በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው የታሰሩ የደኅንነት ሠራተኞች የሚስጥር ስም ‹‹አቤ ከቤ›› እንደነበር ተገለጸ

በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው የታሰሩ የደኅንነት ሠራተኞች የሚስጥር ስም ‹‹አቤ ከቤ›› እንደነበር ተገለጸ



በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሠራተኞች የነበሩ ግለሰቦች የሚስጥር ስም፣ ‹‹አቤ ከቤ›› እንደነበር ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤት ተናገረ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 943/2008 ድንጋጌ ሥልጣን እንደተሰጠው በመግለጽና በችሎት ተገኝቶ እንደ መርማሪ ፖሊስ ሆኖ መከራከር እንደሚችል አመልክቶ በፍርድ ቤቱ ይሁንታን ያገኘው ዓቃቤ ሕግ፣ የተጠርጣሪዎቹ ሚስጥር ስም ‹‹አቤ ከቤ›› እንደነበር የገለጸው በተርጣሪዎቹ ጉዳት የደረሰባቸውን ግለሰቦች ቃል ሲቀበል ነግረውት መሆኑን አስረድቷል፡፡

የሰብዓዊ መብት ጥሰት የደረሰባቸውን ምስክሮች እነማን ጉዳቱን እንዳደረሱባቸው ሲጠየቁ ስማቸውን እንደማያውቁ፣ ነገር ግን የሚጠራሩት ‹‹አቤ ከቤ›› እየተባባሉ መሆኑን እንዳስረዱ ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡

በተጠርጣሪዎቹ የተፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ውስብስብ መሆኑንና በርካታ የምርመራ ሥራዎች ማከናወኑን ዓቃቤ ሕግ ጠቁሞ፣ የምስክሮችን ቃል መቀበሉንና የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን ገልጿል፡፡ ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመባቸውን ግለሰቦች ቃል መቀበል፣ ተጠርጣሪዎችን በተጎጂዎች ማስለየትና ሌሎች በሥውርና በመደራጀት በቡድን የተፈጸሙ ወንጀሎች ስለሆኑ ተገቢውን ምርመራ በማድረግ የማጣራት ሥራ ለማከናወን ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በራሳቸውና በጠበቆቻቸው አማካይነት ባደረጉት ክርክር፣ ምርመራ እየተካሄደ ያለው እነሱን ለመጉዳት መሆኑን ለፍርድ ቤት ተናግረዋል፡፡ ተፈጽሟል የተባለው ችግር የእነሱ ሳይሆን የሥርዓት ችግር መሆኑን ጠቁመው፣ በዕለቱ የቀረቡት ዓቃቤ ሕግ በወቅቱ እነሱ መርምረው በሚያቀርቡላቸው ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ በመመሥረት ሲከራከሩ እንደነበር በእጃቸው በመጠቆም ተናግረዋል፡፡ እንደ አገርና እንደ ሥርዓት ለጠፋ ወይም ለደረሰ ጉዳት እነሱ ብቻ መጠየቅ እንደሌለባቸውም ተናግረዋል፡፡ እነሱ የተጠረጠሩበት ጉዳይና ምርመራ እየተካሄደበት ያለው ሒደት እንደማይገናኝና ትክክል እንዳልሆነም አክለዋል፡፡ ዓላማው ክስ ለመመሥረት ከሆነ እስካሁን (ላለፉት ሰባት ወራት) የተደረገው ምርመራ በቂ በመሆኑ ክስ መመሥረት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርታ ከጠየቁ እነሱም የማይጠይቁበት ምክንያት እንደሌለ ጠቁመው፣ 27 ዓመታት ሙሉ ለተፈጸመ ጥፋት ግን እነሱ ብቻ ሊጠየቁ እንደማይገባም አስረድተዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮች እያለ የሚጠራቸው ሰዎች በዚህ ችሎች በተመሳሳይ ዓቃቤ ሕግ ክስ ተመሥርቶባቸውና ጥፋተኛ ተብለው ቅጣት የተጣለባቸው ከመሆኑ አንፃር፣ በእነሱ ላይ ምስክር አድርጎ መቁጠር ተገቢ ነው ብለው እንደማያምኑ አስረድተዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ተደጋጋሚና ተመሳሳይ የምርመራ ሒደት ለፍርድ ቤቱ ሲያቀርብ ‹‹በቃህ›› ሊባልና ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሊፈቀድለት እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡ ከመንግሥት በሚመጣላቸው ትዕዛዝ መሠረት ሲሠሩ ኖረው ብቻቸውን ተጠያቂ መሆናቸው ተገቢ እንዳልሆነና መጠየቅ ካለባቸውም ሌሎቹም ሊጠየቁ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ለአምስት ወራት ምርመራ ሲካሄድባቸው እንደነበር ለሕዝብ ይፋ ማድረጋቸውንና ከታሰሩም ሁለት ወራት እንዳለፋቸው ጠቁመው፣ ለሰባት ወራት በጊዜ ቀጠሮ መቆየታቸው ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ ሁልጊዜ ምርመራው ውስብስብ መሆኑን ቢናገርም ቀላል መሆኑን ጠቁመው፣ ውስብስብ የሆነበት የአራት ተቋማት ሠራተኞች በጅምላ በማቅረቡ ስለሆነ አሁን ለያይቶ በማቅረብ ሊያጠናቅቅ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ የምትመራው በተጻፈ ሕግ በመሆኑ ‹‹ወንጀል የሆነው ወንጀል ይሆናል፡፡ ወንጀል ያልሆነው አይሆንም፡፡ ይኼ ሕግና መርህ ነው ያሉት ተጠርጣሪዎቹ፣ በእነሱ ላይ ያለውንና የተፈለገውን ነገር በመሥራት የተፋጠነ ፍትሕ ከመስጠት ይልቅ፣ በክልሎች ምስክሮችንና ተቋማት በመፈለግ ወንጀል ፍለጋ ላይ መጠመድ እንደሌለበትና ተገቢም እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በየክልሉ እየሄደ ተጎጂ ከመፈለግ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች በኩል የፈለገውን መረጃ ማግኘት እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ መርማሪ ቡድኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል እያለ እነሱ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እያደረሰባቸው መሆኑን አክለዋል፡፡

የሠሩት ሥራ ሕገ መንግሥቱን አምነውና አገራቸውን ወደው በመሆኑና ብቻቸውን ሳይሆን ከታች እስከ ላይ ድረስ በሰንሰለት የተያያዘ ሥራ ስለሆነ፣ ብቻቸውን ተለይተው መጠየቃቸው ተገቢ እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡ ከቂሊንጦ እስረኞች ሞትና ቃጠሎ ጋር በተገናኘ ዘጠኝ ሰዎች ተመርጠው መታሰራቸው ተገቢ አለመሆኑን ጠቁመው፣ የፍትሕ ሚኒስትሩ በቦታው ተገኝተው በሰጡት ትዕዛዝ የተፈጸመን ሥራ (ተጠርጣሪዎች ወደ ሸዋ ሮቢትና ዝዋይ ማረሚያ ቤቶች እንዲወሰዱ) እነሱን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ምስክሮችን ማስታጠቃቸውንና ቤትም ሰጥተው ጥበቃ እየተደረገላቸው ስለሆነ የሚያስፈራቸው ነገር ባለመኖሩ፣ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ጠይቀዋል፡፡

የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤት ተጠርጣሪዎቹን አራት ቦታ በመክፈል ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ፈቅዷል፡፡ በአቶ ተስፋዬ ገብረ ፃድቅ፣ በአቶ ዮሐንስ ውበት፣ በኦፊሰር አሰገደ ወልደ ጊዮርጊስና በዋና ሱፐር ኢንቴንደንት አሰፋ ኪዳኔ ላይ 14 ቀናት ተጨማሪ ጊዜ ፈቅዷል፡፡ አቶ ጎሃ አጽብሃን ጨምሮ በ16 ተጠርጣሪዎች ላይ 12 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ፈቅዷል፡፡ ምክትል ኮማንደር ዓለማየሁ ኃይሉና ምክትል ኢንስፔክተር የሱፍ ሐሰንን ጨምሮ አምስት ሰዎች ላይ አሥር ቀናት፣ እንዲሁም ኦፊሰር ዋና ሳጅን ርዕሶም ክህሽንን ጨምሮ በዘጠኝ ተጠርጣሪዎች ላይ ሰባት ተጨማሪ ቀናት በመፍቀድ ለጥር 13፣ 15 እና 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ምንጭ፦ ሪፖርተር

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page