ስንክሳር ዘወርኀ ጥቅምት ፴
@YeBiruk ዲያቆን ቡሩክ ይርጋ ዘውብ✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
አሜን
✍"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
ቀናችንን በጸሎት እንጀምር
ስንክሳር ዘወርኀ ጥቅምት ፴
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥቅምት ሠላሳ በዚች ቀን መኑፍ ከሚባል አገር በገድል የተጸመደ ቅዱስ አባት ባሕታዊ አብርሃም አረፈ።በግብፅ ምድር ያሉ ጣዖታትን ፈጽሞ ያጠፋ እስከ ኢትዮጵያም ድረስ መጥቶ ወንጌልን ያስተማረ በመጨረሻም አረማዊያን አካሉን በበሬ አስጎትተው ሥጋው ተበጣጥሶና ተቆራርጦ እስኪያልቅ ድረስ ያሠቃዩት፣ የቀረውንም አካሉን ሰብስበው በእሳት ያቃጠሉት፣ የከበረች ወንጌልን የጻፈ፣ ሐዋርያው ቅዱስ ማርቆስ ልደቱ ነው፡፡
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❖ ማርቆስ ማለት ‹‹አንበሳ፣ ንብ›› ማለትነው፡፡ የቀድሞ ስሙ ዮሐንስ ነው፤ እናቱ ማርያም ቅዱሳን ሐዋርያትን ታገለግል ስለነበር ቤቷንም ለጸሎት እንዲሆን አደረገች፡፡
❖ ቅዱስ ማርቆስ በትውልዱ ዕብራዊ ሲሆን ቤተሰቦቹ ግን ይኖሩ የነበሩት በሰሜን አፍሪካ ቀሬና በተባለችውና በዛሬዋ ምዕራባዊ ሊቢያ ጠረፍ አካባቢ ነበር፤ ነገር ግን የሰሜን አፍሪካ ዘላን ጎሳዎች የሆኑት በርበሮች በየጊዜው ከተማቸውን እየዘረፉና ጥቃት እየሰነዘሩ ሲያስቸግሯቸው እናቱ ማርያምና አባቱ አርስጦቡሎስ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ኢየሩሳሌም በመመለስ በዚያው መኖር ጀመሩ፡፡
❖ ቅዱስ ማርቆስም በዚያው ስላደገ በዘመኑ ይሰጥ የነበረውን ትምህርት ተምሯል፤ የላቲን፣ የግሪክና የዕብራይጥ ቋንቋዎችን በደንብ ያውቅ ነበር፡፡
❖ ወንጌልን መጀመሪያ ከጌታችን በኋላም ከቅዱሳን ሐዋርያት እየዞረ ስለተማረ ንብ ተብሏል፣ አንበሳ የተባለበትም ምክንያት አንበሳ ላምን እንደሚሰብር ማርቆስም እንዲሁ በላም አምሳል ተሠርተው ሲመለኩ የነበሩ የግብፅ ጣዖታትን ሰባብሮ አጥፍቷልንና ነው፡፡
❖ ጌታችን በይሁዳ አውራጃዎች እየተዘዋወረ ሲያስተምር ቅዱስ ማርቆስ ያንጊዜ ገና ሕፃን ነበር፤ ለዚህም ነው ጌታችን መከራ መስቀሉን እየተቀበለ ወደ ቀራንዮ ሲሄድ ማርቆስ ዕርቃኑን በነጠላው ሸፍኖ ሲከተለው አይሁድ ሊይዙት ባሰቡ ጊዜ ጨርቁን ጥሎ ራቁቱን የሸሸው፡፡
❖ ሐዋርያት ዓለምን ዕጣ በዕጣ ተከፋፍለው ሲወጡ ቅዱስ ማርቆስ በበርናባስ አቅራቢነት ከቅዱስ ጳውሎስ ጋር በመጀመሪያ ጉዞው በ46 ዓ.ም ለስብከተ ወንጌል ወጥቶ ነበር፤ ነገር ግን ጵንፍልያ በምትባል ከተማ ላይ ‹‹እናቴ ናፈቀችኝ›› ስላለ በርናባስ ይዞት ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሷል፤ ነገር ግን ሐዋርያት ከሄዱበት ተመልሰው ስላደረጓቸው ተአምራት ሲናገሩ ሲሰማ ተጸጸተ፤ ድጋሚም ከበርናባስ ጋር ሄደ፤ በርናባስም ካረፈ በኋለ ወደ ሮሜ ሄዶ ቅዱስ ጴጥሮስን ተቀላቅሎ ደቀ መዝሙሩ ሆነ፡፡
❖ በዚያም ቅዱስ ጴጥሮስ የተረጎመለትን ወንጌል ጻፈ፤ በሮሜ ሀገርም አስተማረበት፤ ከዚህም በኋላ በጌታችንም ትእዛዝ በ60 ዓ.ም ወደ ሰሜን አፍሪካ መጥቶ እስክንድርያ ደረሰ በሀገሪቱም አምልኮተ ጣኦት በስፋት ተንሰራፍቶ ስለነበር ወንጌልን እንዴት አድርጎ መስበክ እንዳለበት እያሰበ በከተማ ሲዘዋወር የእግሩ የጠፈር ጫማው ተበጠሰና ለአንድ ሰፊ ሰጠው፡፡
❖ ጫማ ሰፊውም ሲሰፋ እጁን ስለወጋው ‹‹ኤስታኦስ›› ብሎ በዮናናውያን ቋንቋ ጮኸ፤ ትርጉሙም አንድ አምላክ ማለት ነው፤ ያን ጊዜም ቅዱስ ማርቆስ ጫማ ሰፊውን ‹‹ለመሆኑ አሁን የጠራሃውን አምላክ ታውቀዋለህን›› ብሎ ጠየቀው፡፡
❖ ጫማ ሰፊውም ‹‹ሲሉ እሰማለሁ እንጂ አላውቀውም›› አለው፤ ቅዱስ ማርቆስም የቆሰለች እጁን በተአምራት ፈወሰውና ወንጌልን ሰበከለት፤ እርሱም ወደ ቤቱ ወሰደውና ለቤተሰቡም ጭምር ወንጌልን ይሰብክ ዘንድ ጋበዘው፡፡
❖ ቅዱስ ማርቆስም ወደ ጫማ ሰፊው (ስሙ አንያኖስ ይባላል) ሄዶ ወንጌልን ሰበከ፤ በግብፅም የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በአንያኖስ ቤት ተመሠረተች፡፡
❖ ቅዱስ ማርቆስም በእስክንድርያ ወንጌልን ሰብኮ አገልጋዮችን ሾሞ ወደ ሰሜን አፍሪካና ሌሎች አምስት ሀገሮች ሄዶ ወንጌልን ሰበከ፤ ወደ ትውልድ ሀገሩ ቀሬናም ሄዶ ሰብኳል፤ ከ2 ዓመትም በኋላ ወደ እስክንድርያ ቢመለስ ክርስቲያኖችን ጸንተው ቤተ ክርስቲያን ሠርተው አገኛቸው፡፡
❖ ከሀዲዎችም ሊገድሉት ሲሞክሩ እየተሰወረባቸው እየወጣ ወደ አምስቱ ሀገራት እየደረሰ ይመለስ ነበር፤ ነገር ግን የትንሳኤን በዓል ለማክበር ወደ እስክንድርያ መጥቶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብቶ እየቀደሰ እያለ ጣዖት አምላኪዎች ሰብረው ገብተው ይዘውት አንገቱን አሥረው ቀኑን ሙሉ ከተማውን እየጎተቱት ሲያዞሩት ዋሉ፡፡
❖ በቀጣዩም ቀን እንዲሁ አስረው መሬት ለመሬት ሲጎትቱት ስለዋሉ በዚያው ዐረፈ፤ እሳት አንድደው ሥጋውን ሊያቃጥሉት ሲሉ ኃይለኛ ዶፍ ዝናብ ስለወረደ ጨረቃና ፀሐይም ስለጨለሙ አረማውያኑ ፈርተው ሸሹ፤ ቅዱስ ማርቆስ ሰማዕትነቱን የፈጸመው በ68 ዓ.ም ሚያዝያ 30 ቀን ነው፡፡
የቅዱስ ማርቆስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፤ በጸሎቱ ይማረን
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
መጥምቁ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❖ የመጥምቁ ዮሐንስ አንገት ከተቆረጠች በኋላ 15 ዓመት በአየር እየበረረች ስታስምር እንደኖረች፤ የመጥምቁ ዮሐንስ ቅድስት ነፍሱ ከተቆረጠች ራሱ ጋራ በአየር ውስጥ እየበረረች 15 ዓመት ስታስተምር ከኖረች በኋላ ጥቅምት 30 ቀን በዐረቢያ ምድር በግልጽ ታይታለች፡፡
❖ ይኸውም የሆነው እንዲህ ነው፤ ሄሮድያዳ ልጅ ርጉም የሆነ ንጉሥ ሄሮድስን በዘፈኗ በጣም አድርጋ ስላስደሰተችው እርሱም በተራው ሊያስደስታት ፈለገና እስከ መንግሥቱ እኩሌታ ድረስም ቢሆን የለመነችውን ይሰጣት ዘንድ በሕዝቦቹና በመኳንንቱ ሁሉ ፊት እንዳይከዳት በፅኑ ቃልኪዳን ማለላት፡፡
❖ እርሱም አስቀድሞ ‹‹የፈለግሽውን ጠይቂኝ፣ የመንግሥቴንም እኩሌታ ቢሆን እሰጥሻለሁ ምን ላድርግልሽ›› እያለ በመሐላ ባላት ጊዜ በእናቷ ምክር የዮሐንስን አንገት ቆርጦ ይሰጣት ዘንድ ለመነችው፤ እርሱም ስለማሐላው የዮሐንስን አንገት እንድትቆረጥ አደረገ፡፡
❖ በመጀመሪያም የሄሮድስ ወታደሮች ሠይፍ ይዘው የዮሐንስን አንገት ይቆርጡ ዘንድ ወደ መኅኒ ቤት ሲሄዱ ቅዱስ ዮሐንስም የሄሮድስ ጭፍሮች ሊገድሉት እንደመጡ በመንፈስ ቅዱስ ፀጋ ስላወቀ ከጨለማው ቤት ውስጥ አንገቱን በመስኮት አውጥቶ እንደሚመቻቸው አድርጎ ጠበቃቸው፡፡
❖ የንጉሡም ጭፍሮች የመጥምቁን ራስ በወጪት አድርገው ለንጉሣቸው ሄሮድስ ሰጡት፤ ሄሮድስም ለሄሮድያዳ ልጅ ሰጣት፤ የመጥምቁ ዮሐንስ ግን በወጪት ላይ ሆና ሕዝቦቹና የመንግሥቱ ታላላቅ ሰዎች እየሰሟት በየመኳንንቱ ፊት ንጉሥ ሄሮድስን ‹‹የወንድምህን የፊሊጶስን ሚስት ማግባት አይገባህም›› እያለች መጀመሪያ ትዘልፈው እንደነበረው ሁሉ አሁንም ዘለፈችው፥ መዓዛዋም እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነበር፣ ዐይኖቹም እንደፀሐይ ያበሩ ነበር፡፡
❖ የሄሮድያዳም ልጅ የመጥምቁን ራስ ወስዳ ለእናቷ ልትሰጣት ስትል ዐይኖቹ እንደፀሐይ ሲያበሩ ብታየው ‹‹ንጉሡን አትፈራውምን›› በማለት ተቆጣች፡፡
❖ በመቀጠልም ‹‹እነዚህን ዐይኖቹን በወስፌ እያወጣሁ እጥላቸዋለሁ፣ ምላሱንም ደግመኛ እንዳይገሥጽ ቆርጨ እጥላቸዋለሁ›› በማለት ፊቱን በጥፊ ለመምታት እጇን ስታነሣ ያንጊዜ የዮሐንስ ራስ ክንፍ አውጥታ በረረች፡፡
❖ በአየር ላይ ሳለችም ዳግመኛ ‹‹የተረገምሽ ሄሮድያዳ የባልሽን ወንድም ሄሮድስን ማግባት አይገባሽም፣ ቀድሞ የምዘልፍሽ አሁንም የምዘልፍሽ እኔ ነኝ›› እያለች የዮሐንስ ራስ የቤቱን ጣሪያ ሰንጥቃ እንደንሥር በአየር በራ ሄደች፡፡
❖ ከዚህም በኋላ ለጥፊ የዘረጋቻቸው የሄሮድያዳ እጆቿ ከትከሻዋ እየተቆረጡ መሬት ላይ ወደቁ፤ እውነቷንም መሬት አፏን ከፍታ ዋጠቻት፤ ዘፋኟ ልጇም አብዳ የቤተ መንግሥቱን ዕቃ ሁሉ መሰባበር ጀመረች፡፡
❖ የንጉሡ አንዱ ጭፍራም የሄሮድያዳን በእሳት እንደተለበለበ የግንድ እሳት የመሰለና የተቆረጠ እጇን አምጥቶ ለሄድሮስ ሰጠውና የሆነውን ነገረው፤ ንጉሡም ነገሩ እውነት መሆኑን ሄዶ ባየ ጊዜ በሀፍረት እጅግ ተሸማቀቀ፤ ዘፍና በማስደሰት የዮሐንስን ራስ እንዲያስቆርጠው ያደረገችው የሄሮድያዳ ሴት ልጅም አብዳ በቤተ መንግሥቱ ስትለፈልፍ አገኛት፡፡
❖ ሄሮድስም መኳንንቶቹን ‹‹በቤተ መንግሥቴ የተደረገውን ይህን ነገር ለማንም አትንገሩ›› ብሎ አማላቸው ነገር ግን ያበደችው የሄሮድያዳ ሴት ልጅ ራሷ ሄዳ ሄሮድስን ‹‹የወንድምህን የፊሊጶስን ሚስት ማግባት ፈጽሞ አይገባህም›› እያለች በመኳንንቶቹ ፊት ገሠጸችው፡፡
❖ ንጉሥ ሄሮድስም ይህን ቃል ከእርሷ በሰማ ጊዜ እጅግ ተናደደና ‹‹ቀደሞ ያልሆነ ሥራ ታሠራ በኋላ ደግሞ ምሥጢር ታወጣ ንሣ በሰይፍ ቁረጣት›› ብሎ አንገቷን በሰይፍ አስቆረጣት፡!፤ ሥጋዋንም ዓሣ አንበሪ ተቀብሎ ዋጣት፡፡
❖ ሄሮድም የወንደሙን ሚስት ሲያገባ አስቀድሞ አግብቷት የነበረችውን ሚስቱን በግፍ አባሯት ነበር፤ እርሷም ይህንን ሄሮድስ ያደረሰባትን ግፍ ለአባቷ አርጣ ብትነግረው አባቷ ብዙ ጦር ሰብስቦ መጥቶ ምድረ ገሊላን በኃይል አፈራረሳት፤ የበላዩ ንጉሥ ቄሳርም የገሊላን መፍረስና መውድም ሲሰማ ምክንያቱን ቢጠይቅ ሄሮደስ ባደረገው ግፍ ምክንያት መሆኑን ነገሩት፤ ቄሳርም ሄሮድስን ከሥልጣኑ ሽሮ አጋዘውና በወህኒ ጣለው፡፡
❖ ሄሮድስም በወህኒ ቤት ሳለ አብዶ ራሱን ስቶ የገዛ አካሉን እየነጨ እየበላ ቷ ብሎ ፈንድቶ ተልቶ ሸቶ እጅግ ክፉ አሟሟት ሞተ፡፡
❖ ከዚህም በኋላ ጌታችን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ራስ መለስ ብሎ እንዲህ በማለት ሥልጣን ሰጣት ‹‹እነሆ መንፈስሽን በራስሽ ውስጥ አድርጌልሻለሁ በሰማይም የምትበሪበት እንደ ንሥር ክንፍ ሰጥቼሻለሁና እንደንስር በሰማይ እየበረርሽ በዓለም ሁሉ እየዞርሽ የሄሮድስንና የሄሮድያዳን ኃጢአት ግለጭባቸው፤ እስከ 15 ዓመት ድረስ ገቢረ ተአምራት የምታደርጊበት ኃይሌን መንፈሴን በእራስሽ ውስጥ አድርጌልሻለሁ›› አላት፡፡
❖ ዳግመኛም ጌታችን ዮሐንስን ‹‹እኔም ከ3 ዓመት በኋላ ለአዳም የሰጠሁትን ተስፋ ፈጽሜ በሞቴ ወደ ሲኦል ወርጄ ነፍሳትን ከዲያብሎስ እጅ ማርኬ በ3ኛው ቀን ከሙታን ተለይቼ ተነሥቼ ወደ ባሕርይ ክብሬ ተመልሼ ወደ ሰማይ አርጌ ባባቴ ቀኝ በተቀመጥኩኝ ጊዜ ከ15 ዓመት በኋላ ርጉም ሄሮድስ ካስፈጃቸው ከትንንሾቹ ሕፃናት ጋራ ትሆን ዘንድ በአባቴ ፈቃድ እራስህን ተሸክመው ወደ አባትህ ወደ ዘካርያስ ያመጧት ዘንድ እኔ መላእክትን አዛቸዋለሁ፡፡
❖ ዛሬ ግን ነፍስህን በእኔ ቀኝ ባባትህ በዘካርያስ አጠገብ አኑሬያታለሁ መንፈስህንም እስከ 15 ዓመት በእራስህ ውስጥ እንድትኖር አዝዣታለሁ፣ ሥጋህም ከነቢዩ ከኤልሳዕ ጋር እንዲቀመጥ አድርጌያለሁ›› አለው፡፡
❖ ከዚህም በኋላ ጌታችን እንዳዘዛት የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ እራስ እንደንስር በአየር ላይ እየበረረች የምታስተምር ሆነች፤ በምሥራቅ በኩል ሄዳ በዐረብ አገር ውስጥ በሰማይ ላይ ስታስተምር በዚህች ዕለት ጥቅምት 30 ቀን በግልጽ ታየች፡፡
❖ ነጋዴዎች ድምጹዋን ሰምተውና አይተዋት እጅግ ተደስተው ገንዘባቸው ሁሉ ጥለው የቅዱስ ዮሐንስን እራስ ለመያዝ ሰውነታቸውን ብዙ አደከሙ፤ ነገር ግን ለመያዝ አልተቻላቸውም፡፡ ከዚህም በኋላ ከሰማይ ‹‹የምትያዝበት ጊዜ ስላልደረሰ ሰውነታችሁን አታድክሙ›› የሚል ድምጽ ከሰማይ መጣላቸው፤ መፈለጋቸውንም ተው፡፡
❖ የቅዱስ ዮሐንስም እራስ 15 ዓመት ስታስተምር ኖራ ሚያዝያ 15 ቀን በዐረብ ሀገር ዐረፈች፤ የታዘዙ ቅዱሳን መላእክትም መጥተው ከቅዱስ ዮሐንስ እራስ ከተባረኩ በኋላ በታላቅ ዝማሬ እያመሰገኑ የቅዱስ ዮሐንስን አንገት ወስደው በነቢዩ ኤልሳዕ መቃብር ውስጥ አብረው ቀበሯት፤ ቅድስትን ነፍሱንም እያመሰገኑ ወደ ሰማይ አሳረጓት፡፡
❖ በዚያም በሥሉስ ቅዱስ ዙፋን ፊት ወድቃ ከሰገደች በኋላ አባቷ ዘካርያስንና እናቷ ኤልሳቤጥን እጅ ነሳቻቸው፤ ከዚህም በኋላ በ3ኛው ሰማይ ውስጥ ተቀመጠች፤ ጌታችን ሦስቱን ሰማየ ሰማያት ርስት ጉልት አድርጎ ሰጥቶታልና፡፡
የመጥምቀ መለኮት የቅዱስ ዮሐንስ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፤ በጸሎቱ ይማረን
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
ባሕታዊ አብርሃም
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❖ የዚህም ቅዱስ ወላጆቹ እግዚአብሔርን የሚፈሩና የሚያመልኩ ናቸው በዚህም ዓለም ገንዘብ እጅግ ባለጸጎች ነበሩ፤ ይህም ቅዱስ በአደገ ጊዜ የምንኵስናን ልብስ ሊለብስ ሽቶ በላዕላይ ግብጽ ወደሚገኝ ወደ ሀገረ አክሚም በመርከብ ተጭኖ ሔደ ወደ አባ ጳኵሚስም ደረሰ እርሱም የምንኲስና ልብስን አለበሰው በገድልም በመጸመድ ሥጋውን አደከመ በአባ ጳኵሚስም ማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ሃያ ሦስት ዓመት ያህል በማገልገል ኖረ።
❖ ከዚህም በኋላ በዋሻ ውስጥ ብቻውን ይኖር ዘንድ እንዲአሰናብተው አባ ጳኵሚስን ለመነው እርሱም ፈቀደለት ዓሣ የሚያሠግሩበትን መረብ የሚሠራ ሆነ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አንድ ሰውን አመጣለት ያም ሰው መረቡን ሽጦ ምግቡን አተር ይገዛለታል የተረፈውንም ለድኆች ይሰጣል የምግቡም መጠን ሁልጊዜ ማታ ማታ አንዲት እፍኝ ከጨው ጋር በውኃ የራሰ አተር ነው።
❖ እንዲህም እየተጋደለ በዚያች ዋሻ ዐሥራ ሰባት ዓመት ኖረ ልብሱም ከገዳም ሲወጣ የለበሰው ከዘመን ርዝመት የተነሣ አርጅቶ ተበጣጠሰ ሥጋውንም በጨርቅ የሚሸፍን ሆነ፤ በየሁለት ዓመትም ወደ መነኰሳቱ ገዳም በመውጣት ሥጋውንና ደሙን ተቀብሎ ወደ በዓቱ ይመለስ ነበር።
❖ በዚያችም ዋሻ መኖር በጀመረባት ዓመት ሰይጣናት ወደ ርሱ በመምጣት ምትሐት እየሠሩ ተፈታተኑት እርሱ ግን ውሻን እንደሚአበር ሰው አበረራቸው፤ ዕረፍቱም በቀረበ ጊዜ ያን ሕዝባዊ ሰው ልኮ የአባ ጳኵሚስን ረድእ አባ ቴዎድሮስን አስጠራው በመጣም ጊዜ ሰግዶ ሰላምታ ሰጠው እንዲጸልይለትና በጸሎቱም እንዲአስበው ለመነው።
❖ ከዚህም በኋላ ሁለቱም በአንድነት ጸለዩ በዚያንም ጊዜ አባ አብርሃም በርከክ ብሎ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ ሰጠ አባ ቴዎድሮስም ወደ መነኰሳቱ ላከ እነርሱም መጥተው ከሥጋው በረከትን ተቀበሉ ሥጋውንም ወሰደው ከቅዱሳን ሥጋ ጋር በአንድነት አኖሩት።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ጻድቅ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
አርኬ
✍️ሰላም እብል ለአብርሃም ነዳይ። እምነ ጥሪት ማሳኒ ወእምኀላፊ ንዋይ። እንዘ ይሴፎ ረኪበ መንግሥተ ሰማይ። ይከድን ሥጋሁ በጸርቅ ብሉይ። ወሕፍነ አተር ይሴሰይ ዘርሑስ በማይ።
በዚችም ቀን የመጥምቁ ዮሐንስ ራስ የታየበት ነው ደግሞም የፋሲለደስ፣ የቢርወካይና የመርቲስ፣ የማርስ፣ የንጉሥ ይስሐቅ መታሰቢያቸው ነው በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
አርኬ
✍️ሰላም ለይስሐቅ እምእግዚአብሔር ዘተከድነ። አምሳለ ጽጌያት ስነ። በምድረ መንግሥቱ ረኪቦ እለ ተግኅሡ ጻድቃነ። ኀበ ይዘርዑ ገራውሀ ወኀበ ይተክሉ ወይነ። ለማኅደሮሙ ፈለጠ መካነ።
በጥቅምት ወር የሚነበብ ንባብ ደረሰ ተፈጸመ፤ ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን አሜን።
📌 ጥቅምት 30 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ማርቆስ ሐዋርያ
2.ቅዱስ አርስጥቦሎስ (አባቱ)
3.ቅድስት ማርያም (እናቱ)
4.ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት
5.አባ አብርሃም ገዳማዊ
6 ቅዱስ ይስሐቅ ንጉሥ
📌 ወርኀዊ በዓላት
1.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ነባቤ መለኮት
2.ቅድስት ሶፍያ ሰማዕት
3.አባ ሣሉሲ ክቡር ጻድቅ
✍️"ባስተዋለም ጊዜ እጅግ ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ ነበረው ማርቆስ ወደ ተባለው ወደ ዮሐንስ እናት ወደ ማርያም ቤት መጣ፤ ዼጥሮስም የደጁን መዝጊያ ባንኳኳ ጊዜ ሮዴ የሚሏት አንዲት አገልጋይ ትሰማ ዘንድ ቀረበች፤ የዼጥሮስ ድምጽ መሆኑንም ባወቀች ጊዜ ከደስታዋ የተነሣ ደጁን አልከፈተችም ነገር ግን ወደ ውስጥ ሮጣ ዼጥሮስ በደጅ ፊት ቆሞ እንዳለ አወራች"
📖ሐዋ 12፥12-15
ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ እምእለ ተፀመድኩ ዘልፈ ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውክፈ እምእለ አብዑ ብዑላን ዘተርፈ።
ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን ሰማዕታት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን ደናግል ዓዲ ወመነኮሳት ኄራን ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን እስከ አረጋዊ ልሂቅ እምንኡስ ሕፃን።
ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ ዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ ወለዘሰምዐ ቃሎ በእዝነ መንፈስ በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኲሉ እምባእስ ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ።
ጌታ ሆይ ከብልፅግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።
እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።
ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን።
✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝
✍"ልብህን በእርጋታ አኑረው፤ የሁሉም መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ለመሆን በጣም ትጋ ለከንቱ ንግግር ዘገምተኛና ሰነፍ ሁን፤ ነገር ግን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል በማወቅ በመስማት ድኅነትን የሚሰጡ ናቸውና ብልህ ሁን"
📚ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ይቆየን
───────────
Channel
🧲 https://telegram.me/Tewahedo12
FB Like Page (የፌስቡክ ፔጅ)
🧲 http://facebook.com/Tewahedo12
YouTube Subscribe (ሰብስክራይብ)
🧲 https://www.youtube.com/channel/UCvYxUdv1D-5juH_P6iE7XXw
───────────