ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም ፳፩

ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም ፳፩

@YeBiruk ዲያቆን ቡሩክ ይርጋ ዘውብ

✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

           አሜን


✍"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         

📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ


         ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም ፳፩

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም ሃያ አንድ በዚች ቀን አምላክን የወለደች የቅድስት ድንግል እምቤታችን ማርያም የበዓሏ መታሰቢያ ነው፤ ሁላችንም የአዳም ልጆች እስከ ዓለም ፍጻሜ የበዓሏን መታሰቢያ በየወሩ ልናደርግ ይገባናል የእግዚአብሔር ልጅ ከእርሷ ሰው በመሆኑ ከጠላታችን ሰይጣን እጅ ድኅነታችን በእርሷ ተደርጎልናልና እርሷም ስለእኛ ሁል ጊዜ ትማልዳለችና ።

የምታድን እርሷን እናቱን ለሰጠን እግዚአብሔር ምስጋና ይሁን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን።


         አርኬ

✍️ሰላም ለኪ ዘደለወኪ ትንበሪ። በየማነ ንጉሥ ፈጣሪ። ማርያም ንግሥት ዘኢትሠዓሪ። ዕድዋነ ዚአነ በመስቀል አግርሪ። ወበመስቀል ካዕበ ዐውደነ ኅዕሪ።



 ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

     ግሼን ደብረ ከርቤ

  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥


❖ ሃገራችን ኢትዮዽያ ሃገረ እግዚአብሔር መሆኗን ታላቁ ቅዱስ_መጽሐፍ ይመሰክራል፤ ሕዝቦቿም የድንግል ማርያምና የቅዱሳን አሥራት ናቸው::

📖መዝ 67፥

📖አሞጽ 9፥7


❖ የኢትዮዽያውያንን ያህል ድንግል ማርያምን የሚወድ ለቅዱስ መስቀሉ ክብርን የሚሰጥ ቅዱሳንንም የሚዘክር ያለ አይመስለኝም "እመ ብርሃንም ፈጽማ ትወደናለች፤ ለዚህ ደግሞ ቅንጣት ታህል አንጠራጠርም" ለዓለም እስከ አሁን ድረስ የ2ቱ (የታቦተ ጽዮንና የቅዱስ ዕፀ መስቀሉ) መገኛ እንቆቅልሽ ነው፤ ለእኛ ግን 2ቱም ያሉት በቤታችን ውስጥ ነውና እንመሠክራለን፤ ክብር ለቀደምት አበው ይድረሳቸውና አስፈላጊውን መንፈሳዊና ሥጋዊ ዋጋ ከፍለው ታቦተ ጽዮንን እና ቅዱስ ዕፀ መስቀሉን አምጥተውልናል።


❖ በዚህች ዕለትም የጌታችንና የመድኃኒታችን ኢየሱስ_ክርስቶስ መስቀል በደብረ ከርቤ ግሼን ማረፉን አስበን በዓልን እናከብራለን፤ ይኸውም ደጉ አፄ ዳዊት በሠይፈ አርዕድ የተጀመረውን ጥረት ቀጥለው በኃይለ እግዚአብሔር አሕዛብን አስደንግጠው እመ ብርሃንንም በጸሎት ጠየቁ::


❖ የአምላክ እናትም ረድታቸው ቅዱስ ዕፀ መስቀሉን ከኩርዓተ ርዕሡ ወንጌላዊ ቅዱስ ሉቃስ ከሳላት ምስለ ፍቁር ወልዳ እና ከብዙ ንዋያተ ቅዱሳት ጋር ተላከላቸው፤ እርሳቸው መስከረም 10 ቀን መስቀሉን ተቀብለው በዓሉን በተድላ አክብረው በመንገድ በ1396 ዓ.ም ዐርፈዋል::


❖ አፄ ዳዊት ካረፉ በሁዋላ ቅዱስ መስቀሉ ለ30 ዓመታት ተቀምጧል፤ አፄዘርዓ ያዕቆብ እስከ ነገሠበት 1426 ዓ/ም ድረስም ከ6 በላይ ነገሥታት አልፈዋል፤ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ከነገሠ ከጥቂት ዓመታት በሁዋላ ለቅዱስ መስቀሉ በመካነ ንግሱ ደብረ ብርሃን ቤተክርስቲያንን ለማነጽ ሲያስብ ጌታችን በራዕይ " አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል" አለው፤ ከዚህ ቀን ጀምሮ ደጉ ንጉሥ የመካነ መስቀሉን ቦታ ይፈልግ ዘንድ ከሠራዊቱ ጋር ብዙ ደክሟል።


❖ በመጨረሻም በነገሠ በ10 ዓመታት ግሼንን አምባሰል ( ወሎ ) ውስጥ አግኝቷት ሐሴትን አድርጉዋል፤ ቦታዋ በሥላሴ ፈቃድ በትእምርተ መስቀል የተፈጠረች ናትና እግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያንን አንጾ መስቀሉን በብረት በመዳብ በናስ በብር በወርቅ ለብጦ ዐፈር እንዳይነካውም አድርጐ አኑሮታል::


❖ በቦታውም ተአምራት ተደርገዋል፤ ጻድቁ ዘርዓ ያዕቆብም 'ጤፉት' የሚባል መጽሐፍን ጽፎ እዚያው አኑሮታል፤ መጽሐፉ እንደሚለው በሃገራችን ያለው ግማደ መስቀሉ (የቀኝ እጁ) ብቻ ሳይሆን ሙሉው ዕፀ መስቀል ነው፤ ይህ የተደረገውም መስከረም 21 ቀን ነው::


ከዕፀ መስቀሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን፤ አገራችን ሰላም ፍቅር ያድርግልን


  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

 ብዙኃን ማርያም (ጉባኤ ኒቅያ)

  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥


❖ ዳግመኛ ይህች ዕለት 'ብዙኃን ማርያም' ትባላለች፤ በቁሙ ሲታይ ድንግል ማርያም የብዙ ቅዱሳን የጸጋ እናት መሆኗን ያመለክታል፤ በምሥጢሩ ግን በዚህች ዕለት በሃገረ ኒቅያ በእመቤታችን እና በአምላክ ልጇ የሚያምኑ 318ቱ ቅዱሳን ሊቃውንት መሰብሰባቸውን የሚያጠይቅ ነው።


❖ የሊብያው ሰው አርዮስ ጌትነት ገንዘቡ የሆነ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ክዶ ሊያስክድ ሲሯሯጥ በፈቃደ እግዚአብሔር በጻድቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ጥሪ 2348 ምሑራን ከመላው ዓለም ተሰበሰቡ፤ ጥሪው የተላለፈው በወርኀ ሚያዝያ ሲሆን በመንገድ ችግር ሁሉም ተጠቃለው ኒቅያ የገቡት በዚህ ቀን ነበር፤ ከተሰበሰበው ብዙ ሰው መካከል የአበውን ደቀ መዛሙርት ሳንቆጥር ሃይማኖታቸው የቀና ምግባራቸው የጸና 318ቱ አበው ሊቃውንት ተገኙ።


❖ እነዚህ አባቶች 'ሊቃውንት' ሲባሉ እንዲሁ በእውቀት ብቻ የበሰሉ እንዳይመስሉን፤ 318ቱ አበው እኩሎቹ በዘመነ ሰማዕታት እጅና እግራቸውን የተቆረጡና ለሃይማኖታቸው ብዙ ዋጋ የከፈሉ ናቸው::


❖ እኩሎቹ ደግሞ በገዳማዊ ሕይወት ያጌጡ ፍቅረ_ክርስቶስ በውስጣቸው የሚነድ የመንፈስ ቅዱስ ቤት ናቸው፤ የጉባኤውን ዜና ግን ሕዳር 9 ቀን የምንመለከት ነንና የዚያ ሰው ይበለን፤ ይህች ቀን ለአባቶቻችን የሱባኤ መጀመሪያ ናት::


የቅዱሳን አባቶቻችን ረድኤት በረከት ይደርብን፤ በጸሎታችን ይማረን


   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

ቅዱስ ቆጵርያኖስና ድንግሊቱ ዮስቴና

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ በዚችም ቀን ቅዱስ ቆጵርያኖስና ድንግሊቱ ዮስቴና በሰማዕትነት አረፉ፤ ይህም ቅዱስ ቆጵርያኖስ አስቀድሞ ከሀዲና ሥራየኛ ነበር እርሱም ለሥራየኞች ሁሉ አለቃቸው ነው።

❖ በሥራዩም ሥራ ከመመካቱ ብዛት የተነሣ በሥራይ የሚበልጠው ካለ ሊያይና ከዚያ ሊማር ከሌለ ግን በእነርሱ ላይ ሊመካባቸው ወደ አንጾኪያ አገር ሔደ።

❖ ቆጵርያኖስም ወደ አንጾኪያ ከተማ በደረሰ ጊዜ ወሬው ተሰማ በአንጾኪያም ከተማ ከሀገር ታላላቆች ተወላጅ የሆነ አንድ ጐልማሳ አለ እርሱም ላህይዋ የሚያምር አንዲቷን ድንግል ብላቴና ተመኛት ወደ ቤተ ክርስቲያን በምትሔድ ጊዜ እያያት በእርሷ ፍቅር ልቡ እንደ እሳት ተቃጠለ በምንም በምን ሊአገኛት አልተቻለውም ገንዘብ በመስጠትም ቢሆን ወይም በማስፈራራት ወይም በሥራይ ሥራ አልሆነለትም።

❖ የቆጵርያኖስም ወሬው በተሰማ ጊዜ እርሱ ከሥራየኞች ሁሉ እንደሚበልጥ ስለርሱ ተነግሮአልና ያም ድንግል ዮስቴናን የተመኛት ጐልማሳ ወደ ቆጵርያኖስ ሒዶ በልቡ ያለውን ጉዳዩን ድንግሊቱን ዮስቴናን እንደተመኛትና እርሷን ማግኘት እንደተሳነው ነገረው ቆጵርያኖስም እኔ የልብህን ፍላጎት እፈጽምልሃለሁ አትዘን አለው።

❖ ከዚያም በኋላ ያን ጊዜ ዮስቴናን ወደርሱ ያመጧት ዘንድ በሥራዩ የአጋንንትን ሠራዊት ወደርሷ ላከ እነዚያም አጋንንት ወደርሷ በቀረቡ ጊዜ እርሷን መውሰድ አልቻሉም ከጸሎቷ የተነሣ ይቃጠላሉና እንዲህም ብዙ ጊዜ ላካቸው ግን ወደርሱ ሊያመጧት አልቻሉም ቆጵርያኖስም ሁሉንም አጋንንት ጠርቶ ድንግል ዮስቴናን ካላመጣችሁልኝ እኔ ከእናንተ ተለይቼ ክርስቲያን እሆናለሁ አላቸው።

❖ ከዚህም በኋላ የሰይጣናት አለቃ ሊሸነግለው አሰበ አንዱንም ሰይጣን ከሰይጣናት ውስጥ በዮስቴና አምሳል ተመስሎ ለቆጵርያኖስ እንዲታየው አደረገ፤ ሰይጣኑም አለቃው እንዳዘዘው እንዲህ አድርጎ ተዘጋጀ እነሆ አሁን የዮስቴናን መምጣት ለቆጵርያኖስ ነገረው እርሱም እውነት መስሎት እጅግ ደስ አለው ሊቀበላትም ተነሣ። በእርሷ አርአያ የተመሰለውንም ምትሐት በአየ ጊዜ የሴቶች እመቤት ዮስቴና መምጣትሽ መልካም ሆነ አለ ይህንንም ስሟን በጠራ ጊዜ ያ በእርሷ አምሳል የተመሰለ ሰይጣን እንደ ጢስ ሁኖ ተበተነ።

❖ በዚያንም ጊዜ የሽንገላው ምክንያት ምትሐቱም ከንቱ እንደሆነ ቆጵርያኖስ አወቀ አስተዋለም በልቡም እንዲህ አለ።

❖ ስሟን በጠሩበት ቦታ እንደ ጢስ የሚበተኑ ከሆነ በፊቷ ሊቆሙ ሊሸነገሏትስ እንዴት ይቻላቸዋል ይህንንም ብሎ ወዲያውኑ የጥንቆላ መጻሕፍቶቹን አቃጠለ።

❖ ከዚህም በኋላ ወደ አንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ሒዶ የክርስትና ጥምቀትን ተጠምቆ የምንኲስና ልብስን ለበሰ ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ዲቁና ሾመው።

❖ ዳግመኛም ቅስና ሾመው በትሩፋት ሥራና በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ከፍ ከፍ ባለ ጊዜ ለሀገሩ ምዕራብ ለሆነች ቅርጣግና ለምትባል አገር ኤጲስቆጶስ ይሆን ዘንድ ተገባው ያን ጊዜም ቅድስት ዮስቴናን ወስዶ ለደናግል ገዳም እመ ምኔት አደረጋት።

❖ በቅርጣግናም የቅዱሳን የአንድነት ስብሰባ በሆነ ጊዜ ከጉባኤው አባላት እርሱ አንዱ ነው፤ ከብዙ ወራት በኋላም ከሀዲው ንጉሥ ዳኬዎስ ስለእነርሱ ሰማ ወደርሱም አስቀረባቸውና የክብር ባለቤት ክርስቶስን ክደው ለጣዖቶቹ እንዲሰግዱ አዘዛቸው።

❖ ትእዛዙንም ባልሰሙ ጊዜ ታላቅ ሥቃይን አሠቃያቸው ብዙ ሥቃይንም ከአሠቃያቸው በኋላ የቅዱስ ቆጵርያኖስንና የቅድስት ደንግል ዮስቴናን የሦስት ወንዶችንም ራሳቸውን አስቆረጠ የሰማዕትነት አክሊልንም በመንግሥተ ሰማያት ተቀበሉ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

     

          አርኬ

✍️ሰላም ለቆጵርያኖስ ሰማዕተ ኢየሱስ ፌማ። በጤገነ እሳት ውዑይ አባላቲሁ ዘሐማ። ምስለ ሠለስቱ ዕደው ዘተሳተፍዎ ፃማ። ወሰላም ለዮስቴና በኀበ ጸውዑ ስማ። ከመ እንተ ጢስ ተዘርወ መስቴማ።


በዚችም ቀን ከሰባ ሁለቱ አርድእት የአንዱ ሐዋርያ የጢባርዮስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው። በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


                 አርኬ

✍️ሰላም ሰላም ለጢባርዮስ ስንዕ። ምስለ 72ቱ አርድእተ እግዚእ። በዕለተ ዕረፍትከ ዮም ሔረ ተድላ ወፍግዕ። ባርከነ ለደቂቅከ በውስተ ዛቲ ምሥዋዕ። እስመ ለመምህር ቡራኬ ሥሩዕ።


በዚችም ቀን ሃይማኖታቸው የቀና የሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት ጳጳሳት ስብሰባ በኒቅያ ከተማ ተደረገ መላውን ዜናቸውን ኅዳር ዘጠኝ ቀን ጽፈናል በረከታቸው ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


             አርኬ

✍️ሰላም ለክሙ ጳጳሳት አዕማድ። ሠለስቱ ምእት ዐሠርቱ ወሰመንቱ በፍቅድ በእንተ ማርያም ጳጦስ ዐዋሪተ ነድ። ንዑ ንዑ መምህራን ትባርኩነ ለውሉድ። እንዘ ትእኅዙ መስቀለ በእድ።


📌 መስከረም 21 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ቅድስት ግሼን ደብረ ከርቤ

2.ብዙኃን ማርያም

3."318ቱ" ቅዱሳን ሊቃውንት

4.ቅዱስ ቆዽርያኖስ ሰማዕት

5.ቅድስት ዮስቴና ድንግል

6.ቅዱስ ጢባርዮስ ሐዋርያ

📌ወርኀዊ በዓላት

1.ቅድስት ድንግል እግዝእትነ ማርያም ወላዲተ አምላክ

2.አበው ጎርጎርዮሳት

3.አቡነ ምዕመነ ድንግል

4.አቡነ አምደ ሥላሴ

5.አባ አሮን ሶርያዊ

6.አባ መርትያኖስ ጻድቅ

✍️"እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል ይላል፤ እንግዲህ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ፤ ከእናንተም ይሸሻል፤ ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ:: ወደ እናንተም ይቀርባል"

📖ያዕ 4፥6


ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ እምእለ ተፀመድኩ ዘልፈ ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውክፈ እምእለ አብዑ ብዑላን ዘተርፈ።

ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን ሰማዕታት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን ደናግል ዓዲ ወመነኮሳት ኄራን ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን እስከ አረጋዊ ልሂቅ እምንኡስ ሕፃን።

ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ ዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ ወለዘሰምዐ ቃሎ በእዝነ መንፈስ በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኲሉ እምባእስ ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ።


ጌታ ሆይ ከብልፅግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።

እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።

ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን።


ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ፤ እኔም ለእናንተ ከአዘጋጀው በኃዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ   


✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝


✍"ልብህን በእርጋታ አኑረው፤ የሁሉም መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ለመሆን በጣም ትጋ ለከንቱ ንግግር ዘገምተኛና ሰነፍ ሁን፤ ነገር ግን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል በማወቅ በመስማት ድኅነትን የሚሰጡ ናቸውና ብልህ ሁን"

📚ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ


             ወስብሐት ለእግዚአብሔር

                             ይቆየን 


───────────

                   Channel

 🧲 https://telegram.me/Tewahedo12

       FB Like Page (የፌስቡክ ፔጅ)

🧲 http://facebook.com/Tewahedo12  

       YouTube Subscribe (ሰብስክራይብ)

🧲 https://www.youtube.com/channel/UCvYxUdv1D-5juH_P6iE7XXw

 ───────────

https://telegra.ph/ስንክሳር-ዘመስከረም-09-28-3


Report Page