ሶሻል ፎቢያ (Social Anxiety Disorder)

ሶሻል ፎቢያ (Social Anxiety Disorder)

Dr. Tena - Bethel


🖐🖐🖐 ሰላም የዶክተር ጤና ቤተሰቦች!! 🖐🖐🖐

 በጥያቄያችሁ መሰረት ሰዎች በበዙባቸው ቦታዎች ላይ የፍርሃት ስሜት በምን ምንያት እንደሚመጣ እና መፍትሔዎቹ እናወራለን፤ አብራችሁን ቆዩ!!

 

ሶሻል ፎቢያ (Social Anxiety Disorder) ምንድነው?

ሰዎች ባሉባቸው ቦታዎች ላይ የፍርሃት ስሜት የተለመደ እና ጤናማ ነው፡፡ ለምሳሌ ከአዲስ ሰው ጋር ቀጠሮ ሲኖረን ወይም ተመልካች ባለበት የምናቀርበው ነገር ሲኖር ልንፈራ እንችላለን ፡፡ ነገር ግን ሶሻል ፎቢያ (Social Anxiety Disorder) በእለት ተእለት እንቅስቃሴ ላይ ከሰዎች ጋር ባለን መስተጋብር በሌሎች የመተቸት ስጋት ስለሚኖር ከባድ ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ የሚከብድ ስሜት እንዲሁም በራስ አለመተማመን ሲሰማ ነው፡፡

 

መሰል ስሜቶች ማህበረሰባዊ መስተጋብርን ጭራሹን ሊያስቀሩት ይችላሉ፡፡ ተያይዞም የትምህርት፣ የስራ፣ እና ሎች እንቅስቃሴዎች ይገደባሉ፡፡


Social Anxiety Disorder አብሮ የሚቆይ የአእምሮ በሽታ ነው፤ የተለያዩ መንገዶችን መለማመድ፣ የንግግር ህክምና እንዲሁም አንዳንድ መድሐኒቶች በራስ መተማመን ስሜትን ዳግም ሊያመጡ እና ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት የማሻሻል ብቃት እንዳላቸው ይነገራል፡፡

 

ምልክቶች

ሰዎች ባሉበት ቦታዎች የማፈር ወይም ያለመመቸት ስሜት በተለይ ልጆች ላይ ሲታይ የሶሻል ፎቢያ ላይሆን ይችላል፡፡ እነዚህ ስሜቶች እንደየ ማህበራዊ ሁኔታዎች ይለያያሉ እንዲሁም እንደየሰዉ የህይወት ልምት የተለያዩ ናቸው፡፡ አንዳንድ በተፈጥሮ ተግባቢ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ የተቆጠቡ ሰዎችም እንዳሉ መዘንጋት የለበትም፡፡

የስሜት ምልክቶች

-        ሰዎች ይፈርዱብኛል ተብሎ የሚታሰቡ ሁኔታዎችን መፍራት

-        እራስን ላለማዋረድ መጠንቀቅ

-        ከአዲስ ሰዎች ጋር በሚነጋገሩ ወቅት ጥልቅ የሆነ የፍራቻ ስሜት

-        ሰዎች እንደተጨነቁ እንዳያውቁ መፍራት

-        ከፍራቻ ጋር አካላዊ ለውጦች (እንደ ላብ፣ የፊት መቅላት፣ የእጅ መንቀጥቀጥ ወይም የድምፅ መቅጠን) ሲታዩ የመሳቀቅ ስሜት

-        ሰዎች የበዙበት ቦታ ላይ አለመናገር

-        አትኩሮት የሚሰበስብ ነገር በጭራሽ አለማድረግ

-        ገና ለገና የሚያስፈሩ ነገሮችን ለማድረግ ሲያስቡ ከባድ ጭንቀት ውስጥ መውደቅ

-        ከማህበራዊ መስተጋብሮች በኋላ ምን እንዳሉ ማሰብ እና የት የት ጋር እንደተሳሳቱ ማንሰላሰል

-        ከሰዎች ጋር በሚኖር ማህበራዊ ቅርርበት ላይ በጣም መጥፎ ነገር ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ

 

አካላዊ ምልክቶች

-        የፊት መቅላት

-        የልብ ምት መጨመር

-        የእጅ መንቀጥቀጥ

-        ላብ

-        የሆድ መረበሽ፣ ማቅለሽለሽ

-        ትንፋሽ ማጠር

-        ራስ ማዞር

-        የጡንቻ ውጥረት

 

የማህበራዊ ግንኙነቶችን ማስወገድ

ለምሳሌ፤

-        ከአዲስ ሰዎች ማግኘት

-        ብዙ ሰው የሚገኝባቸው ቦታዎች መሄድ

-        ስራ ወይም ትምህርት ቤት መሄድ

-        ንግግር መጀመር

-        ፆታዊ ግንኙነት መጀመር

-        ሰዎች ከተቀመጡ በኋላ መግባት

-        ሰዎች ፊት መብላት

-        የጋራ መጸዳጃ ቤቶችን መጠቀም

 

ምልክቶቹ ከጊዜ እና ከሁኔታዎች ጋር ይለዋወጣሉ፡፡ ውጥረት ውስጥ ካለን ሊነሳ ይችላል፡፡ መሰል ስሜቶችን የሚያመጡ ሁኔታዎችን ማስወገድ ለጊዜው ጥሩ ስሜት ቢሰጥም የፍርሃት ስሜቱን በተገቢው መፍትሔ ካልተፈለገለት አብሮ ይቆያል፡፡

 

ሃኪሞት ጋር መቼ ሄድ አለቦት?

በፍርሃት፣ መሳቀቅ እና ጭንቀት ምክንያት የተለመዱ የማህበራዊ ግንኙነቶችን እና መሰል ሁኔታዎችን የሚፈሩ እና የሚሸሹ ከሆነ የህክምና እርዳታ ያስፈልጎታል፡፡

 

በምን ምክንያት ይመጣል?

እንደሌሎች የስነ-አእምሮ በሽታዎች ይሄም በጣም ብዙ ምክንያቶች እንደሚያመጡት ይታመናል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፤

1.      ከቤተሰብ የሚወረስ

2.      የአእምሮ ክፍል ችግር

3.      የአካባቢ ተፅዕኖ

 

 ተጋላጭነት

·        በቤተሰብ ተመሳሳይ ችግር ካለ

·        መጭፎ ልምድ

·        ተጨቁኖ ማደግ

·        አዲስ ማህበራዊ ወይም የስራ ሁኔታ

·        የሰዎችን ትኩረት የሚስብ ገፅታ

 

ምን ሊያመጣ ይችላል?

-         የወረደ በራስ መተማመን ስሜት

-         ስለራስ ጥሩ ያልሆነ አስተሳሰብ

-         ትችትን መፍራት

-         የማህበራዊ ግንኙነት ቀውስ

-         ማህበራዊ ተግባቦቶችን ማስወገድ እና መለየት

-         የስራ እና የትምህርት ውጤት መቀነስ

-         ሱስ ውስጥ መግባት (እንደ አልኮል፣ ጫት…)

-         ራስን ለማጥፋት መሞከር ወይም ማድረግ

 

እንዴት መከላል ይቻላል?

ይህን መሰል የፍርሃት ስሜት ማን ላይ ወይም በምን ሰዓት ሊከሰት እንደሚችል መገመት አይቻልም፡፡ ነገር ግን እንደዚህ አይነት ስሜቶች ሲኖሩ ለመቀነስ ወይም እንዳኖሩ ለማድረግ የሚከተሉትን ማድረግ ይመከራል፤

·        ሳይዘገዩ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ

·        የእለት ተእለት ውሎን መፃፍ

·        በህይወት ውስጥ ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች መለየት

·        ሱስ ከሚያስይዙ ነገሮች መራቅ

 

ምርመራ

ሃኪም ጋር ሲቀርቡ የተለያዩ አካላዊ ምርመራዎች በማድረግ፣ ጥያቄዎች በመጠየቅ ስለሁኔታው ይበልጥ ለመረዳት ይሞክራል፡፡ የቤት ስራዎችን ሊሰጦትም ይችላል፤ እንደ የፍርሃት ስሜት ሊያመጡ የሚችሉ ሁኔታዎችን መዘርዘር፣ ስሜቱን በደንብ አዳምጦ መመዝገብ እና ሌሎችም፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ ባሉ መስፈርቶች አንፃር የፍርሃቱን አይነት ለማወቅ ይሞክራል፤ ከዚያም ወደ መፍትሔው ይሄዳል፡፡

 

ህክምናው

ስሜቱ የእለት ተእለት እንቅስቃሴን የሚጎዳበት መጠን የህክምናውን አይነት ይወስናል፡፡ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት የንግግር ህክምና ወይም የሚዋጡ መድሐኒቶች ይታዘዛሉ፡፡

 

አስታውሱ!!

-         የህክምናው ውጤት ቢዘገይም ተስፋ እንዳይቆርጡ፤ ምክንያቱም እስከ ወራት ሊወስድ ስለሚችል

-         ለእርሶ የሚሆን የህክምና መንገድ መምረጥ ሙከራዎች ያስፈልጉታል

-         አንዳንዶች ህክምናውን ለረጅም ጊዜ መውሰድ ይኖርባቸዋል፤ ሌሎች ደግሞ በጥቂት ጊዜ መሻሻል ሊያሳዩ ይችላሉ

-         መድሐኒት ማቋረጥ በሽታው እንዲብስ ያደርገዋል

-         የሃኪሞትን ምክር በተገቢው መልኩ ተግባራዊ ያድርጉ

 

 ይህንን መረጃ ሼር በማድረግ ለሌሎች ያጋሩ!!

                            

ተጨማሪ የጤና መረጃ እንዲደርሶ፦

        የዶክተር ጤና ቴሌግራም ገፅ

                          t.me/DoctorTena

         የዶክተር ጤና ፌስቡክ ገፅ፦

                        fb.com/DoctorTenaEthiopia

 

Report Page