ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም ፲፮

ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም ፲፮

@YeBiruk ዲያቆን ቡሩክ ይርጋ ዘውብ

✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

           አሜን


✍"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         

📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ

         ቀናችንን በጸሎት እንጀምር

ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም ፲፮


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም ዐሥራ ስድስት በዚች ቀን ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ላይ ቤተ ክርስቲያን የታነፀችበትና የተቀደሰችበት ነው። ደግሞ በኢየሩሳሌም አገር ንግሥት ዕሌኒ የገለጠቻቸው የከበሩ ቦታዎች ሁሉ የተሠሩበትና የከበሩበት ሆነ።

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

   ሕንጸታ ለኢየሩሳሌም

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ ይህም እንዲህ ነው ልጇ ቁስጠንጢኖስ በነገሠ በሃያ ዓመት ቅዱሳን የሆኑ ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት አባቶችን በኒቅያ ከተማ ከሰበሰበ በኋላ ቅድስት እናቱ ዕሌኒ እንዲህ አለችው ልጄ ሆይ እኔ ወደ ቅድስት አገር ኢየሩሳሌም በመሔድ የክብር ንጉሥ የሆነ የክርስቶስን ዕፀ መስቀል ፈልጌ አወጣ ዘንድ ለእግዚአብሔር ስዕለትን ተስያለሁ።

❖ ቁስጠንጢኖስም ሰምቶ በዚህ ነገር ደስ አለው ከብዙ ሠራዊትም ጋር ብዙ ገንዘብ ሰጥቶ ላካት የከበሩ የግምጃ ልብሶችንም ሰጣት እርሷም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰች ጊዜ ከከበሩ ቦታዎች ተባረከች።

❖ ከዚህም በኋላ ስለ ከበረና አዳኝ ስለ ሆነ ዕፀ መስቀል መረመረች በታላቅ ድካምና ችግር አገኘችውና ታላቅ ክብርን አከበረችው በታላቅ ምስጋናም አመሰገነችው።

❖ ከዚህም በኋላ በጎልጎታ በቤተ ልሔምም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ዋሻ ደግሞ በጽርሐ ጽዮን የእመቤታችን ማርያም ሥጋዋ በተቀበረበት በጌቴሴማኒ በደብረ ዘይትም በከበሩ ቦታዎች ሁሉ የቤተ መቅደስ መሠዊያ እንዲሠሩ አዘዘች፤ ዳግመኛም በዕንቁ በወርቅና በብር እንዲአስጌጧቸው አዘዘች።

❖ በኢየሩሳሌምም ስሙ መቃርስ የሚባል ኤጲስቆጶስ አለ፤ እርሱም ንግሥት ዕሌኒን እንዲህ ብሎ መከራት ይህን እንዲህ አትሥሪ ከጥቂት ዘመናት በኋላ በዚህ አገር ሊነግሡ አሕዛብ ይመጣሉ።

❖"ሁሉን ይማርካሉ ቦታዎችንም ያፈርሳሉ ወርቁን፣ ብሩን፣ ዕንቁውን ይወስዳሉና ነገር ግን ጠንካራ የሆነ የማይናወጽና የማይፈርስ ጥሩ ሕንፃ ልታሠሪ ይገባል ከዚህ የሚተርፈውንም ለድኆችና ለችግረኞች ስጪአቸው አላት።

❖ እርሷም የአባ መቃርስን ምክሩን ተቀብላ መኳንንቱ ሁሉ ለአባ መቃርስ በመታዘዝ በከበሩ ቦታዎች ሁሉ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲአንፁ አዘዘቻቸው።

❖ ከዚህም በኋላ ንግሥት ዕሌኒ ወደ ልጅዋ ንጉሥ ቁስጠንጢኖስ በተመለሰች ጊዜ በኢየሩሳሌም ያደረገችውን ሁሉ ነገረችው ሰምቶ እጅግ ደስ አለው እንደገና ሌላ ብዙ ገንዘብና ሕንፃውን ተቆጣጥረው የሚያሠሩ ሹሞችን ላከ ለሚገነቡና ለሕንፃው ሥራ ለሚአገለግሉ ሁሉ ደመወዛቸውን ሳያጓድሉ ሁል ጊዜ ወደ ማታ እንዲሰጧቸው ንጉሡ አዘዘ።

❖ ስለ ደመወዛቸው እንዳይጮኹና እንዳያዝኑ እግዚአብሔርም ስለ ጩኸታቸው በእርሱ ላይ እንዳይቆጣ ይፈራልና።

❖ ጻድቅ ንጉሥ ቁስጠንጢኖስም በነገሠ በ፴ ዓመቱ የከበሩ ቦታዎች ሕንፃቸው በተፈጸመ ጊዜ ንዋየ ቅዱሳትን ዋጋቸው ብዙ ድንቅ የሆነ የከበሩ የግምጃ ልብሶችንም ላከ።

❖ ደግሞም ወደ ቁስጥንጥንያ ሊቀ ጳጳሳት ኤጲስቆጶሳቶቹን በመያዝ እንዲዘጋጅ እንዲሁም ወደ አንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳትና ወደ እስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት ወደ አባ አትናቴዎስ ኤጲስቆጶሳቶቹን በመያዝ ሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ኢየሩሳሌም ተሰብስበው በከበሩ ቦታዎች ውስጥ የተሠሩትን ወይም የታነፁትን አብያተ ክርስቲያናት እንዲያከብሩ።

❖ ንጉሡም እንዳዘዘ ሁሉም ተሰበሰቡ እስከ መስከረም ወር ዐሥራ ስድስት ቀን ኑረው በዚች ቀን ሁሉንም አብያተ ክርስቲያናት መሠዊያቸውንም አከበሩአቸው የቁርባን ቅዳሴንም ቀድሰው ለምእመናን ሥጋውንና ደሙን አቀበሉ በዚችም ቀን ከቶ እንደርሱ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ ደስታን ሆነ።

❖ የከበረ መስቀልንም በመሸከም በነዚያ በከበሩ ቦታዎች ዞሩ በውስጣቸውም ለእግዚአብሔር ሰገዱ አመሰገኑትም መስቀሉንም አከበሩት ወደ ሀገሮቻቸውም በሰላም በፍቅር ተመልሰው ገቡ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን በመስቀሉ ኃይልም ሁላችን የክርስቲያን ወገኖችን ይጠብቀን ለዘላለሙ አሜን።

        

                  አርኬ

✍️ሰላም ለኢየሩሳሌም ዘተሐንፀ መዝበራ። በጥበበ ቈስጠንጢኖስ ንጉሥ ወለዕሌኒ በምክራ። እለ ነጸሩ ሥርዓታ ወእለ ርእዩ ግብራ። ስብሐት ይብሉ ለክርስቶስ በውስተ ኲሉ አሠራ። እምነ ዓለማት ዘአዕበያ ወአልዓለ ክብራ።

             

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

     የገባኤል ልጅ ጦቢት

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ በዚችም ቀን በፋርስ ንጉሥ አሜኔሶር እጅ ተማርኮ ወደ ነነዌ አገር የተወሰደ ከንፍታሌም ነገድ የገባኤል ልጅ ጦቢት አረፈ።

❖ ይህም ጻድቅ ጦቢት በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ዕውነትና ቅን በሆነ ሕግ ጸንቶ የሚኖር ነው ከወገኖቹም ጋር ከመማረኩ በፊት ለችግረኞች ብዙ ምጽዋትን ይሰጥ ነበር ብዙ ጊዜም የበጎቹን ጠጉርና ከእህሉ ዐሥራቱን ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ይወጣ ነበር ከገንዘቡም ከሦስት አንዱን ለድኆች የሚሰጥ ነው።

❖ በዚያን ጊዜ ሕዝቡ ሁሉም ክደው በዓልና ደማሊ ለሚባሉ ጣዖታት ይሠው ነበር፤ ወገኖቹም ወደ ነነዌ በተማረኩ ጊዜ ሁሉም የአሕዛብን እህል በሉ እርሱ ግን ሰውነቱን ይጠብቅ ነበር የአሕዛብን መብል እንዳይበላ እግዚአብሔርን ያስበው ነበርና

❖ በአንዲት ዕለትም በአደባባይ የወደቀ በድን አግኝተው ነገሩት ወዲያውኑ እህል ሳይቀምስ ተነሥቶ ሔደ ፀሐይም እስከሚገባ ወደ አንድ ቤት ውስጥ አስገብቶ አኖረው ፀሐይ ሲገባም ቆፍሮ ቀበረው በዚያች ሌሊትም እንደ ኃጢአተኛ ሁኖ በእድሞ ሥር ተኝቶ አደረ።

❖ በእድሞውም ላይ ወፎች መኖራቸውን ስለ አላወቀ ፊቱን ገልጦ ሳለ ኩሳቸውን ከዐይኖቹ ላይ ጣሉበት ዓይኖቹም ተቃጠሉ ከእሳቸውም ጢስ ወጣ ታወሩም ባለመድኃኒትም ሊያድነው አልቻለም።

❖ በዚያንም ጊዜ ጦቢት ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ለመነ አቤቱ በቸርነትህ አስበኝ ወደ ችግረኛነቴም ተመልከት ለመማረክና ለመዘረፍ በአደረግኸን በእኔና በአባቶቼ ኃጢአት ተበቅለህ አታጥፋኝ፤ አሁንም በፊትህ ደስ የሚያሰኝህን ነገር አድርግ ከመኖር ሞት ይሻለኛልና በሞት እሰናበት ዘንድ አፈርም እሆን ዘንድ ነፍሴን የሚቀበል መልአክን እዘዝ።

❖ በዚያችም ዕለት የራጉኤል ልጅ ሣራን በጭኗ ያደረ ክፉ አስማንድዮስ የሚባል ጋኔን ለሰባት ባሎች አጋብተዋት ወደርሷ ሲገቡ ሁሉንም ስለገደላቸው ስለዚህ የአባቷ አገልጋዮች ያሽሟጥጧት ነበርና ከሽሙጣቸው ያድናት ዘንድ እያለቀሰች ወደ እግዚአብሔር ትለምን ነበር ጸሎቷና የጦቢት ጸሎትም በልዑል እግዚአብሔር በጌትነቱ ልዕልና ፊት ተሰማ።

❖ ጦቢትም በገባኤል ዘንድ አደራ ያስጠበቀውን የብሩን ነገር አሰበ ልጁ ጦብያንም ጠርቶ ሳልሞት በገባኤል ዘንድ አደራ ያስጠበቅሁትን ብር ትቀበል ዘንድ ከአንተ ጋራ የሚሔድ በደመወዝ የሚቀጠር አሽከር ፈልግ አለው።

❖ ጦብያም አባቴ ሆይ ያዘዝከኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለ ከዚህም በኋላ አሽከር ሊፈልግ ሔደ ቅዱስ ሩፋኤልንም አሽከር በሚሆን ሰው አምሳል አገኘው እርሱም ከጦብያ ጋር መጣ ስሙንም አዛሪያ ነኝ አለ ጦቢትም ላካቸው፤ ሲሔዱም በመሸ ጊዜ ወደ ጤግሮስ ወንዝ ደረሱ ጦብያም ገላውን ይታጠብ ዘንድ ወረደ።

❖ ታላቅ ዓሣም ሊውጠው ተወረወረ ሩፋኤልም ጦብያን ዓሣውን ያዘው አትፍራው እረደውና ጉበቱን፣ ልቡንና፣ አሞቱን ያዝ አለው እርሱም እንዳዘዘው አደረገ።

❖ ጦብያም ሩፋኤልን አንተ ወንድሜ አዛርያ ይህ የዓሣ ሐሞት ጉበቱና ልቡ ምን ይደረጋል አለው፤ አዛርያ የተባለ መልአክም እንዲህ ብሎ መለሰለት ጋኔን ያደረበት ሰው ወንድ ወይም ሴት ጉበቱንና ልቡን ከደቀቀ ዕጣን ጋራ ያጤሱለት እንደሆነ ጋኔን ይሸሻል ሐሞቱም ዐይኖቹ የታወሩ ሰውን ቢኩሉት ይድናል።

❖ ሁለተኛም የራጉኤልን ልጅ ሣራን ያገባት ዘንድ ተናገረው እግዚአብሔርም ይጠብቀዋልና እንዳይፈራ አጽናናው፤ ወደራጉኤል ቤትም በደረሱ ጊዜ ሣራ ተቀብላ ደስ አሰኘቻቸው ከዚህም በኋላ ጦቢያ ሣራን ወደዳት፤ እርሷንም ይሰጠው ዘንድ አባቷን ጠየቀው አባቷም ለሰባት ባሎች አጋብቷት ሰባቱም እንደሞቱ ነገረው ጦብያም የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን አለ።

❖ ወደ ጫጉላ ቤትም በአገቧቸው ጊዜ ሩፋኤል የነገረውን ቃል አስታወሰ የዓሣውንም ጉበትና ልብ ከደቀቀ ዕጣን ጋር አጤሰ ያን ጊዜ አስማንድዮስ የተባለ ጋኔን ሸሸ መልአክ ሩፋኤልም ይዞ ለዘላለሙ አሠረው።

❖ ጦቢያም ሚስቱን ሣራን ይዞ ደስ ብሎት ወደ አባቱ ቤት ተመለሰ አባትና እናቱም በደስታ ተቀበሉት የአባቱንም ዐይኖች በኳለ ጊዜ እንደ ጭጋግ ሁኖ ከዐይኖቹ ተገፈፈ ዐይኑን ዐሸ ወዲያውኑ ድኖ ልጁን አየ።

❖ ከዚህም በኋላ የከበረ መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ራሱን ገለጠላቸው ብዙ ነገርንም ነግሮአቸው ወደ ሰማይ ዐረገ።

❖ ከዚህም በኋላ ከወገኖቹ ጋር ተድላ ደስታን አደረገ ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ መከራ እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ እርሱ በኃጢአታችን ይገርፈናል ደግሞ እርሱ ይቅር ይለናል ሁለተኛም መከራህን የሚያስቡ የተመሰገኑ ናቸው፤ እነርሱ ክብርህን በአዩ ጊዜ በአንተ ደስ ይላቸዋልና አለ።

❖ ዳግመኛም ስለ ኢየሩሳሌም መታነፅ እንዲህ ብሎ ትንቢት ተናገረ ኢየሩሳሌም ሰንፔር መረግድ በሚባል በከበረ ዕንቁ ትሠራለች ድልድልዋ፣ ቅጽርዋ፣ አደባባይዋ፣ ደጆቿም በከበረ ዕንቊ በጠራም ወርቅ ይሠራሉ አደባባይዋም ቢረሌ፣ አትራኮስ፣ ሶፎር በሚባል ዕንቁ ይሠራልና በመንገድዋ ሁሉ ሁሉም እግዚአብሔርን አስቀድሞ የነበረ ወደፊትም የሚኖር እያሉ ያመሰግኑታል ደግሞም ከዓለማት ሁሉ ጽዮንን ከፍ ከፍ ያደረጋት እግዚአብሔር ይመስገን ይላሉ።

❖ ሁለተኛም የእስራኤል ምርኮኞች ከባቢሎን ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚመለሱ ትንቢት ተናገረ ሁለተኛም ደግሞ ዮናስ ከነነዌ እንዲወጣ ልጁን ጦብያን አዘዘው።

❖ ዳግመኛም ልጁን እንዲህ አለው ልጄ ሆይ ምጽዋት እንደምታድንና እንደምታጸድቅ ተመልከት ይህን ተናግሮ በዐልጋው ላይ ሳለ በመቶ ኀምሳ ስምንት ዘመኑ አረፈ በክብርም ቀበሩት።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


                  አርኬ

✍️ሰላም ለጦቢት መፍቀሬ ምጽዋት ዘተብህለ። እስመ ይገብር ምጽዋተ ወብዙኅ ሣህለ። እንዘ ምስለ ሕዝቡ ይሄሉ ሀገረ ነነዌ ማዕከለ። እምከመ ረከበ በእሴ ቅቱለ። እንበለ ይቅብሮ ኢይጥዕም እክለ።

 

❖ በዚችም ቀን ዳግመኛ የቅዱሳን የወርቅላ፣ የስምዖን፣ የመርቄኖስ፣ የሐሊ፣ የሮቂኖስ፣ የሉክያኖስ፣ የአርዝማኖስ፣ የጴጥሮስ፣ የሐና መታሰቢያቸው ሆነ ተርታ ነገርንም እንዳይናገር ደንጊያ ጎርሶ የኖረ የአባ አጋቶን ዕረፍቱ ነው በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


      አርኬ

✍️ ሰላም ለአጋቶን አምሳለ በቀልት ዘፈረየ። ክምረ ክምር ጽድቁ እስከ አስተርአየ። ሰዓተ ፍዳ ወደይን ሶበ ውእቱ ሐለየ። ለዘይነብብ ጽሩዐ ከመ ቦ ሥቃየ። በከናፍሪሁ ማዕዖ ሰብን ወደየ።


📌 መስከረም 16 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.ሕንጸታ ለኢየሩሳሌም

2.ቅድስት እሌኒ ንግሥት

3.ቅዱስ ጦቢት ነቢይ

4.ቅዱሳን ጦብያና ሣራ

5.አባ አጋቶን ባሕታዊ


📌 ወርኀዊ በዓላት

1.ኪዳነ ምሕረት (የሰባቱ ኪዳናት ማሕተም)

2.ቅድስት ኤልሳቤጥ (የመጥምቁ ዮሐንስ እናት)

3.ቅዱስ ገብረ ማርያም ጻድቅ ንጉሠ ኢትዮዽያ (የቅ/ላሊበላ ወንድም)

4.ቅዱስ አኖሬዎስ ንጉሥ ጻድቅ

5.አባ አቡናፍር ገዳማዊ

6.አባ ዳንኤል ጻድቅ

7.ቅዱስ አባ ዮሐንስ ጻድቅ (ወንጌሉ ዘወርቅ)


✍️" ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሒድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ፤ ኢየሩሳሌም ሆይ እግሮቻችን በአደባባይሽ ቆሙ፤ ኢየሩሳሌምስ እርስ በርሷ እንደ ተገለጠች ከተማ ተሠርታለች፤ ስለ ወንድሞቼ ስለ ባልንጀሮቼም በውስጥሽ ሰላም ይሁን አልሁ፤ ስለ አምላካችን ስለ እግዚአብሔር ቤት ላንቺ መልካምነትሽን ፈለግሁ"

📖መዝ 121፥1-9


ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ እምእለ ተፀመድኩ ዘልፈ ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውክፈ እምእለ አብዑ ብዑላን ዘተርፈ።

ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን ሰማዕታት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን ደናግል ዓዲ ወመነኮሳት ኄራን ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን እስከ አረጋዊ ልሂቅ እምንኡስ ሕፃን።

ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ ዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ ወለዘሰምዐ ቃሎ በእዝነ መንፈስ በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኲሉ እምባእስ ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ።


ጌታ ሆይ ከብልፅግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።

እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።

ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን።


ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ፤ እኔም ለእናንተ ከአዘጋጀው በኃዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ   


✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝


✍"ልብህን በእርጋታ አኑረው፤ የሁሉም መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ለመሆን በጣም ትጋ ለከንቱ ንግግር ዘገምተኛና ሰነፍ ሁን፤ ነገር ግን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል በማወቅ በመስማት ድኅነትን የሚሰጡ ናቸውና ብልህ ሁን"

📚ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ


             ወስብሐት ለእግዚአብሔር

                             ይቆየን

 

───────────

                   Channel

 🧲 https://telegram.me/Tewahedo12

       FB Like Page (የፌስቡክ ፔጅ)

🧲 http://facebook.com/Tewahedo12  

       YouTube Subscribe (ሰብስክራይብ)

🧲 https://www.youtube.com/channel/UCvYxUdv1D-5juH_P6iE7XXw

 ───────────


Report Page