦና እንዲሁም ከትምህርት ገበታችን እንድንገለል ሆነናል ብለዋል። 

ለወራቶች እንደ አሁኑ በይፋ ባይወጣም አለመግባባቶች እንደነበሩም ሰምተናል። እንደ መረጃ ምንጮቻችን ባሳለፍነዉ ዓርብ በተከበረዉ በኢድ አልፈጥር በዓል ዕለት በእስልምና ተከታዮች ሰላማዊ ሰልፍ የተደረገ ሲሆን ዋነኛዉ ጥያቄያቸው "በኒቃባቸዉ ምክንያት ከትምህርታቸው የተገለሉት ተማሪዎች ይመለሱ፣ መብታችን ይከበር" የሚሉት ይገኙበታል። 

ሚያዚያ 15፤ 2015 ዓ.ም. ምሽት ላይ ለሦስት ሰዓታት ተደርጓል በተባለው ጥቃት በተመረጡ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ የሆኑ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ንብረቶች ላይ ዉድመትና ዝርፊያ እንዲሁም ድብደባ ተፈፅሟል የሚሉት ምንጮቻችን "እኔ የማዉቃቸዉ የአራት ሰዎች መኖሪያ ቤት ላይና ግለሰቦቹ ላይ ጥቃት ደርሶባቸዋል" ሲሉም የአይን እማኛችን ተናግረዋል። 

ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ጥቃት አይደለም የሚሉት ነዋሪዎቹ ሆን ተብሎ "የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በሚያስብ ጥቂት ቁጥር ያላቸዉ ቡድኖች" የተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። 

ዛሬ ሰኞ ሚያዝያ 16፤ 2015 ዓ.ም. እስከ ረፋዱ አራት ሰዓት ገደማ ድረስ በከተማዋ ዉጥረት የነገሰ ቢሆንም የፌደራል ፖሊስ በመግባት ዉይይት በማካሄድ እንዲረጋጋ ማድረጉን ነዋሪዎች ለሁሌ አዲስ ተናግረዋል። 


ለወቅታዊ እና ለፈጣን መረጃዎች የሁሌ አዲስ ሚዲያ የማህበራዊ ሚዲያዎችን ይቀላቀሉ።

Facebook : https://www.facebook.com/Huleadissmedia/

Telegram : https://t.me/Hulaadiss

YouTube Channel https://www.youtube.com/@huleaddismedia


Report Page