ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም ፲፩
@YeBiruk ዲያቆን ቡሩክ ይርጋ ዘውብ✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
አሜን
✍"ችግር ለራሳችን እንድንጸልይ ያነቃቃናል፤ ፍቅር ደግሞ ለሌሎች ሰዎች እንድንጸልይ ያስገድደናል"
📚ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ
ቀናችንን በጸሎት እንጀምር
ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም ፲፩
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በውልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም ዐሥራ አንድ በዚች ቀን ለአንጾኪያ ነገሥታት አባታቸውና መካሪያቸው የሆነ ቅዱስ ፋሲለደስ በሰማዕትነት አረፈ።
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
ቅዱስ ፋሲለደስ
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❖ እርሱም ለሮም ንጉሥ የሠራዊት አለቃ ነው መንግሥቱም ሁለመናዋ በእርሱ ምክር የጸናች ናት፤ ብዙዎችም ወንዶችና ሴቶች የቤት ውልዶች አገልጋዮች አሉት።
❖ ዝምድናውም እንዲህ ነው ስሙ ኑማርያኖስ የተባለ የሮም ንጉሥ ለቴዎድሮስ በናድሌዎስ እናቱ የሆነች የቅዱስ ፋሲለደስን እኅት አግብቶ ዮስጦስን፣ ገላውዴዎስን፣ አባዲርን ወለደችለት እሊህም ለቅዱስ ፋሲለደስ የእኅቱ ልጆች ናቸው።
❖ የቅዱስ ፋሲለደስም ሚስት ለቅዱስ ፊቅጦር እናት እኅት ናት ከእርሷም ስማቸው አውሳብዮስና መቃርስ የተባሉ ሁለት ልጆችን ወለደ።
❖ በዚያም ወራት የቊዝና የፋርስ ሰዎች የሮምን ሰዎች ሊወጓቸው በላያቸው ተነሡ ያን ጊዜ የንጉሥ ልጅ ዮስጦስን የፋሲለደስ ልጅ አውሳብዮስን ከጦር ሠራዊቶቻቸው ጋር ለውጊያ ላኳቸው ።
❖ ንጉሡ ኑማርዮስም ሌሎች ጠላቶች በተነሡበት በኩል ለጦርነት ሒዶ በውጊያው ውስጥ ሞተ የሮም መንግሥትም የሚጠብቃትና የሚመራት የሌላት ሆነች።
❖ እንዲህም ሆነ በዚያ ወራት ስለ ጦርነት ለመደራጀት የሮም ሰዎች ከሀገሩ ሁሉ አርበኞች የሆኑ ሰዎችን ሰበሰቡ ከውስጣቸውም ከላይኛው ግብጽ ስሙ አግሪጳዳ የሚባል የፍየሎች እረኛ የሆነ አንድ ሰው አለ፤ እርሱንም መኳንንቱ ወስደው በመንግሥት ፈረሶች ላይ ባልደራስ አድርገው ሾሙት እርሱም በጠባዩና በሥራው ሁሉ ኃይለኛና ብርቱ ነበር።
❖ ከንጉሥ ኑማርያኖስ ሴቶች ልጆች አንዲቱ ወደርሱ በመስኮት ተመለከተች ወደደችውም መልምላም ወስዳ አገባችው ስሙንም ዲዮቅልጥያኖስ ብላ ሰይማ አነገሠችው።
❖ ከጥቂት ቀኖችም በኋላ ሰማይና ምድርን የፈጠረ እግዚአብሔርን ትቶ ጣዖታትን አመለከ ቅዱስ ፋሲለደስም ሰምቶ እጅግ አዘነ የመንግሥትንም አገልግሎት ተወ።
❖ ከዚህም በኋላ የንጉሥ ኑማርያኖስ ልጅ ዮስጦስና የፋሲለደስ ልጅ አውሳብዮስ ጠላቶቻቸውን ድል አድርገው የጠላቶቻቸውንም አገሮች አጥፍተው ደስ ብሏቸው ተመለሱ፤ ነገር ግን የነገሠው ዲዮቅልጥያኖስ የክብር ባለቤት ክርስቶስን ክዶ አምልኮ ጣዖትን አቁሞ አገኙት እጅግም አዘኑ ተቆጥተውም ተነሡ ሰይፎቻቸውን መዝዘው ዲዮቅልጥያኖስን ገድለው የንጉሥ ኑማርያኖስን ልጅ ዮስጦስን ሊያነግሡ ወደዱ ፋሲለደስም ከዚህ ሥራ ከለከላቸው።
❖ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ፋሲለደስ ዘመዶቹን፣ ሠራዊቱን፣ አገልጋዮቹንም ሁሉ ሰበሰባቸውና በክብር ባለቤት በክርስቶስ ስም ደሙን ሊያፈስ እንደፈለገ አስረዳቸው ሁሉም እንዲህ ብለው መለሱለት አንተ በምትሞትበት ሞት እኛ ከአንተ ጋር እንሞታለን በዚህም ምክር በአንድነት ተሰማሙ።
❖ ከዚህም በኋላ በንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ፊት ቁመው ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ ከእርሳቸውም ግርማ የተነሣ ታላቅ ፍርሃትን ፈራ እነርሱ የመንግሥት ልጆች ናቸውና።
❖ የቅዱስ ፊቅጦር አባት ኀርማኖስም ወደ ግብጽ አገር ይልካቸው ዘንድ በዚያም እንዲአሠቃዩአቸው መከረው ሁሉንም እየአንዳንዳቸውን ለብቻቸው አድርጎ ላካቸው አባዲርንና እኀቱ ኢራኒን ወደ አንዲት አገር፣ አውሳብዮስንና ወንድሙ መቃርስን ወደሌላ ቦታ፣ ገላውዴዎስንም እንዲሁ አደረጉ፤ በናድሌዎስ ቴዎድሮስም እሼ በሚባል ዕንጨት ላይ በመቶ ሃምሳ ሦስት ችንካር ተቸንክሮ ገድሉን ፈጸመ።
❖ ቅዱስ ፋሲለደስን ግን አምስት ከተማዎች ወዳሉበት ወደ አፍሪካ ምድር ወደ መኰንኑ ወደ መጽሩስ ላከው መጽሩስም በአየው ጊዜ መንግሥቱን ክብሩን ስለ ተወ እጅግ አደነቀ።
❖ ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስም መልአኩን ልኮ በመንፈስ ወደ ሰማይ አውጥቶ በብርሃን ያጌጠ መንፈሳዊ ማደሪያን አሳየው ነፍሱም እጅግ ደስ አላት ከዚህም በኋላ ወደነበረበት መለሰው።
❖ ባሮቹን ግን ነፃ ያወጣቸው አሉ የቀሩትም ከእርሱ ጋር የሰማዕትነት አክሊልን የተቀበሉ ሰባት ሺህ ሠላሳ ሦስት የሚሆኑ አሉ።
❖ ቅዱስ ፋሲለደስንም ታላቅ ስቃይን አሰቃዩት በመንኰራኲርና በተሣሉ የብረት ዘንጎች ሥጋውን ሰነጣጥቀውት ሞተ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ያለ ጥፋት ከሞት አድኖ አስነሣው አሕዛብም ሁሉ ይህን ድንቅ
ተአምር በአዩ ጊዜ አደነቁ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም አመኑ መኰንኑንም ረገሙት ጣዖቶቹንም ሰደቡ በእነርሱ ላይም ተቆጥቶ ራሶቻቸውን በሰይፍ ይቆርጧቸው ዘንድ ወታደሮቹን አዘዘ የሰማዕትነት አክሊልንም ተቀበሉ ቊጥራቸውም ዐሥራ አራት ሺህ ሰባት መቶ ወንዶች ሠላሳ ሰባት ሴቶች ናቸው።
❖ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ፋሲለደስን ሥጋው ሁሉ ቀልጦ እንደ ውኃ እስከሚሆን በብረት ምጣድ ውስጥ አበሰሉት መኰንኑም በተራራ ላይ ጥልቅ ጒድጓድ ቆፍረው በዚያ እንዲቀብሩት አዘዘ እንዲሁም አደረጉ።
❖"ያን ጊዜም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ፋሲለደስን ከሞት ደግሞ አስነሣው ወደ መኰንኑም መጥቶ እንዲህ ብሎ ጮኸ መኰንን መጽሩስ ሆይ እፈር ከሀዲ ንጉሥህም የረከሱ ጣዖቶችህም ይፈሩ እነሆ ክብር ይግባውና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ጉዳት ከሞት ጤነኛ አድርጎ አስነሥቶኛልና።
❖ ሕዝቡም ይህን ተአምር በአዩ ጊዜ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምነው በሰማዕትነት ሞቱ ቁጥራቸውም ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ሆነ።
❖ ከዚህም በኋላ ቅዱስ ፋሲለደስን በውስጧ መጋዝ ካላት መንኰራኲር ላይ አውጥቶ ታላቅ ሥቃይን አሠቃየው ዳግመኛም በብረት ዐልጋ ላይ በሆዱ አስተኝተው ከበታቹ እሳትን አነደዱ ያን ጊዜም ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገለጠለት ከዚያ ስቃይም ውስጥ አንስቶ ያለ ጉዳት ጤነኛ አደረገው እንዲህም ብሎ ቃል ኪዳን ሰጠው ፋሲለደስ ሆይ ዕውቅ መታሰቢያህን ለሚያደርግ ሁሉ ወይም ለድኆች በስምህ ምጽዋትን ለሚሰጥ ወይም ለተራቈተ ልብስን ወይም በመታሰቢያህ ቀን ለቤተ ክርስቲያን መባ ለሚሰጥ በብዙም ቢሆን በጥቂት መታሰቢያህን ለሚያደርጉ ሁሉ እኔ በደላቸውን ሁሉ እተውላቸዋለሁ መኖሪያቸውንም በመንግሥተ ሰማያት ከአንተ ጋራ አደርጋለሁ ።
❖ ጌታችንም ይህን ካለው በኋላ በታላቅ ክብር ወደ ሰማያት ዐረገ ቅዱስ ፋሲለደስም በፍጹም ደስታ ደስ ተሰኘ።
❖ ከዚህም በኋላ መጽሩስ መኰንን ከአማካሪዎቹ ጋር ተማከረ እንዲህም አላቸው ስሙ ፋሲለደስ ስለሚባል ስለዚህ ሰው ምን ላድርግ እርሱን ያላሠቃየሁበት የሥቃይ መሣሪያ ምንም የቀረ የለም ከሐሳቡም አልተመለሰም እነርሱም እንዲህ ብለው መከሩት ራሱን በሰይፍ ቆርጠህ ከእርሱ ተገላገል እነሆ የዚች አገር ሰዎች በእርሱ ምክንያት አልቀዋልና።
❖ በዚያንም ጊዜ የቅዱስ ፋሲለደስን ራስ በሰይፍ እንዲቆርጡ መኰንኑ አዘዘና ቆረጡት የድል አክሊልን ተቀበለ ንቆ ሰለ ተዋት ምድራዊት መንግሥት ፈንታም ሰማያዊት መንግሥት አገኘ፤ ከሥጋውም ድንቆች የሆኑ ታላላቅ ተአምራት ተገለጡ ከእርሱም ጋር ሰማዕት ሁነው የሞቱ ሁሉም ቊጥራቸው ሃያ ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ዘጠና ሦስት ሆነ።
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ፋሲለደስና በሰማዕታት ሁሉ ጸሎት ይማረን በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
አርኬ
✍️ ሰላም ለፋሲለደስ እምነ ክሣዱ ዘአንጠብጠበ። ደመ ቀይሐ ወጸዓድዒደ ሐሊበ። ምስለ አዝማዲሁ ወሰብኡ እስመ ለሞት ተውህበ። በከመ ኮኖሙ ዲበ ምድር አበ። ዘበሰማያት ተሠይመ አቡሆሙ ካዕበ።
✍️ሰላም ለክሙ ለፋሲለደስ ማኅበሩ። እለ አንሶሰውክሙ ፍና አሠሩ። ርኅሩኃን አጋእዝትየ ዘኢትትዔወሩ። ቃልየ ሕልቀተ በልብክሙ አንብሩ። ወከመ ማዕተብ በመዝራዕት ጽራሕየ ፁሩ።
✍️ ሰላም ለከ አበ ሰማዕታት ዘአንጾኪያ። ወክቡር በኢትዮጵያ። ፋሲለደስ ርእሰከ ሶበ መተሩ ሕዝበ ሮምያ። ለቀበላከ ወረዱ እምሰማይ እንዘ ይብሉ ሃሌ ሉያ። መላእክቲሁ ኩሎሙ ለክርስቶስ ኬንያ። አመ አቀሙከ ዐውደ መኳንንተ ላኳ ወጋእዝ። ዐጽቀከ እስከ ይመትሩ እምጒንደ ክሣድከ አርዝ። ፋሲለደስ ትቤ በንባብከ ሐዋዝ። ኢይፈርህ አንሰ ሞተ ሥጋ ወሰሪበ ስቴ ዘሕምዝ። ዳግመ እምዝ ኢይረክቦ ሞት ከመዝ ዳግመ እምዝ።
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
ቅድስት በነፍዝዝ ሰማዕት
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❖ በዚች ቀን የስሟ ትርጓሜ ጣፋጭ የሆነ የከበረች በነፍዝዝ በሰማዕትነት አረፈች፤ ይቺም ቅድስት በእድሜዋ ፈጽማ የሸመገለች ነበረች በፋርስ ንጉሥ በሳቦር ዘመንም መከራ ተቀበለች ከዘጠኝ መቶ ክርስቲያን ጋር ማርከው ወስደው አሠሩዋት የሠራዊቱም አለቃ ታላቅ ሥቃይን አሠቃይቶ ከዚያ በኋላ ራሷን በሰይፍ ቆረጠ።
❖ ራሷንም ከአስቆረጣት በኋላ ከአንገቷ የፈሰሰው ደም እስከ ራቀ ድረስ ወደ ላይ ወጣ ከዚያ የተቀመጡ ጠላቶችም ኃይላቸው ደከመ። የፀሐይ ብርሃንም ጨለመ በዚያም ቦታ ደግሞ ጣፋጭ የሆነ መዐዛ ተመላ።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
አርኬ
✍️ሰላም እብል ለሰማዕት በነፍዝዝ። ብሂለ ጼና ምዑዝ። አመ ኮነት ስምዐ በኃይለ ሃይማኖት አዚዝ። በሰዓተ ሞታ ደመነ ቤዝ። ወጼና ዕፍረት ጼነወ ዘጥቀ ሐዋዝ።
✍️ ሰላም ለክሙ ማኅበረ በነፍዝዝ ሙቁሐን። ተሰዓቱ ምእት ዘኁልቊክሙ ክርስቲያን። ወምስሌክሙ እቁም ዐዐደ ፍሡሐን። ያስተርኢ አምሳለ ቅብዕ ውስተ ገጽየ ኅዙን። እምብርሃንክሙ ዘተወልደ ስን።
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
ሱርስ፣ አጤኬዎስ፣ መስተሐድራ
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❖ በዚችም ቀን ስማቸው ሱርስ፣ አጤኬዎስ፣ መስተሐድራ የሚባል ሦስት ገበሬዎች የእስና አገር ሰዎች በሰማዕትነት አረፉ።
❖ አርያኖስም ከሀገሪቱ በስተደቡብ ምንም ሳያስቀር ወታደሮቹ እስከ ደከሙ ድረስ ሰይፋቸውንም ወደ አፎቱ መልሰው ነበር የአገር ሰዎችን ጨርሶ ገድሎ ሲመለስ እሊህ ሦስቱ ገበሬዎች ከዱር ሲመለሱ በከተማ መካከል በተገናኙት ጊዜ እኛ ክርስቲያኖች ነን ብለው በግልጥ ጮኹ አርያኖስም ሰምቶ ወታደሮቹን እሊህን ገበሬዎች ትገድሏቸው ዘንድ ይገባል አላቸው።
❖ ወታደሮቹም እኛ ደክመናል ሰይፎቻችንንም ወደ አፎታቸው አስገብተናል አሉት እሊህ ቅዱሳንም ሰምተው እነሆ መቆፈሪያዎች ከእኛ ጋራ አሉ በእነርሱ ግደሉን አሉ ከዚያም አንገታቸውን በደንጊያ ላይ አድርገውላቸው ቆረጡአቸው
እግዚአብሔርም በጸሎታቸው ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
አርኬ
✍️ ሰላም እብል ነሣእያነ ሕማም ወመከራ። ሠለስቱ ዕደው ለገራህተ እስና ተቅራመ ማእረራ። ከመ ኢይኩኑ እሉ ንቱጋነ እማኅበራ። ሶበ ተኀጥአ መጥባሕት ለክሣዶሙ ዘይመትራ። መክርያቲሆሙ ወሀቡ ለሐራ።
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
ጻድቅ ሰው ቆርኔሌዎስ
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❖ በዚችም ቀን የጭፍራ አለቃ የሆነ ትሩፋቱና ገድሉም ያማረ ጻድቅ ሰው ቆርኔሌዎስ የዕረፍቱ መታሰቢያ ነው እርሱም በቅዱሳን አባቶቻችን ሐዋርያት ዘመን እግዚብሔርን ያገለገለ ነው።
❖ የእግዚአብሔር መልአክም ተገልጦለት ሐዋርያ ጴጥሮስን ይጠሩት ዘንድ ሰዎችን እንዲልክ ጴጥሮስም ወደርሱ እንዲመጣ ሊሠራው የሚገባውን ከእርሱ ከጴጥሮስ እንዲሰማ አዘዘው።
❖ ጴጥሮስም ወደርሱ በደረሰ ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል አስተማረው ለርሱና ከእርሱ ጋር ላሉት ሁሉ ከሁሉ ቤተሰቡ ጋር አምኖ ተጠመቀ።
❖ ከዚህ በኋላ ጴጥሮስ ለእስክንድርያ አገር ቅስና ሾመው ወደርሷ በደረሰ ጊዜ የጣዖታትን አምልኮ ተመልታ አገኛትና አስተማራቸው ብዙዎችንም ወደቀናች ሃይማኖት መልሶ አጠመቃቸው መኰንኑ ድሜጥሮስም አምኖ ከወገኖቹ ጋር በእርሱ እጅ ተጠመቀ።
❖ የኑሮውን ዘመንና ሐዋርያዊ ተጋድሎውን አድርሶ በሰላም አረፈ እርሱም ከአሕዛብ አስቀድሞ ያመነ የመጀመሪያ አማኒ ነው።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
ቅድስት ታዖድራ
✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥
❖ በዚችም ቀን ከእስክንድርያ አገር በንጉሥ ዘይኑን ዘመን ቅድስት ታዖድራ አረፈች።
❖ ይችንም ቅድስት ሌላ ሰው አስገድዶ ከባሏ ወስዶ ከባሏ ጋር ያላትን አንድነት አበላሸ ያን ጊዜም ታላቅ ኀዘን በማዘን ተጸጸተች መሪር ልቅሶንም አለቀሰች የወንዶችንም ልብስ ለብሳ ወንድ መሰላ ከእስክንድርያ በሥውር ወጣች ስሟንም ቴዎድሮስ ብላ ሰየመችና ወደ ወንዶች ገዳም ገባች የምንኲስና ልብስንና የመላእክትን አስኬማ ለበሰች።
❖ የሚያዩዋት ሁሉ እርሷ እንደ ጃንደረባ የሆነች ወንድ ትመስላቸው ነበር እርሷ ግን በረኃብ፣ በጽምዕ ሌሊት በመትጋት ቀን በመቆም ጸንታ በመጋደል ላይ ታገሠች እንዲህም በመጋደል ተጠምዳ ብዙ ዘመን ኖረች።
❖ በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ አንድ ሰው ከአንዲት ብላቴና ጋር አመነዘረ እርሷም ፀንሳ ወንድ ልጅን ወለደች ወላጆቿም ድንግልናሽን ያጠፋው ማነው ብለው ጠየቋት እርሷም በገዳም ውስጥ የሚኖር አባ ቴዎድሮስ እርሱ ደፍሮኝ ከእርሱ ፀነስኩ ብላ በዚች ቅድስት ታኦድራ ላይ በሐሰት ተናገረች።
❖ ወላጆቿም በሰሙ ጊዜ እጅግ አዘኑ ሕፃኑንም ወደዚያ ገዳም አበ ምኔት ወሰዱት እንዲህም አሉት ይህ ሕፃን የልጅህ የመነኵሴው የቴዎድሮስ ልጅ ነው።
❖ ያን ጊዜም አበ ምኔቱ ይቺን ቅድስት ታኦድራን ጠራትና እንዲህ አላት ይህን ክፉ ሥራ ለምን ሠራህ በመነኰሳቱም ሁሉ ላይ ኀፍረትንና ጒስቁልናን አመጣህ እርሷ ሴት መሆኗን አላወቀምና እርሷም አባቴ ሆይ በድያለሁና ይቅር በለኝ አለችው።
❖ አበ ምኔቱም ተቆጥቶ ከገዳሙ አስወጥቶ አባረራት በበረሀ ውስጥ ሰባት ዓመት ኖረች ያም ሕፃን ከእርሷ ጋር ሁኖ ከሰይጣናት በሚመጡባት በብዙ መከራዎች ብዙ መከራዎች ላይ ታገሠች ብዙ ሥቃያትንም ፈጽሞ አሠቃዩዋት።
❖ ከዚህም በኋላ ዳግመኛ ተቀብለው ወደ ገዳም አስገቡአት ጥቂት ቀንም ኖረች መልካም ተጋድሎዋንም ፈጽማ በሰላም አረፈች ነፍሷንም በእግዚአብሔር እጅ ሰጥታ የዘላለም ሕይወትን አገኘች።
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቷ ይማረን ለዘላለሙ አሜን።
አርኬ
✍️ሰላም እብል ለብፅዕት ታኦድራ። እግዚአብሔር ዘአፍቀራ። በስምዐ ሐሰት እኩይ አመ ሰደድዋ እምደብራ። ነበረት ውስተ ገዳም በብዙኀ መከራ። ዘኢወለደት ሕፃነ ፀዊራ።
❖ በዚችም ዕለት የቅዱሳን የባስልዮስ ሰማዕትና የኢየሩሳሌም ኤጲስቆጶስ የቴዎድሮስ የሰማዕታት አለቃ የቀውስጦስም መታሰቢያቸው ነው።
በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
📌 መስከረም 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
1.ቅዱስ ፋሲለደስ ሰማዕት
2.ቅድስት ታኦድራ እናታችን
3.ቅዱስ ቆርኔሌዎስ ሐዋርያዊ (ሐዋ. 10ን ያንብቡ)
4.ቅድስት በነፍዝዝ ሰማዕት
5. "3ቱ" ገበሬዎች ሰማዕታት (ሱርስ፣ አጤኬዎስና ፣ መስተሐድራ)
📌 ወርሐዊ በዓላት
1.ቅዱስ ያሬድ ካህን
2.ማር ገላውዴዎስ ሰማዕት
3.ብፁዐን ኢያቄምና ሐና
4.አቡነ ሐራ ድንግል ጻድቅ
✍️"ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ወይስ ጭንቀት ወይስ ስደት ወይስ ራብ ወይስ ራቁትነት ወይስ ፍርሃት ወይስ ሰይፍ ነውን? 'ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን እንደሚታረዱ በጐች ተቈጠርን' ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው፤ በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን"
📖ሮሜ 8፥35
ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ እምእለ ተፀመድኩ ዘልፈ ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውክፈ እምእለ አብዑ ብዑላን ዘተርፈ።
ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን ሰማዕታት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን ደናግል ዓዲ ወመነኮሳት ኄራን ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን እስከ አረጋዊ ልሂቅ እምንኡስ ሕፃን።
ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ ዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ ወለዘሰምዐ ቃሎ በእዝነ መንፈስ በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኲሉ እምባእስ ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ።
ጌታ ሆይ ከብልፅግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።
እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።
ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን።
ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ፤ እኔም ለእናንተ ከአዘጋጀው በኃዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ
✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝
✍"ልብህን በእርጋታ አኑረው፤ የሁሉም መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ለመሆን በጣም ትጋ ለከንቱ ንግግር ዘገምተኛና ሰነፍ ሁን፤ ነገር ግን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል በማወቅ በመስማት ድኅነትን የሚሰጡ ናቸውና ብልህ ሁን"
📚ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ይቆየን
🇹 🇪 🇼 🇦 🇭 🇪 🇩 🇴
Share
─────────────────
Channel
https://telegram.com/Tewahedo12
FB Like Page (የፌስቡክ ፔጅ)
http://facebook.com/Tewahedo12
YouTube Subscribe (ሰብስክራይብ)
https://www.youtube.com/channel/UCvYxUdv1D-5juH_P6iE7XXw
─────────────────