ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም ፳፰
@YeBiruk ዲያቆን ቡሩክ ይርጋ ዘውብ✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
አሜን
✍"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
ቀናችንን በጸሎት እንጀምር
ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም ፳፰
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም ሃያ ስምንት በዚች ቀን ቅዱስ አባዲርና እኅቱ ኢራኢ በሰማዕትነት አረፉ።
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
ቅዱስ አባዲርና እኅቱ ኢራኢ
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❖ ይህም ቅዱስ ለአንጾኪያ መንግሥት የሠራዊት አለቃ ለሆነ ለፋሲለደስ የእኅቱ ልጅ ነው እርሱም በአባቱ መንግሥት የሠራዊት አለቃ ነበር በውስጡም የሚጸልይበት እልፍኝ አለው፤ ከሌሊቱም እኩሌታ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለትና እንዲህ አለው የሰማዕትነት አክሊልን ትቀበል ዘንድ እኅትህ ኢራኢን ይዘህ ወደ ግብጽ አገር ሒድ፤ ስለ ሥጋችሁም እንዲአስብ ሳሙኤል የሚባለውን አንድ ሰው እኔ አዛለሁ ከዚህም በኋላ ሰላምታ ሰጥቶት በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ።
❖ እንዲሁ ለእኅቱ ኢራኢ ተገልጦላት እንዲህ አላት የወንድምሽን ቃሉን ስሚው ትእዛዙንም አትተላለፊ ከእንቅልፏም ነቅታ እጅግ ተንቀጠቀጠች ወደ ወንድሟም ሒዳ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተገለጠላትና እንደ ተናገራት አስረዳችው። እጅግም ደስ አላቸው ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስም ስለ ስሙ ወደ ግብጽ አገር ሒደው ደማቸውን ያፈሱ ዘንድ በዚህ ምክር ተስማሙ።
❖ የቅዱስ አባዲር እናትም ይህን ነገር በአወቀች ጊዜ ልብሷን ቀዳ አለቀሰች ከባሮቿም ጋር ወደ ቅዱስ አባዲር መጥታ በሰማዕትነት እንዳይሞት ታምለው ጀመር እርሱም ስለ ሰማዕትነት ነገር ዲዮቅልጥያኖስን እንዳይናገረው ማለላት በዚያንም ጊዜ ከልቅሶዋ ታግሣ ጸጥ አለች።
❖ ወደ ሌላ ቦታ ሒዶ በሰማዕትነት እንደሚሞት ግን አላሰበችም፤ ቅዱስ አባዲርም በየሌሊቱ ሁሉ እንዲህ የሚያደርግ ሆነ ልብሱንም ለውጦ ከቤቱ ይወጣል በወህኒ ቤት ላሉ እሥረኞችም ውኃ በመቅዳት ያጥባቸዋል እስከሚነጋም እንዲህ ያደርጋል በር የሚጠብቀውንም እንዲህ ብሎ አዘዘው ይህን ለማንም አትናገር ይህንንም ሥራ ብትገልጥ እኔ ራስህን በሰይፍ እቆርጣለሁ።
❖ ከዚህም በኋላ ቅዱስ አባዲር ተነሣ እኅቱን ኢራኢንም ይዞ ወደ ግብጽ አገር ሒዶ እስክንድርያ ደረሰ፤ ከወታደሮችም ያወቁት አሉ አንተ የሠራዊት አለቃ ጌታችን አባዲር አይደለህም እንዴ አሉት፤ እርሱም ፈገግ ብሎ ብዙዎች እንዲሁ ይሉኛል እኔ ግን እመስለው ይሆናል እንጂ እርሱን አይደለሁም አላቸው ከዚያም ወደ ሌላ ቦታ ሔደ፤ በዚያም እንደቀድሞው እርሱ አባዲር እንደ ሆነ ተናገሩት እርሱም አይደለሁም ይላቸው ነበር።
❖ ከዚህም በኋላ ከእስክንድርያ ከተማ ወጥቶ ወደ ታላቋ የምስር ከተማ ሔደ በዚያም ከአባ አበከረዙን ጋር ተገናኝተው ከእርሱ ቡራኬ ተቀበሉ፤ ከዚያም ወደ እስሙናይን ደርሰው ከዲያቆን ሳሙኤል ጋር ተገናኙ በማግሥቱም ወደ እንጽና ከተማ ሔዱ በመኰንን አርያኖስም ፊት ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ታመኑ።
❖"መኰንኑም ጽኑዕ ሥቃይን ሊአሠቃያቸው ጀመረ ቅዱስ አባዲርም በሥቃይ ውስጥ ያጸናቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ለመነ ያን ጊዜ ጌታችን የእርሱን ነፍስና የእኅቱን ነፍስ ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ወስዶ ሰማዕታት የሚኖሩበትን የብርሃን ቤቶችን አሳያቸውና ከዚህም በኋላ ወደ ሥጋቸው መለሳቸው።
❖ መኰንኑም ማሠቃየት በሰለቸ ጊዜ ራሳቸውን በሰይፍ እንዲቆርጡ አዘዘ፤ ራሳቸውንም ከሚቆርጧቸው በፊት መኰንኑ አርያኖስ ቅዱስ አባዲርን እንዲህ አለው አንተ ማን እንደሆንክ ስምህም ማን እንደሆነ አንተም ከወዴት እንደሆንክ ትነግረኝ ዘንድ በፈጣሪህ አምልሃለሁ አለው።
❖ ቅዱስ አባዲርም በነገርኩህ ጊዜ ራሳችንን እንዲቆርጡ ያዘዝከውን ትእዛዝ እንዳትለውጥ አንተም ማልልኝ አለው መኰንኑም ማለለት ያን ጊዜም የሠራዊት አለቃ እኔ አባዲር ነኝ አለው መኰንኑ አርያኖስም እንዲህ ብሎ ጮኸ ወዮልኝ ጌታዬ ሆይ በአንተ ፈንታ እኔ ልሞት ይገባኛል ይህን ሁሉ ጽኑ ሥቃይ እስከ አሠቃየሁህ ድረስ አንተ ጌታዬ እንደሆንክ እንዴት አላስረዳኸኝም ቅዱስ አባዲርም አንተም እንደኔ በሰማዕትነት ትሞት ዘንድ አለህና አትዘን አሁንም ምስክርነታችንን በፍጥነት ፈጽም ብሎ መለሰለት።
❖ በዚያንም ጊዜ ራሳቸውን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አርያኖስ አዘዘና እርሱንና እኅቱ ኢራኢን ቆረጧቸው፤ ያማሩ ልብሶችንም ዘርግተው ገነዙአቸው ዲያቆን ሳሙኤልም የመከራው ወራት እስከሚያልፍ ወደ ቤቱ ወስዶ አኖራቸው ከዚያም በኋላ ያማረች ቤተ ክርስቲያን ታነፀችላቸውና ሥጋቸውን በውስጧ አኖሩ ከእርሳቸውም ታላላቅ ድንቆች ተአምራት ተገለጡ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሰማዕታት ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
አርኬ
✍️ ሰላም ለከ አባዲር መዋዒ። ኃይለ ዐር ወምክረ ጸላኢ። እምወይነ ኪዳንከ አባ ዘያስተፌሥሕ ልበ ሰማዒ። ትጸግወኒ ምጽዋተ በእደ አኅትከ ኢራኢ። ባዕለ ጸጋ ንዴትየ ርኢ። ሰላም እብል ለዘኅበርክሙ ፈቃደ። ማኅበረ አባዲር ለሰይፍ ከመ ትመጥዉ ክሣዶ። ዘሕማም ወገድል ኀበ ትሔልዉ ዐዐደ። ኦ ጽጌያት ስነክሙ ጸዓድዒዶ። እግዚአብሔር ይርአይ እምሰማይ ወረደ።
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
ቅድስት ሶስና
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❖ በዚችም ቀን የኬልቅዩስ ልጅ ቅድስት ሶስና አረፈች፤ ዜናዋም እንዲህ ነው ይችን ቅድስት ሶስናን በባቢሎን የሚኖር ስሙ ኢዮአቄም የሚባል አንድ ሰው አገባት እርሷ እጅግ መልከ መልካም የሆነች ፈጣሪ እግዚአብሔርንም የምትፈራው ነበረች።
❖ እናትና አባቷም ደጋግ ነበሩ ለልጃቸውም ሙሴ የጻፋትን ኦሪት አስተምረዋት ነበር፤ ባሏ ኢዮአቄም ግን እጅግ ባለጸጋ ነበር በቤቱም አጠገብ የተክል ቦታ ነበረው ከሁሉ እርሱ ይከብር ነበርና አይሁድ ወደርሱ ይመጡ ነበር።
❖ ኃጢአት ከባቢሎን አገር ሕዝቡን እንጠብቃቸዋለን ከሚሉ ከግብዞች ወገኖች እንደ ወጣች እግዚአብሔር ስለነርሱ የተናገረባቸው ግብዞች የሆኑ ሁለት መምህራን በዚያ ወራት ታዩ።
❖ እነርሱም በኢዮአቄም ቤት የለመዱ የሚአገለግሉም ናቸው፤ የሚፈራረዱም ሁሉ ወደ እርሱ ይመጡ ነበር፤ ሕዝቡ ሁሉ ወደ ቤታቸው ከገቡ በኋላ ቀትር በሆነ ጊዜ ሶስና ወደ ባሏተክል ቦታ ገብታ በዚያ ትመላለስ ነበር።
❖ ገብታ በተመላለሰች ጊዜ እነዚያ መምህራን ሁልጊዜ ያዩዋት ነበርና ተመኙዋት፤ ልቡናቸውንም ለወጡ ሰማይንም እንዳያዩ ዐይኖቻቸውን ግልብጥብጥ አደረጉ ሰማያዊ እግዚአብሔርን እንዳያስቡ እውነትኛ ሕግን አላሰቡም።
❖ ሁለቱም ሁሉ ወደዷት ፈቃዳቸውን መናገር አፍረዋልና እርስበርሳቸው በልቡናቸው ያለውን ነገር አልተነጋገሩም ይደርሱባትም ዘንድ ይወዱ ነበር ያገኟትም ዘንድ ሁልጊዜ ይጠብቋታል።
❖ አንዱም አንዱን የምሳ ጊዜ ነውና ወደ ቤታችን እንግባ አለው እየራሳቸውም ተለያይተው ሔዱ፤ ተመልሰውም በጎዳና አንድነት ተገናኙ ሁለቱም ተያዩ ያን ጊዜም ፍላጎታቸውን ተነጋገሩ ብቻ ለብቻ እሷን የሚያገኙበትን ጊዜ ተቃጠሩ::
❖ ከዚህም በኋላ በቀን ሲጠብቋት ሶስና ሁል ጊዜም ትገባ እንደነበር ከሁለቱ ደንገጡሮቿ ጋር ገባች አልቧታልና በተክል ውስጥ ትታጠብ ዘንድ ወደደች፤ ተሠውረው ከሚጠብቋት ከሁለቱ ረበናት በቀር በዚያ ማንም ማን አልነበረም::
❖ ዘይትና ሽቱ አምጥተው ያጥቧት ዘንድ ልትታጠብ የተክሉንም ደጅ ይዘጉ ዘንድ ደንገጡሮቿን አዘዘቻቸው፤ እነርሱም እንዳዘዘቻቸው አደረጉ የተክሉን ደጃፍ ዘግተው ያዘዘቻቸውን ያመጡ ዘንድ በስርጥ ጐዳና ወጡ የተሠወሩ እነዚያን ረበናት ግን አላዩአቸውም።
❖ እነዚያ ደንገጡሮች ከወጡ በኋላ ሁለቱ ረበናት ተነሥተው ወደርሷ ሮጡ እነሆ የተክሉ ደጃፍ ተዘግቷል የሚያየን የለምና እንደርስብሽ ዘንድ እንወዳለንና እሺ በይን አሏት፤ ይህ ካልሆነ ካንቺ ጋር ሰውን እንዳገኘን ተናግረን እናጣላሻለን ስለዚህም ደንገጡሮችሽን ከአንቺ አሰወጥተሽ ሰደድሽ::
❖ ሶስናም አለቀሰች በሁሉም ፈጽሞ ተጨነቅሁ ባደርገው እሞታለሁ ባላደርገውም አልድንም ከእጃቸው ማምለጥንም አልችልም በእግዚአብሔር ፊት ከምበድል ኃጢአት ሳልሠራ በእጃችሁ መውደቅ ይሻለኛል አለች::
❖ ሶስና ቃሏን አሰምታ ጮኸች፤ እነዚያም ረበናት ከእርሷ ጋር ጮኹ አንዱ ሩጦ ሒዶ የተክሉን ደጃፍ ከፈተ በቤቷም ያሉ በተክል መካከል ጩኸትን ሰምተው ወጡ ምን እንደሆነ ያዩ ዘንድ በሥርጥ ጐዳናም ሮጡ።
❖ እነዚህ ሁለቱ ረበናት ይህንን ነገር በተናገሩ ጊዜ በሶስና ላይ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ ተሰምቶ አያውቅም ነበርና ዘመዶቿና አሽከሮቿ እጅግ አፈሩ፤ በማግሥቱም ሕዝቡ በባሏ በኢዮአቄም ዘንድ ተሰበሰቡ እነዚያም ሁለቱ ረበናት ሶስናን ያስገድሏት ዘንድ ከዓመፀኛ ልባቸው ጋራ መጡ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ያመጡአት ዘንድ ወደ ኢዮአቄም ሚስት ወደ ሶስና ላኩ ብለው አዘዙ ወደርሷም ላኩባት፤ እርሷም ከእናት ከአባቷ ከወገኖቿ ከዘመዶቿ ከሚያውቋትም ሁሉ ጋር መጣች።
❖ ሶስና ግን እጅግ ደመ ግቡ ነበረች መልኳም ያማረ ነው፤ ዓመፀኞች የሆኑ እነዚያ ሁለቱ ረበናት መልኳን ለመጥገብ ይገልጧት ዘንድ አዘዙና ገለጧት፤ አባቷ፣ እናቷ፣ ቤተሰቦቿ፣ የሚያውቋትም ሁሉ አለቀሱላት፤ እነዚያም ሁለቱ መምህራን በሕዝቡ መካከል ተነሥተው እጆቻቸውን በራሷ ላይ አኖሩ፤ እርሷ ግን ልቡናዋ በእግዚአብሔር ታምኗልና እያለቀሰች ወደ ሰማይ ተመለከተች።
❖ እነዚያም ረበናት ብቻችንን በተክል ውስጥ ስንመላለስ እርሷ ከሁለቱ ደንገጡሮቿ ጋር ገባች ደንገጡሮቿንም ልካቸዋለችና የተክሉን ደጃፍ ዘግተው ሔዱ ከዚያም በኋላ አንድ ጐልማሳ ከተሠወረበት መጥቶ አብሮዋት ተኛ፤ እኛ ግን በዚያ ተክል ዳርቻ ሁነን ኃጢአታቸውን አየን ወደነርሱም ሮጥን አንድነት ተኝተውም አገኘናቸው፤ እኛም እርሱን መያዝ ተሳነን እርሱ በርትቶብናልና አመለጠን የተክሉንም ደጃፍ ከፍቶ ወጣ፤ እርሷን ግን ይዘን ሰውዬው ማን እንደ ሆነ ጠየቅናት ግን አልነገረችንም ለዚህም ነገር ምስክሩ እኛ ነን አሉ።
❖ የሕዝቡ መምህራንና መኳንንትም ነበሩና በአደባባይ የተሰበሰቡ ሰዎች ነገራቸውን አመኑላቸው ትሙት በቃ ብለውም ፈረዱባት፤ ሶስናም ቃሏን አሰምታ ጮኸች ዘለዓለም ጸንተህ የምትኖር የተሠወረውን የምታውቅ የሚደረገውን ሁሉ ሳይደረግ የምታውቅ ፈጣሪ ሆይ በሐሰት እንዳጣሉኝ አንተ ታውቃለህ እነዚህ መምህራን ክፉ ነገርን ባደረጉብኝ ገንዘብ የሠራሁት ኃጢአት ሳይኖር እነሆ እሞታለሁ አለች፤ እግዚአብሔርም ቃሏን ሰማ፤ ይገድሏት ዘንድ ሲወስዷት እግዚአብሔር ስሙ ዳንኤል በሚባል ልጅ ላይ ልቡናን አነሣሣ እኔ ከዚች ሴት ደም ንጹሕ ነኝ ብሎ ቃሉን አሰምቶ ተናገረ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደርሱ ተመልሰው አንተ የምትናገረው ይህ ነገር ምንድን ነው አሉ።
❖ ዳንኤልም በመካከላቸው ቁሞ አላዋቆች የምትሆኑ እናንተ የእስራኤል ልጆች ሳትመረምሩና ነገሩን ሳትረዱ በእስራኤል ልጅ ላይ እንዲህ አድርጋችሁ እንደዚህ ያለ ፍርድን ትፈርዳላችሁን አለ እነዚህ መምህራን በሐሰት አጣልተዋታልና ወደ አደባባይ ተመለሱ አላቸው።
❖ ሕዝቡም ሁሉ እየሮጡ ወደ አደባባይ ተመለሱ አለቆችም ዳንኤልን እግዚአብሔር አንተን አልቆሃልና በመካከላችን ተቀምጠህ ተናገር አሉት፤ ዳንኤልም እየራሳቸው አራርቃችሁ አቁሙአቸው እኔም ልመርምራቸው አላቸውና አንዱንም አንዱን አራርቀው አቆሟቸው።
❖ ዳንኤልም ከእርሳቸው አንዱን ጠርቶ ከዚያ ሰው ጋር በምን ዕንጨት ሥር ሲነጋገሩ አየሃት አለው በኮክ ዕንጨት ሥር ሲነጋገሩ አየኋቸው አለ እርሱንም አርቆ ሁለተኛውን ሲነጋገሩ ያየህበት ዕንጨት ምንድን ነው አለው ሮማን ከሚባል ዕንጨት ሥር ነው አለ፤ ሕዝቡም ሁሉ ቃላቸውን አሰምተው በመጮህ ያመነችበት ሶስናን ያዳናት እግዚአብሔርን አመሰገኑት።
❖ ከቃላቸው የተነሣ ዳንኤል አስነቅፏቸዋልና ምስክርነታቸውንም ሐሰት አድርጎባቸዋልና በነዚያ በሁለቱ መምህራን ላይ በጠላትነት ተነሥተው ገደሏቸው።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በቅድሳን ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
አርኬ
✍️ሰላም ለሶስና ዘተዓገሠት ምንዳቤ። አመ አዕተቱ እምገጻ ወእምላዕለ ርእሳ ግልባቤ። ሶበ ፈተዉ ምስሌሃ ረበናተ አይሁድ ሩካቤ። ወዲቅ ይኄሰኒ ወኢ ገቢር ሶቤ። ለአምላኪየ እምአብስ ትቤ።
❖ በዚችም ዕለት የሰማዕታት ኢራኒ፣ የጳውፍርና የሐና የመነኰስ ሉቃስም መታሰቢያቸው ነው በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
አርኬ
✍️ሰላም ለክሙ ምሉዓነ ጽጌ ልምሉም። ዘኢያየብሶ ሐሩረ ኃጋይ ጌጋየ ዓለም ገዳም። አብርሃም ይስሐቅ ወያዕቆብ ክቡራነ ስም። እለ ፆርክሙ ብርሃነ እንዘ ጽልመት ዓለም። ከመ ማኅቶተ ይፀውር ተቅዋም፤ፐአፉሁ ዘይጸውም እምነገረ በክ ወዘርቅ። ወእምነ አልባሰ ቀጠንት አባለ ሥጋሁ ዕሩቅ። ኪሮስ ኅሩይ ዘተክለ ሃይማኖት ዐጽቅ፤በዕለተ ዕረፍቱ ለዝንቱ ጻድቅ፤ ተዘብጠ ሎቱ ከበሮ ዘወርቅ።
❖ ሰላም ለዕንቈ ማርያም ወለእስጢፋኖስ ወልዱ፤ እለ በኲናት ተረግዙ ወእለ በመጥባሕት ተሐርዱ፤ በቅድመ አረሚ ርኲሳን ሶበ ስመ ክርስቶስ አግሀዱ፤ በክዕወተ ደሞሙ ተማሕፀንኩ ከመ ላዕሌየ ያውርዱ፤ ጸጋ ጽድቆሙ ብዙኅ እመስፈርት ዘየዓዱ።
📌 መስከረም 28 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ አባዲር ሰማዕት
2.ቅድስት ኢራኢ እህቱ
3.ቅድስት ሶስና እናታችን
4.ቅዱስ ሉቃስ መነኰስ
5.ቅዱስ ዻውፍርና
📌 ወርኀዊ በዓላት
1.አማኑኤል ቸር አምላካችን
2.ቅዱሳን አበው (አብርሃም፣ይስሐቅና ያዕቆብ)
3.ቅዱስ እንድራኒቆስና ሚስቱ ቅድስት አትናስያ
4.ቅድስት ዓመተ ክክርስቶስ
5.ቅዱስ ቴዎድሮስ ሮማዊ (ሰማዕት)
✍️ "ሶስናም ቃሏን አሰምታ ጮኸች 'ዘላለም ጸንተህ የምትኖር የተሠወረውን የምታውቅ የሚደረገውን ሁሉ ሳይደረግ የምታውቅ ፈጣሪ ሆይ! በሐሰት እንደ ጣሉኝ አንተ ታውቃለህ፤ እነዚህ መምህራንም ክፉ ነገርን ባደረጉብኝ ገንዘብ፤ የሠራሁት ኃጢአት ሳይኖር እነሆ እሞታለሁ' አለች፤ እግዚአብሔርም ቃሏን ሰማት"
📖ሶስና 1፥41
ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ እምእለ ተፀመድኩ ዘልፈ ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውክፈ እምእለ አብዑ ብዑላን ዘተርፈ።
ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን ሰማዕታት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን ደናግል ዓዲ ወመነኮሳት ኄራን ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን እስከ አረጋዊ ልሂቅ እምንኡስ ሕፃን።
ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ ዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ ወለዘሰምዐ ቃሎ በእዝነ መንፈስ በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኲሉ እምባእስ ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ።
ጌታ ሆይ ከብልፅግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።
እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።
ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን።
ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ፤ እኔም ለእናንተ ከአዘጋጀው በኃዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ
✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝
✍"ልብህን በእርጋታ አኑረው፤ የሁሉም መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ለመሆን በጣም ትጋ ለከንቱ ንግግር ዘገምተኛና ሰነፍ ሁን፤ ነገር ግን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል በማወቅ በመስማት ድኅነትን የሚሰጡ ናቸውና ብልህ ሁን"
📚ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ይቆየን
───────────
Channel
🧲 https://telegram.me/Tewahedo12
FB Like Page (የፌስቡክ ፔጅ)
🧲 http://facebook.com/Tewahedo12
YouTube Subscribe (ሰብስክራይብ)
🧲 https://www.youtube.com/channel/UCvYxUdv1D-5juH_P6iE7XXw
───────────