ስንክሳር ዘወርኀ ኅዳር ፫

ስንክሳር ዘወርኀ ኅዳር ፫

@YeBiruk ዲያቆን ቡሩክ ይርጋ ዘውብ

✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

       አሜን


✍"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"      

📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ


     ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


ስንክሳር ዘወርኀ ኅዳር ፫


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ኅዳር ሦስት በዚች ቀን ከቆሮንቶስ አገር ቅዱስ አባት ኪርያቆስ አረፈ።


   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

     ቅዱስ አባት ኪርያቆስ

  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥


❖ የዚህም አባት ወላጆቹ ሃይማኖታቸው የቀና የከበሩ ናቸው የቤተክርስቲያንን ትምህርትና የቀናች ሃይማኖትን አስተማሩት ከዚህም በኋላ የቆሮንቶስ አገር ኤጲስቆጶስ ወደ ሆነ ወደ አባ ጴጥሮስ አቀረቡት እርሱም በላዩ ጸልዮ አናጒንስጢስነት ሾመው ለአባ ጴጥሮስም የወንድሙ ልጅ ነው።


❖ ከዚህም በኋላ ዘወትር መጻሕፍትን የሚያነብ የቃላቸውንም ትርጓሜ የሚመረምር የቤተ ክርስቲያንንም ሥርዓቷንና ሕጓን የሚያጸና ሆነ በትምህርቱና በእውቀቱም ከብዙዎች ከፍ ከፍ አለ ኤጲስቆጶሱም መጻሕፍት ማንበብን እንዳያቋርጥ ያዝዘው ነበር እርሱም ለሕዝቡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለኤጲስቆጶሱም በቤቱ ያነብለት ነበር፤ መጻሕፍትንም በሚያነብለት ጊዜ ኤጲስቆጶሱ በእርሱ ደስ ይለው ነበርና።


❖ ዕድሜውም ዐሥራ ስምንት ዓመት በሆነ ጊዜ ሚስትን ያጩለት ዘንድ ወላጆቹ ጠየቁት እርሱ ግን ይህን አልወደደም ግን ከገዳማት ወዳንዱ ይሔድ ዘንድ እንዲአሰናብቱት ወላጆቹን ለመናቸው ከዚያም በኋላ አዘውትሮ ወደ ገዳማት የሚሄድና ወደ ወላጆቹ የሚመለስ ሆነ፤ መመላለሱም ከበዛ ዘንድ የከበረች የምንኲስናን ልብስ ሊለብስ ወዶ ወደ ኢየሩሳሌም ሔደ ከኢየሩሳሌሙ ኤጲስቆጶስ ከአባ ቄርሎስ ጋር ተገናኝቶ ስለ ምንኲስና ኀሳቡን ሁሉ ነገረው፤ እርሱም በጎ ሥራን ወደሃል አለው ታላቅ አባትም እንደሚሆንና በእርሱም የብዙዎች ነፍሳት ብሩሃን እንደሚሆኑ ትንቢት ተናገረለት ።


❖ ከዚህም በኋላ የመነኰሳት አባት ወደ ሆነ በፍልስጥዔም ወደ ሚኖር ወደ ክቡር አባ ሮማኖስ ላከው እርሱም በደስታ ተቀብሎ የምንኵስናን ልብስ አለበሰው።


❖ የምንኵስናንም ሥርዓት ያስተምረው ዘንድ የሰይጣንንም ተንኮል ያስረዳው ዘንድ በዚያው ገዳም ለሚኖር አንድ አረጋዊ ሰጠው።


❖ ከዚህም በኋላ በጾም በጸሎት በስግደት በመትጋት በታላቅ ድካም በቀንና በሌሊት በገድል ተጸምዶ በትዕግሥት በትሕትና በቅንነት ኖረ።


❖ እግዚአብሔርም የመፈወስን ሀብት ሰጥቶት ወደርሱ የሚመጡትን በሽተኞች ሁሉ የሚፈውሳቸው ሆነ የትሩፋቱና የቅድስናውም ዜና በሁሉ ቦታ ተሰማ።


❖ የኢየሩሳሌሙ ኤጲስቆጶስ አባ ቄርሎስም የክብር ባለቤት የሆነ መንፈስ ቅዱስን ስለ አቃለለ መቅዶንዮስ መቶ ሃምሳው ኤጲስቆጶሳት አንድነት ወደሚሰበሰቡበት ወደ ቊስጥንጥንያ በሚሔድ ጊዜ ይህን አባት ኪርያቆስን አባ ቄርሎስ ከእርሱ ጋር ወሰደው በላያቸው በአደረ መንፈስ ቅዱስ ስም ተከራክረው ከሀዲ መቅዶንዮስን ረቱት ከምእመናንም ለይተው አሳደዱት።


❖ ከዚህም በኋላ በመልካም ሽምግልና እግዚአብሔርን አገልግሎ በሰላም አረፈ፤ ከዕረፍቱም በኋላ እግዚአብሔር ድንቆች የሆኑ ብዙ ተአምራትን ከሥጋው ገለጠ ከእርሳቸውም አንዱ ከኢየሩሳሌም ገዳማት በአንዱ ሥጋው ይኖራል።


❖ከአረፈበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ ሥጋው አልተለወጠም ወደ ኢየሩሳሌም የሚሔዱ ሁሉ ያዩታል እነርሱም በቅርብ ጊዜ እንዳረፈ ያስባሉ እርሱ ግን ያረፈው ለአኖሬዎስና ለአርቃዴዎስ አባታቸው በሆነ በታላቁ ንጉሥ ቴዎዶስዮስ ዘመን ነው።


ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ጻድቅ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


            አርኬ

✍️ሰላም ወአምኃ ለኪርያቆስ እፌኑ። ወተአምሪሁ እዜኑ። ለእለ ይመጽኡ ሕዝብ ያርአይዎ ውስተ መካኑ። ይትረከብ ከዊኖ ሐዲሰ በድኑ። እንዘ ሰዓ ሞቱ ርኁቅ ወጒንዱይ ዘመኑ።



✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

  አቡነ መድኃኒነ እግዚእ

 ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥


❖ በዚችም ቀን የመነኰስ መድኃኒነ እግዚእ መታሰቢያው ነው፤ ይኸውም ከደጋግ ክርስቲያኖች ከቀሲስ ሰንበት ተስፋነ እና ከኅሪተ ማርያም በ1180 ዓ.ም በሥዕለት የተወለዱት አቡነ መድኃኒነ እግዚእ እጅግ አስደናቂ ገድልና ትሩፋት ያላቸው ጻድቅ ቢሆኑም ብዙው ሕዝበ ክርስቲያን እንደሚገባቸው መጠን ያላወቃቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡


❖ መዘንጋታቸው እጅግ ከሚያስቆጩን አባቶች መካከል ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት የደብረ በንኮሉ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ናቸው፤ እስቲ ቀጥሎ ስማቸውን የጠቀስኳቸውን እነዚህን ቅዱሳን አባቶች ታሪካቸውንና የጽድቅ ሕይወታቸውን አስታውሱት፤ እነርሱም

➱አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባ፣

➱አቡነ ሳሙኤል ዘቆየፃ፣

➱አቡነ ታዴዎስ ዘባልታርዋ፣

➱አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ ዘጉጉቤ እና አቡነ ዮሐንስ ዘጉራንቄ እነዚህን የመላእክትን ሕይወት በምድር የኖሩ ታላላቅ የሀገራችንን ቅዱሳን አስተምረውና አመንኩሰው ለጽድቅ ያበቋቸው አባት አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ናቸው፡፡


❖ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ እነዚህን ሰባቱን ቅዱሳን በአንድ ጊዜ ሲያመነኩሷቸው በዚያው ቅጽበት መንፈስ ቅዱስ ወርዶ ገዳሙን ደብረ በንኮልን በብርሃን አጥለቅልቆት ታይቷል፤ከሰማይም የምስክርነት ድምፅ ተሰምቷል፡፡


❖ በዚህም ምክንያት አንድ ላይ የመነኮሱት እነዚህ ሰባቱ ቅዱሳን ‹‹ሰባቱ ከዋክብት›› እየተባሉ ይጠራሉ፤ እነዚህም ሰባቱ ከዋክብት የጣናን ባሕር በእግራቸው ጠቅጥቀው ተሻግረው ብዙዎቹን ደሴቱ ላይ ያሉ አስደናቂ የጣና ገዳማትን የመሠረቱት ናቸው፤ ከእነርሱም ውስጥ ትልቅ ጠፍጣፋ ድንጋይን እንደጀልባ ተጠቅመው በእርሱ ላይ ሆነው ወደ ደሴት የገቡ አሉ፤ በእግራቸውም እየረገጡ ባሕሩን የተሻገሩ አሉ፤ በሌላም ቦታ በየብስ የተሰማሩትም ቢሆኑ መጻሕፍቶቻቸውን በአንበሳ ጭነው የተጓዙ አሉ፡፡



❖ አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ለአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ‹‹ስፍር ቁጥር የሌላቸው ከዋክብት ቅዱሳንን›› በመንፈስ ቅዱስ እንደሚወልዱ ትንቢት ተናግረውላቸው ነበር፤ የተንቤኑን አቡነ ዐቢየ እግዚእን፣ የዞዝ አምባውን አቡነ አብሳዲን ጨምሮ አባታችን መድኃኒነ እግዚእ ብርሃን ሆነው በጣም ብዙ ቅዱሳንን የለኮሱ ታላቅ ጻድቅ ናቸው፤ በዚህም ምክንያት ‹‹ወላዴ አእላፍ ቅዱሳን›› ይባላሉ፡፡


❖ የአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ልጆች ዛሬ ግሸን ላይ በክብር ተቀምጦ ሀገራችንን ከመዓት እየጠበቀ ያለውን የጌታችንን ቅዱስ መስቀል ያመጡትም እነርሱ ናቸው፤ ዐፄ ዳዊት በዘመናቸው ረኃብ ስለነተሳ የደብረ ቢዘኑን አቡነ ፊሊጶስን ከገዳማቸው አስጠርተው ‹‹ምን ባደርግ ይሻለኛል›› ብለው አማከሯቸው።


❖ አቡነ ፊሊጶስም ‹‹የጌታችንን መስቀል ያስመጡ›› ብለው መከሯቸው፤ ንጉሡ ዐፄ ዳዊትም ከኢየሩሳሌም፣ ከቍስጥንጥንያና ከእስክንድርያ መንግሥታት ጋር ተጻጽፈው ዓሥሩን ታላላቅ ቅዱሳን መርጠው ይዘው ሄደው መስቀሉን መስከረም 10 ቀን አምጥተውታል፤ በጽድቅ ሥራቸውና ተአምራትን በማድረግ በወቅቱ ታዋቂ የነበሩትና ቅዱስ መስቀሉን ያመጡት ዐሥሩ ቅዱሳንም የደብረ ቢዘኑ አቡነ ፊሊጶስ፣ የጣና ደሴቱ አቡነ ኂሩተ አምላክ፣ የጣና ደሴቱ አቡነ እንድርያስ፣ አቡነ በትረ ማርያም፣ አቡነ ዮሐንስ፣ አቡነ ታዴዎስ፣ አቡነ ያፍቅረነ እግዚእ፣ አቡነ ዘካርያስ፣ አቡነ ያሳይና አቡነ ቶማስ ናቸው፡፡


❖ የአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ተአምራታቸው እጅግ ብዙ ነው፤ አራዊት ሁሉ እንደሰው ያገለግሏቸው የነበር፤ ውኃ የሚያመላልስላቸውንና የሚያገለግላቸውን አህያ አንበሳ ቢበላባቸው በአህያው ምትክ አንበሳውን ድፍን 7 ዓመት ለገዳማቸው ውኃ አስቀድተውታል፤ ነገሩ እንዲህ ነው፡- ለአባታችን ውኃ የሚያመላልስላቸውና የሚያገለግላቸው አንድ አህያ ነበራቸው፤ ውኃው የሚገኘው እርሳቸው ካሉበት በጣም እርቆ በእግር የ3 ሰዓት መንገድ ከተሄደ በኋላ ነው፤ ነገር ግን አህያቸው እንደ ሰው እየተላላካቸው ይቀዳላቸው ነበር፤ አንድ ግን ከመንገድ አንበሳ አግኝቶት ግማሽ አካሉን በልቶት ሄደ፡፡


❖ አባታችንም የአህያቸውን ተረፈ በድን አግኝተው በማዘን ‹‹ውኃ የሚያመላልስልኝ ረዳቴ ይህ አህያ ብቻ ነበር፣ አሁንም አህያዬን የበላህ አውሬ እንድታነጋግረኝ እፈልጋለሁ›› ቢሉ በአንበሳ ተበልቶ የሞተው የአህያው ግማሽ አካል አፍ አውጥቶ አንድ አንበሳ እንደበላው ነገራቸው፡፡ 

❖ አቡነ መድኃኒነ እግዚእም በዚህ እጅግ ደስ ተሰኝተው ፈጣሪያቸውን ካመሰገኑ በኋላ አህያቸውን የበላውን አንበሳ ከጫካው ውስጥ ጮኸው ጠሩት፤ አንበሳውም ከሌሎቹ አንበሳ ተለይቶ ወደ እርሳቸው በመምጣት እግራቸው ሥር ወድቆ ሰገደ፡፡


❖ አባታችንም ‹‹አህያዬን የበላኸው አንተ ነህን›› ብለው ሲጠይቁት አንበሳውም በሰው አንደበት ‹‹አዎ እኔ ነኝ›› አላቸው፤ እርሳቸውም ፈጣሪያቸውን በድጋሚ ካመሰገኑ በኋላ አንበሳውን ‹‹በል ና ተከተለኝ በአህያዬ ምትክ ታገለግለኛለህ›› አሉት፡፡


❖ አንበሳውም ተከትሏቸው ወደ በዓታቸው በመግባት ለ7 ዓመታት እንደ አህያቸው ውኃ እየቀዳ አገልግሏቸዋል፤ የአንበሳው ቆዳ ዛሬም በገዳማቸው ደብረ በንኮል በክብር ተቀምጠቷል፡፡


❖ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባንም አመንኩሰው መርቀው ሲሸኟቸው እንዲያገለግሏቸው አንበሶችን ከጫካ ጠርተው ያዘዙላቸው አባታቸው አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ናቸው፤ የዋልድባው አቡነ ሳሙኤል አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ከመነኮሱ በኋላ በደብረ በንኮል 12 ዓመት አባታችንን ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ እሳት እስከማያቃጥላቸው ድረስ ከብቃት ደረጃ ላይ ሲደርሱ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ መርቀው በማሰናበት በዓት እንዲያጸኑ ሲያደርጓቸው አቡነ ሳሙኤል በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ጣና ደሴት ገብተው ሱባኤ ያዙ፡፡


❖ በዚያም ሳሉ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ማረፋቸውን በመንፈስ ዐውቀው ሲያለቅሱ ጌታችን የአቡነ መድኃኒነ እግዚእን ነፍስ በእቅፉ አድርጎ ወደ ገነት ሲያሳርጋት አሳያቸው፤ ወዲያውም ጌታችን በብርሃን ሰረገላ አድርጎ አቡነ ሳሙኤል ዘዋልድባን ደብረ በንኮል አድርሷቸዋል፡፡ 



❖ የጻዲቁ የአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ዕረፍታቸው ኅዳር 3 ቀን 1360 ዓ.ም ሲሆን ጠቅላላ ዕድሙያቸውም 180 ዓመት ነው፡፡


❖ ዐፄ ፋሲል ጻድቁ የተከሏቸውን የጥድ ዛፎች በሙሉ ተቆርጠው የአክሱም ቤተክርስቲያን እንዲሠራበት አዋጅ አወጁና መልእክተኞች መጥተው ዛፎቹን ሲቆርጡ መነኮሳቱ ግን ‹‹ጻድቁ አባታችን የተከሏቸው የጥድ ዛፎች መቆረጥ የለባቸውም›› ብለው ቢከራከሩም ሰሚ አላገኙም፡፡


❖ መነኮሳቱም ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክቱ ጩኸታቸው ተሰምቶላቸው ወዲያው እየተቆረጡ ያሉት የጥድ ዛፎች በሙሉ በተአምራት ወደ ወይራ ዛፍነት ተለወጡ፤ የወይራ ዛፎቹም ለዐፀድ እንጂ ለሕንፃ የማይመቹ ጎባጣ ሆኑ፡፡


❖ የዚህም ምልክቱ ዛሬም ድረስ አለ፤ ግንዱ ጥድ ዛፉ ግን ወይራ የሆነ ትልቅ ዛፍ ‹‹ወይራ ዘገብረ ተአምር›› በሚባል ቦታ አሁንም ድረስ ቆሞ ይታያል፡፡


❖ ጻድቁ አቡነ መድኃኒነ እግዚእ በ1312 ዓ.ም የመሠረቱት ገዳማቸው ደብረ በንኮል ከአክሱም በእግር ሦስት ሰዓት ያስኬዳል፤ ይኸውም በንግሥተ ሳባ ቤተ መንግሥት አድርጎ የቀዳማዊ ሚኒሊክን መቃነ መቃብር አልፎ በመሄድ ነው ወይም በመኪና ለመጓዝ አክሱም ጉበዱራን አቋርጦ ውቅሮ ማራይ ከተማን አልፎ በስተ ሰሜን አቅጣጫ 10 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ይገኛል፤ በስተ ምዕራብ የአቡነ አላኒቆስ ዘማይበራዝዮን ገዳም፣ በስተ ምሥራቅ የአቡነ ሰላማን ገዳም እየተለመከቱ እንደተጓዙ ጥቅጥቅ ባለ ደን የተሸፈነውን ደብረ በንኮልን ያገኙታል፡፡


❖ ኅዳር 20 ጻድቁ ስለሚነግሱ ገዳሙም ለአክሱም ቅርብ ስለሆነ ይህ ለአክሱም ጽዮን ተጓዦች ተጨማሪ ትልቅ በረከት ነው፤ ደብረ በንኮል ማለት ‹‹ሙራደ ቃል›› ማለት ነው፤ ትርጉሙም የምሥጢር መውረጃ ማለት ነው፤ በቦታው ላይ ሱባኤ ለያዘ ሰው እንደ ቅዱስ ያሬድና እንደ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ምሥጢር እንደሚገለጥለት የሚጠቁም ነው።


❖ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩት ደጋግ መነኮሳት ሕይወታቸውን በሙሉ በምንኩስና፣ በጸሎትና በታላቅ ተጋድሎ መኖር ሲፈልጉ ከደብረ ዳሞ፣ ከሐይቅ እስጢፋኖስ፣ ከደብረ ሊባኖስና ከሌሎቹም የሀገራችን ክፍሎች እየተነሡ ወደ ደብረ በንኮል አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ገዳም ነበር የሚሄዱት፡፡


📌 የአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ቃልኪዳን

❖ ጻድቁ ባርከው ያፈለቁት ጸበላቸው ላበደ ሰው መድኃኒት ነው፤ ከመቃብራቸው ላይ የሚነሣውን አፈር ጻድቁ ባርከው ባፈለቁት ጸበላቸው ታሽቶ በእጃቸው መስቀል ተባርኮና ታሽቶ የሚዘጋቸውን የአቡነ መድኃኒነ እግዚእን እምነታቸውን በእምነት ሆኖ የያዘን ሰው ንብረቱን ሌባ ቀማኛ ዘራፊ አይሰርቀውም፤ የመኪና አደጋ አይደርስበትም፤ ጥይት አይመታውም ‹‹በእምነት ሆኖ የያዘን ሰው›› መባሉን ልብ ይሏል፤ ይኸውም ለጻድቁ የተሰጣቸው ታላቅ ቃልኪዳን ነው፡፡


የአቡነ መድኃኒነ እግዚእ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፤ በጸሎታቸው ይማረን


               አርኬ

✍️ሰላም ለርእስከ ዘተከለለ ቆብዐ። አርአያ አክሊሉ ለክርስቶስ በዲበ መስቀል ሶበ ተመርዐ። መድኃኒነ እግዚእ አፉየ አመ ስመከ ጸውዐ። ነዓ ነዓ ምስለ ሳሙኤል ነዓ። ምስሌየ ትግበር ሰላመ ወስንዓ።


   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

 ጻድቁ ንጉሥ ቅዱስ ነዓኵቶ ለአብ

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥


❖ ከላስታ (ከዛጉዌ) ነገሥታት መካከል ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ፣ ቅዱስ ገብረ ማርያም፣ ቅዱስ ላሊበላና ቅዱስ ነአኵቶለአብ እነዚህ አራቱ ነገሥታት እንደ መልከጼዴቅ ክህነትን ከንግሥና፣ ቅድስናን ከንጽሕና ጋር አንድ አድርገው በመያዝ እግዚአብሔርንም ሰውንም በቅድስና አገልግለው አልፈዋል፡፡

📖ዘፍ 14፥18


❖ በንግሥናቸው አገርን በመልካም ሥራና በቅድስና ከማስተዳደራቸው በተጨማሪ ቅዱሳን ጻድቃን ሆነው እግዚአብሔርን በብዙ ድካም በመልካም ተጋድሎአቸው ያገለገሉና አገልግሎታቸውም ሆነ ቅድስናቸው በእግዚአብሔር ዘንድ የተመሰከረላቸው ቅዱሳን ናቸው፡፡


❖ ከእነርሱም ውስጥ ሞትን ሳያይ እንደነ ሄኖክና ኤልያስ የተሰወረ አለ፤ ከእነርሱም ውስጥ በባሕር ላይ ቤተ መቅደሱን ያነጸ አለ፤ ከእነርሱም ውስጥ የታዘዘ መልአክ መጥቶ ወደ ሰማይ ነጥቆ ወስዶት የቤተ መቅደሶቹን አሠራር ራሱ ጌታችን በቃሉ ያስረዳው አለ፡፡


❖ ከእነርሱም ውስጥ በክህነቱ ሲቀድስ 40 ዓመት ሙሉ ቅዱስ ቁርባኑን መላእክት ከሰማይ እያመጡለት የነበረ አለ፤ እነዚህ ቅዱሳን ነገሥታት ገድላቸውና ትሩፋታቸው፣ ምግባር ሃይማኖታቸው እጅግ ድንቅ ነው፡፡


❖ የእነዚህ ቅዱሳን ነገሥታቱን የዘር ሐረጋቸው ከሰሎሞን ዘር ሲያያዝ የመጣ ነው፤ ከ10ኛው እስከ 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (920-1253 ዓ.ም ገደማ) በላስታ ቡግና ምድር የነገሡ የላስታ ቡግና ተወላጅ የሆኑ የኢትዮጵያ ቅዱሳን ነገሥታት የንግሥናቸው መጠሪያ ‹‹የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት›› ወይም ‹‹የላስታ መንግሥት›› በመባል ይታወቃል፡፡


❖ ከዛጉዌ ነገሥታት ውስጥ የመጀመሪያው ንጉሥ መራ ተክለሃይማኖት የዐፄ ድልነአድን ልጅ መሶበወርቅን አግብቶ አራት ልጆችን ወልዷል፤ ሦስቱ ወንዶች ጠንጠውድም፣ ግርማ ስዩምና ዣን ስዩም ይባላሉ፤ ጠንጠውድም ገብረ መስቀልን ወለደ፣ ግርማ ስዩም ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ወለደ፣ ዣን ስዩም ደግሞ ቅዱስ ገብረማርያምንና ቅዱስ ላሊበላን ወለደ፡፡


❖ ገብረ መስቀልም ጣራው ክፍት ሆኖ ዝናብ የማያስገባውን ገዳም መሠረቱትን የዘመቄቱን ታላቁን አባት አቡነ አሮንን ወለደ፡፡

❖ ቅዱስ ገብረማርያም ደግሞ ቅዱስ ነዓኵለአብን ወለደ፤ ይኸውም ቅዱስ ነዓኵ ለአብ በዛሬዋ ዕለት ሞትን ሳያይ እንደነ ሄኖክና ኤልያስ የተሰወረ ነው፡፡


❖ ‹‹ነዓኵቶ ለአብ›› ማለት የስሙ ትርጓሜ ‹‹እግዚብሔር አብን እናመስግነው›› ማለት ነው፤ የቅዱስ ላሊበላ የወንድም ልጅ ሲሆን ከ11ዱ የዛጉዌ ነገሥታት ውስጥ 10ኛው ነው፤ አባቱ ቅዱስ ገብረ ማርያም ሥልጣኑን ለወንድሙ ለቅዱስ ላሊበላ ትቶ በመመንኮስ በበዓት ተወስኖ በጾም በጸሎት ሲጋደል ጌታ ተገልጾለት ‹‹ክብሩ እንደ መላእክት የሆነ ልጅ ትወልዳለህና ወደቤትህ ተመለስ›› ብሎ አዘዘው፡፡


❖ ንጉሡ ገብረማርያምም ‹‹40 ዓመት ስነግሥ ያልወለድኩትን አሁን ዓለም በቃኝ ስል ትወልዳለህ የተባልኩት ልጅ ምን ዓይነት ልጅ ይሆን!›› እያለ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ሚስቱን መርኬዛንም መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ካበሰራት በኋላ ነአኵቶለአብ ጌታ በተወለደበት ዕለት ታኅሳስ 29 ቀን ተወለደ፡፡


❖ ቅዱስ ላሊበላም ቀደም ብሎ የተወለደው እንዲሁ በጌታ የልደት ቀን ታኅሳስ 29 ቀን 1101 ዓ.ም ነው፤ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ነአኵቶ ለአብ እንደሚወለድ ቀድሞ ለንጉሥ ላሊበላ ነግሮት ነበርና እንደነገረውም እርሱ ሲወለድ ‹‹ያ የነገርኩህ ሕፃን ተወልዷልና ወስደህ በሃይማኖት አንጸህ አሳድገው›› ብሎታል፡፡


❖ ቅዱስ ላሊበላም ሃይማኖቱን ጠንቅቆ እያስተማረ በእንክብካቤ አሳደገው፤ ግብፅ ሄዶ ከአቡነ ቄርሎስ ዲቁናን ተቀበለ፤ በኋላም ቅስናን ተቀበለ፡፡ ቅዱስ ላሊበላ ቤተ መቅደሶቹን ሠርቶ ከጨረሰ በኋላ በሕይወት ሳለ መንግሥቱን ስላወረሰው ከላሊበላ በኋላ ነግሦ ኢትዮጵያን ለ40 ዓመት (ከ1197 ዓ.ም-1237 ዓ.ም) ድረስ መርቷል፡፡


❖ ዕድሜው ሲደርስ መልአኩ ሚስት እንዲያጭለት ለቅዱስ ላሊበላ ነግሮት ሲያጭለት እግዚአብሔርን በድንግልና ማገልገል ይፈልግ ነበርና በዚህም እጅግ ሲያዝን እመቤታችን ተገልጻለት ጋብቻው ከእግዚአብሔር መሆኑን ነግራ አጽናንታዋለች፡፡


❖ ‹‹የጌታህ ፈቃድ ነውና አትዘን ይልቁንም አግባ፣ ክብርህም ከደናግላን አያንስም›› ብላ ስለነገረችው ሚስት ቢያገባም ልክ እንደ ቅዱስ ዲሜጥሮስና ልዕልተወይን ንጽሕናቸውንና ድንግልናቸውን ለመጠበቅ በመማከር በግብር ሳይተዋወቁ ለ25 ዓመታት በድንግልና ሆነው በትዳር ኖረዋል፡፡


❖ እህት ወንድሞች ሆይ እስቲ ልብ በሉ! በሕግ ካገባት ሚስቱ ጋር ለዚያውም በእመቤታችን ትእዛዝ አግብቶ ሳለ በግብር ሳያውቃት አብሮ ከድንግል ሴት ጋር በትዳር 25 ዓመት መኖር ይህ እንዴት ያለ ቅድስና ነው በእውነት።


❖ ከዚህ በኋላ መልአክ መጥቶ ‹‹በንጽሕና የተጋባችሁት ልትወልዱ ነው እንጂ ዝም ብላችሁ ልትኖሩ አይደለም›› ብሏቸው አንድ ቀን ብቻ በግብር ተዋወቁና እጅግ የሚያምርና የሚያሳሳ ልጅ ወለዱ፡፡


❖ ልጁም እጅግ የሚያምርና የሚያሳሳ ቢሆንም ንጉሡ ቅዱስ ነአኵቶለአብ ግን በእግዚአብሔር መንፈስ የወደፊቱን ያውቅ ነበርና ሱባኤ ገብቶ ‹‹በእኔ እግር ተተክቶ ሲነግሥ ፍርድ አጣሞ አንተንም ሰውንም ከሚበድል ይህን ልጄን ቅሰፍልኝና ሄሮድስ ካስፈጃቸው ሕፃናት ጋር ደምርልኝ›› በማለት ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ 


❖ እንደ ጸሎቱም ጌታችን የካቲት 16 ቀን ልጁን በሰላም አሳርፎለት ሄሮድስ ካስፈጃቸው ሕፃናት ጋር ደምሮለታል፤ በዚህም ጊዜ መኳንንቶቹ፣ መሳፍንቶቹና ሕዝቡ ሁሉ ለልቅሶ ቢመጡ እርሱ ግን በቤተ መንግስቱ በልቅሶ ፈንታ ታላቅ የደስታ ድግስ አድርጎ ስለጠበቃቸው ‹‹የንጉሡ ልጅ ሞተ የተባለው ውሸት ነው›› ብለዋል፡፡


❖ ቅዱስ ነአኵቶ ለአብ ክህነትን ከንግሥና ቅድስናን ከንጽሕና ጋር አስተባብረው ይዘው ኢትዮጵያን ከመሩ ከአራቱ የዛጉዌ ነገሥታት አንዱ ሲሆን በነገሠበት 40 ዓመት ሙሉ ዓርብ ዓርብ ቀን የክርስቶስን ሕማም እያሰበ በዕንቁና በወርቅ በተሽቆጠቆጠው ዘውዱ ፈንታ የእሾህ አክሊልን ደፍቶና በአምስቱ ቅንዋተ መስቀሎች ምሳሌ አምስት ጦር ዙሪያውን ተክሎ እያለቀሰ ይጸልይና ይሰግድ ነበር፡፡

❖ በዙፋኑም ላይ ለፍርድ በተቀመጠ ጊዜ ከንግሥና ልብሱ ውስጥ በስውር ማቅ ለብሶና ሰውነቱን በሰንሰለት አስሮ ከላይ ግን በክብር ልብሱ ተሸፍኖና በወርቅ ወንበር ተቀምጦ ይፈርድ ነበር፤ ፍርድ ሲሰጥም ሁሉንም ነገር በመንፈስ ቅዱስ እያውቅ ነበር፤ ምስክሮችን አይሻም ይልቁንም ሰዎቹ ገና ሳይመጡ ሌሊት በምን ወንጀል ተካሰው እንደሚመጡ በመንፈስ ይገለጽለት ነበር፤ ወደ እርሱም በመጡ ጊዜ እነርሱ ጉያቸውን ከመናገራቸው በፊት እርሱ አቀድሞ አስማምቶ በጽድቅ ፈርዶላቸው ወደየመጡበት ይመልሳቸዋል፡፡


❖ ሰዎቹም ‹‹…ይህስ በእውነት የመንፈስ ቅዱስ ፍርድ እንጂ የሰው ፍርድ አይደለም›› እያሉና እያደነቁ ይመለሳሉ፡፡


❖ ጻዲቁ ቅዱስ ነአኵቶ ለአብ በዘመኑ ግብፆች ‹‹ግብር አንሰጥም›› ብለው ስላመፁበት የዓባይን ወንዞች በጸሎቱ ወደ ሌላ ቦታ እንዲፈስ ስላደረገባቸው ግብፆች ከበፊቱ ጨምረው ግብራቸውን አምጥተው ሰጥተውት ግዝቱን አንስቶላቸዋል፡፡


❖ ቅዱስ ነአኵቶ ለአብ መላ ዘመኑን ሁሉ የክርስቶስን መከራ እያሰበ ያለቅስ ስለነበር የመድኃኔዓለምን መራራ ሐሞት መጠጣት እያሰበ ሁልጊዜ ዓርብ ዓርብም ኮሶ ይጠጣ ነበር፡፡ 


❖ በመጨረሻም ውለታን የማይረሳ አምላክ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ተገልጦለት እንዲህ አለው ‹‹ወዳጄ ነአኵቶ ለአብ ሆይ! እኔ ለዓለም ደሜን ያፈሰስኩት አንድ ቀን ነው፤ አንተ ግን 40 ዓመት ሙሉ ስለ እኔ ብለህ ደምህንንና እንባህን ስታፈስ ኖርክ፣ ይበቃሃል አሁን ወደ እኔ ልወስድህ ነው›› አለው፡፡


❖ ቅዱስ ነአኵቶ ለአብም ጌታችንን ‹‹ጌታዬ ሆይ! እዚህ ቦታ እኔን ብለው የሚመጡ ወገኖቼን ማርልኝ›› አለው፤ ጌታችንም ‹‹እውነት እልሃለው ከተፀነስክበት ቀን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ያለውን ገድልህን እያነበበ ዝክርህን የዘከረውን፣ በዓልህን ያከበረውን፣ ለቤተ ክርስቲያንህ መባ ያገባውን ሁሉ ኃጢአቱ ቢበዛም ‹ቅዱስ ነአኵቶ ለአብ አማልደኝ› ያለውን ኃጢያቱ ምን ቢበዛ እምርልሃለው፤ ዳግመኛም እልሃለው 40 ዓመት ሙሉ እንባህን ያፈሰስክባት ይህች ምድር እስከ ዕለተ ምጽአት እያነባች ትኖራለች፣ ይኸውም የእኔን መከራ እያሰብክ ከዐይንህ ዕንባ ሳይቋርጥ እንዳለቀስክልኝ ሁሉ ከቤተ መቅደስህ በእንባ መልክ የሚንጠባጠብ ጠበል ይፍለቅልህ፣ ይህም የዕንባህ ምሳሌ ነው፤ ከዚህ ለሚጠጡ ለሚጠመቁ ድኅነት ይሁናቸው›› የሚል የምሕረት ቃልኪዳን ሰጥቶታል፡፡

❖ ጌታችን ይህን አስገራሚ ቃልኪዳን ከሰጠው በኋላ ቅዱስ ነአኵቶ ለአብን በሞት ፈንታ እንደነ ሄኖክና ኤልያስ ኅዳር 3 ቀን ሰውሮታል፤ በቃልኪዳኑም መሠረት ብዙ ፈውስን የሚሰጠው ጠበሉ ዛሬም ድረስ ልክ እንደሰው ዕንባ ቤተ መቅደሱ ካለበት ዋሻ ላይ እየተንጠባጠበ ወደ ታች ይወርዳል፣ ምንም እንኳን ከዋሻው በላይ ያለው መሬት ሜዳ ቢሆንም ቃልኪዳኑ ነውና የጠበሉ መጠን ክረምት ከበጋ አይጨምርም አይቀንስም፤ ይልቁንም በሰው ዕንባ መጠን ጠብ ጠብ እያለ በመውረድ ከእርሱ ለሚጠመቁት ፈውስን እየሰጠ ይገኛል፡፡


የቅዱስ ነአኵቶ ለአብ ረድኤት በረከቱ ይደርብን፤ በጸሎቱ ይማረን


 ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

     አቡነ ፍሬ ካህን

 ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥


❖ ጻድቁን በመጀመሪያ ከጎጃም ተነሥተው በታዘዘ መልአክ መሪነት ትግራይ ደብረ በንኮል አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ገዳም ሄደው መንነው መነኮሱ፡፡


❖ ጻድቁ ስድስት ክንፍ የተሰጣቸው ሲሆኑ በታላቅ መንፈሳዊ ተጋድሎ ይታወቃሉ፤ አቡነ ፍሬ ካህን ወንጌልን ሲሰብኩ ሙታንን እያስነሡ በሲኦል ውስጥ ስላለው መከራና ሥቃይ እንዲመሰክሩ ያደርጓቸው ነበር፡፡


❖ ጻድቁ ሐይዳ ገዳም ታቦት ተቀርጾላቸው ገድል የተጻፈላቸው ቢሆንም ሙሉ ገድላቸው ታትሞ ለምእመኑ አልተዳረሰም፡፡

❖ አቡነ ቶማስ ካረፉ በኋላ አቡነ ፍሬ ካህን ገዳማቸውን ተረክበው በጽድቅ መንገድ መነኮሳቱን አስተዳድረዋል፡፡

❖ አቡነ ፍሬ ካህን አፈር ከኢየሩሳሌም አምጥተው ዋልድባ ሲደርሱ መነኮሳቱ ‹‹ገዳሙን በአህያ አታስረግጥ›› ቢሏቸው አህዮቹን ክንፍ አውጥተው እንዲበሩ አድርገዋቸዋል፤ አባታችን ሽሬ ደብረ ሐይዳ አቡነ ፍሬ ካህን የተባለ ትልቅ ገዳም አላቸው፡፡


❖ ገዳሙ ከአቡነ ቶማስ ዘሐይዳ ገዳም ጋር አንድ ነው፤ ወደዚህ ገዳም ውስጥ ሥጋና ቅቤ ተበልቶም ሆነ ተይዞ መውጣት ፈጽሞ አይቻልም፤ አልታየሁም ተብሎ በድብቅ ሥጋ ተይዞ ቢገባ ሥጋው ይተላል፤ ሥጋና ቅቤ የበላ ሰውም ዕለቱን በድፍረት ወደ ገዳሙ ቢገባ ሆዱ በኃይል ይነፋል በዚህም ይታወቅበታል፤ ከብቶችም ቢሆኑ ወደ ገዳሙ አይወጡም፣ ማንም ሳይመልሳቸው ራሳቸው ይመለሳሉ፤ የአቡነ ፍሬ ካህን ዕረፍታቸው ኅዳር 3 ነው፡፡


የአቡነ ፍሬ ካህን ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፤ በጸሎታቸው ይማረን

     

በዚችም ቀን አባ አትናቴዎስና እኅቱ ኢራኢ አረፉ። እሊህንም ቅዱሳን ከሀዲ ንጉሥ መክስምያኖስ ጽኑዕ የሆነ ሥቃይን አሠቃያቸው። በማሠቃየትም በደከመ ጊዜ ዕራቁታቸውን ከጉድጓድ ጨመራቸው በላያቸውም የጒድጓዱን አፍ ዘጋ በውስጧም ነፍሳቸውን አሳለፉ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


           አርኬ

✍️ሰላም ለአትናቴዎስ ወለኢራኢ ዘተአኃዉ። ለገቢረ ጽድቅ እንዘ ይሰነዓዉ። በእንተ ክርስቶስ ኅቡረ ከመ ደሞሙ ይክዓዉ። ሶበ ላዕሌሆሙ አፈ ግብ ዐጸዉ። ዘበውስቴታ ነፍሶሙ መጠዉ።


   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

     ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል

  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥


❖ በዚችም ቀን ለኢትዮጵያ ነገሥታት ለዘርዐ ያዕቆብ፣ ለበእደ ማርያም፣ ለእስክንድር የሠራዊት አለቃ የሆነ ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል አረፈ።   


❖ የዚህም ቅዱስ የአባቱ ስም ገላውዴዎስ የእናቱም ስም ኤልሳቤጥ ነው እነርሱም በዚህ ዓለም ገንዘብ ይልቁንም በሃይማኖትና በበጎ ሥራ የበለጸጉ ናቸው፤ ይህንንም ቅዱስ በቅዱሳን አርባዕቱ እንስሳ በዓል ወለዱት ስሙንም ዓምደ ሚካኤል ብለው ሰየሙት።


❖ ከተወለደም አንድ ዓመት ሲሆነው ከቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከመንበሩ ከርሠ ሐመር ውስጥ ማንም ያየው ሳይኖር እየዳኸ ገብቶ ሦስት ቀን ሰነበተ ወላጆቹም እርሱ እንደሞተ ተጠራጥረው እያለቀሱለት ኖሩ።


❖ ከዚህም በኋላ በሦስተኛው ቀን ቄሱ ሊዓጥን ገባ ዕጣንንም ሲፈልግ በከርሠ ሐመሩ ውስጥ ሕፃኑን በሕይወት አገኘው በበታቹም ምንም ምን ጉድፈት አልነበረም፤ ቄሱም ለወላጆቹ ነገራቸው እነርሱም እጅግ ደስ እያላቸው መጥተው ከዚያ ወሰዱት።


❖ ከዚያንም ጊዜ ጀምሮ በጥበብና በዕውቀት አደገ ነገሥታት ገዥ እስከ አደረጉት ድረስ በቤት ውስጥ በሚሠራው ላይ ሁሉ አሠለጠኑት፤ እርሱም ለድኆች በፍርዱና በምጽዋቱ አባት ሆናቸው በገንዘቡም አብያተ ክርስቲያናትን ሁሉ አደሰ በዘመኑም ሰላም ሆነ በጾሙና በጸሎቱ በምጽዋቱም በቅዱሳንም የጸሎት ርዳታ በወዲያም በወዲህም አገሮችን የሚያጠፉ ጠላቶችንና ዐመፀኞች ጠፉ፤ ጠላቶችም ሁሉ ለነገሥታቱ ተገዙና ግብርን ገበሩ።


❖ የዚህም ቅዱስ ዐምደ ሚካኤል ልቡ በእግዚአብሔር ፍቅር የታሠረ ነው በተጸለየበት ውኃ ሳይጠመቅና ሳይጠጣ አይመገብም ነበር ገንዘቡንም ሁሉ በምጽዋት ጨረሰ።


❖ እግዚአብሔርም በጎ ሥራውን በአየ ጊዜ እንዲፈተን ፈቀደለት ዐመፀኞች ሰዎችም በእርሱ ላይ ተነሡ እንዲገድለውም በንጉሥ ዘንድ በሐሰት ነገር ወነጀሉት ንጉሡ ግን እጅግ ስለሚወደው ራራለት በነገራቸውም በዘበዘቡትና በአስጨነቁትም ጊዜ ከጭንቀት የተነሣ ወደ ሩቅ አገር አሥሮ አጋዘው።


❖ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም የሚራዳው ሆነ ሰማያዊ ኅብስት የወይን ጽዋ እያመጣለት ይመግበዋል፤ ቅዱስ ቁርባንንም መቀበል በሚሻ ጊዜ የክብር ባለቤት የሆነ የክርስቶስን ሥጋውንና ደሙን አምጥቶ ይመግበዋል።


❖ ከዚህም በኋላ እሊያ ነገረ ሠሪዎች ይገድሉት ዘንድ ንጉሥ እንዲፈቅድላቸው ተማከሩ በፈቀደላቸውም ጊዜ ወደ ንጉሥ የፍርድ ሸንጎ አምጥተው ገደሉት።


❖ በዚያችም ሌሊት እግዚአብሔርን የሚፈራ አንድ መነኵሴ በድኑን ሊያይ ተነሥቶ ሔደ ሥጋውንም ሲያጥኑ ሦስት መላእክትን አገኛቸው፤ እርሱም እንዳልዋሸ በሕያው እግዚአብሔር ስም እየማለ ይህን ተናገረ።


❖ ዳግመኛም የብርሃን ፋና ከሰማይ ሲወርድለት ብዙ ቀን የተመለከቱም አሉ፤ ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ አዘነ ተጸጸተም በጎ ሥራውንም ሁሉ አሰበ እነዚያንም ሐሰተኞች ረገማቸው በሞትም ቀጣቸው ቅዱስ ዐምደ ሚካኤልም በአባቶቹ መቃብር አክብረው እንዲቀብሩት አዘዘ፤ እርሱ ቅዱስ እንደሆነ በበጎ ስም አጠራር እንዲጠሩት እንጂ ስሙን በክፉ እንዳይጠሩ አዋጅ አሳወጀ፤ መታሰቢያውንም አቆመለት ልጆቹንም አከበራቸው እጅግም ወደዳቸው።


❖ ከዚህም በኋላ ልብነ ድንግል በነገሠ ጊዜ ከእርሱ ጋር ያለውን የአባቱ የበእደ ማርያምን ቃል ኪዳን ሰምቶ ከዚያ አፍልሰው ወደ አትሮንስ ማርያም እንዲወስዱትና በዚያ በነገሥታት መቃብር እንዲቀብሩት አዘዘ።


ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


📌 ኅዳር 3 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ጻድቅ (ዘደብረ በንኮል)

2.ቅዱስ ዓምደ ሚካኤል ጻድቅ (የሠራዊት አለቃ)

3.ቅዱስ ኪርያቆስ ሊቅ

4.ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ ንጉሥ (ልደቱ)

5.ቅዱሳን አትናቴዎስና እህቱ ኢራኢ (ሰማዕታት)

6.አቡነ ፍሬ ካህን (አፈር ከኢየሩሳሌም አምጥተው ዋልድባ ሲደርሱ መነኮሳቱ ‹‹ገዳሙን በአህያ አታስረግጥ›› ቢሏቸው አህዮቹን ክንፍ አውጥተው እንዲበሩ ያደረጉ)


📌 ወርኀዊ በዓላት

1.በዓታ ለእግዝእትነ ማርያም ድንግል ወላዲተ አምላክ

2.ቅዱሳን ኢያቄም ወሐና

3.ቅዱሳን ሊቃነ ካህናት አበው (ዘካርያስና ስምዖን)

4.አባ ሊባኖስ ዘመጣዕ

5.አቡነ ዜና ማርቆስ

6.ቅዱስ ቄርሎስ ሊቅ (ዓምደ ሃይማኖት)


✍️"በረከት በጻድቅ ሰው ራስ ላይ ነው ፤ የኀጥአንን አፍ ግን ግፍ ይከድነዋል፤ የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው ፤ የኀጥኣን ስም ግን ይጠፋል"

📖ምሳሌ 10፥6-7


ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ። እምእለ ተጸምዱከ ዘልፈ። ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ። እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውኩፈ። እምእለ አብኡ ብዑላን ዘተርፈ።

ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን። ሰማዕት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን። ደናግል ዓዲ ወመነኰሳት ኄራን። ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን። እስከ አረጋዊ ልሒቅ ወንኡስ ሕፃን።

ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ። ለዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ። ወለዘሰምዐ ቃሎ በዕዝነ መንፈስ። በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኵሉ እምባእስ። ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ።


ጌታ ሆይ ከብልጽግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።

እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።

ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን።


✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝


✍"ልብህን በእርጋታ አኑረው፤ የሁሉም መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ለመሆን በጣም ትጋ ለከንቱ ንግግር ዘገምተኛና ሰነፍ ሁን፤ ነገር ግን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል በማወቅ በመስማት ድኅነትን የሚሰጡ ናቸውና ብልህ ሁን"

📚ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ


        ወስብሐት ለእግዚአብሔር

               ይቆየን 


───────────

          Channel 

 🧲 https://telegram.me/Tewahedo12


    FB Like Page (የፌስቡክ ፔጅ) 

🧲 http://facebook.com/Tewahedo12  


    YouTube Subscribe (ሰብስክራይብ)

🧲 https://www.youtube.com/channel/UCvYxUdv1D-5juH_P6iE7XXw

 ───────────

Report Page