ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም ፯

ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም ፯

@YeBiruk ዲያቆን ቡሩክ ይርጋ ዘውብ

✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

           አሜን


✍"በቸርነትህ ዓመታትን ታቀናጃለህ"

📖መዝ 64፥11

         ቀናችንን በጸሎት እንጀምር

ስንክሳር ዘወርኀ መስከረም ፯

አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም መስከረም ሰባት በዚች ቀን የከበረና የተመሰገነ የእስክንድርያ አገር ሊቀ ጳጳሳት አባ ዲዮስቆሮስ አረፈ እርሱም ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሃያ አምስተኛ ነው።


   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

    ሊቀ ጳጳሳት አባ ዲዮስቆሮስ

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ ስለ ቀናች ሃይማኖትም ታላቅ ተጋድሎን ከተጋደለ በኋላ ዕረፍቱ በተሰደደበት በደሴተ ጋግራ ሆነ፤ ይህም እንዲህ ነው ንጉሥ መርቅያኖስ ወደ ሰበሰበው ጉባኤ በጠሩት ጊዜ ሲደርስ ብዛታቸው ስደስት መቶ ሠላሳ ስድስት የሆነ ታላቅ ጉባኤን አየ፤ አለ እንዲህም ይህ ታላቅ ጉባኤ እስቲሰበሰብ ድረስ በሃይማኖት ላይ የተገኘው ጉድለት ምንድን ነው።

❖ ይህ ጉባኤ የተሰበሰበው በንጉሥ ትእዛዝ ነው አሉት፤ እንዲህም አላቸው ይህ ጉባኤ ስለ ክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቢሆን ኖሮ እኔ ተቀምጬ እግዚአብሔር በሰጠኝ በአንደበቴ እናገር ነበር ግን የዚህ ጉባኤ መሰብሰብ በንጉሥ ትእዛዝ ከሆነ የሰበሰበውን ጉባኤ ንጉሡ እንዳሻው ይምራ።

❖ ከዚህም በኋላ አንዱን ክርስቶስን ከተዋሕዶ በኋላ ሁለት ባሕርይ ሁለት ምክር የሚያደርግ የክህደት ቃል በውስጡ የተጻፈበትን የሮሜ ሊቀ ጳጳሳት ልዮን የላከውን ደብዳቤ የከበረና የተመሰገነ ዲዮስቆሮስ ቀደደ።

❖ በመንፈስ ቅዱስ የሚናገር የከበረ ዲዮስቆሮስም በጉባኤው ፊት እንዲህ ብሎ አስረዳ ሰው እንደመሆኑ ወደ ሠርግ ቤት የጠሩት ጌታችን ክርስቶስ አምላክ እንደመሆኑ ውኃውን ለውጦ ወይን ያደረገው ከሀሊ ስለሆነ ሰውነቱና መለኮቱ በሥራው ሁሉ የማይለይ አንድ ነው።

❖ ደግሞ የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቄርሎስ ከተናገረው የአካላዊ ቃል ተዋሕዶ እንደ ነፍስና ሥጋ እንደ እሳትና ብረት ተዋሕዶ ነው ያለውን ቃል ምስክር አድርጎ በማምጣትም አስረዳ።

❖ እሌህም የተለያዩ ሁለቱ ጠባዮች ስለ ተዋሕዷቸው አንድ ከሆኑ እንዲሁም የክብር ባለ ቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ አንድ መሲሕ አንድ ጌታ አንድ ባሕርይ አንድ ምክር ነው እንጂ ወደ ሁለት አይከፈልም አላቸው።

❖ ከዚያም ከተሰበሰበው ጉባኤ ውስጥ ማንም ሊከራከረው የደፈረ የለም ከውስጣቸውም የእግዚአብሔር ጠላት ስለሆነው ስለ ከሀዲው ንስጥሮስ በኤፌሶን ጉባኤ አስቀድሞ ተሰብስበው የነበሩ አሉ።

❖ ወደ ንጉሥ መርቅያኖስና ወደ ሚስቱ ንግሥት ብርክልያ ከእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ከአባ ዲዮስቆሮስ በቀር ስለ ሃይማኖት ትእዛዛችሁን የሚቃወም የለም ብለው ነገር ሠሩበት።

❖ ቅዱስ ዲዮስቆሮስንም ወደ ንጉሥ አቀረቡት ከእርሱም ጋር ታላላቅ ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስቆጶሳት ከጉባኤው የሆኑ ነበሩ ከጥዋትም እስከማታ እርስበርሳቸው ሲከራከሩ ዋሉ።

❖ የከበረ ዲዮስቆሮስም የቀናች ሃይማኖቱን አልለወጠም ንጉሡና ንግሥቲቱ በእርሱ ተቆጥተው እንዲደበድቡት አዘዙ ስለዚህም ደበደቡት ጽሕሙን ነጩ ጥርሶቹንም ሰበሩ እንዲህም አደረጉበት።

❖ ከዚህም በኋላ የተነጨውን ጽሕሙን ያወለቁትንም ጥሩሱን ሰብስቦ ወደ እስክንድርያ አገር ላካቸው እነሆ የቀናች ሃይማኖት ፍሬ ይህ ነው አላቸው።

❖ ለጉባኤውም የተሰበሰቡ ኤጲስቆጶሳትአሉት በዲዮስቆሮስ ላይ የደረሰውን መከራ በአዩ ጊዜ እጅግ ፈሩ በእርሱ የደረሰ በእነርሱ ላይ እንዳይደርስ ስለዚህም ከመናፍቁ ንጉሥ ከመርቅያኖስ ጋር ተስማሙ፤ በሲኦል ውስጥ ይቆርጡት ዘንድ ባለው ምላሳቸውም ለክርስቶስ ሁለት የተለያዩ ባሕርያት ብለው በንጉሡ መዝገብ ላይ በእጆቻቸው ጽፈው ፈረሙ።

❖ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም ተመልሶ ያን በውስጡ የጻፉበትን ደብዳቤ ያመጡለት ዘንድ ወደእሳቸው ላከ እነርሱም ላኩለት እነርሱ እንደጻፉ በውስጡ እርሱ የሚጽፍ መስሏቸዋልና፤ ኤጲስ ቆጶሳት እርሱ ግን አባቶቻችን ሐዋርያት ከአስተማርዋት ከቀናች ሃይማኖት በኒቅያ የተሰበሰቡ ሃይማኖታቸው የቀና ሦስት መቶ ዐሥራ ስምንት አባቶቻችን ከሠሩት ሕግ የሚወጣውን ሁሉ በደብዳቤው ግርጌ ጽፎ አወገዘ።

❖ መናፍቁ ንጉሥም ተቆጥቶ ጋግራ ወደም ትባል ደሴት እንዲአግዙት አዘዘ ወደዚያም ወሰዱት፤ ከእርሱም ጋር የሀገረ ቃው ኤጲስቆጶስ አባ መቃርስ አብሮ ተሰደደ፤ ሌሎችም አራት መነኰሳት የሸሹ አሉ።

❖ እሊህም ስድስት መቶ ሠላሳበአጋዙት ስድስት ኤጲስቆጶሳት ተቀምጠው በኬልቄዶን ለራሳቸው መመሪያ የሚሆናቸውን ሥርዓት ሠሩ።

❖ የከበረ ዲዮስቆሮስንም ጊዜ ከዚያች አገር ኤጲስቆጶስ ጭንቅ የሆነ መከራ ደረሰበት ኤጲስቆሱ ንስጥሮሳዊ ስለሆነ ታላቅ ጒስቍልናንም አጐሳቈለው በእጆቹ ላይ ድንቆች ታላላቅ ተአምራቶችን እግዚአብሔር እስከገለጠ ድረስ።

❖ የደሴቱም ሰዎች ሁሉ ሰገዱለት አከበሩት ከፍ ከፍም አደረጉት እግዚአብሔርም የመረጣቸውን በቦታው ሁሉ ያከብራቸዋልና።

❖ አባ ዲዮስቆሮስም አባ መቃርስን አንተ በእስክንድርያ አገር የሰማዕትነት አክሊልን ትቀበል ዘንድ አለህ አለው።

❖ ከዚህም በኋላ ከምእመናን ነጋዴዎች ጋር ወደ እስክንድርያ ላከው በእርሱ ላይ ትንቢት እንደተናገረ ገድሉን በዚያ ፈጸመ።

❖ የከበረ አባት ዲዮስቅሮስ ግን መልካም ተጋድሎውን በፈጸመ ጊዜ ክብር ይግባውና እግዚአብሔርንም አገልግሎሥጋውንም ከዚች ኃላፊት ከሆነች ኑሮው ወጥቶ ሔደ የሃይማኖቱንም ዋጋ አክሊልን ተቀብሎ ወደ ዘላለም ዕረፍት ገባ ያረፈውም በዚያች በደሴተ ጋግራ ነው በዚያው አኖሩ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ አባት ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።


             አርኬ

✍️ሰላም ለዲዮስቆሮስ ይማኖተ ንጉስ ዘተሣለቀ፡፡ ተዋሕዶተ አምላክ ወሰብእ አመ ለክልኤ ነፈቀ፡፡ ያስተጻንዕ ህየ እለ ሀለዉ ደቂቀ፡፡ ዘተነጽየ እምነ ጽሕሙ ወእምአስናኒሁ ዘወድቀ፡፡ ፍሬ ሃይማኖቱ ፈነወ ብሔረ ርኁቀ፡፡


በዚችም ቀን የመጥምቁ ዮሐንስ እናት የከበረች ኣልሳቤጥ አረፈች በጸሎቷ የሚገኝ በረከቷ ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን ።

              አርኬ

✍️ሰላም ለገብርኤል ለኤልሳቤጥ ዘአስተፍሥሓ ቀዲሙ፡፡ ይመጽ ቃል ለልዑል እምአርያሙ፡፡ ተፈሥሒ ዘይበል ከመ ለማርያም እሙ፡፡ ዲዮስቆሮስ እስመ ውስተ ቤተ ሐዲስ ዓለሙ፡፡ ዐስበ ጥረሲሁ ውዱቅ ወንጹይ ጽሕሙ፡፡ ሰላም ለኤልሳቤጥ ለሶፍያ ወለታ፡፡ ወለማርያም እኅታ። ነሥአኪበውስተ ገዳም ነጺሮ ከመ ይእቲ ባሕቲታ፡፡ መንፈሰ ስምዖን ነቢይ ወመንፈሰ ዘካርያስ ምታ፡፡ እግዚብሔር አዘዘ ይምጽኡ በሞታ፡፡


   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

        አባ ሳዊርያኖስ

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ በዚችም ቀን የገብላ ኤጲስቆጶስ የከበረ አባት አባ ሳዊርያኖስ አረፈ፤ የዚህም ቅዱስ የአበባቱ አብርስርያኖስ ይባላል የሀገረ አቴናንም ፍልስፍና ተማረ ከዚያም ወደ ቂሣርያ ሔዶ እውቀታቸውን ሁሉ ተማ፤ ወደ ሮሜ ከተማ ተመልሶ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ተማረ ከጥቂት ዘመናት የብሉይንና የሐዲስን መጸሕፍት አጠና።

❖ ዳግመኛምከዚህም በኋላ ቁጥር የሌለው ብዙ ገንዘብን ትተውለት ወላጆቹ አረፉ ስለርሱ ፈንታ መቶ ዕጥፍ ይቀበል ዘንድ ወዶ ያንን ገንዘብ ለክብር ባለቤት ሊሰጥ ወደደና ድኆችን መጸተኞችን ምስኪኖችን ችግረኞችንም በውስጥ ይቀበል ዘንድ የእንግዳ መቀበያ ቤትን ሠራ።

❖ ለክርስቶስአታእልትም ተከለ ፍሬዎችን ተሸክመው የሚያመጡላቸውን ሠራተኞችን አደረገ እነዚያም ስለ ድኆችና ስለ ችግረኞች የተሠሩ ቦታወች እስከ ዛሬ በስሙ የሚጠሩ ሆኑ።

❖ አገረ ገዥ የሆነ አጎቱን በሮሜው ንጉሥ በአኖሬዎስ ዘንድ እንዲህ ሲል ወነጀለው በከበረ ወንጌል ቃል ኪዳን እንደ ገባ ከእርሱ ዘንድ ስለ ርሱ መቶ እጥፍ እቀበላለሁና እኔ ገንዘቤን ክብር ይግባውና ለክርስቶስ እሰጠዋለሁ በማለት ሳዊርያሮስ ገንዘቡን ሁሉ እንደበተነ ።

❖ ይህም ነገር ለንጉሡ ደስ አሰኘው ፈጸሞም በእርሱ ደስያድራሉ አለው እጅግም ወደደው ከእርሱም ከቤተ መንግስቱ እንዳይለይ ንጉሡ አኖሬዎስ አዘዘው ከእርሱም ጋር ሁል ጊዜ ወደ ቤተክርስቲያን በመሔድ ሌሊቱን ሁሉ ቁመው ንጉሥ አኖሬዎስም የመነኰሳትን ስራዎች ስለሚሠራ ከልብሰ መንግሥቱ በታች በሥጋው ላይ ማቅ ይለብስ ነበር።

❖ በዚህም ወራት ለሮሜ አገር ሊቀ ጳጳሳት ሁኖ የነበረ አባ ዮናክንዲኖስ ነው ለእርሱም ሳዊርያኖስ በብዙ ሕዝብ ላይ ኤጲስቆጶስ መሆን እንዲገባው እግዚአብሔር ገለጸለት።

❖ ሊቀ ጳጳሳቱም እጅግ የሚወደውና የሚያከብረው ሆነ ከቶ እንድለየውም አይሻም ነበር በሁሉም ዘንድ ተወዳድ ሆነ ዜናውም በቍስጥንጥንያው ንጉሥ በቴዎዶስዮስ ዘንድ ተሰማ ።

❖ ሰዎች ሁሉ እንደሚያከብሩት በአየ ጊዜ ድካሙ በውዳሴ ከንቱ እንዳይጠፍ ከዚያች ቦታ በሥውር ሊወጣ ወደደ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክም ተገለጸለት ወደ ሀገረ ገብላ ሒዶ ለብዙ ነፍሳት የገዳም አባት እንዲሆን አዘዘው አበሌሊትም ወጥቶ ሔደ የምንኰስና ለብስን ከለበሰ በኋላ ደቀመዝሙሩ ቴዎድሮስ ከእርሱ ጋር ነበር ክብር ይግባውና እግዚአብሔር ወደ ገብላ ገዳም እስከሚደርስ በፊቱ የምትሔድና የምትመራው በመኰራኵር አምሰል የብርሃን ሠረገላ ላከለት።

❖ በዚያም ገዳም አበ ምኔት የሆነ ጻድቅ ሰው ነበር የቅዱስስለእርሱ ሳዊርያኖስንም መምጣት ጌታችን በራእይ አስረዳው ወደርሱ መጥቶ ተቀበለው ሰላምታም ሰጠውና ጌታችን በራእይ ተገልጾለት እንዳስረዳው ነገረው የጌታንም ቸርነት እጅግ አደነቁ፤ ዜናውም በሀገሮች ሁሉ ተሰማ የማይቈጠሩ ብዙ ሰዎች ወደርሱ ተሰበሰቡ።

❖ ንጉሥ ቴዎዶስዮስም ለከበረ ሳዊርያኖስ ገዳማትን የሚሠሩለት ብዙዎች ሰዎችን ሹሞችንም ከእርሱ ዘነድ ላከ የእግዚአብሔርም መልአክ በውስጣቸው ገዳማት የሚሠሩባቸውን ቦታዎች ወሰነላቸው ብዙ ነፍሳትንም የሚያጽናና የሚያረጋጋ ሆነ።

❖ ክብር ይግባውና እግዚአብሔርም በእጆቹ ላይ ድንቆች የሆኑ ብዙዎች ተአምራትን አደረገ ከእርሳቸውም በሀገረ ገብላ መኰንን ልጅ ሰይጣን እንደደረባትና መኰንኑንም ሳዊርያኖስን ከዚህ አገር ካላበረርክ ከልጅህ አልወጣም ያለው ነው።

❖ መኰንኑም ይህን ገነር በሰማ ጊዜ ተነሥቶ ወደ ከበረ ሳዊርያኖስ ሒዶ ሰይጣን ያለውን ነገረው ደግሞም ልጁን ያድናት ዘንድ ለመነው።

❖ ቅዱስ ሳዊርያኖስም እንዲህ ብሎ ደብዳቤን ጻፈለት ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሰሱስ ክርስቶስ ስም ከእሷ ወጥተህ ሒድ አባቷም ያንን ደብዳቤ ተቀብሎ ወደልጁ ደሰደ ያን ጊዜም ከመኰንኑ ልጅ ሰይጣን ወጥቶ ሔደ ልጅቷም ዳነች።

❖ ዳግመኛም ታላቅ ሠራዊት እስቲሆኑ ድረስ ብዙዎች ወንጀለኞች ሰዎች ተሰበሰቡ ወደ ከበረ ሳዊርያኖስም ገዳም ገብተው ሊያፈርሱት ፈለጉ ክብር ይግባውና እግዚአብሔርም በላያቸው ጨለማን አመጣ ምንም ምን ሳያዩ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ኖሩ ቅዱስ ሳዊርያኖስንም ይቅር ይለቸው ዘንድ ብዙ ዕንባ በማፍሰሰ ለመኑት እርሱም ወደ ቦታዎቻቸው መልሶ ሰደዳቸው።

❖ ዳግመኛም በገዳማቱ ውስጥ ያለ በእርሱ የሚተዳደሩ መነኰሳት ሁሉ ከእነርሱ የታመመ ቢኖር በላያቸው በመጸለይ ያድናቸዋው የሚያጸናናቸውና ሁሉም እንደ እግዚአብሔር መላእክት እስቲሆኑ ፈሪሀ እግዚአብሔር የሚያስተምራቸው ሆነ።

❖ እንዲህም ሆነ ስሙ ፈላታዎስ የሚባል የዚያች አገር ኤጲስቆጶስ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሆነ እራይ ተገልጦለት ቅዱስ ሳዊርያኖስ በእርሱ ፈንታ ኤጲስቆጶስነት ይሾም ዘንድ እንዳለው አወቀ ያን ጊዜም ወደ ሕዝቡ ሁሉ ላከ ቅዱስ ሳዊርያኖስንም ኤጲስቆጶስነት እንዲሾሙት አዘዛቸው ለዚች ሹመት እግዚአብሔር መርጦታና።

❖ ወዲያውኑ ደጋጏች ነገሥታት አኖሬዎስና አርቃዴዎስ ወስደው ገብላ በሚባል አገር ላይ ኢጶስቆጶስነት ሹሙት ስለ መንጋዎቹና ስለ ወገኖቹም አጠባበቅ ታላቅ ተጋድሎ ተጋደለ።

❖ በዚያችም አገር እጅግ አዋቂ የሆነ የሙሴን ሕግ በማወቁ የሚመካ አንድ ስሙ ስቅጣር የሚባል ይሁዳዊ ነበር፤ እርሱም ወደ ቅዱስ ሳዊርያኖስ መጥቶ ከእርሱ ጋር ተከራከረ ግን ከቅዱስ ሳዊርያኖስ አንደበት የሚመጣውን ቃል ይሰማ ዘንድ አልተቻለውም።

❖ ከዚህም በኋላ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሲስ ክርስቶስ ለቅዱስ ሳዊርያኖስ በራእይ ተገልጦለት ይህ አይሁዳዊ እርሱ ራሱ ክርስቶስ ከአከበራቸውና ከባረካቸው ወገን ውስጥ ሊሆን እንዳለው አስረዳው።

❖ ያ አይሁዴዊውም ወደ ቤቱ በገባ ጊዜ አስጨናቂዎች የሆኑ የሥቃይ ቦታዎች በሕልሙ በማየት እንዲህ የሚለውን ቃል ታላቅ በሆነ የዘላለም ሥቃይ ውስጥ የሚኖሩ እሊህን ከሀዲዎች ዘመዶችህ አይሁድን እነሆ እይ እነርሱም ክብር ይግባውና በክርስቶስ ያላመኑ ናቸው።

❖ በማግሥቱም ያ አይሁዳዊ ወደ ቅዱስ ሳዊርያኖስ መጥቶ በታች ወድቆ ሰገደለት ክርስቲያንም ያደርገው ዘንድ ለመነው ያን ጊዜም እርሱንና ቤተሰቦቹን የሀገር ሰዎችንም ሁሉ ከእግሩየክርስትና ጥምቀትን አጠመቃቸው።

❖ የቀሩትም አይሁድ ሁሉ አለቃቸው ክርስቲያን እንደሆነ ጊዜ አምነው ተጠምቀውበሥራያቸው ክርስቲያኖች ሆኑ።

❖ እንዲሁም ኒሞንጦስ የሚባሉ በሰሙሌሎች ሥራየኞች ሰዎችን ወደ ክርስቲያን ሃይማኖት እንዲገቡ ቅዱስ ሳዊርያኖስ ለመናቸው እነርሱ ግን ስለሚታበዩ ከእርሱ ቃሉን አልሰሙም እነርሱም ባዕድ ወደ እነርሱ የመጣ እንደሆነ በፊቱ አረ ፈርን ይበትናሉ ምንም ምን ማየት አይችልም።

❖ ቅዱስ ሳዊርያኖስንም ወደ ቀናትምን ሃይማኖቱ እሊህን ሥራየኞች ሰዎች ያስገባቸው ዘንድ ዕንባን በማፍሰስ ክብር ይግባውና ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመነው እግዚአብሔርም በእርሱ ላይ ብቻ ጽኑዕ ደዌ አመጣ ወደ ክርስቲያን ወገኖች ግን ምንም አልደረሰም።

❖ በግብጽ አገር በፈርዖንና በሠራዊቱ በግብጻውያንም ላይ መቅሠፍት ሲታዘዝ ወደ እስራኤል ወገን እንዳልደረሰ እንዲሁ ሆነ።

❖ በዚያም ወራት እንዚያ ሥራየኞች የቅዱስ ሳዊርያኖስን ቃል ሰምተው ትእዛዙን ስለ አልተቀበሉ ስለዚህም ይህ ጽኑ ደዌ በላያቸው እንደመጣ አወቁ፤ ወደ ቅዱስ ሳዊርያኖስም መጥተው በደላቸውን ይቅር ይላቸው ዘንድ ክርስቲያኖችም ያደርጋቸው አንድ ለመኑት እርሱም ተቀበላቸው አስተምሮ አጥምቆ ክብር ይግባውና ከክርስቶስ መንጋዎች ጋር አንድ አደረጋቸው፤ ያቺ አገር ሁለመናዋ አንድ ማኅበር አንድ መንጋ ሆነች።

❖ ሰይጣንም ልብሱ በተቀደደ ሽማግሌ አማሳል ሆኖ ፈጽሞ የሚጮህ ሆነ እንዲህም አለ፤ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ በአለው ቦታ ሁሉ ጨነቀኝ በግብጽ አገርም ጠንካሮች መነኰሳት ተመሉባት በሮሜ አገርም ሊቀ ጳጳሳት ዮናክንዲኖስ በውስጧ ይኖራል ደግሞ በቁስ ጥንጥንያ ዮሐንስ አፈወርቅ አለ ይህ ቦታ ለእኔ ቀረልኝ ብዬ ነበር እነሆ ሳዊርያኖስ ከእጄ ውስጥ ነጠቀኝ አለ።

❖ እንዲህም ሆነ የፋርስ ሰዎች ሊወጉአቸው ሽተው ወደ አኖሬዎስና ወደ አርቃዴዎስ መልእክትን ላኩ እሊህ ደጋጎች ነገሥታትም የፋርስ ሰዎች የላኩትን ደብዳቤ ወደ ቅዱስ ሳዊሮያኖስ ላኩት።

❖ እርሱም ያቺን ደብዳቤ በአነበባት ጊዜ የደብዳቤውን መልስ ወደ ነገሥታት አኖሬዎስና አርቃዴዎስ እያስረዳ እንዲህ ብሎ ጻፈ እኛ የክርስቶስ ከሆን መንግሥታችንም የክርስቶስ ነው። እንዲህም ከሆነ የጦር መሣሪያን የጦር ሠራዊትንም አንሻም።

❖ እግዚአብሔርም ከቀደሙ ነገሥታት ጋር ሁኖ ያደረገውን እንዴት እንዳዳናቸው ጠላቶቻቸውንም እንዴት ድል እንዳደረጓቸው አስታወሳቸው።

❖ ታላቁም ጾም ሳይደርስ የፋርስ ሰዎች አፍረው ከእነርሱ ዘንድ ተመልሰው ሔዱ፤ ስለ ዮሐንስ አፈወርቅም ከኤጲስቆጶሳት ጋር በአመጡት ጊዜ ንግሥት አውዶክስያን በምክሩ ሁሉ መክሮዋትና ገሥጿት ነበር።

❖ ስለ ዮሐንስ መሰደድም እርሱ ምንም ምን ያደረገው ስምምነት የለምእሊህም ንግሥቲቱም ምክሩን ባልሰማች ጊዜ ወደ አገሩ ተመለሰ።

❖ ብዙዎች ድርሳናትንና ተግሣጻትንም ደረሰ ሃይማኖታቸው የቀናች ሰዎች በአሉባቸው አብያተ ክርስቲያናት እስከ ዛሬ ይኖራሉ።

❖ ቅዱስ ሳዊርያኖስም ሸመገለ ዕድሜውም መቶ ዓመት ሆነው ከሥጋውም ከመለየቱ በፊት በዐሥር ቀን የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጾለት ከዚህ ዓለም ከድካምም ወደ እረፍት እንደ ሚወጣ ነገረው።

❖ ከዚህም በኋላ ሕዝቡን ጠራቸው ክብር ይግባውና የእግዚአብሔርን ሕግ በመጠበቅ ጸንተው እንዲኖሩ አዘዛቸውና በሰላም በፍቅር አረፈ። ነፍሱንም በፈጣሪው ክርስቶስ እጅ ሰጠ።ዕረፍቱም የቆጵሮስ ኤጲስቆጶስ ኤጲፋንዮስ በአረፈ በሁለት ዓመት ዮሐንስ አፈወርቅ በአረፈ በአንድ ዓመት ነው።

❖ ሥጋውንም እንደ ሚገባ በንጹሕ ልብስ ገነዙ ብዙ መዝሙራትንና ምስጋናዎችን አድርገውለት በክብር ቀበሩት።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎቱ ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

            አርኬ

✍️ ሰላም ለከ ለቤተ ክርስቲያን አክሊላ፡፡ ሳዊርያኖስ ሐናፂ ለፈላስያን ማኅደረ ተድላ፡፡ እም ወለተ ብእሲ መኮንን ገብላ፡፡ ሰይጣን ጐየ ፈሪሆ እንተ ፈቀደ ያህጕያ፡፡ ለክታበ መልዕክትከ ሶበ ሰምዐ ቃላ፡፡

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

ቅዱሳን አጋቶን ዼጥሮስ ዮሐንስ

   ✥•••••●◉ ✞ ◉●•••••✥

❖ በዚች ዕለት የከበሩ አጋቶንና ጴጥሮስ ዮሐንስና አሞን እናታቸውም ራፈቃ በሰማእትነት አረፉ፤ እሊህ ቅዱሳንም በላይኛው ግብፅ ቁቊስ ከሚባል አውራጃ ከቆንያ ከተማ ናቸው፤ ለእርሳቸውም ክብር ይግባውና ጌታችን ተገልጾላቸው፤ ከእነርሱ የሚሆነውን ስብራ በምትባል ከተማ እርሷም ወደ እስክንድርያ ክፍል ናት በዚያ የምስክርነት ክርስቶስአክሊል እንደሚቀበሉ ስጋቸውንም ወደ ግብጽ ደቡብ ነቅራሃ ወደሚባል አገር እንደሚወስዱ አስረዳቸው ቅዱሳኑም በዚች ራእይ ደስ አላቸው።

❖ በማለዳም ተነሥተው ገንሰባቸውን ሁሉ ለድኆችና ለችግረኞች ሰጡ ከእነርሱም የሚበልጥ ወነድማቸው አጋቶን በሀረጉ ሹም ነበር በሁሉም ዘንድ የተወደደ ነው ራፊቃ እናታቸውም ክብር ይግባውና ስለ ክርስቶስ በመከራ ስቃይ ላይ የሚጸኑና የሚታገሡ እንዲሆኑ ታበረታታቸው ነበር።

❖ ከዚህም በኋላ ቊስ ወደ ሚባል አገር ሲደርሱ በመኰንኑ በዲዮናሲዮስ ፊት ቁመው ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታመኑ። ከእርሳቸውም አስቀድሞ እናታቸው ራፊቃን አሰቃያት እርሷም በስቃይ ውስጥ በመታገስ ደስተኛ ነበረች ከዚህም በኋላ አራቱን ልጆቿን አሰቃያቸው።

❖ እነርሱንም በማሰቃየት በሰለቸ ጊዜ ወደ እስክንድርያ እንዲልካቸው ወገኖቹ መከሩትሰዎች በእነርሱ ምክንያት ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ሕዝቡ እንዳያምን ፈርተዋልና፤ እነርሱ በሁሉ ዘንድ የተወደዱ ስለሆኑ በእርሳቸውም ምክንያት ከዚህ በፊት ብዙዎች በክብር ባለቤት በክርስቶስ አምነው በሰማእትነት ሙተዋልና የሰማእትነት አክሊልንም ተቀብለዋልና።

❖ ወደ እስክንድርያም ገዥ ወደ አርማንዮስ ቅዱሳኑን በአመጡአቸው ጊዜ በዚያን ወቅት ስሟ ስብራ በምትባል አገር በዚያ ነበር፤ የተጋድሎአቸውንም ጽናት አውቆ ጽኑ ስቃይን አሰቃያቸው ስጋቸውንም ቆራርጦኢየሱስ ከመንኰራኵር ውስጥ ጨመራቸው ።

❖ ዳግመኛም ዘቅዝቀው ሰቀሉአቸው በዚህም ሁሉ ክብር ይግባውና ጌታችን ክርስቶስ መኰንኑና የርሱ ሰዎች ሁሉ እስቲአፍሩ ያለ ምንም ጥፋትና ጉዳት የሚያነሳቸው ሆነ።

❖ ከዚህም በኋላ ራሶቻቸውን ይቆርጡ ዘንድ ስጋቸውንም በባሕር ሊጥሉ እንዲአሠጥሙ አዘዘ በዚያም ራሶቻቸውን በሰይፍ ቆረጡ ሥጋቸውን ወደባለ ወደ በሕር ሊጥሉ በታናሽ ታንኳ ጫኑአቸው።

❖ በዚያንም ጊዜ ከግብጽ በስተደቡብ መጺል ከሚባል አውራጃ ነቅራሃ ከምትባል መንደር ወደ አንድ ጸጋ እግዚአብሔር መልአኩን ላከ።

❖ የቅዱሳኑንም ሥጋ እንዲወስድ አዘዘው፤ እርሱም ወሰዳቸው የጽድቃን ማደሪያቸው ይህ ነው የሚል ቃልን ሰማ የመከራውም ወራት እስከሚአልፍ በዚያ አኖሩአቸው።

❖ ከዚህም በኋላ ገለጡአቸው ውብ የሆነች ቤተ ክርስቲያንንም ሰርተውላቸው ሥጋቸውን በውስጧ አኖሩ።እግዚአብሔር ከሥራምች ድንቆች የሆኑ ታላላቅ ተአምራትን ገለጠ በዚያም ወራት ሥጋቸውን ስሙንጥያ ወደሚባል አገር አፈለሱ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በጸሎታቸው ይማረን ለዘላለሙ አሜን።

          አርኬ

✍️ሰላም ለክሙ ሰማዕታተ ወልድ ኃምስ፡፡ አጋቶን ወአሞን ጴጥሮስ ወዮሐንስ፡፡ ወእምክሙ ራፊቃ ምልእተ መንፈስ ቅዱስ፡፡ ዘተኀፍረ እምጽንእክሙ በቅድመ ጣዖቱ ርⷈስ፡፡ መኮንን ቍዝ ዘስሙ ዲዮናስ፡፡



❖ በዚችም ቀን ደግሞ እናት ሺህ ሰዎች ከቅዱስ ፋሲለደስ ጋር በሰማዕትነት ሞቱ የጋንግራ ሰው ዳስ የአንጾኪያ ኢጲስቆጶስ ናውላ የመነኲሴውም የጴጥሮስ መታሰቢያቸው ነው።የእምቤታችን እናት የቅድስት ሐናም የልደቷ መታሰቢያ ነው።በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

                  አርኬ

✍️ዘተወከፍከ ጥምቀተ በእደ ዮሐንስ ብጹዕ፡፡ ምስለ ነፍሰ ፋሲል ተወከፍ አምሳለ ንጹህ መባዕ፡፡ ሶበ አስተብቋዕኩከ አንሰ ወሰአልኩከ ኃጥእ፡፡ ዘበእንቲአሁ ኢትበለኒ እግዚዕ፡፡ እኁኒ እኅወ ዚአሁ ኢያድኅን ሰብእ፡፡
      

📌 መስከረም 7 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት

1.እናታችን ቅድስት ኤልሳቤጥ

2.ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ሊቅ (የተዋሕዶ ሃይማኖት አባት)

3.ታላቁ ቅዱስ ሳዊርያኖስ

4.ቅድስት ሐና (የእመ ብርሃን እናት-ልደቷ ነው)

5.ቅዱሳን አጋቶን፣ ዼጥሮስ፣ ዮሐንስ፣ አሞንና እናታቸው ራፊቃ (ሰማዕታት)

📌 ወርሐዊ በዓላት

1.ሥሉስ ቅዱስ (አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ)

2.አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ

3.አባ ሲኖዳ (የባሕታውያን አለቃ)

4.አባ ዳንኤል ዘገዳመ ሲሐት

5.አባ ባውላ ገዳማዊ

6.ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ

7.ቅዱስ አግናጥዮስ (ለአንበሳ የተሰጠ)

✍️"ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ጽንሱ በማሕጸኗ ውስጥ ዘለለ፤ በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት፤ በታላቅ ድምጽም ጮኻ እንዲህ አለች 'አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ የማሕጸንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፤ የጌታየ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? . . . ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብጽዕት ናት"

📖ሉቃ 1፥ 41

      

ዘአቅረብኩ ማኅሌተ አዘኪርየ አእላፈ እምእለ ተፀመድኩ ዘልፈ ለለአነብብ ተወከፍ ዘንዴትየ መጽሐፈ እንተ ረሰይከ እግዚኦ ጸሪቀ መበለት ውክፈ እምእለ አብዑ ብዑላን ዘተርፈ።

ነቢያት ቅዱሳን ወሐዋርያት ሰባኪያን ሰማዕታት ወጻድቃን ወመላእክት ትጉሃን ደናግል ዓዲ ወመነኮሳት ኄራን ባርኩ ባርኮ ጉባኤ ዛቲ መካን እስከ አረጋዊ ልሂቅ እምንኡስ ሕፃን።

ለዘጸሐፎ በክርታስ ወለዘአጽሐፎ እንዘ ይደርስ ዘአንበቦ ወለዘተርጐሞ በልሳን ሐዲስ ወለዘሰምዐ ቃሎ በእዝነ መንፈስ በጸሎተ እሙ ማርያም ዐራቂተ ኲሉ እምባእስ ኅቡረ ይምሐረነ ኢየሱስ ክርስቶስ።

ጌታ ሆይ ከብልፅግናቸው ብዛት የተነሳ ብዙ መባ ካገቡት ይልቅ የደሀዪቱን አነስተኛ መባ እንደተቀበልህ ለሁል ጊዜ የሚያገለግሉህ አእላፍ መላእክትን እያሳሰብሁ በችግሬ ጊዜ የማቀርብልህን ምስጋና ተቀበል።

እናንተም ቅዱሳን ነቢያት የወንጌል ሰባኪያን ሐዋርያት ሰማዕታትና ጻድቃን ትጉሃን መላእክት ፍጹማን ደናግል እንዲሁም ደጋጎች መነኰሳት ሆይ ልጅ አዋቂ ሳይለይ የምንሰበሰብበትን የጉባኤ ቦታ ባርኩ።

ይህን መጽሐፍ ወረቀት አዘጋጅቶ ብራና ደምጦ የጻፈውና ያጻፈውም ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጐመውን ቃለ ንባቡን በእርጋታ መንፈስ እና በተመስጦ ሕሊና ያዳመጠ በደለኛን ሁሉ የምታስምር የጌታ እናቱ በማርያም ጸሎት ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድነት ይማረን።


ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ፤ እኔም ለእናንተ ከአዘጋጀው በኃዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ   


✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝💚💛❤️✝

✍"ልብህን በእርጋታ አኑረው፤ የሁሉም መጨረሻ እና የሁሉም አገልጋይ ለመሆን በጣም ትጋ ለከንቱ ንግግር ዘገምተኛና ሰነፍ ሁን፤ ነገር ግን የቅዱሳት መጻህፍትን ቃል በማወቅ በመስማት ድኅነትን የሚሰጡ ናቸውና ብልህ ሁን"

📚ታላቁ ባስልዮስ ዘቂሳሪያ


             ወስብሐት ለእግዚአብሔር

                             ይቆየን 


───────────

                   Channel

 🧲 https://telegram.me/Tewahedo12


       FB Like Page (የፌስቡክ ፔጅ)

🧲 http://facebook.com/Tewahedo12  


       YouTube Subscribe (ሰብስክራይብ)

🧲 https://www.youtube.com/channel/UCvYxUdv1D-5juH_P6iE7XXw

 ───────────


Report Page