ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም ፲፬

ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም ፲፬

@YeBiruk ዲያቆን ቡሩክ ይርጋ ዘውብ

✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

           አሜን

✍"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"         

📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ


         ቀናችንን በጸሎት እንጀምር


ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም ፲፬


አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም ዐሥራ አራት በዚች ቀን ቅዱስ አባት አባ አጋቶን ዘዓምድ አረፈ።

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

     አባ አጋቶን ዘዓምድ 

  ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥


❖ ይህም ቅዱስ ለግብጽ አገር ደቡብ ከሆነ ተንሳ ከሚባል መንደር የሆነ ነው ወላጆቹም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ለድኆችና ለችግረኞች መመጽወትን የሚወዱ ደጎችና ቸሮች ነበሩ። የአባቱም ስም መጥራ የእናቱም ማርያ ነው የምንኲስና ልብስን ይለብስ ዘንድ የሚተጋና በልቡም ሁል ጊዜ የሚያስብና የሚታወክ ሆነ።

❖ ዕድሜውም ሠላሳ አምስት ዓመት በሆነው ጊዜ ቅስና ተሾመ ከዚህ ዓለምም የሚወጣበትን መንገድ ይጠርግለት ዘንድ ወደ ገዳም ሒዶ በዚያ እንዲመነኲስ እግዚአብሔርን እየለመነው የከበረች ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል የተጠመደ ሆነ።

❖ ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያት ሰጥቶት ከሀገሩ ወጣ መርዩጥ ወደሚባልም አገር ገባ ከዚያም ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ በመነኰስ አምሳል ከእርሱ ጋር በመጓዝ ወደ ቅዱስ አባ መቃርስ ገዳም እስከ አደረሰው ድረስ እየመራው ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደ፤ ለከበሩ አረጋውያንም ለአባ አብርሃምና ለአባ ገዐርጊ ደቀ መዝሙር ሁኖ ከእሳቸው ጋር ሦስት ዓመት ያህል ኖረ።

❖ ከዚህም በኋላ በአባ ዮሐንስ ቤተ መቅደስ ፊት አቆሙት በምንኵስናው ልብስና በአስኪማው ላይ ሦስት ቀኖች ያህል ጸልየው አለበሱት ከዚያችም ቀን ወዲህ ተጋድሎውንና የእግዚአብሔርን አገልግሎት እጥፍ ድርብ አደረገ።

❖"ተጋድሎውም ሁል ጊዜ በቀንና በሌሊት በመጾም፣ በመጸለይ የሥጋው ቆዳ ከዐጥንቱ እስቲጣበቅ ያለ ምንጣፍም በምድር ላይ በመተኛት ሆነ።

❖ ሁል ጊዜም የአባ ስምዖን ዘዓምድን ገድል ያነብ ነበረ መንፈሳዊ ቅናትንም ቀንቶ ራሱን በገድል እሥረኛ ሊያደርግ በልቡ አስቦ ለከበሩ አባቶች አማከራቸው እነርሱም ይህ ሀሳብ መልካም ነው አሉት በላዩም ጸለዩ ከእርሳቸውም በረከትን ተቀብሎ ከገዳም ወጣ ለዓለም ቅርብ ወደ ሆነ ስካ ወደሚባል አገር ሒዶ በአንዲት ትንሽ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተቀመጠ ምእመናንም ዓምድ ሠሩለት፤ በዚያ ላይም ወጥቶ እየተጋደለና እያገለገለ ሃምሳ ዓመት ያህል ቆመ።

❖ በዘመኑም ሰይጣን ያደረበት ሰው ተገለጠ ብዙ ወገኖችንም አሳታቸው እርሱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚቀመጥ ሁኖ ትምህርቱን የሚሰሙ ሕዝቦች የዕንጨት ቅርንጫፎችን በመያዝ በዙሪያው ይቀመጣሉ አባ አጋቶንም ልኮ ወደርሱ አስመጣው በላዩም ጸለየና በሰውዬው ላይ አድሮ ለሰዎች በመናገር የሚያስተውን ሰይጣን ከእርሱ አስወጣው።

❖ እንዲሁም ሰማዕት ሚናስ ያነጋግረኛል የምትል ሴት ተነሥታ በቅዱስ ሚናስ ስም የውኃ ጒድጓድ እንዲቆፍሩ በጠበሉ ውኃ ተጠምቀው ከደዌያቸው እንዲፈወሱ የአገርዋን ሰዎች አዘዘቻቸው ያቺንም ሴት ወደርሱ አስመጥቶ በላይዋ ጸለየ ርኵስ መንፈስንም ከእርሷ አስወጣው የዚያችንም የአገርዋን ሰዎች አዘዘቻቸው ያችንም ሴት አዘዛቸው።

❖ ዳግመኛም ሌላ ሰው ተነሣ እርሱም ጋኔን ይዞ ያሳበዳቸውን ሰበሰባቸው ሲደበድባቸውም ለጥቂት ጊዜ ጋኔኑን ያስተዋቸዋል ብዙዎችም ጋኔን የያዛቸው ወደርሱ ተሰበሰቡ ቅዱስ አባ አጋቶንም ወደርሱ እንዲመጣ ወደ ሰውዬው ላከ ሰውዬውም ትእዛዙን ሰምቶ አልመጣም የስሕተት ሥራውንም አልተወም። የዚያችም አገር ገዥ ሲያልፍ የሰበሰባቸው እብዶች ሰደቡት ረገሙትም ስለዚህ ያን ሰው መኰንኑ ይዞ ጽኑ ሥቃይን አሠቃየውና በሥቃዩ ውስጥ ሞተ።

❖ ሌላው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድ ቄስ ነበረ እርሱም ከአንዲት ሴት ጋር በዝሙት ወደቀ የአካሉም እኩሌታ በደዌ ተበላሸ ተሸክመውም ወደ አባ አጋቶን አደረሱት እርሱም ጸልዮለት በእግዚአብሔር ስም አዳነው ያንንም ቄስ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ እንዲጠነቀቅና በክህነቱም እንዳያገለግል አዘዘው።

❖ ይህም ቅዱስ አባ አጋቶን ብዙ ተአምራትን አደረገ ብዙዎች በሽተኞችንም አዳናቸው። ከዚህም በኋላ በመላእክት አምሳል በመልካም ዝማሬ በመዘመር እያመሰገኑት ሰይጣናት ተገለጡለት እርሱ ግን የክብር ባለቤት ክርስቶስ በሰጠው ጸጋ ሽንገላቸውን አውቆ አዳኝ በሆነ በመስቀል ምልክት አማተበባቸው ፈጥነውም ከፊቱ ተበተኑ።

❖ ክብር ይግባውና እግዚአብሔርም ከዚህ ዓለም ድካም ሊአሳርፈው በወደደ ጊዜ ጥቂት ታሞ ነፍሱን በእግዚአብሔር እጅ አስረከበ። ከዚህም በፊት ሕዝቡ ወደርሱ ይሰበሰቡና የእግዚአብሔርን መንገድ ያስተምራቸውና በጸሎቱም ከበሽታቸው ይፈውሳቸው ስለነበር አሁን በአረፈበት ላይ በአገኙት ጊዜ መሪር ልቅሶን አለቀሱ እነርሱ የሚያጽናናቸውን አባታቸውን በማጣት ከእርሱ ከቅዱስ አባት በመለየት የሙት ልጆች ሁነዋልና።

❖ መላው የሕይወቱ ዘመንም መቶ ዓመት ሆነ ከርሱም ሠላሳ አምስቱን በዓለም ውስጥ ኖረ። ዐሥራ አምስቱን ዓመት በገዳም ኖረ ኃምሳውን በዓምድ ላይ ቁሞ ኖረ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ ጻድቅ ጸሎት ይማረን በረከቱም  ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


      አርኬ

✍️ሰላም ለአጋቶን አክሊላ ወሞገሳ። ለሀገረ ተንሳ። በብዙኅ ጻሕቅ ለመንግሥተ ሰማይ እንዘ የኃሥሣ። ፃመወ ዓመታተ እስራ ወሠላሳ። ወበላዕለ ዓምድ አዝማናተ ኃምሳ።

      

      

❖ በዚችም ቀን ቀሲስ ዴግና አረፈ። ደግሞ የሰማዕት መቃራ፣ የበርተሎሜዎስ፣ የአውዳራና፣ የናሶን መታሰቢያቸው ነው።

እግዚአብሔርም በጸሎታቸው ይማረን ለዘላለሙ አሜን።


       አርኬ

✍️ሰላም ለከ ዴግና ካህን። ዘተዓርግ ዘልፈ ጸሎተ ቅዱስ ቊርባን። እማየ ንስሐ ንዝኃኒ በእራኅከ ዘይምን። ኢይትአተት በአበሳየ እምስብሐተ ክርስቶስ መድኅን። እለ ኢትቀርቡ ጻኡ ሶበ ይብል ዲያቆን።


❖ በዚችም ቀን ደግሞ የፃና መምህራን ለሆኑ አባቶች ዐሥራ አንደኛ የሆነ የፃና መምህር ቅዱስ አባት አባ ጴጥሮስ አረፈ።

❖ ይህም በሥራው ሁሉ እውነተኛና ንጹሕ በቀንና በሌሊትም በጾምና በጸሎት የተጠመደ ሆነ። ሕዝቡም በጎ ሥራውንና ቅድስናውን በአዩ ጊዜ ለመምህርነት መርጠው ሾሙትና በሹመቱ ወንበር አርባ ስምንት ዓመት በሰማዕት ገላውዴዎስ መቅደስ ኖረ።

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱሳን ሁሉ ጸሎት ይማረን ለዘላለሙ አሜን።


📌 መስከረም 14 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.አባ አጋቶን ዘዓምድ

2.አቡነ ያሳይ ዘመንዳባ

3.አባ ዼጥሮስ መምሕረ ጻና (ጣና)

4.ቅዱስ ዴግና ቀሲስ


📌 ወርሐዊ በዓላት

1.አቡነ አረጋዊ (ዘሚካኤል)

2.ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ መርዓዊ

3.ቅዱስ ፊልዾስ ሐዋርያ

4.ቅዱስ ሙሴ (የእግዚአብሔር ሰው)

5.አባ ስምዖን ገዳማዊ

6.አባ ዮሐንስ ጻድቅ

7.እናታችን ቅድስት ነሣሒት


✍️ "ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፤ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል፤ ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ውሃ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ እውነት እላችኋለሁ ዋጋው አይጠፋበትም"

📖ማቴ 10፥41-42


ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ እምእለ ተፀመድኩ ዘልፈ ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውክፈ እምእለ አብዑ ብዑላን ዘተርፈ።

ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን ሰማዕታት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን ደናግል ዓዲ ወመነኮሳት ኄራን ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን እስከ አረጋዊ ልሂቅ እምንኡስ ሕፃን።

ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ ዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ ወለዘሰምዐ ቃሎ በእዝነ መንፈስ በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኲሉ እምባእስ ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ።


ጌታ ሆይ ከብልፅግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።

እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።

ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን።


ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ፤ እኔም ለእናንተ ከአዘጋጀው በኃዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ   


✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝


✍"ልብህን በእርጋታ አኑረው፤ የሁሉም መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ለመሆን በጣም ትጋ ለከንቱ ንግግር ዘገምተኛና ሰነፍ ሁን፤ ነገር ግን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል በማወቅ በመስማት ድኅነትን የሚሰጡ ናቸውና ብልህ ሁን"

📚ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ


             ወስብሐት ለእግዚአብሔር

                             ይቆየን 


───────────

                   Channel

 🧲 https://telegram.me/Tewahedo12

       FB Like Page (የፌስቡክ ፔጅ)

🧲 http://facebook.com/Tewahedo12  

       YouTube Subscribe (ሰብስክራይብ)

🧲 https://www.youtube.com/channel/UCvYxUdv1D-5juH_P6iE7XXw

 ───────────


Report Page