ስንክሳር ዘወርኀ ታኅሣሥ ፲፬
@YeBiruk ዲያቆን ቡሩክ ይርጋ ዘውብ✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
አሜን
✍"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
ቀናችንን በጸሎት እንጀምር
ስንክሳር ዘወርኀ ታኅሣሥ ፲፬
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በውልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ታኅሣሥ ዐሥራ አራት በዚች ቀን ከፍ ከፍ ካለች ከመኑፍ ከተማ ቅዱስ ሰምዖን በሰማዕትነት አረፈ።
እርሱም በእስላሞች ዘመን ከመሳፍንቶቻቸው ከአንዱ ጋር ተከራከረና ቅዱስ ስምዖን ረትቶ አሳፈረው ያም እስላም ወደ መሳፍንቱ አለቃ ሒዶ ይህ ስምዖን የእስላሞችን ሃይማኖት ያቃልላል ብሎ ወነጀለው ስለዚህም ይዘው በጽኑዕ ሥቃይ አሠቃዩት ከዚያም በኋላ ራሱን በሰይፍ ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልን በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
በዚችም ቀን ቅዱሳን አባ ብሑርና አረጋዊ ሚናስ በሰማዕትነት አረፉ። በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
አርኬ
✍️ሰላም ለስምዖን ምቱረ ክሣድ በሰይፍ። ዘሀገረ መኑፍ። ለብሑር ወሚናስ ዘወንጌል አዕዋፍ። ዑሩኒ በመዝራዕት ወሕዝሉኒ በክንፍ። ከመ ታዕድዉኒ እምቀልቀል ወጸድፍ።
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
ቅዱሳን መርምህናምና እኅቱ ሣራ አርባ
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❖ በዚችም ቀን የቅዱሳን መርምህናምና እኅቱ ሣራ አርባ አገልጋዮቹም በሰማዕትነት አረፉ። የዚህም ቅዱስ አባቱ የአቶር ንጉሥ የተቀረጹ ስማቸው ቤል፣ አጵሎን የሚባሉ ጣዖቶችን የሚያመልክ ነው እናቱ ግን ክርስቲያን ናት።
❖ ይህም ቅዱስ መርምህናም ወደ ዱር ሒዶ አራዊትን ያድን ዘንድ እንዲፈቅድለት አባቱን ለመነው በፈቀደለትም ጊዜ ወደ እናቱ ሒዶ አራዊትን ለማደን ወደበረሀ እሔዳለሁ አላት እናቱም የሰማይና የምድር አምላክ እግዚአብሔር በላይህ በረከትን ያሳድር አለችው።
❖ ከዚህም በኋላ ከአርባ ፈረሰኞች አገልጋዮቹ ጋር ወጥቶ ሔደ መቅሉብ ወደሚባል ተራራም ደርሶ በዚያ አደረ፤ በሌሊትም የእግዚአብሔር መልአክ ጠራው እንዲህም አለው መርምህናም ሆይ ተነሥተህ ወደዚህ ተራራ ላይ ውጣ ስሙ ማቴዎስ የሚባል ቅዱስ ሰው ታገኛለህ እርሱም የሕይወትን ነገር ይነግርሃል ሲነጋም ወደ ተራራው ወጣ እንደ በግ ጠጉር ለብሶ አባ ማቴዎስን አገኘው መርምህናም በአየው ጊዜ ፈራ ቅዱስ አባ ማቴዎስም ልጄ ሆይ ወደ እኔ ቅረብ እኔም የእግዚአብሔር ፍጥረቱ የሆንኩ እንዳተ ሰው ነኝ አለው።
❖ መርምህናምም ከአባቴ አማልክቶች በቀር አምላክ አለን አለው አባ ማቴዎስም የክርስትና ሃይማኖትን ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የክርስቶስን ህልውና በተለየ አካሉ ሰው መሆኑንና መከራ ተቀብሎ መሞቱን መነሣቱን ወደ ሰማይ ማረጉንም የፍርድ ቀንም እንዳለ ለጻድቃን በጎ ዋጋ ለኋጢአተኞች ቅጣት እንዳለ አስተማረው።
❖ መርምህናምም ከራስዋ እስከ እግርዋ ለምጽ የያዛት እኅት አለችኝ የአምላክህን ስም ጠርተህ በጸሎትህ ብታድናት እኔ አምንበታለሁ አለው አባ ማቴዎስም እኔ አድናታለሁ ና በአንድነት እንውረድ አለው ከተራራው በወረዱ ጊዜ አባ ማቴዎስን በመንገድ ትቶ ቅዱስ መርምህናም ወደ እናቱ ሒዶ ሁሉን ነገራት እኀቱንም በሥውር ወደ አባ ማቴዎስ ወሰዳት አባ ማቴዎስም ወደ እግዚአብሔር ጸለየና ምድሪቱን አመሳቅሎ መታት በዚያን ጊዜ ውኃ መንጭቶ እንደ ባሕር ሆነ ወደ ባሕሩም አውርዶ እጁን በራሳቸው ላይ አድርጎ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቃቸው አሽከሮቹን አርባ ሰዎችንም ሥጋውንና ደሙንም አቀበላቸው ወዲያውኑ ሣራ ከለምጽዋ ነጻች።
❖ ከዚህም በኋላ አባ ማቴዎስ ስለ ከበረ ስሙ በላያቸው የሚመጣውን መከራ በሚቀበሉ ጊዜ ክብር ይግባውና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን እንዲጸኑ መከራቸው ከዚህም በኋላ በላያቸው ጸለየና በፍቅር አንድነት አሰናበታቸው።
❖ ቅዱስ መርምህናምም በመጣ ጊዜ ወደ እናቱ ቤት ገባ ወደ አባቱ ወይም ወደ አማልክቶቹ አልሔደም አባቱም ሰምቶ ተቆጣ ወደ አማልክቶቹ ቤትም እንዲጠሩት አዘዘ ቅዱስ መርምህናም ግን ከእኅቱና ከሠራዊቱ ጋር ስሟ ቅሳር ወደ ምትባል ተራራ ሒዶ ከላይ ወጥቶ በዚያ ተቀመጠ።
❖ አባቱም በሰማ ጊዜ ከልብሰ መንግሥትና ከዘውድ ጋር መኳንንቱን የመንግሥቴን ሥልጣን ተረከብ ብሎሃል እንዲሉት ላካቸው እርሱ ግን በቁጣ ተመለከታቸውና እኔ ክብር ይግባውና የጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስን ፈጽሞ የማይጠፋ መንግሥት እሻለሁ አላቸው፤ የአቶር ንጉሥ አባቱም በዚያን ጊዜ ተቆጣ ልቡ ፈርቶ ይመለስ ዘንድ አገልጋዮቹን በፊቱ እንዲገድሏቸው ካልተመለሰ ግን እርሱንም እኅቱንም እንዲገድሉ አዘዘ።
❖ ቅዱስ መርምህናምም ሰምቶ የተመኘውን ይሰጠው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ ጸሎትህን ሰማሁ ልብህ የወደደውንም ሰጠሁህ የሚል ቃል ከሰማይ መጣ፤ ከዚህም በኋላ የቅዱሳኑን ራሳቸውን በሰይፍ ቆረጡና ከጉድጓድ ውስጥ ጣሏቸው ሥጋቸውንም ያቃጥሉ ዘንድ ብዙ ዕንጨቶችን ሰበሰቡ ግን አላገኙአቸውም እግዚአብሔር ሠውሮዋቸዋልና።
❖ ወዲያውኑ ንውጽውጽታ ሆነ ፀሐይም ጨለመ ወታደሮችም ፈርተው ሸሹ ሰይጣንም በአቶር ንጉሥ በሰናክሬም ላይ አድሮ አሳበደው እንደእሪያም ጮኸ የቅዱስ መርምህናምም እናት አይታ ወደ አባ ማቴዎስ ልካ አስመጣችውና የንጉሡን ነገር ነገረችው እርሱም በዘይት ላይ ጸልዮ ቀባው ሰይጣንም በእሪያ አምሳል ከርሱ ወጣ፤ በዚያንም ጊዜ ንጉሡ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አመነ ከቤተሰቦቹና በሚገዛው አገር ካሉ ሰዎች ሁሉ ጋር ተጠመቀ።
❖ ከዚህም በኋላ አምላክን በወለደች በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስም ቤተ ክርስቲያን እንዲሠሩ ገንዘቡንም ለድኆችና ለችግረኞች እንዲበትኑ አዘዘ ሁሉንም እንዳዘዛቸው አደረጉ።
❖ የቅዱስ መርምህናምም እናት ከከበሩ ደንጊያዎች አርባ ሣጥኖችን አሠራች የልጅዋ ጭፍራ የነበሩ የእነዚያን አርባ ሰማዕታት አጥንቶቻቸውን አሰብስባ በየአንዳንዱ ሣጥን ጨመረቻቸው ለልጆቿም ብርሌ ከሚመስል ዕንቁ ሁለት ሣጥን አሠርታ በውስጣቸው አድረጋ በሠራችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አኖረቻቸው ከሥጋቸውም ታላላቅ የሆኑ ቁጥር የሌላቸው ተአምራት ተገለጡ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
አርኬ
✍️ሰላም ለመርምህናም እንተ ዔለ በድወ። ሃይማኖተ ክርስቶስ ይኀሥሥ ድኅረ ሐልዮቱ ንዒወ። ነጺሮ ደሞ በእንተ ሃይማኖት ክዕወ። ከመ ሐራውያ ንጉሥ ነቀወ። ወፀሐየ ራማ ብርሃኖ ሐሰወ።
✍️ሰላም ሰላም ዕደወ ኃይል ሐራ። ዘኁላቌሆሙ ካዕበተ እስራ። በእንተ ክርስቶስ ዘዖሩ ለክበደ ዕለት ፃዕራ። ዘመርምህናም እግዚኦሙ ሶበ ነጸሩ መከራ። ወዘምስሌሁ እንተ ሐመት ሣራ።
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
17 እልፍ ሰማዕታት
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❖ በዚችም ዕለት ዳግመኛ ከቅዱስ መርምህናም አባት ከአቶር ንጉሥ ከሰናክሬም ሠራዊት የአሥራ ሰባት እልፍ ሰማዕታት መታሰቢያቸው ሆነ፤ ይህም እንዲህ ነው የአቶር ንጉሥ ሰናክሬም ከሞተ በኋላ መንግሥቱን መጠበቅና ማዘዝ የማይችል ታናሽ ብላቴና ልጁ በእርሱ ፈንታ ነገሠ ግን እናቱ ስለርሱ ሹሞችን ታዝዛቸዋለች እነርሱም ይታዘዙላት ነበር።
❖ ከለዳዊ ንጉሥም ይህን በሰማ ጊዜ የአቶርን መንግሥት ለመውሰድ ስለዚህ ሠራዊቱን ሰብስቦ ለመዋጋት መጣ የሰናክሬምም አሽከሮችና መቃብሩን ጠባቂዎች የሆኑ የቅዱስ መርምህናም አሽከሮችም ሊከላከሉ ወጡ የከለዳውያን ንጉሥም አሸንፎ ከተማዪቱን ከፍቶ ገባ ብላቴናውንም ንጉሥ ይዞ ከእናቱ ጋር ገደለው ከዚህም በኋላ የአቶር አገር ሰዎች ተገዙለት በላያቸውም ነግሦ መንግሥትን ያዘ።
❖ ከጥቂት ቀኖችም በኋላ የአቶርን አገር ሰዎች ሰብስቦ ስለ ሃይማኖት ጠየቃቸው እነርሱም ክርስቲያን ነን አሉት፤ እርሱም ለጣዖት እንዲሰግዱ አዘዛቸው ከእነርሱም ውስጥ ሃይማኖታቸውን ለውጠው ለጣዖት የሰገዱ አሉ።
❖ የቅዱስ መርምህናምና የአባቱ አገልጋዮች መጥተው እንዲህ አሉት እኛ የክርስቶስ አገልጋዮች የሆን በግልጥ ክርስቲያኖች ነን ጌታችን ያስተማረንን ሃይማኖታችንን አንክድም በእኛ ላይ የፈለግኸውን አድርግ አሉት በዚያንም ጊዜ ተቆጣ ይገድሏቸውም ዘንድ አዘዘ ቁጥራቸውም አንድ መቶ ሰባ ሺህ ሆነ እነርሱም የቅዱስ መርምህናም ማኀበር ተብለው ተጠሩ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
እለተ ብርሃን
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❖ ቅድስት ቤተክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስንና የቅዱስ ያሬድን አስተምሕሮ መሠረት አድርጋ ይህንን ዕለት (ታህሳስ 14) "እለተ ብርሃን" ሳምንቱን (ከታህሳስ 14-20 ያለውን) ደግሞ "ሰሙነ ብርሃን" ስትል ታስባለች::
❓"ብርሃን" ማለት
❖ በቁሙ የእግዚአብሔር ስሙ #አንድም የባሕርይ ገንዘቡ ነው::
✍"እግዚአብሔር ብርሃን ነውና፤ ጨለማም በእርሱ ዘንድ የለችምና"
📖ዮሐ. 1፥4
❖ በዚህ ዕለት "ብርሃን" በሚል መነሻ ቤተክርስቲያን እነዚህን ታስተምሠራለች
❶ እግዚአብሔር ብርሃን መሆኑን::
📖ዮሐ 1፥5
❷ አምላካችን በመጀመሪያው የፍጥረት ቀን (በእለተ እሑድ) ዲያብሎስ ቅዱሳን መላእክትን ሲረብሽ "ለይኩን ብርሃን" ብሎ ብርሃንን መፍጠሩን::
❸ ነቢያት አበው በጨለማው ዓለም ሆነው መከራ ሲበዛባቸው
✍"ፈኑ ብርሃነከ
👉ብርሃንህን ላክልን" እያሉ መጮሃቸውን::
📖መዝ 42፥3
❹ ጩኸታቸውን የሰማ ከሦስቱ አካላት አንዱ ወልድ (እውነተኛው ብርሃን) ወደዚህ ዓለም መምጣቱን::
📖ዮሐ 9፥5
❺ ብርሃነ መለኮቱን በገሃድ መግለጡን::
📖ማቴ 17፥1
❻ ብርሃን የሆነችውን ሕግ ወንጌልን እንደ ሠራልን::
📖1ኛ ዮሐ 2፥9
❼ ድንግል እመቤታችን ብርሃን የብርሃንም እናቱ መሆኗን::
📖ሉቃ 1፥26
📖ራዕ 12፥1
❽ ቅዱሳኑ ብርሃን መባላቸውን::
📖ማቴ 5፥14
❾ እኛ በሰው ፊት ሁሉ እንድናበራ መታዘዛችን::
📖ማቴ 5፥16
❖ ከላይ የተጻፋት ሁሉ ይታሰባል፤ እርሱ ፈጣሪያችን ክርስቶስ ጨለማውን በምሕረቱ አርቆልናልና ዳግመኛ ወደ ጨለማ እንዳንሄድ እየለመንን እናመስግነው::
✍"ክርስቶስን ብርሃን ዘአሰሰልከ ጽልመተ፤ ላዕለ ኪሩቤል ነቢረከ ዘትሬኢ ቀላያተ፤ ስቡሕኒ ወልዑል አንተ"
📘መልክአ ኢየሱስ
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
ሊቀ ጳጰሳት አባ ገብረ ክርስቶስ
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❖ በዚችም ቀን ቅዱስ አባት የእስክንድርያ ሊቀ ጳጰሳት አባ ገብረ ክርስቶስ አረፈ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ስድሳ ስድስተኛ ነው።
❖ በዚህም አባት ዘመን ብዙዎች አስደናቂዎች ተአምራት ተደረጉ፤ እነሆ እንዱልስ በሚባል አገር በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስም የተሠራች አንዲት ቤተ ክርስቲያን እንዳለች በደጃፍዋም የደረቀች የወይራ ዕንጨት እንዳለች በእመቤታችንም በበዓልዋ ቀን እንደምትለመልም እንደምታብብና ብዙ እንደምታፈራ በዓሉም ከተፈጸመ በኋላ ተመልሳ እንደምትደርቅና እንደ ቀድሞዋ እንደምትሆን ሰማ።
❖ ስለዚህም ይህን ተአምር ይገልጽለት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ለመነ በዚያችም በእመቤታችን በዓል ዕለት ከእግዚአብሔርም የታዘዘ መልአክ ነጥቆ ወደዚያች ቤተ ክርስቲያን አደረሰው ያቺንም ዕንጨት ደረቅ ሁና አያት ያን ጊዜም ለመለመች አበበችና ብዙ ፍሬንም አፈራች ከበዓሉ ፍጻሜ በኋላም ወደ ደረቅነቷ ተመለሰች ይህንንም ለሕዝቡ ቢነግራቸው እነርሱ ተጠራጠሩ።
❖ ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ከዚያች እንዱልስ ከምትባል አገር ስሙ ዮሐንስ የሚባል መኰንን መጣ ሊቀ ጳጳሳቱ አባ ገብረ ክርስቶስም በካህናቱና በሕዝቡ ሁሉ ፊት እንዲህ ብሎ ጠየቀው እንዱልስ በሚባል አገር በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ደጃፍ የደረቀች የዘይት ዕንጨት እንዳለች በእመቤታችንም የበዓል ቀን እንደምትለመልምና እንደምታፈራ የሰማነው እውነት ነውን አሉት።
❖ ያም መኰንን እንዲህ ብሎ መለሰ አባቴ ሆይ እውነት ነው እኔ በዚያ ነበርኩ በእመቤታችንም በቅድስት ድንግል ማርያም በዓል ቀን በፊት ደረቅ እንደሆነች አየኋት በእመቤታችንም በዓል ቀን ፀሐይ በወጣ ጊዜ ያቺ ዕንጨት ለመለመች አብባም መጠን የሌለው ብዙ ፍሬን አፈራች ሕዝቡም ሁሉ በግልጽ ያይዋታል።
❖ የበዓሉንም አከባበር ሥራ ከፈጸሙ በኋላ የቤተ ክርስቲያኑ ሹም ይወጣል ካህናቱም ሁሉ ወጥተው እነዚያን ፍሬዎች ሰብስበው ለቤተ ክርስቲያን መብራትና ለምግባቸው እስከ ዓመት ድረስ የሚበቃቸውን ያዘጋጃሉ ሕዝቡም ለበረከት እያሉ በየጥቂቱ ይወስዳሉ፤ ከዚህም በኋላ ትደርቃለች ፤ ሕዝቡም ሰምተው እጅግ አደነቁ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምንም አመሰገኑዋት።
❖ በዚህም አባት ዘመን ስሙ ቆሪል የሚባል አንድ ሰው ወደ ኢትዮጵያ አገር ሒዶ በሐሰት ራሱን ጳጳስ አደረገ ለግብጽ ንጉሥም ብዙ ገንዘብ ላከለትና እንዲህ አለው በአለሁበት በኢትዮጵያ ሀገር የጵጵስና ሹመት እንዲሾመኝና የሹመት ደብዳቤ እንዲልክልኝ ሊቀ ጳጳሳት አባ ገብረ ክርስቶስን እዘዘው እኔም እጅ መንሻህን በየዓመቱ ብዙ ወርቅ እልክልሃለሁ አለው።
❖ ንጉሡም ሊቀ ጳጳሳቱን ጠርቶ እንዲህ አለው ቆሪልን በአለበት በኢትዮጵያ አገር ጵጵስና ሹመውና የሹመቱን ደብዳቤ ላክለት ሊቀ ጳጳሳቱም ወደዚህ ሰውዬው ሳይቀርብ ይህ ሊሆን አይገባም ብሎ ለንጉሡ መለሰለት ንጉሡም እኔ እንዳዘዝኩህ አድርግ አለው፤ እርሱም ፈቃድህ ይሁን ብሎ ወጣ።
❖ እጅግም እያዘነ ተመለሰ ኤጲስቆጶሳቱን ሁሉንም ሰበሰባቸውና ንጉሥ ያዘዘውን ነገራቸው እነርሱም ሲሰሙ እጅግ አዘኑ ከሐሰተኛውም ከቆሪል ተንኰል ያድናቸው ዘንድ በአንድነት ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ ማለዱ።
❖ በዚያም ወራት ሐሰተኛው ቆሪል ተነሣ ብዙ ወርቅንም ይዞ ከኢትዮጵያ አገር ሸሽቶ ወደ ዳኅላክ ደረሰ የዳኅላክም ንጉሥ ይዞ ከኢትዮጵያ አገር የሰረቀውን ገንዘብ ሁሉ ወረሰው፤ እርሱንም አሥሮ ወደ ግብጽ ንጉሥ አስተላለፈው እርሱም የግብጽ ንጉሥ ስድስት ወር አሥሮ ከዚያ በኋላ ራሱን በሰይፍ አስቆረጠው በክፉ አሟሟትም ሞተ የሊቀ ጳጳሳት አባ ገብረ ክርስቶስን ጸሎት እግዚአብሔር ተቀብሏልና፤ ይህም አባት በወንጌላዊ ማርቆስ ወንበር ሠላሳ ዓመት ኖረ ክብር ይግባውና ጌታችንንም አገልግሎ በሰላም አረፈ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
አርኬ
✍️ሰላም ለገብረ ክርስቶስ በቅብዐ ክህነት ዘተኀትመ። አበ ድኩማን ይኩን ወዘመዓስባን ቃውመ። ከመ ርእየ ይቤ በቤተ ማርያም መድምመ። ይቡስ ዕፀ ዘይት እስከ ይፈሪ ጥዑመ። ለለበዓላ ሠሪዖ ይየይብስ ዳግመ።
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
አባ አሞንዮስ
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❖ በዚችም ቀን የሀገረ እስና ኤጲስቆጶስ አባ አሞንዮስ በምስክርነት አረፈ፤ አርያኖስም ወደ እስና ከተማ በደረሰ ጊዜ ብዙ ሰዎችን ከአባ አሞንዮስ ዘንድ ተሰብስበው የሃይማኖትን ትምህርት ሲማሩ አገኛቸውና ሁሉንም ይዞ ገደላቸው አባ አሞንዮስን ግን አሥሮ ወሰደው ለጣዖትም እንዲሰግድ ብዙ አግባባው።
❖ አባ አሞንዮስም ለፈጣሪህ እግዚአብሔር ትሰግድ ዘንድ እርሱንም ብቻውን ታመልክ ዘንድ ተጽፎአልና ከንቱ የሆነ የእንቆቅልሽ ጨዋታችሁን ብላሽ የሆነ ነገራችሁንም መስማት አልወድም የረከሱ አማልክቶቻችሁንም ማየት አልሻም ፈራሽ በሆነ የጣዖት ቤታችሁም መመላለስን የከረፋ የሸተተ ማዕጠንታችሁንና መሠዊያችሁን አልይዝም አለው።
❖ መኰንኑ አርያኖስም የዚህ አባት ልብ ፈጽሞ እንደማይበገር በአየ ጊዜ በሕይወት ሳለ በእሳት እንዲአቃጥሉት አዘዘ አባ አሞንዮስም እስከሚጸልይ ጥቂት ይጠብቁት ዘንድ ወታደሮቹን ለመናቸውና እጆቹና አግሮቹም እንደታሠሩ ቆመ የወንጌልንም ጸሎት ጸለየና ሀገሩን ሕዝቡን በክርስቶስም የሚታመኑትን ሁሉ ባረከ ዳግመኛም ስለ መኰንኑ አርያኖስ ጸለየ በሰማዕትነትም እንደሚሞት ስለርሱ ትንቢት ተናገረ ደግሞ ነፍሱን አሰናበተ።
❖ ጸሎቱንም ሲፈጽም ወደ እሳት ወረወሩትና ያማረ ተጋድሎውን ፈጸመ ከዚህም በኋላ እሳቱ በጠፋ ጊዜ ከእሳት ቃጠሎ የነካው ሳይኖር ንጹሕ ሁኖ ሥጋውን አገኙት በአማሩ ልብሶችም ገንዘው በእንጽና ከተማ በስተምዕራብ የንጉሥ በጥሊሞስ ልጅ ንግሥት አክላወባጥራ በአሠራችው ግምብ ውስጥ ቀበሩት ከሥጋውም ታላላቅ አስደናቂዎች ተአምራት ተገለጡ።
ለእግዚአበሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
አርኬ
✍️ሰላም ለአሞንዮስ ለአድያመ እንጽና ዘዖዳ። ምስለ ቃለ ምክር ሠናይ ማዕከለ ብዙኃን ውሉዳ። በጊዜ ፈጸመ ሰምዖ ለእቶነ እሳት በነዳ። ድኅረ አርመመ ማዕበላ ወድኅረ ኀድዐ ሞገዳ። በአምሳለ በረድ ተረክበ ሥጋሁ ፀዓዳ።
✍️ሰላም እብል አርያኖስሃ ቀሲሰ። ወለአርክሊስ እኁሁ ፈሪሀ እግዚአብሔር ዘለብሰ። ደቂቀ ጎርጎርዮስ እሉ ዘኢየአምሩ ደነሰ። አሐዱ በኂሩቱ ተሠይመ ጳጳሰ። ወካልኡኒ መኒኖ ገዳመ ፈለሰ።
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
ቅድስት ነሳሒት
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❖ በዚችም ቀን የውሲም ኤጲስቆጶስ አባ ያዕቆብ ስለርሷ እንደተናገረ የሮም ንጉሥ ልጅ ስሟ ነሳሒት የተባለ አረፈች፤ እንዲህም አለ በአንዲት ዕለት አምላክን በወለደች በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያለሁ የገዳሙን ደጅ ሰው ሲያንኳኳ ሰማሁ ተነሥቼም ወደ በሩ ሔድኩ ያረጀ ዓጽፍ የለበሰ ፊቱንም የተሸፋፈነ ሰው አየሁ ከወዴት መጣህ ወዴትስ ትሔዳለህ አልሁት።
❖ ከአባ መቃርዮስ ገዳም መጣሁ በዚች ሌሊት ከዚህ ገዳም አድሬ ቊርባንን መቀበል እሻለሁ አለኝ ያን ጊዜ ቀዳሚት ሰንበት ነበረች እኔም ፊትህን ካላሳየኸኝ አልከፍትልህም አልሁት እርሱም ፊቴን ማየት አትሻ ፊቴ በኃጢአቴ የጨለመ ነውና ፊቴንም ለሚያይ የከፋች ሥራዬ ትታየዋለች አለኝ ።
❖ በከለከልኩትም ጊዜ ወደ ዱር ሊመለስ ወደደ እኔም ተርቦ ወይም ተጠምቶ እንደሆነ ብዬ በልቤ አሰብኩ ስለዚህም ከፈትኩለትና ወደ ማደሪያዬ አስገባሁት መብልንም አመጣሁለት እርሱም ከነገ ከቊርባን በኋላ በቀር እኔ አልበላም በማለት እምቢ አለኝ።
❖ ከዚህም በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባና በጨለማ ቦታ ቆመ ከዚያ ያሉ መነኰሳትም እስከ አደነቁ ድረስ የዳዊትን መዝሙር ሲያነብ ድምፁን እንደ መላእክት ድምፅ ሁኖ ሰማሁት በነጋም ጊዜ በእግሮቹ ላይ ተቀመጠ ምንም ምን ማንበብ አልሻም፤ እኛ ግን ይጸልይልን ዘንድ ልንለምነው ቀረብን እርሱም አባቶቼ ሆይ በበደሌ ብዛት ፊቴን ያጨለምኩ ስሆን ስለ እናንተ እንዴት እጸልያለሁ አለን።
ቁ❖ ርባንንም በምናሳርግ ጊዜ በእግሩ ቆሞ የጳውሎስን መልእክት የሐዋርያትንም መልእክትና የሐዋርያትን ሥራ ማንበብ ጀመረ በአራተኛም ጊዜ በመሠዊያው ፊት ቁሞ የዮሐንስን ወንጌል ማንበብ ጀመረ በፊቱም ላይ የተከናነበውን ልብስ አስወገደ ከፊቱም ብርሃን ገናናነት የተነሣ ሊያዩት አልተቻላቸውም።
❖ እኛ ቊርባንን ከተቀበልን በኋላ ቆረበ ከነገሥታት ልጆች ወገንም እንደሆነ ተጠራጠርን መብልንም በአቀረብንለት ጊዜ ከእኛ አልተቀበለም ነገር ግን ሰይጣን በእነርሱ ከሚያስትባቸው ሴቶችን ከማየት እንርቅ ዘንድ መከረን።
❖ ሮማዊ የሆነ አንድ ደግ ጻድቅ አረጋዊ መነኵሴ ነበር እርሱም አባቴ ያዕቆብ ሆይ ይቺ ከነገሥታት ልጆች ውስጥ የሆነች ሴት ናት ስለዚህም እንዳትታወቅ ፊቷን ከሰው ትሠውራለች አለኝ።
❖ ከዚህም በኋላ ሥራዋን ከእኔ ሳትሠውር እንድትነግረኝ በክርስቶስ ስም አምላት ዘንድ ወደርሷ ሔድሁ። ግን አላገኘኋትም ከአምስት ወርም በኋላ ከንጉሥ አባቷ ዘንድ የተላኩ ብዙ ሰዎች እርሷን እየፈለጉ መጡ። እነርሱም ቤተሰቦቿ ከተኙ በኋላ በሌሊት እንደወጣች እነርሱም እርሷን ሲፈልጉ ዐሥራ ሁለት ዓመት እንደሆናቸው ሥራዋን ነገሩን። ከዚህም በኋላ መጻተኞች ሰዎች በዚች ቀን እንዳረፈች ነገሩን።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋራ ይኑር ለዘላለሙ አሜን።
አርኬ
✍️ ሰላም ለወለተ ንጉሥ ነሳሒት ስማ። ከዊና ግኅሥተ እምነ አቡሃ ወእማ። እንበለ ታጠይቅ ገጻ በመካነ ጽልመት ቀዊማ። እንዘ ታደምፅ መዝሙረ ከመ ድምፀ መልአክ ዘራማ። ገድላ ፈጸመት ወሠለጠት ፃማ።
በዚችም ዕለት መድኃኒታችን በዓለም ውስጥ ብርሃንን ገለጠ። እርሱ የታሠሩትን ይፈታ ዘንድ በበደል ምክንያት የመጣውን ጨለማ ያርቅ ዘንድ ወደ ዓለም የመጣ ብርሃን እንደመሆኑ ለእርሱም ክብር ምስጋና ይሁን ለዘላለሙ አሜን።
አርኬ
✍️ ሰላም ለብርሃን በብሔረ ጽልመት ዘጸደለ። ሙቁሐነ ይፍታሕ ወይኪድ ሲኦለ። እግዚአብሔር አቡሁ እንዘ ይጠዓጥዕ ቃለ። አመ ቀዳሚ ኲነኔሁ በከመ ይቤ ብሂለ። ብርሃነ መለኮት መጽአ ወለብሰ አባለ።
✍️ሰላም ለብርሃን እምቅድመ ዓለም ዘተዓውቀ። ዘውእቱ ቃል ሕያው አመ በሥጋ ሠረቀ። ሙሴ በደብር እስከ ደንገፀ ወወድቀ። ወኤልያስኒ ፈሪሆ ዘርኅቀ።
📌 ታኅሣሥ 14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ዕለተ ብርሃን
2.ቅዱስ መርምሕናምና እህቱ ሣራ
3."40" ሰማዕታት (የቅዱሱ ተከታዮች)
4."170,000" ሰማዕታት (የቅዱሱ ሠራዊት)
5.ቅድስት ነሣሒት ቡርክት
6.ቅዱስ ስምዖን ሰማዕት
7.ቅዱስ አሞንዮስ ሰማዕት
8.አባ ገብረ ክርቶስ ሊቀ ዻዻሳት
📌 ወርኀዊ በዓላት
1.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)
2.አባ ስምዖን ገዳማዊ
3.አባ ዮሐንስ ጻድቅ
4.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ (ከ72ቱ አርድእት)
5.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ
6.ቅዱስ ሙሴ መርዓዊ
✍️"ብርሃን ወደ ዓለም መጥቷልና፤ ሰውም ሥራው ክፉ ስለ ሆነ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን መርጧልና፤ ሥራው ክፉ የሆነ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ክፉም ስለ ሆነ ሥራው እንዳይገለጥበት ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚሠራ ግን ሥራው ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል፤ ስለ እግዚአብሔር ብሎ ይሠራልና"
📖ዮሐ 3፥19
ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ። እምእለ ተጸምዱከ ዘልፈ። ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ። እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውኩፈ። እምእለ አብኡ ብዑላን ዘተርፈ።
ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን። ሰማዕት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን። ደናግል ዓዲ ወመነኰሳት ኄራን። ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን። እስከ አረጋዊ ልሒቅ ወንኡስ ሕፃን።
ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ። ለዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ። ወለዘሰምዐ ቃሎ በዕዝነ መንፈስ። በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኵሉ እምባእስ። ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ።
ጌታ ሆይ ከብልጽግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።
እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።
ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን።
✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝
✍"ልብህን በእርጋታ አኑረው፤ የሁሉም መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ለመሆን በጣም ትጋ ለከንቱ ንግግር ዘገምተኛና ሰነፍ ሁን፤ ነገር ግን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል በማወቅ በመስማት ድኅነትን የሚሰጡ ናቸውና ብልህ ሁን"
📚ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ይቆየን
───────────
Channel
🧲 https://telegram.me/Tewahedo12
FB Like Page (የፌስቡክ ፔጅ)
🧲 http://facebook.com/Tewahedo12
YouTube Subscribe (ሰብስክራይብ)
🧲 https://www.youtube.com/channel/UCvYxUdv1D-5juH_P6iE7XXw
───────────