በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ከኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) የተሰጠ መግለጫ

በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ከኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) የተሰጠ መግለጫ


የህዝቦች ወንድማማችነትና የአብሮነት መልካም እሴቶች በአፍራሽ ሃይሎች ተልዕኮ አይደናቀፉም!

**********************************

በአገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቶ ማንኛዉም አካል በነጻነት የመደራጀት፣ የፈለገዉን የፖለቲካ አጀንዳ በሰላማዊ መንገድ እንዲያራምድ፣ የሀገራችን ህዝቦች ለዘመናት የታገሉለትና ዉድ መስዋዕትነት የከፈሉበት እዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እዉን እንዲሆን በርካታ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ፡፡

በዚህ ረገድ ተስፋ ሰጪ ተጨባጭ ዉጤቶችም በመመዝገብ ላይ ናቸዉ፡፡

ሆኖም አንዳንድ የፖለቲካ ሃይሎች ዴሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋት የተፈጠረዉን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመዉ በሰለጠነና በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ አጀንዳቸዉን ከማራመድ ይልቅ የብሄር ጽንፈኛ አስተሳሰብን አንግበዉ በመነሳት፣ ህጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንቅስቃሴን ከህገ ወጥና የግጭት መንገድ ጋር እያጣቀሱ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ታይቷል፡፡

እነዚህ ጽንፈኛ የፖለቲካ ሃይሎች የከሰሩ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ለዘመናት በአብሮነት እና በፍቅር የኖረን ህዝብ ሊያቃቅሩ ብሎም ሊያጋጩ የሚችሉ አጀንዳዎቸን በመቅረጽ ህዝብን ከህዝብ ጋር በማጋጨትና ንፁሃን ዜጎችን በእሳት በመማገድ ሀገራችን ከማትወጣበት የግጭት አዙሪት ዉስጥ በመክተት የለዉጥ እንቅስቃሴዉን ማደናቀፍ ዋነኛ አላማቸዉ አድርገዉ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡

ሰሞኑንም በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደርና በክልሉ በሰሜን ሸዋ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች በነዚህ ሃይሎች ቀስቃሽነት ግጭቶች መከሰታቸዉና በሰዉ ህይወት፣በአካልና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል፡፡ኦዲፒ በግጭቱ ለጠፋዉ የሰዉ ህይወት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ዉድመት የተሰማዉን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ በግጭቱ ዉድ ህይወታቸዉን ያጡ ወገኖች ፈጣሪ ነብሳቸዉን በገነት እንዲያኖር እየተመኘ ለተጎጂ ቤተሰቦችም መፅናናትን ይመኛል፡፡ የጥፋት ድርጊቱንም አጥብቆ ያወግዛል፡፡

በህዝብ ደም የሚነግዱ የፖለቲካ ቁማርተኞች የተፈፀመዉ ጥፋት በየትኛዉም መልኩ ተቀባይነት የሌለዉና ማንኛዉንም ህዝብ የማይወክል መሆኑን አዲፒ ይገነዘባል፡፡ የግጭቱን ጠንሳሾች እና ተሳታፊዎች ለህግ ለማቅረብ በህግ አስከባሪ አካላት የሚደረገዉን የህግ የበላይነት የማስከበር እንቅስቃሴ እንዲሳካ ፓርቲያችን ያልተቆጠበ ድጋፍ ያደርጋል፡፡

ፓርያችን ኦዲፒ የተፈጠረዉን ችግር ለማረጋጋት እና ተመሳሳይ ችግር ዳግም እንዳይከሰት ለመከላከል ከአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና ከአማራ ክልላዊ መንግስት ጋር በመቀናጀት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

በእኩይ የጥፋት ድርጊት የሰከሩ ሀይሎች ሰሞኑን የለኮሱት የጥፋት እሳት የህዝብ ለህዝብ ግጭት በማስመሰልና ችግሩ በኦሮሚያ ክልል እንዲስፋፋ በማድረግ ለዘመናት በወንድማማችነትና በመተሳሰብ በሰላም አብረዉ እየኖሩ ያሉ የኦሮሞና የአማራ ወንድማማች ህዝቦችን በግጭት እሳት በመማገድ ጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙ ታዉቋል፡፡

በሰላም አብሮ የሚኖሩትን ወንድማማች ህዝቦች ለማጋጨት የሚደረግ ማንኛዉም ሙከራና ድርጊት ህዝቦች ለዘመናት ባካበቱት የአብሮነት ዕሴት እና የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሴራዉን ለማክሸፍ ኦዲፒ ዛሬም እንደ ትናንቱ ጠንክሮ ይሰራል፡፡

በዚህ አጋጣሚም የኦሮሞ ህዝብ በተለመደዉ የአቃፊነት ባህሉ ወንድም ከሆነዉ የአማራ ህዝብ እና ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ያለዉን አብሮነት በማጠናከር፣ በክልሉ በህዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚደረጉ የጥፋት ሀይሎቸን ሴራ ለማጋለጥ እና ለማክሸፍ እንዲንቀሳቀስ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

ኦሮሚያ የሁሉም ኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ቤት እንደሆነች ኦዲፒ በጽኑ ያምናል፡፡ በክልላችን የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች አሁን የደረሰንበት የለዉጥ ምዕራፍ ላይ እንድንደርስ ከኦሮሞ ህዝብ ጋር አንድ ሆነዉ ከመሪዉ ፓርቲ ኦዲፒ ጎን ተሰልፈዉ ታግለዋል፡፡ ዉድ መስዋዕትነትም ከፍለዋል፡፡ ፓርቲያችን ኦዲፒ ለዚህም ታላቅ አክብሮት እንዳለዉ በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ ይወዳል፡፡

በክልላችን ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በሰላም፣ በእኩልነት፣ በወንድማማችነት እና በነጻነት እንዲኖሩ ችግሮች ሲከሰቱም ከአሁን ቀደም እየፈታናቸዉ በመጣንበት መንገድ እየተወያየን መፍትሄ እየሰጠን ለመሄድ ዝግጁ መሆናችንና ለጽንፈኛ እና ለከሰሩ የፖለቲካ ሃይሎች የሚከፈት በር እንደማይኖር፤ ለዚህም ፓርቲያችን መላዉን የክልሉን ህዝብ ከጎኑ በማሰለፍ ከማንኛዉም ጊዜ በበለጠ ትግሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡

ፓርቲያችን ኦዲፒ የህዝቦች ወንድማማችነት፣ የኢትዮጵያን አንድነት እና የለዉጡን እንቅስቃሴ ለመገዳደር የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ እና የከሰሩ የፖለቲካ ሃይሎችን ከመላዉ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን እንዲሁም ከለዉጥ ኃይሎች ጋር በመተባበር በጽናት የሚታገላቸዉ መሆኑን ደግመን እናረጋግጣለን!

የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ

ሚያዚያ 01፣ 2011

Report Page