ስንክሳር ዘወርኀ ታኅሣሥ ፲፭

ስንክሳር ዘወርኀ ታኅሣሥ ፲፭

@YeBiruk ዲያቆን ቡሩክ ይርጋ ዘውብ

✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

           አሜን


✍"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         

📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

         ቀናችንን በጸሎት እንጀምር

ስንክሳር ዘወርኀ ታኅሣሥ ፲፭


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ታኅሣሥ ዐሥራ አምስት በዚች ቀን ያለ ደም መፍሰስ ሰማዕት የሆነ የአርማንያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ጎርጎርዮስ አረፈ።


  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ጎርጎርዮስ (ዘአርመንያ)

  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ ይህንንም ቅዱስ የንጉሡን ትእዛዝ ስለመተላለፉና ለአማልክት አልሠዋም ስላለ የአርማንያ ንጉሥ ድርጣድስ አሠቃይቶ ጥልቅ ወደ ሆነ ደረቅ ጒድጓድ ውስጥ ጨመረውና በዚያ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበር አንዲቷን አሮጊትም ሁል ጊዜ ምግቡን እንድታመጣለት አደረጋት ሕያው እንደሆነም የሚያውቅ የለም።

❖ ንጉሥ ድርጣድስም ቅድስት አርሴማን ሊአገባት ሽቶ ነበርና በእርሷ ምክንያት ደናግሎችን ገደላቸው፤ የእሊህ ደናግልም ሥጋቸው በተራራ ላይ እንደ ወደቀ ነበር ንጉሡም ስለ ገደላቸው ደናግል ይልቁንም ውበቷንና ደም ግባቷን እያሰበ ስለ ቅድስት አርሴማ አብዝቶ የሚያዝንና የሚጸጸት ሆነ።

❖ ከዚህም በኋላ ወገኖቹ ለመኑት እንዲህም አሉት አውሬ ታድን ዘንድ በፈረስ ተቀመጥና ወደ ዱር እንውጣ የልብህም ኀዘን ይወገድልሃል፤ በዚያንም ጊዜ አውሬ ለማደን በፈረሱ ተቀምጦ ወደ ዱር ወጣ፤ ወዲያውኑ ሰይጣን አደረበትና ሥጋውን የሚነክስ ሆነ ወገኖቹንም ነከሳቸው እግዚአብሔርም መልኩን ለውጦ እንደ እሪያ አደረገው ያገኘውን ሁሉ የሚነክስ ሆነ፤ እንዲሁም ከቤተ መንግሥት ሰዎች በብዙዎቹ ላይ ሰይጣን አደረባቸው ታላቅ ድንጋጤም ሆነ ይህም ሁሉ የሆነ ስለ ቅዱሳት ድናግልና ስለቅድስት አርሴማ ነው።

❖ የንጉሡ እኅት ግን ጎርጎርዮስን ከጒድጓድ ካላወጣችሁት ድኅነት የላችሁም የሚላትን ሰው በራእይ አየች ይህንንም ለወገኖቿ ነገረች እርሱ አስቀድሞ በጎድጓድ ውስጥ የሞተ ስለ መሰላቸው ደነገጡ።

❖ በዚያንምም ጊዜ ወደ ጒድጓድ ሔዱ በሕይወት እንዳለም ያውቁ ዘንድ ወደ ጒድጓዱ ውስጥ ገመዶችን አወረዱና ገመዶቹን እንዲይዝ ወደርሱ ጮኹ እርሱም ገመዶችን ያዘ ስበው አወጡት አጥበውም ንጹሕ ልብስን አለበሱት በበቅሎም አስቀምጠው ወደ ቤተ መንግሥት አደረሱት።

❖ በዚያንም ጊዜ በሰማዕትነት ስለሞቱ ደናግል ሥጋ ጠየቀ እነርሱም የደናግሉ ሥጋቸው ወዳለበት መርተው አደረሱት የዱር አራዊትና አዕዋፍ ሳይበሏቸው በደኅና አገኛቸው ያማሩ ቦታዎችን አዘጋጅተው በውስጣቸው ያኖሩዋቸው ዘንድ አዘዘ እንዳዘዛቸውም አደረጉ።

❖ ከዚህም በኋላ ንጉሡን ያድነው ዘንድ ሕዝቡ ለመኑት ንጉሡም ወዳለበት ዱር አደረሱት እርሱም ከክፉ ሥራህ ትመለሳለህን ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታምናለህን አለው፤ እሪያ የሆነውም ንጉሥ አዎን እንደሚል ራሱን ዘንበል አድርጎ አመለከተ በዚያንም ጊዜ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ጸለየ ከንጉሡም ላይ በእሪያ አምሳል ሰይጣንን አስወጣው።

❖ የንጉሡም አእምሮውና መልኩ እንደ ቀድሞው ተመለሰለት ነገር ግን ዳግመኛ እንዳይታበይ ከእግሩ ላይ የእሪያ ጥፍር አስቀረ ለፈጣሪውም ተገዢ ይሆን ዘንድ ዳግመኛም የቤተ መንግሥት ሰዎችን ሁሉንም አዳናቸው ከላያቸውም አጋንንትን አስወጥቶ ሰደዳቸው።

❖ ከዚህም በኋላ የአርማንያን ሰዎች ሁሉንም ሰበሰባቸውና ሥርዓትን ሠራላቸው ስምንት ቀንም እንዲጾሙ አዘዛቸው እንዳዘዛቸውም አደረጉ የእግዚአብሔርንም ሕግ እያስተማራቸው ኖሩ።

❖ ዳግመኛም ክብር ይግባውና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆኑን አስተማራቸው ታላቆችም ታናሾችም ትምህርቱን ተቀበሉት ለአርማንያም ሰዎች ሃይማኖትን የመቀበላቸው ምክንያት ይህ ነው።

❖ ከዚህም በኋላ የክርስትና ጥምቀትን ያጠምቃቸው ዘንድ ቅዱስ ጎርጎርዮስን ለመኑት እርሱም እኔ ካህን ስለአልሆንኩ አይገባኝም ነገር ግን የሚያጠምቃችሁን ካህን ይልክላችሁ ዘንድ ወደ ሮሜ ሊቀ ጳጳሳት መልእክተኞችን ላኩ አላቸው።

❖ በዚያንም ጊዜ ከርሱ ጋር ወደ ንጉሥ አኖሬዎስና ወደ ሊቀ ጳጳሳቱ መልክተኞችን ልከው የአርማንያ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር እንደተመለሱ አስረዱአቸው ንጉሡም ሊቀ ጳጳሳቱም ሰምተው ደስ አላቸው ከዚህም በኋላ ሊቀ ጳጳሳቱ የአርማንያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ይሆን ዘንድ ቅዱስ ጎርጎርዮስን ሾመው ወደ አርማንያን ንጉሥ ወደ ድርጣድስም በክብር ላከው።

❖ ቅዱስ ጎርጎርዮስም ተሹሞ ወደ አርማንያ አገር በደረሰ ጊዜ በመምጣቱ ደስ ተሰኙበት እርሱም የአርማንያን ሰዎች ሁሉንም አጠመቃቸው በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያምም ስም ያማረች ቤተ ክርስቲያን ሠራላቸው በሃይማኖትም ከአጸናቸውና መልካም ጎዞውንም ከፈጸመ በኋላ በሰላም በፍቅር አረፈ።

ለእግዚአብሔርም ምሥጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ለዘላለሙ ትኑር አሜን።

 

      አርኬ

✍️ ሰላም ለጎርጎርዮስ ዘተዓገሠ ሥቃየ። በሌሊት ቊረ ወበመዓልት ዋዕየ። ዓመታተ ዐሠርተ ወኃምስተ አመ ውስተ ግብ ተወድየ። ወሰላም ለአረጊት ዘተልእከቶ ሠናየ። እንዘ ትዌግር ሎቱ በኅቡእ ሲሳየ።


  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

  አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ረባን

  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ ሐዋርያዊው ጻድቅ ኢትዮዽያዊ (ኤርትራዊ) ሲሆኑ በዓለም ደረጃ የሚታወቅ አገልግሎት ያላቸው አባት ናቸው፤ በመካከለኛው ዘመን የኢትዮዽያ ታሪክ የኤወስጣቴዎስንና የተክለ ሃይማኖትን ያህል ስሙ የጐላ ጻድቅ አይገኝም::

❖ ጻድቁ በ1265 ዓ.ም አካባቢ እንደ ተወለዱ ሲታመን ወላጆቻቸው ክርስቶስ ሞዐና ስነ ሕይወት ይባላሉ፤ የጻድቁ የመጀመሪያ ስም "ማዕቀበ እግዚእ" (ለጌታ የተጠበቀ) ነው፤ ኤዎስጣቴዎስ የተባሉ በሁዋላ ነው፤ ገና ከልጅነታቸው መንፈሰ እግዚአብሔር አድሮባቸዋልና ለዚህ ዓለም ግድ አልነበራቸውም::

❖ ከመምሕር ዘንድ ገብተው ቅዱሳት መጻሕፍትን ተምረው ዲቁናን ተቀብለው ያገለግሉ ገቡ፤ በዲቁና አገልግሎታቸው ስሉጥ (ፈጣን) በመሆናቸውም የዘመኑ አበው "ዳግማዊ እስጢፋኖስ" እያሉ ይጠሯቸው ነበር::

❖ ከዚያ በወጣትነት እድሜአቸው ምናኔን መርጠው ጾምና ጸሎትን ከስግደት ጋር አዘወተሩ፤ እንዲህ ባለ ሕይወት ሳሉ አንድ ቀን ለስም አጠራሩ ጌትነት ይሁንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ዘንድ መጣ፤ በዘባነ ኪሩብ በግርማው ቢያዩት ደነገጡ፤ ጌታ ግን "ወዳጄ ኤዎስጣቴዎስ ገና ከእናትህ ማሕጸን መርጬሃለሁ፤ ከኢትዮዽያ እስከ አርማንያም ሐዋርያ ትሆን ዘንድ ሹሜሃለሁ::

✍"ዘኪያከ ሰምዐ ኪያየ ሰምዐ

👉አንተን የሰማ እኔን ሰማ አንተን እንቢ ያለ እኔን እንቢ አለ" ብሏቸው ባርኩዋቸው ዐረገ::

❖ ጻድቁ ፈጣሪያቸውን ስለ ስጦታው እያመሰገኑ ቅስናን ተቀብለው ስብከትን ጀመሩ፤ ስም አጠራራቸውም ፈጥኖ በሃገሪቱ ተሰማ በየቦታው እየዞሩ ያላመነውን አሳምነው እያጠመቁ ያመነውን በሥርዓተ ቤተክርስቲያን እያጸኑ ሕይወተ ገዳምን እያስፋፉ ኖሩ፤ አሁን ኤርትራ ውስጥ የሚገኘውንና እርሳቸው የመሠረቱትን ገዳም ጨምሮ ለገዳማዊ ሕይወት መስፋፋት አስተዋጽኦ አድርገዋል፤ በገዳማቸውም አባ አብሳዲን ጨምሮ በርካታ አርድእትን አስተምረዋል አፍርተዋል::

❖ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በተለይ የሚታወቁት ቀዳሚት ሰንበት እንዳትናቅ (እንድትከበር) ባደረጉት ጥረት ነው፤ ደግሞም ተሳክቶላቸዋል፤ ቅርብ ጊዜ ከምናየው የድፍረት ሥራ በቀር በሃገራችን 2ቱም ሰንበቶች ክቡር ናቸው::

❖ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ 2 ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም በእግራቸው ተጉዘዋል፤ መሔዳቸው ግን ለመሳለም ብቻ አይደለም፤ ይልቁኑ የወንጌል ዘርን እየዘሩ ፍሬውንም እየለቀሙ እንጂ፤ እርሳቸው መቼም ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን ቸል አይሉምና::

❖ በመጨረሻ ሕይወታቸውም በገዳማቸው ላይ ደቀ መዝሙራቸውን አባ አብሳዲን ሹመው ለአዲስ ጉዞ ተነሱ፤ እኩሎች ልጆቻቸውን በገዳማቸው ትተው እኩሎችን አስከትለው ጉዞ ወደ አርማንያ ተደረገ::

❖ በመንገድም ወደ ባሕረ ኢያሪኮ ሲደርሱ የሚሻገሩበት መርከብ አጡ፤ ድንቅ አባት ናቸውና በእምነት አጽፋቸውን (ኩታቸውን) አውልቀው ባሕሩ ላይ ጣሉት፤ በላዩ ላይም በትእምርተ መስቀል አማትበው ተቀመጡበት::

❖ ደቀ መዛሙርቶቻቸውም ባሕሩ ላይ በተነጠፈው ኩታ ላይ ከበው ተቀመጡ፤ ከሰማይም ጌታችን ወርዶ በመካከላቸው ቆመ፤ ሚካኤል በቀኝ ገብርኤልም በግራ ቆሙ፤ ጻድቁ ደግሞ ልጆቻቸውን ያስተምሯቸው ይተረጉሙላቸው ገቡ::

❖ በመካከል ግን አንዱ (የማነ ብርሃን ይሉታል በቅኔ ቤት) በመጠራጠሩ እርሱ የተቀመጠባት ብቻ ተቀዳ ሰጠመ በሁዋላ ግን ጻድቁ ተመልሰው አውጥተው ከሞት አስነስተውታል፤ በዚህም ምክንያት 'ዘአደወ ባሕረ ማዕበልን የተሻገረ' ይባላሉ::

❖ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ በአርማንያ ለዘመናት ሰብከው ሕይወተ ገዳምን አስፋፍተው ብዙ ተአምራትን ሠርተው በተወለዱ በ80 ዓመታቸው በ1345 ዓ.ም ዐርፈዋል፤ በብዙ ዝማሬ በመቅደሰ መርምሕናም ተቀብረዋል፤ በኢትዮዽያ፣ ኤርትራ፣ ግብጽናና አርማንያ ይከብራሉ፤ ዛሬ ጻድቁ ማዕበሉን የተሻገሩበት መታሰቢያ ቀን ነው::

አምላከ ቅዱሳን ስለ አባቶቻችን ሲል በምሕረቱና በቸርነቱ ይጐብኘን፤ ከበረከታቸውም ረድኤታቸውም ይደርብን፤ በጸሎታቸው ሀገራችን ሰላም ፍቅር ያደርግልን

   

        አርኬ

✍️ሰላም ለሉቃስ ዘፃመወ ፃማ። በልብሰ ኀፂን ይትጋደል ወይትቃተል ምስለ መስቴማ። መዋዕለ ጾሙ ስዱስ እስከ ይትፌጸማ። ለዕርቅት ከርሡ እንዘ ይሠርዕ ዓቅማ። በዕለተ ሰንበት ይሴሰይ አሐደ ጳኩሲማ።
✍️ሰላም ለከ ይምላህ። መዝገበ ረድኤት ወንጽሕ። ውስተ ቤተ ትፍሥሕት አብአኒ በስነ ጽድቅከ ብሩህ። እምነ ኃጥአን እለ ከማየ በጊዜ ሐተታ ወፍትሕ። አምሳለ ፈለግ ብዙኅ አመ ይደምፅ ላህ።


 ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

   አቡነ ሉቃስ ዘዓምድ

✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ ሀገሩ ፋርስ ሲሆን በመቶ የንጉሡ ጭፍራ ላይ መኰንን ሆኖ ተሹሞ ነበር፤ በኋላም ሹመቱን ትቶ ገዳም ገብቶ መነኮሰ፤ በምሥራቅ ካሉ ገዳማት ውስጥ በአንዱ ገብቶ ብዙ ዘመን ሲጋደል ኖረ፤ ልብሱንም የብረት ልብስ በማድረግ እስከ 6 ቀን የሚጾም ሆነ፡፡

❖ ከዚህም በኋላ ከዓምድ ላይ ወጥቶ በዚያ ላይ ሦስት ዓመት ለጸሎት ቆመ፥ የታዘዘ መልአክም መጥቶ ከዚያ ዓምድ ላይ እንዲወርድ ነግሮት በብርሃን መስቀል እየመራው ወስዶ አንድ ገዳም አደረሰው፡፡

❖ በዚያም ብዙ ተአምራት እያደረገ ኖረ፤ ከዚህም በኋላ አቡነ ሉቃስ አርምሞ ያዘ፤ ከቶ እንዳይናገርም በአፉ ውስጥ ድንጋይ ነክሶ ያዘ፤ አሁንም መልአኩ ወደ ቍስጥንጥንያ ዳርቻ ቦታ ይዞት እየመራ ወስዶት በዚያም አንዲት ምሰሶ ላይ ወጥቶ ታላቅ ተጋድሎን እየተጋደለ በላይዋ ላይ 45 ዓመት ኖረ፡፡

❖ በዚያም አስደናቂ ተአምራትን እያደረገ ብዙዎችን በመፈወስና ወንጌልን በማስተማር ብዙ ደከመ፤ ታህሳስ 15 ቀን ካረፈ በኋላ ሊቀ ጳጳሳቱና ካህናቱ መጥተው በክብር ወደ ቍስጥንጥንያ ከተማ ወሰዱት፤ በዚህም ጊዜ በድውያን ላይ ታላቅ ፈውስ ሆነ።

የአባ ሉቃስ ረድኤቱ በረከቱ ይደርብን፤ በጸሎቱ ይማረን


 ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

  የእኔ ቢጤው አባ ቆራይ

 ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ አባ ቆራይ እጅና እግር የሌላቸውና የእኔ ቢጤ የነበሩት ጽድቃቸውን ማንም ሳያውቅባቸው የኖሩት አባ ቆራይ ጻድቅ መሆናቸው ካረፉ በኋላ ነው የታወቀው፤ ገዳማቸው ትግራይ ተንቤን ውስጥ ይገኛል፡፡

❖ ቅዱሱ በአፄ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግሥት በትግራይ ተንቤን አውራጃ አዲ ራእሶት የራሶች (የታላላቅ ሰዎች አገር) በሚባለው ቦታ የእግርና የእጅ ጣቶች የሌሏቸው አባ ቆራይ ወንበር በምትመስል ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ተገለጡ፡፡

❖ አንድ የአካባቢው ሰው በመንገድ ሲያልፍ አባ ቆራይ ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ጸሎት ሲያደርጉ አያቸውና በሁኔታው ተገርሞ ወደ እርሳቸው ጠጋ ብሎ ስማቸውንና የመጡበትን አገር ጠየቃቸው፤ እርሳቸውም ‹‹ስሜ አባ ቆራይ ይባላል አገር ግን የለኝም›› አሉት፥ እርሱም እባክዎን ወደ መንደር እንሂድና የጸሎትና ቤት ሠርተንልዎት በዚያ ይቀመጡ›› አላቸው፡፡

❖ አባ ቆራይ ግን ‹‹ማረፊያዬ ይህቺ ናት ከዚህች ሥፍራ አልነሣም›› አሉት፤ፐአባ ቆራይም በዚያው እንደተቀመጡ ዝናቸው በሁሉ ዘንድ ተሰማና ሰዎች መጥተው በተቀመጡበት ድንጋይ ዙሪያ ጎጆ ቀለሱላቸው፡፡

❖ ከዚህም በኋላ መንደርተኞቹ በየተራ በምግብ ሊረዷቸው ዕጣ ተጣጥለው ወደ የቤታቸወ ሄዱ፤ በመጀመሪያ ተራ የደረሰው ሰው ከአንድ ሰዓት በኋላ ምግብ ይዞ ቢመለስ የአባ ቆራይ ጎጆ በብርሃን ተሞልታ አገኘ፤ ወደ ጎጆዋም ሲጠጋ ነበልባሉ እየፈጀው አላስቀርበው አለ፡፡

❖ እርሱም በድንጋጤ ወደ መንደሩ ተመልሶ ለአካባቢው ሰው ነግሮ ሁሉም ተሰብስበው መጡ፤ መንደርተኛውም ካህናትን ይዘው ብዙ የምሕላ ጸሎትና እግዚኦታ ካደረሱ በኋላ እግዚአብሔር ወደ ጎጆዋ እንዲገቡ ፈቀደላቸውና ገቡ፤ ነገር ግን አባ ቆራይን በሕይወት አላገኟቸውም፡፡

❖ አስክሬናቸውን ብርሃን ከቦት አገኙት፤ ከአስክሬናቸው አጠገብ ‹‹የአባ ቆራይን አስክሬን ከዚህች ጎጆ ውስጥ እንድትቀብሩት፤ ወደ ሌላ ቦታ ወይም ቤተክርስቲያን ወስደን እንቀብራለን ብላችሁ እንዳታስቡ፤ ነገሩን በድፍረት ብትፈጽሙት በሀገሩ ላይ እግዚአብሔርን ቁጣ ታመጣላችሁ›› የሚል ትእዛዝ በብራና ተጽፎ ተገኘ፡፡

❖ በዚሁ ትእዛዝ መሠረት የአገሩ ሕዝብ ተሰብስቦ አባ ቆራይን ታህሳስ 15 ቀን እዚያው ቀበሯቸው፤ ከጥቂት ዘመናት በኋላ ባልና ሚስት የሆኑ ሰዎች መቆመም ሆነ መራመድ የማይችል ድውይ ልጃቸውን ይዘው ወደ ጸበል ሲሄዱ መሸባቸውና በአካባቢው ማደሪያ ሲፈልጉ የአባ ቆራይ ጎጆ ክፍት ሆኖ ታያቸውና ልጃቸውን ይዘው ሄደው ገቡ፡፡

❖ ድውይ ልጃቸውን በአባ ቆራይ መቃብር ላይ ቢያስተኙት የኤልሳዕን አጥንት እንደነካውና ፈጥኖ እንደተነሣው ሙት ይህ ድውይ ልጅም በአባ ቆራይ መቃብር ላይ እንዳረፈ ወዲያው አፈፍ ብሎ በመነሣት እንደ እንቦሳ ጥጃ መዝለል ጀመረ፤ ወላጆቹም እልልታቸውን አቀለጡት፤ ወላጆቹም በነጋ ጊዜ ወደ መንደርተኛው ሄደው የተደረገላቸውን ተአምር ተናገሩ፡፡

❖ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ የአባ ቆራይ በዓል በአካባቢውና አጎራባች ቦታዎች ሁሉ ዘንድ መከበር ጀመረ፤ የእረፍታቸውም በዓል ታህሳስ 15 ቀን ሆነ፤ አባ ቆራይ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ለይተው እንደ ቅዱስ አልዓዛር

📖ሉቃ 16፥19-35

❖ ለዚህ ዓለም ውዳቂ መስለው ለታላቅ ክብር የበቁ ጻድቅ አባት ናቸው፤ ዛሬም ልብሳቸውንና አካላቸውን ብቻ እያየን የምንንቃቸው ሰዎች እንደ አባ ቆራይ ያሉ ቅዱሳን ሊሆኑ ይችላሉ፤ ከልዑል እግዚአብሔር በቀር ማን ማንም የሚያውቅ የለምና።

የአባ ቆራይ ረድኤታቸው በረከታቸው ይደርብን፤ በጸሎቱ ይማረን


📌 ታኅሣሥ 15 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ ጐርጐርዮስ ሊቅ (ዘአርማንያ)

2.አቡነ ኤዎስጣቴዎስ ረባን

3.ቅዱስ ሉቃስ ዘዓምድ

4.አባ ይምላህ


📌 ወርኀዊ በዓላት

1.ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ (አፈ በረከት)

2.ቅድስት እንባ መሪና

3.ቅድስት ክርስጢና

4.ቅዱስ ሚናስ ሰማዕት

5.ቅዱስ ቂርቆስ ሰማዕት

4.ብጽዕት ኢየሉጣ ሰማዕት


✍️"ጻድቃን ጮኹ ፥ እግዚአብሔርም ሰማቸው ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው፤ እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው ፥ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል፤ የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው ፥ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል፤ እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል ፥ ከእነርሱም አንድ አይሰበርም"

📖መዝ 33፥17-20


ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ። እምእለ ተጸምዱከ ዘልፈ። ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ። እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውኩፈ። እምእለ አብኡ ብዑላን ዘተርፈ።

ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን። ሰማዕት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን። ደናግል ዓዲ ወመነኰሳት ኄራን። ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን። እስከ አረጋዊ ልሒቅ ወንኡስ ሕፃን።

ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ። ለዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ። ወለዘሰምዐ ቃሎ በዕዝነ መንፈስ። በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኵሉ እምባእስ። ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ።


ጌታ ሆይ ከብልጽግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።

እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።

ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን።


✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝


✍"ልብህን በእርጋታ አኑረው፤ የሁሉም መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ለመሆን በጣም ትጋ ለከንቱ ንግግር ዘገምተኛና ሰነፍ ሁን፤ ነገር ግን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል በማወቅ በመስማት ድኅነትን የሚሰጡ ናቸውና ብልህ ሁን"

📚ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ

             ወስብሐት ለእግዚአብሔር

                             ይቆየን 


───────────

                   Channel

 🧲 https://telegram.me/Tewahedo12


       FB Like Page (የፌስቡክ ፔጅ)

🧲 http://facebook.com/Tewahedo12  


       YouTube Subscribe (ሰብስክራይብ)

🧲 https://www.youtube.com/channel/UCvYxUdv1D-5juH_P6iE7XXw

 ───────────


Report Page