ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም ፳፭

ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም ፳፭

@YeBiruk ዲያቆን ቡሩክ ይርጋ ዘውብ

✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

           አሜን

✍"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         

📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

         ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም ፳፭


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም ሃያ አምስት በዚች ቀን ታላቅ ነቢይ ዮናስ አረፈ።



   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

       ታላቅ ነቢይ ዮናስ

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ ይህም እውነተኛ ነቢይ ዮናስ የሲዶና ክፍል በምትሆን ስራጵታ በምትባል አገር ለምትኖር መበለት ልጅዋ የሆነ ነቢይ ኤልያስም ከሙታን ለይቶ ያሥነሣው ኤልያስንም ያገለገለውና የትንቢት ጸጋ የተሰጠው ነው።

❖ ከዚህም በኋላ ስሙ ከፍ ከፍ ያለና የተመሰገነ እግዚአብሔር ወደ ነነዌ አገር ሒደህ ሀገራቸሁ እስከ ሦስት ቀን ድረስ ትጠፋለች ብለህ አስተምር ብሎ አዘዘው።

❖ እግዚአብሔርም ይህን በአለው ጊዜ ዮናስ በልቡ እንዲህ ብሎ አሰበ እግዚአብሔር ሊአጠፋቸው ቢወድ ኖሮ ሒደህ አስተምር ብሎ ባላዘዘኝ ነበር እግዚአብሔር መሐሪ ነውና ሲምራቸው እኔ በእነርሱ ዘንድ ሐሰተኛ ነቢይ እንዳልባል እፈራለሁ ከቶ ትምህርቴን አይቀበሉኝም ወይም ይገድሉኛል ወደዚያች አገርም ሒጄ እንዳላስተምር ከእግዚአብሔር ፊት ብኰበልልና ብታጣ ይሻለኛል።

❖ወንድሞች ሆይ ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር ፊት ለፍጡር ማምለጥ ይቻለዋልን፤ ይህስ ዮናስ የእስራኤልን ልጆች ከሚያስተምሩ ነቢያት ውስጥ ሲሆን ይህን አያውቅምን ነገር ግን አግዚአብሔር በረቀቀ ጥበቡ ይህን አደረገ እንጂ የዮናስ በዓሣ አንበሪ ሆድ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት አድሮ መውጣት መድኃኒታችን በመቃብር ሆድ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት አድሮ ከዚህ በኋላ ከሙታን ተለይቶ ለመነሣቱ ምልክት ይሆን ዘንድ ነው።

❖ ዮናስም ከዓሣ አንበሪ ሆድ ያለ ምንም ጥፋት እንደመጣ እንዲሁ መደኃኒታችን ያለመለወጥ ተነሥቷልና።

❖ እንዲህም ሆነ ከእግዚአብሔር ፊት ዮናስ ሸሽቶ ወደ ተርሴስ አገር ሊሔድ ተነሣ ወደ ኢዮጴ አገርም ወርዶ ወደ ተርሴስ አገር የሚሔድ መርከብን አግኝቶ በገንዘቡ መርከቡን ተከራየ።

❖ ከእግዚአብሔር ፊት ኰብልሏልና ከእነርሱ ጋር ወደ ተርሴስ ይሔድ ዘንድ ወደ መርከቡ ወጣ እግዚአብሔርም ታላቁን ነፋስ ወደ ባሕር አመጣ የባሕሩም ማዕበል ከፍ ከፍ አለ መርከባቸውም ሊሰበር ቀረበ፤ ቀዛፊዎችም ፈርተው ወደ ጣዖቶቻቸው ጮኹ መርከባቸውም ይቀልላቸው ዘንድ ገንዘባቸውን፣ ዕቃቸውን አውጥተው ወደ ባሕር ጣሉ። ዮናስ ግን በዚያን ጊዜ ወደ ከርሠ ሐመሩ ወርዶ ተኝቶ ያንኰራፋ ነበር።

❖ መርከቡንም የሚቀዝፍ ቀዛፊ ወደ ርሱ ወርዶ ምን ያስተኛሃል እንዳንሞት እግዚአብሔር ያድነን ዘንድ ተነሥተህ የፈጣሪህን ስም ጥራ አለው። ይህች መከራ ያገኘችን ስለማናችን ኃጢአት እንደ ሆነ እናውቅ ዘንድ እርስ በርሳቸው ኑ ዕጣ እንጣጣል ተባባሉ በተጣጣሉም ጊዜ ዕጣ በዮናስ ወጣበት፤ እነርሱም ይህች መከራ ያገኘችን በማናችን ኃጢአት እንደሆነ ንገረን አንተስ የምታመልከው ምንድንነው ከወዴትስ መጣህ አገርህስ የት ነው ወዴትስ ትሔዳለህ ወገንህስ ማንነው አሉት።

❖ ዮናስም እኔስ የእግዚአብሔር ባርያው ዕብራዊ ነኝ ፈጣሪዬም ምድርንና ሰማይን ባሕሩንና የብሱን የፈጠረ እግዚአብሔር ነው አላቸው፤ እነዚያም ሰዎች ታላቅ ፍርሀትን ፈርተው ምን አድርገሀል አሉት እሱ ነግሮአቸዋልና ከእግዚአብሔር ፊት ኰብልሎ እንደሔደ እነርሱም አወቁት።

❖ ባሕሩ ይታወክ ነበርና ታላቅ ማዕበልም ተነሥቶ ነበርና ባሕሩ ይተወን ዘንድ እንግዲህ ምን እናድርግህ አሉት።

❖ ዮናስም አንሥታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ ባሕሩም ይተዋችኋል ይህ ታላቅ የማዕበል ሞገድ የመጣባችሁ በእኔ ምክንያት እንደ ሆነ አውቃለሁ አላችው።

❖ ባሕሪቱ ትታወካለችና ማዕበሊቱም በእነሣቸው ትነሣለችና እነዚያ ሰዎች ወደ ምድር ሊመለሱ ወደዱ ነገር ግን ተሳናቸው።

❖ ሁሉም አንድ ሁነው ወደ እግዚአብሔር ጮኹ አቤቱ ስለዚህ ሰው በእውነት ልታጠፋን አይገባህም አቤቱ እንደ ወደድክ አድርገሃልና የጻድቅ ሰው ደም አታድርግብን አሉ።

❖ ከዚህም በኋላ ዮናስን አንሥተው ወደ ባሕር ጣሉት ባሕርም ድርጎዋን ተቀብላ ጸጥ አለች፤ እነዚያም ሰዎች እግዚአብሔርን ፈሩት ለእርሱም መሥዋዕትን ሠዉ ስእለትንም ተሳሉ።

❖ እግዚአብሔርም ታላቅ ዓሣ አንባሪን ዮናስን ይውጠው ዘንድ አዘዘው ዮናስም በዓሣ አንባሪ ሆድ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ኖረ።

❖ ዮናስም በአንበሪ ሆድ ውስጥ ሳለ ጸሎትን ጸለየ ከዚህም በኋላ በነነዌ አገር በኩል ያ ዓሣ አንበሪ ዮናስን ወደ የብስ ምድር ተፋው።

❖ የእግዚአብሔርም ቃሉ ዳግመኛ ወደ ዮናስ መጣ ቀድሞ አስተምር ብዬ እንደ ነገርኩህ ወደ ታላቂቱ የነነዌ አገር ተነሥተህ ሒደህ አስተምራቸው አለው።

❖ ዮናስም እግዚአብሔር አስተምር ብሎ እንደ ነገረው ተነሥቶ ወደ ነነዌ ሔደ። ነነዌ ግን ለእግዚአብሔር ታላቅ አገር ናት በዙሪያዋ ያለ ቅጽርዋም ከበር እስከ በር ድረስ በእግር የሦስት ቀን ጐዳና ነው፤ ወደ ከተማም ሊገባ ደርሶ ያንድ ቀን መንገድ ሲቀረው ነነዌ እስከ ሦስት ቀን ትጠፋለች ብሎ አስተማረ።

❖ የነነዌም ሰዎች በእግዚአብሔር ቃል አመኑ ጾምን እንጹም ብለው አዋጅ ነገሩ የክት ልብሳቸውንም ትተው ማቅ ምንጣፍ ትልቁም ትንሹም ለበሱ።

❖ የነነዌ ንጉሥም ይህን ሰምቶ ከዙፋኑ ተነሣ ልብሰ መንግሥቱንም ትቶ ማቅ ለበሰ በአመድ በትቢያ ላይም ተቀመጠ።

❖ ሰዎችም ቢሆኑ ከብቶችም ምንም ምን አይብሉ ትልልቆችም ትንንሾችም አይጠጡ እንስሶችም ወደ ሣር አይሠማሩ ውኃም አይጠጡ ብሎ አዋጅ ነገረ፤ እግዚአብሔርም ከክፉ ሥራቸው እንደ ተመለሱ አይቶ በእነርሱ ላይ ያደርገው ዘንድ ከተናገረው ክፉ ነገር ተመለሰ በእነርሱ ላይም ክፉ ጥፋትን አላደረገም።

❖ ዮናስም ጽኑ ኀዘንን አዘነ ወደ ፈጣሪው እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ለመነ ጥንቱን በአገሬ ሳለሁ እንዲህ ብዬ የተናገርሁ አይደለሁምን አንተ ይቅር ባይ ርኅሩኅም ከመዓት የራቅህ ቸርነትህ የበዛ እውነተኛ የሆንክ ክፉ ነገርን ከማምጣት እንደምትመለስ አውቃለሁ ስለዚህ ከአንተ ኮብልዬ ወደ ተርሴስ ሔድሁ።

❖ ነቢየ ሐሰት እየተባልኩ ከመኖር ሞት ይሻለኛልና አቤቱ አሁን ነፍሴን ከሥጋዬ ለያት አለ፤ እግዚአብሔርም ዮናስን በዚህ ነገር አንተ እጅግ ታዝናለህን አለው እርሱም አዎን አዝናለሁ አለ።

❖ ከዚህም በኋላ ዮናስ ከከተማ ወጥቶ ከከተማው ውጭ ተቀመጠ ጎጆም ለራሱ ሠራ በአገር ላይ የሚደረገውን ነገር እስኪያይ ድረስ ከጥላዋ ሥር ተቀመጠ።

❖ ይበቅል ዘንድ በዮናስ ራስ ላይ ይሸፍነው ዘንድ እግዚአብሔር ቅልን አዘዘ ቅሉም በዚያን ጊዜ በቅሎ የዮናስን ራስ የፀሐይ ትኩሳት እንዳያሳምመው በዮናስ ራስ ላይ ሸፈነው ዮናስም በቅሊቱ መብቀል ታላቅ ደስታ አደረገ።

❖ እግዚአብሔርም በማግሥቱ ትሉን ይምጣ ቅሉንም ይምታ ብሎ አዘዘ ቅሊቱንም ቆረጣት እርሷም ደረቀች እግዚአብሔርም ፀሐይ በወጣ ጊዜ የሚያቃጥል ሐሩር ያለበት ነፋስ ይምጣ ብሎ ዳግመኛ አዘዘ።

❖ ነፋሱም መጥቶ የዮናስን ራስ አሳመመው እርሱም አእምሮውን እስከማጣት ደርሶ በልቡናውም ተበሳጭቶ ከመኖር ሞት ይሻለኛል አለ።

❖ እግዚአብሔርም ዮናስን በቅሊቱ መድረቅ እጅግ አዘንክን አለው እርሱም አዎን ልሙት እስከ ማለት ደርሼ አዘንኩ አለ።

❖ እግዚአብሔርም አንተስ በአንድ ሌሊት በቅላ በአንድ ሌሊት ለደረቀች ውኃ ላላጠጣሃት ላልደከምክባት ቅል ታዝናለህ፤ ቀኝና ግራቸውን ላልለዩ ከዐሥራ ሁለት እልፍ የሚበዙ ሰዎች እንዲሁም ብዙ እንስሶች ላሉባት ታላቅ አገር ለሆነች ነነዌ እኔ አላዝንላትምን ከበደሉ ተመልሶ ንስሐ ለሚገባ እኔ መሐሪና ይቅር ባይ ነኝና አለ፤ ከዚህም በኋላ ዮናስ ተነሥቶ ወደ አገሩ ተመልሶ በሰላም አረፈ መላው ዕድሜውም መቶ ሰባ ነው።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

              አርኬ

✍️ሰላም ለዮናስ በከርሠ አንበሪ ዘኖመ። አምሳለ ክርስቶስ ይኩን ዘውስተ መቃብር ተኀትመ። እግዚአብሔር ይቤሎ ጊዜ በሐሩር ሐመ። ኢይሣሃላኑ ለነነዌ ወኢይምሕካኑ ፍጹመ። እንዘ አንተ ትምሕክ ዘኢተከልከ ሐምሐመ።


በዚች ቀን የፎቃ፣ የዮሐንስ፣ የእንድራዎሰ፣ የጴጥሮስ፣ የጳውሎስ፣ የእንጦንዮስ፣ የበርባራ መታሰቢያቸው ሆነ በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

            

                    አርኬ

✍️ሰላመ ለዕፀ መስቀል ደመ መለኮት ዘተነዝኅ። እስመ ቈጽሰ ሕይወት አሥረዐ ወጽጌ አምሳል ንጹሐ። በዛቲ ዕለተ ብሔረ አግዓዚ ዘበጽሐ። ከመ ተመነየ ነጺሮ ዕለቶ ስቡሐ። ርእየሂ ወተፈሥሐ እስክንድር ብዙኅ። ሰላም ለክሙ ጽጉባነ ኦሪት ወወንጌል። እምአጥባዕተ መርዓት ክልኤ ከመ ዕጒለ መንታ ዘወይጠል። ሠናየ ጽጌ ኬፋ ወጥዑመ ፍሬ ሳውል። ይሠየም በክሣድየ ዐርዑትክሙ ቀሊል። ወይሰወጥ በአእናፍየ ጼናክሙ ኮል። ሰላም ለበርባራ ወለዮልያና አምሳላ። በዛቲ ዕለት ዘአስተርአየት ኃይላ። በክልኤ ዕደው ዘሰረቁ መጽሐፈ ገድላ። ፈደየቶ ለአሐዱ እንባዜ እምኀበ ማርያም ስኢላ። ወለዐይነ ቢጹ ካልዕ አጽለመት ጸዳላ።

             

✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

     የክረምት መውጫ

  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ ዳግመኛም ይኽች ዕለት የክረምት መውጫ ሆናለች፤ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር (የጊዜ ቀመር) መሠረት በዓመት ውስጥ አራቱ ወቅቶች አሉ፡፡ እነዚህም ክረምት፣ መፀው (መኸር ወይም መከር)፣ ሐጋይ (በጋ) እና ፀደይ (በልግ) ናቸው።

❖ አራቱ ሊቃነ ከዋክብት የሚባሉት ናርኤል፣ ብርክኤል፣ ምልኤል እና ኅልመልሜሌክ እነዚህ እያንዳንዳቸው አራቱን ወቅቶች በየተራ ይመግባሉ፡፡

❖ አንድ ዓመት በውስጡ 13 ወራትን የያዘ ሆኖ በአራት ወቅቶች የተከፈለ ነው፤ ቅዱስ ያሬድ በድርሰቱ አንዱን ዓመት በአራት ክፍለ ዘመን ከፍሎታል፡፡

📌 አራቱ ክፍላተ ዘመን የሚባሉትም

1. ክረምት ማለት ከሰኔ 26- መስከረም 25 ያለው ነው፡፡

2. መፀው (መከር) ማለት ከመስከረም 26- ታኅሣሥ 25 ያለው ነው፡፡

3. በጋ (ሐጋይ) ማለት ከታኅሣሥ 26-መጋቢት 25 ያለው ነው፡፡

❖ ከክረምት በስተቀር እያንዳንዱ ወቅት በውስጡ ዘጠና ዘጠና ቀናት ይዟል፤ ክረምት ግን ለብቻው 95 ቀናትን የያዘ ነው፡፡

📌 ዘመነ መፀው

❖ መፀው በሌላ አነጋገር ጥቢ ይባላል፤ እንደ ሌሊት ከብዶ የሚታየው ክረምት አልፎ መስከረም ከጠባ በኋላ በ4ኛው ሳምንት ስለሚጀምር ነው ጥቢ የሚባል ተጨማሪ ስያሜ የተሰጠው፡፡

❖ ዘመነ መፀው ከመስከረም 26 እስከ ታኅሣሥ 25 ድረስ ያለው ጊዜ ነው፤ የዕለቱ ቁጥርም 90 ይሆናል፡፡

❖ ከዘመነ ክረምት ቀጥሎ በመሆኑ ዘመነ ክረምትን በማስቀደም ፅጌንና መፀውን በማስተባበር ቅዱስ ያሬድ የሚከተለውን ብሏል፡፡

✍“ግሩም በሆነው ኃይልህ እንመካ ዘንድ አንተ ዘመናትን ሠራህ ክረምትን ለዝናባት መፀውን ለአበቦች ሰጠህ”

📚ድጓ ዘጽጌ

❖ መፀው መሬት በክረምት የተሰጣትን ዘር አበርክታ፣ አብዝታ ለፍሬ የምታደርስበት የምርት ወቅት ነው፤ መፀው በአብዛኛው የአዝመራ መሰብሰቢያ ጊዜው ነው፡፡

📌ዘመነ ሐጋይ

❖ ዘመነ ሐጋይ (በጋ) ይህ የበጋ ወቅት ነው፤ “ሐጋይ”….በጋ ሆነ ከሚለው የግዕዝ ቃል የተገኘ ነው፤ ይህም ከታኅሣሥ 26 እስከ መጋቢት 25 ቀን ያለውን ጊዜ ያጠቃልላል፤ ሐጋይ የጥርን፣ የየካቲትንና የመጋቢትን ወር ይይዛል፡፡

❖ ዘመነ ሐጋይ የቃሉ ትርጓሜ ዘመነ ፀሐይ ማለት ሲሆን ሥርወ ቃሉም ኃገየ … ከሚለው ግእዝ የተገኘ ነው፤ ከአራቱ ክፍላተ ዘመን አንዱ እጅ ወይም አንድ አራተኛው ሐጋይ ይባላል፤ የሐጋይ ፍቺ በጋ እንደሆነ ሁሉ እንዲሁም መፀውም ጸደይም በእርሱ ስም በጋ ይባላሉ፡፡

✍“ዘጠኝ ወር በጋ” እንዲሉ፣ አንዳንድ ጊዜም መጽሐፍት በሁለት ከፍለው ይናገራሉ “ክረምትና በጋን አንተ ሠራህ” ፤ “በበጋም በክረምትም እንዲህ ይሆናል”

📖መዝ 75፥17፣

📖ዘካ 14፥10፣

📖ዘፍ 10፥22

❖ ኃጋይ ማለት መገኛ መክረሚያ በጋ፣ ፀደይ፣ ደረቅ ወቅት ነው፤ በዚህ ወቅት በመፀው ያሸተውና ያፈራው መኸር የሚታጨድበት፣ የሚሰበሰብበትና በየማሳው ከተከመረ በኋላ የሚበራይበት፣ በጎተራ የሚከተትበት በመሆኑ “የካቲት” የሚለውን ወር ይዞ እናገኘዋለን፡

❖ የግብርናው ኅብረተሰብ እህሉን በጎተራው ከትቶ ለተወሰነ ጊዜ የሚያርፍበት በመሆኑ የዓመት በዓላት እንደ ልደት፣ ጥምቀት ያሉት፣ ዘመነ መርዓዊ የሚባለው የጋብቻ ዘመን በዚህ ወቅት የተካተቱ ናቸው፡፡

📌ዘመነ ጸደይ

❖ በአብዛኛው ግን ዘመነ በልግ ነው፤ ቅዱስ ያሬድ በድጓው “ይሁብ ዝናመ ተወን” የበልግ ዝናምን ይሰጣል እንዳለው የበልግ ወቅት ነው፡፡

✍“አንድ ሰኔ የነቀለውን ሁለት ሰኔ አይተካውም” እንደሚባለው የግብርናው ኅብረተሰብ ቀጣይ የግብርና ሥራውን በትጋት የሚሠራበት ወቅት ነው፡፡

📌 ዘመነ ክረምት

❖ ዘመነ ክረምት ማለት ዘመነ ውሃ ማለት ነውና በዚህ ዘመን ውኃ ይሰለጥናል፤ ውሃ አፈርን ያጥባል፣ እሳትን ያጠፋል፣ ቢሆንም በብሩህነቱ ከእሳት፣ በቀዝቃዛነቱ ከነፋስ፣ በእርጥብነቱ ከመሬት ጋር ተስማምቶ ይኖራል፡፡

❖ ክረምት በውስጡ አራት ወራትን (ሐምሌ፣ ነሐሴ፣ ጳጉሜንና መስከረም) የያዘ ነው፤ ቅዱስ ያሬድ “ያረሁ ክረምተ በበዓመት፣ ይሰምዑ ቃሎ ደመናት፣ በየዓመቱ ክረምትን ያገባል፤ ደመናትም ቃሉን ይሰሙታል” ሲል በድጓው እንደነገረን የዘመናት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር በየዓመቱ አዙሮ የሚያመጣልን ወቅት ነው፡፡

❖ ደመናትም ለቃሉ ትእዛዝ ተገዢዎች በመሆን ዝናመ ምሕረቱን ጠለ በረከቱን የሚያወርዱበት ጊዜ ነው፤ ከሰኔ 26 እስከ መስከረም 25 ድረስ ያለውን ጊዜ ይይዛል፡፡


            አርኬ

✍️ድኅረ ሐለፈ ክረምት ወገብአ ዝናም። ዘአርአይከ እግዚኦ ጽጌያተ ገዳም። አፈወ ሃይማኖት ነዓልድ ወፍሬ ምግባር ጥዑም። አትግሐነ ለስብሐቲከ ከመ ትጋሆሙ አዳም። ለጽብስት ንህብ ወነአስ ቃሀም።

📌 መስከረም 25 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ጸአተ ክረምት (የክረምት መውጫ)

2.ቅዱስ ዮናስ ነቢይ

3.ቅዱስ እንጦንዮስ

4.ቅድስት በርባራ

5.ሐዋርያት ዼጥሮስ ወዻውሎስ

6.ቅዱስ ዕፀ መስቀል


📌 ወርሐዊ በዓላት

1.ቅዱስ መርቆሬዎስ ሰማዕት

2.ቅድስት ቴክላ ሐዋርያዊት

3.ቅዱስ አበከረዙን ሰማዕት

4.ቅዱስ ዱማድዮስ ሶርያዊ

5.አቡነ አቢብ (አባ ቡላ)

6.ቅዱስ አባ አቡፋና ጻድቅ

7.ታላቁ አባ ቢጻርዮን ገዳማዊ


✍️"ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፤ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም፤ ዮናስ በአሣ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት እንደ ነበረ: እንዲሁ የሰው ልጅ በምድር ልብ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይኖራል፤ የነነዌ ሰዎች በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሃ ገብተዋልና፤ እነሆም ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ"

📖ማቴ 12፥39

      

ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ እምእለ ተፀመድኩ ዘልፈ ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውክፈ እምእለ አብዑ ብዑላን ዘተርፈ።

ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን ሰማዕታት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን ደናግል ዓዲ ወመነኮሳት ኄራን ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን እስከ አረጋዊ ልሂቅ እምንኡስ ሕፃን።

ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ ዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ ወለዘሰምዐ ቃሎ በእዝነ መንፈስ በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኲሉ እምባእስ ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ።


ጌታ ሆይ ከብልፅግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።

እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።

ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን።


ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ፤ እኔም ለእናንተ ከአዘጋጀው በኃዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ


✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝


✍"ልብህን በእርጋታ አኑረው፤ የሁሉም መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ለመሆን በጣም ትጋ ለከንቱ ንግግር ዘገምተኛና ሰነፍ ሁን፤ ነገር ግን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል በማወቅ በመስማት ድኅነትን የሚሰጡ ናቸውና ብልህ ሁን"

📚ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ


             ወስብሐት ለእግዚአብሔር

                             ይቆየን 


───────────

                   Channel

 🧲 https://telegram.me/Tewahedo12

       FB Like Page (የፌስቡክ ፔጅ)

🧲 http://facebook.com/Tewahedo12  

       YouTube Subscribe (ሰብስክራይብ)

🧲 https://www.youtube.com/channel/UCvYxUdv1D-5juH_P6iE7XXw

 ───────────


Report Page