ስንክሳር ዘወርኀ ታኅሣሥ ፳፯

ስንክሳር ዘወርኀ ታኅሣሥ ፳፯

@YeBiruk ዲያቆን ቡሩክ ይርጋ ዘውብ

✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

          አሜን

✍"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         

📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

         ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


ስንክሳር ዘወርኀ ታኅሣሥ ፳፯


አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ታኅሣሥ ሃያ ሰባት በዚች ቀን የከበረ ኤጲስቆጶስ አባ አብሳዴ በሰማዕትነት ሞተ።


   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

          አባ አብሳዴ

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ ያን ጊዜ ታላላቆች የሆኑ የላይኛው ግብጽ ኤጲስቆጶሳት አባ አብሳዲና አባ አላኒቆስ የክብር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሆነች በቀናች ሃይማኖት ሕዝቡን እንደሚያጸኑአቸው የአማልክትንም አምልኮ እንደሚሽሩ ዜናቸውን ዲዮቅልጥያኖስ በሰማ ጊዜ መልእክተኞችን ልኮ ወደርሱ አስመጥቶ ታላቅ ሥቃይን አሠቃያቸው።

❖ የከበረ አባ አብሳዲ ግን አንዲት ቀን እንዲታገሡት መልእክተኞችን ለመናቸውና የቊርባን መሥዋዕትን አዘጋጅቶ ቅዳሴ ቀድሶ ለሕዝቡ ሥጋውንና ደሙን አቀበላቸው።

❖ በቀናች ሃይማኖትም እንዲጸኑ አስተማራቸው ከዚህም በኋላ በሰላምታ ተሰናብቷቸው ከእርሳቸው ዘንድ ወጣ ሰውነቱንም በእግዚአብሔር ላይ ጥሎ ከመልእክተኞች ጋር ሔደ ወደ እንዴናው ገዥ ወደ አርያኖስ ወሰዱት።

❖ መኰንኑም የአባ አብሳዲን ገጽ በአየ ጊዜ ከአርአያውና ከግርማው የተነሣ አደነቀ ራራለትም እንዲህም አለው አንተ የከበርክና የምታስፈራ ሰው ለነፍስህ እዘን የንጉሥንም ቃል ስማ።

❖ አባ አብሳዲም እንዲህ ብሎ መለሰ እኔ የንጉሥን ቃል ሰምቼ በዚህ በኃላፊው ዓለም ሕይወት መንግሥተ ሰማያትን አልለውጥም በመካከላቸውም ብዙ የነገር ምልልስ ሆነ ከበጎ ምክሩ ባለተመለሰ ጊዜ በመንኰራኲር ያሠቃዩትና ከእሳት ማንደጃ ውስጥም ይጨምሩት ዘንድ መኰንኑ አዘዘ ይህን ሁሉ ታገሠ እግዚአብሔርም ያለ ጉዳት በጤና አስነሣው።

❖ ከዚህም በኋላ ራሱን ይቆርጡት ዘንድ አዘዘ አባ አብሳዲም ሰምቶ ፈጽሞ ደስ አለው ልብሰ ተክህኖ ለብሶ እጆቹንም ዘርግቶ አንገቱን ለሰይፍ ሰጠ የከበረች ራሱንም ቆረጡት የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበለ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


     አርኬ

✍️ሰላም ለክሙ ኤጲስቆጶሳት ዘግብጽ። አባ አብሳዲ ወአላኒቆስ አብያጽ። እምታምልኩ ዕብነ ወእምትስግዱ ለዕፅ። ዘአጥባዕክሙ ረዊፀ እንበለ ተዓቅፎ ወዳኅጽ። መንገለ መጥባሕት በሊሕ ወእሳት ብቁጽ።


በዚችም ዕለት የአባ በግዑና የአባ ፊልጶስ የሰማዕታት ፍጻሜ የሆነ የኖላዊ መታሰቢያቸው ነው። የመድኃኒታችንም የስቅለቱ መታሰቢያ ነው።



✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

       አባ በግዑ

✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ አባ በግዑ በመጀመሪያ ሽፍታ የነበረ ሲሆን በመንገድ ላይ ንብረት የያዘን ሰው ማንንም የማያሳልፍ ቀማኛ ሰው ነበር፤ ከኃይለኛነቱ የተነሳ ሕዝቡም ሁሉ ይፈራው ነበር፤ በእጁ ሰይፍና ጦር ይዞ ሊዘርፍ ወደ ወደደው ሀገር ይገባል፡፡

❖ እየዘረፈ በሚያገኘው ገንዘብም ራሱን በተለያዩ ምግቦችና መጠጦች ያስደስት ነበር፤ ባማሩ ልብሶችም ይዋብ ነበር፤ ገንዘቡ የተወሰደበት ሰውም እርሱ እንደወሰደበት ባወቀ ጊዜ ዳግመኛ መጥቶ የተረፈውን ቀምቶ እንዳይወስድበት ምንም አይከሰውም ነበር፤ በጉልምስናው ኃይለኛና ብርቱ ስለነበር ወደ እርሱ ማንም አይቀርብ ነበር፡፡

❖ በእንደዚህ ያለ የውንብድና ሥጋ ብዙ ዓመታት ከኖረ በኋላ አባ በግዑ በስም ክርስቲያን ነበረና ከዕለታት በአንደኛው ቀን መንፈስ አነሳስቶት ወደ ቤተክርስቲያን ሄደ፤ ካህኑም ባየው ጊዜ ከመንገድ ገለል አደረገውና

✍‹‹የሕይወት ዘመንህን ሁሉ በከንቱ አሳለፍክ ዛሬ ስማ ልንገርህ፣ በዘመንህ ፍጻሜ እግዚአብሔር ይጎበኝሃል፣ በመንፈስ ቅዱስም ያድርብሃል፣ ፍጹም መነኩሴ ትሆናለህ፣ በብዙ መከራና ተጋድሎ ትኖራለህ በዚያም የነፍስህ መዳኛ ይሆናል፣ እግዚአብሔርንም ደስ ታሰኘዋለህ›› አለው፡፡

❖ ከዚህም የበዛውን ብዙ ነገር ነገረው፤ ከዚህም በኋላ ወደ ቤተክርስቲያን ገብቶ ቁርባን ተቀበለ፤ ወደ ቤቱም ከተመለሰ በኋላ ካህኑ የነገሩትን እያሰበ

✍‹‹እስከመቼ በስንፍናዬ እኖራለሁ እስከመቼስ የነፍሴን መዳኛ ሳላስብ እኖራለሁ …›› እያለ አሰበ፡፡

❖ ከዚህም በኋላ ከዘመዶቹ ተለይቶ ከሀገሩ ወጥቶ ሄደና ወደ ባሕር ዳርቻ ደርሶ የቅዱስ እስጢፋኖስን ቤተክርስቲያን እጅ ነሣ፤ ከመነኮሳትም ማኅበር ገብቶ እነርሱን ማገልገል ጀመረ፡፡

❖ ዓቢይ ጾም ሲመጣም ከሰኞ እስከ ቀዳሚት ሰንበት ምንም ሳይቀምስ የሚጾም ሆነ፤ ውኃንም ሳይጠጣ ኖረ ማንም ሰው ሳያውቅብ ለ5 ወር ምንም ውኃ ሳይጠጣ ተቀመጠ፡፡

❖ ከ5 ወር በኋላም የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ወደ አባ በግዑ መጣና ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ሰላም ለአንተ ይሁን በምን ትታወካለህ ምንስ ያሳዝንሃል ››አለው፤ አባ በግዑም ‹‹ጌታዬ ከውኃ ጥም የተነሣ በጣም ስለተጨነቅሁ ነው›› አለው፤ መልአኩም ነጥቆ ወደ ገነት ወሰደውና ከገነት ቅጠል አንሥቶ አቀመሰው፤ ወዲያም የአባ በግዑ ሰውነት ታደሰች፡፡

❖ ከዚህም በኋላ ‹‹ውኃ ሳልጠጣ ተጋድሎዬን እፈጽም ይሆን›› የሚለው የኅሊና መታወክ ከእርሱ ጠፋለት፤ ከዕለታትም በአንደኛው ቀን አባ በግዑ ለሚወደው ለአንድ ወዳጁ ለማንም እንዳይናገር በእግዚአብሔር ስም ካስማለው በኋላ ለ5 ወር ምንም ውኃ እንዳልጠጣ ምሥጢሩን ነገረው፤ ያ ወዳጁም ይህን ሲሰማ ደንግጦ አለቀሰ፡፡

❖ አባ በግዑም አብሮት አለቀሰ፤ ወዳጁም ‹‹እስከ ዛሬ ከውኃ የተከለከለ በማን ዘንድ ሰማህ አሁንም ቅዱሳን መነኮሳትና አበ ምኔቱ አያምኑህም፤ ይህን ምሥጢር ዛሬ ብሸሽግ በመጨረሻ ይገለጣል፤ ሕዝቡ ነገሥታቱና መኳንንቱም ይህን ነገር ይሰማሉ ነገር ግን አያምኑም፤ አሁንም የምነግርህን ስማኝና ትኅርምቱን ትተህ ውኃ ጠጣ›› አለው፡፡

❖ የእግዚአብሔር ሰው አባ በግዑም ‹‹የነገርከኝ ሁሉ እውነት ነው ሐሰት የለውም ነገር ግን እኔ ከዚህ በኋላ እስክሞት ድረስ ዳግመኛ ውኃ እንዳልጠጣ ስለ እግዚአብሔር ትቻለሁ፤ ሰዎች ባያምኑ እኔ ምን ገዶኝ ነገር ግን በዚህ ገድል እግዚአብሔር ረዳት ይሆነኝ ዘንድ ጸልይልኝ›› አለው፡፡

❖ ‹‹አበ ምኔቱን ጥራልኝ›› አለውና ጠራለት፤ አባ በግዑም አበ ምኔቱ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ሲመጣ በፊቱ ሰገደለትና ‹‹አባቴ ሆይ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እፈጽም ዘንደ በላዬ ላይ ጸልይልኝ›› አለው፤ ‹‹ከዛሬ ጀምሮ ከበዓቴ አልወጣም ሰውም ወደኔ አይገባም›› አለው፡፡

❖ አቡነ ኢየሱስ ሞዐም በላዩ ከጸለየለት በኋላ ‹‹ለእኔም ጸልይልኝ›› አለው፤ አባ በግዑም በቅዱስ ሚካኤል በዓል ቀን በአባ ኢየሱስ ሞዐ እጅ ቁርባንን ከተቀበለ በኋላ እጆቹንና እግሮቹን በብረት ችንካር ታስሮ ብቻውን ዘግቶ በጽኑ የተጋድሎ ሕይወት ኖረ፤ በዓቱንም ዙሪያውን መውጫ መግቢያ እንዳይኖረው መረገው፤ ለምግብ የሚሆነውን የዛፍ ፍሬና የሜዳ ቅጠል ማስገቢያ የሚሆን ትንሽ ቀዳዳን አበጃና ያ ወዳጁ ያስገባለታል፡፡

❖ መቆምም አይችልም ነበርና መነኮሳቶቹ ለቁርባን በቃሬዛ አድርገው ወደ ቤተክርስቲያን ይወስዱት ነበር፤ የእግዚአብሔር ሰው አባ በግዑ በእንደዚህ ዓይነቱ ለመስማት በሚከብድ እጅ የበዛ ጽኑ ተጋድሎ ካደረገ ከብዙ ድካም በኋላ በዚህች ዕለት ታህሳስ 27 ቀን ዐረፈ፡፡

❖ ነቢይ ኢሳይያስም የሜዳ ጎመን እየቆረጠ ከእርሱም እየተመገበ ውኃም እየጠጣ በተራራ እየጾመ ኖረ፤ እግዚአብሔር ስሙን ‹የበረሃ ኮከብ› ብሎ የጠራው የመነኰሳት በኩር የሆነ አባ እንጦንስና አባ መቃርስም በደረቅ ኅብስትና በውኃ ብቻ ሲጋደሉ ኖሩ፤ እኚህ ምድራዊያን ሲሆኑ ሰማያውያን ሆኑ፡፡

❖ ነቢይ ኤልያስም በኅብስትና በውኃ ብቻ በምድረ በዳ ሲጋደል ኖረ፤ ይህ የእግዚአብሔር ሰው አባ በግዑ ግን ሰባት ዓመት ሙሉ ውኃ ሳይቀምስ ኖረ፤ ከመነነ በኋላ እስከሞተበት ዕለት ድረስ እህል የሚባል አልቀመሰም፤ እርሱ ግን ራሱን በእግዚአብሔር ፊት ዝቅ ያደርግና በትህትናም ሆኖ ስለ ኃጢአቱ ሁልጊዜ ያለቅስ ነበር፡፡

❖ ይህም የእግዚአብሔር ሰው አባ በግዑ ይህን ሁሉ የተጋደለ በራሱ ኃይል አይደለም፤ በእግዚአብሔር ኃይል ነው እንጂ፤ አንተም ወንድሜ ሆይ ራስህን ዕወቅ፤ ምንም ተጋድሎን ብታደርግ ጾምኩ፣ ተራብኩ፣ ስለ እግዚአብሔርም ብዬ ራሴን አደከምኩ፣ እግዚአብሔርንም ስላገለገልኩ በሥራዬም እድናለሁ አትበል፤ መጨረሻህን አታውቅም አንተ ግን ስለ እግዚአብሔር ብለህ ራስህን ኃጥእ አድርግ ያን ጊዜ እግዚአብሔር ያጸድቅሃልና፤ ወዳጄ ሆይ በእግዚአብሔር ዘንድ እንድትመሰገን ራስህን አታመስግን፤ ሌሎችም ያመሰግኑህ ዘንድ አትውደድ፤ ክብር ታገኝ ዘንድ ትሕትናን ገንዘብ አድርግ››

የእግዚአብሔር ሰው የአባ በግዑ ረድኤት በረከታቸው ይደርብን፤ በጸሎት ይማረን


📌 ታኅሣሥ 27 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅዱስ አብሳዲ ሰማዕት

2.አባ አላኒቆስ ሰማዕት

3.አባ በግዑ ጻድቅ

4.አባ ፊልዾስ


📌 ወርኀዊ በዓላት

1.ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ

2.አቡነ መብዓ ጽዮን ጻድቅ

3.ቅዱስ መቃርስ (የመነኮሳት ሁሉ አለቃ)

4.ቅዱስ ያዕቆብ ዘግሙድ 

5.ቅዱስ ገላውዴዎስ ሰማዕት (ንጉሠ ኢትዮዽያ)

6.ቅዱስ ቢፋሞን ጻድቅና ሰማዕት

7.ማር ቅዱስ ፊቅጦር ሰማዕት


✍️"መቶ በግ ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ ዘጠና ዘጠኙን በበርሃ ትቶ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ሊፈልገው የማይሔድ ከእናንተ ማን ነው? ባገኘውም ጊዜ ደስ ብሎት በጫንቃው ይሸከመዋል፤ ወደ ቤትም በመጣ ጊዜ ወዳጆቹንና ጐረቤቶቹን በአንድነት ጠርቶ 'የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ' ይላቸዋል፤ እላችሁአለሁ እንዲሁ ንስሃ ከማያስፈልጋቸው ከዘጠና ዘጠኝ ጻድቃን ይልቅ ንስሃ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በሰማይ ደስታ ይሆናል"

📖ሉቃ 15፥3-7


ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ። እምእለ ተጸምዱከ ዘልፈ። ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ። እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውኩፈ። እምእለ አብኡ ብዑላን ዘተርፈ።

ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን። ሰማዕት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን። ደናግል ዓዲ ወመነኰሳት ኄራን። ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን። እስከ አረጋዊ ልሒቅ ወንኡስ ሕፃን።

ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ። ለዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ። ወለዘሰምዐ ቃሎ በዕዝነ መንፈስ። በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኵሉ እምባእስ። ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ።


ጌታ ሆይ ከብልጽግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።

እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።

ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን።


✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝

✍"ልብህን በእርጋታ አኑረው፤ የሁሉም መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ለመሆን በጣም ትጋ ለከንቱ ንግግር ዘገምተኛና ሰነፍ ሁን፤ ነገር ግን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል በማወቅ በመስማት ድኅነትን የሚሰጡ ናቸውና ብልህ ሁን"

📚ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ

             ወስብሐት ለእግዚአብሔር

                             ይቆየን 

───────────

                   Channel

 🧲 https://telegram.me/Tewahedo12


       FB Like Page (የፌስቡክ ፔጅ)

🧲 http://facebook.com/Tewahedo12  


       YouTube Subscribe (ሰብስክራይብ)

🧲 https://www.youtube.com/channel/UCvYxUdv1D-5juH_P6iE7XXw

 ───────────




Report Page