ሠለስቱ ደቂቅን ያዳናቸው የትኛው መልአክ ነው?

ሠለስቱ ደቂቅን ያዳናቸው የትኛው መልአክ ነው?

http://t.me/Ethiopiabarbara

ጠባቂ መላእክት (ዑቃቢ መላእክት) በድኅነታችን ውስጥ ትልቅ ስፋራ የሚሰጣቸው ናቸው። በእርግጥም እነርሱ የሌሉበት ድኅነት የለም።

ዑቃቢ (ግእዝ) = ጠባቂ [ዐቃቤ ሕግ = ሕግን የሚጠብቅ እንዲል]

ለሁሉም ሰው ጠባቂ መላእክ እንዳለው በአንዳንዶቹ ታሪኮች ላይ መገለጣቸው፣ በአንዳንዶቹ ላይ ደግሞ ተገልጠው ለሰው አለመታየታቸው ቢስተዋልም ጌታችንም በወንጌል ‹‹ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው ዘወትር በሰማያት ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁና፤›› በማለት የተናገረው ስለ ጠባቂ መላእክቶቻችን ነው /ማቴ.፲፰፥፲/፡፡

በእያንዳንዱ እንቅስቃሴአችንና ፈተናችን ላይ ወደ እግዚአብሔር እያመለከቱ የሚጠብቁን፣ የሚያድኑን፣ የሚያስፈርዱልን ወይም የሚያስፈርዱብንም እነርሱ (ቅዱሳን መላእክት) ናቸውና፡፡ እንደናቡከደነፆር ያለውን አስፈርደውበት አውሬ አድርገው ሣር ያስግጡታል፡፡ እርሱ ራሱም ‹‹አንድ ቅዱስ ጠባቂ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤›› ብሎ አሁንም እውነቱን አረጋግጧል /ዳን.፬፥፲፫/፡፡

እንደ ሄሮድስ ያለውን ደግሞ ‹‹ለእግዚአብሔርም ክብር ስላልሰጠ ያን ጊዜ የጌታ መልአክ መታው፤ በትልም ተበልቶ ሞተ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈው /ሐዋ.፲፪፥፳፫/፣ በእግዚአብሔር አስፈርደው ይቀሥፉታል፡፡

እንደ ዳንኤል፣ ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ጻድቁ ዮሴፍ፣ ሠለስቱ ደቂቅ ያሉትን ደግሞ በጠባቂነታቸው ያድኗቸዋል፡፡ ‹‹… እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ፣ ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃልና። በላባዎቹ ይጋርድሃል፤ በክንፎቹም በታች ትተማመናለህ፡፡ እውነት እንደ ጋሻ ይከብሃል። ከሌሊት ግርማ፣ በቀን ከሚበርር ፍላጻ፣ በጨለማ ከሚሔድ ክፉ ነገር፣ ከአደጋና ከቀትር ጋኔን አትፈራም። በአጠገብህ ሺሕ በቀኝህም ዐሥር ሺሕ ይወድቃሉ፤ ወደ አንተ ግን አይቀርቡም። በዓይኖችህ ብቻ ትመለከታለህ፤ የኀጥአንንም ብድራት ታያለህ። አቤቱ አንተ ተስፋዬ ነህና ልዑልን መጠጊያህ አደረግህ። ክፉ ነገር ወደ አንተ አይቀርብም፤ መቅሠፍትም ወደ ቤትህ አይገባም። በመንገድህ ዅሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል … ›› ተብሎ ተጽፏልና /መዝ.፺፥፩-፲፪/፡፡

🌿 ሠለስቱ ቅዱሳን ደቂቅ 🌿

ሠለስቱ ደቂቅንም ጠባቂ መላእክቶቻቸው የሚያድኗቸው ቢኾንም ‹‹ለናቡከደነፆር የታየው አንድ መልአክ ኾኖ ሳለ ሦስቱ መላእክት እንዳዳኗቸው ተደርጎ ለምን ይገለጻል?››

እንዲህ ያሉትን ምሥጢራት መረዳት የምንችለው በቅዱሳት መጻሕፍት ያሉትን ተመሳሳይ ታሪኮችና ይህ የሚኾንበትን ምክንያት ስናውቅ ነው፡፡

ለምሳሌ ያህል የጌታችንን ትንሣኤ አራቱም ወንጌላውያን መዝግበውልናል፤ አራቱም የመዘገቡበት መንገድ ተቃርኖ ባይኖረውም ልዩነት ግን አለው፡፡

ዐበይት ልዩነቶቹም ሦስት ነገሮች ላይ ይስተዋላሉ፤ ይኸውም የተገለጹት መላእክት፣ ወደ መቃብሩ የመጡት ሴቶች ማንነት እና ሴቶቹ የመጡበት ሰዓት በአዘጋገብ ይለያያል፡፡ ለርእሰ ጉዳያችን ቅርበት ባለው ትምህርት ላይ ትኩረት አድርገን ጥቂት ምሳሌዎችን እንደሚከተለው እናቀርባለን፤

ቅዱስ ማቴዎስ፦ ‹‹እነሆም የጌታ መልአክ ከሰማይ ስለ ወረደ ታላቅ የምድር መናወጥ ኾነ፤ ቀርቦም ድንጋዩን አንከባሎ በላዩ ተቀመጠ። መልኩም እንደ መብረቅ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። ጠባቆቹም እርሱን ከመፍራት የተነሣ ተናወጡ እንደ ሞቱም ኾኑ።

መልአኩም መልሶ ሴቶቹን አላቸው፤ ‹እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁና። እንደ ተናገረ ተነሥቶአልና በዚህ የለም። የተኛበትን ስፍራ ኑና እዩ። ፈጥናችሁም ሒዱና ከሙታን ተነሣ፤  እነሆም ወደ ገሊላ  ይቀድማችኋል፡፡ በዚያም ታዩታላችሁ፤›  ብላችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ንገሯቸው፤›› ሲል የገለጸውን /ማቴ.፳፰፥፪-፯/፣

ቅዱስ ማርቆስ፦ ‹‹ወደ መቃብሩም ገብተው ነጭ ልብስ የተጎናጸፈ ጎልማሳ በቀኝ በኩል ተቀምጦ  አዩና ደነገጡ  … ›› በማለት መዝግቦታል /ማር.፲፮፥፭/፡፡

ቅዱስ ሉቃስ ደግሞ፦  ‹‹እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ እነሆ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ ›› ብሎ ጽፎታል /ሉቃ.፳፬፥፬/፡፡

ቅዱስ ዮሐንስም ስለ ትንሣኤው ብዙ ነገር ካተተ በኋላ፦  ‹‹ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች፤›› ሲል መዝግቦልናል /ዮሐ.፳፥፲፩-፲፪/፡፡

እነዚህን አገላለጾች ስናያቸው የአዘጋገብ ልዩነት ቢታይባቸውም ተቃርኖና የእውነታ ልዩነት ግን የላቸውም፡፡ ቅዱስ ማቴዎስና ቅዱስ ማርቆስ ስለ አንድ መልአክ ሴቶችን ማነጋገር ቢገልጹም ሌላ መልአክ እንዳልነበረ ግን አላመለከቱም፡፡

ወንጌላውያኑ ስለ አንድ መልአክ መታየት ይመዝግቡልን እንጂ የተናገሩት ግን ስለ ተለያዩ መላእክት ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ ከመቃብሩ ወጭ ድንጋዩን አንከባሎ ስለ ተቀመጠው መልአክ ዘግቦ ከመቃብሩ ውስጥ በቀኝ በኩል (በራስጌ ወይም በግርጌ) ስላለው መልአክ አልመዘገበም፡፡ ቅዱስ ማርቆስ ደግሞ ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ ስላለው መልአክ መዝግቦ ከውጭ በኩል ስላለው ወይም የመቃብሩ ድንጋይ ላይ ስላለው መልአክ አልመዘገበም፡፡ ሁለቱም ግን ‹‹ሌላ መልአክ አልነበረም›› በሚያሰኝ መንገድም አልገለጹልንም፡፡

ቅዱስ ሉቃስና ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ሁለቱም መላእክት መኖራቸውንና በግርጌና በራስጌ መኾናቸውን ገልጸውልናል፡፡ ስለዚህ ዅሉም ትክክል ናቸው ማለት ነው፡፡ የተለያዩና የማይቃረኑ የተባለውም ስለዚህ ነው፡፡

የተለያዩትስ ለምንድን ነው ስንል ደግሞ አንድ መሠረታዊ መልእክት እናገኛለን፤ ይኸውም ስለ መላእክቱ የተለያየ ዓይነት መገለጥ የገለጹት ለተለያዩ ሰዎች በትንንሽ የጊዜ ልዩነት የታየውን መገለጥና ለአንዳንዶችም በተቀራራቢ፣ ነገር ግን በተለያየ ጊዜ የተገለጠውን ስለ መዘገቡ ነው፡፡

ለምሳሌ ቅዱስ ዮሐንስ ለመግደላዊት ማርያም የተደረገውን የአንድ ጊዜ መገለጥ ብቻ ሲነግረን፣ ቅዱስ ሉቃስ ደግሞ ለሌሎች ሴቶች የተደረገውን (ምክንያቱም ተመላልሰው ያዩም አንድ ጊዜም ያዩ አሉ፤ እንደዚሁም ብዙ ታሪኮች በውስጡ አሉና) እያሉ ከነሰዓቱ ስለ መዘገቡ እንጂ አንዱን ነጠላ ድርጊት ለያይተውና አሳሰተው መዝግበውት አይደለም፡፡

ስለዚህ የሠለስቱ ደቂቅ ድኅነትን በተመለከተ በድርሳነ ሚካኤል ላይ ሚካኤል፤ በድርሳነ ገብርኤል ላይ ገብርኤል፤ በድርሳነ ሩፋኤል ላይ ደግሞ ሩፋኤል አዳናቸው ተብሎ መገለጹ ከላይ በወንጌል እንዳየነው ትውፊቱን ለያይቶ መዘገብ እንጂ ተቃራኒ ነገር አይደለም፡፡

በዚሁ መሠረት ሦስቱን ሕፃናት አናንያ፣ አዛርያና ሚሳኤልንም ያዳኗቸው ጠባቂ መላእክቶቻቸው፥ እነዚህም ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ ገብርኤልና ቅዱስ ሩፋኤል ናቸው፡፡ ልክ ሥላሴ ለአብርሃም በተገለጹለት መንገድ ሦስት ኾነው ከሦስቱ በስተጀርባ ቆመው መታየት ነበረባቸው ካላልን በስተቀር ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በተላለፈው ትውፊት ሦስቱ መላእክት የሦስቱ ሕፃናት ጠባቂ መላእክት ነበሩ፡፡ እንኳን ሰዎቹ ሦስት ኾነው ይቅርና አንድም ሰው ቢኾን ሦስትና ከዚያ በላይ መላእክት ሊገኙ ይችላሉ፡፡

ዮናታን ወልደ ሳዖል ‹‹በብዙ ወይም በጥቂት ማዳን እግዚአብሔርን አያስቸግረውምና፤››  እንዳለው /፩ኛሳሙ.፲፬፥፮/፣ በአንድም በብዙም መንገድ ማዳን የእግዚአብሔር ፈቃድና ምሥጢር እንጂ የመላእክቱ የማነስና የመብዛት ጉዳይ የሚከራክር አይደለም፡፡

እንዲህ ያለው ነገር እንኳን በመላእክት ዘንድ ቃል ኪዳን ተቀብለው በሚያማልዱ፣ በሚያድኑ ሰማዕታትና ቅዱሳንም ታሪክ ላይ በተደጋጋሚ የተገለጸ መኾኑን ከተለያዩ ገድላት ለመረዳት ይቻላል፡፡

ለምሳሌ አንድ ዓሣ አስጋሪ ሰው ‹‹መርምሕናም እርዳኝ?›› እያለ ቅዱስ መርምሕናምን ሲማጸን ቅዱስ ጊዮርጊስና ቅዱስ መርምሕናም በአንድነት መጥተው ዓሣ አስጋሪውን እንደ ረዱት ‹‹ወበጊዜሃ መጽኡ ኅቡረ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወቅዱስ መርምሕናም ተጽዒኖሙ ዲበ አፍራሲሆሙ ….›› ተብሎ በተአምረ ጊዮርጊስ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ይህ ግን በዋናነት ሊገለጽ የሚችለው በገድለ መርምሕናም እንደ ኾነ የታወቀ ነው፡፡

ቅዱስ መርምሕናም ሰማዕት፣ እኅቱ ቅድስት ሣራ እና አባ ማቴዎስ 🌿

ስለዚህ በቅዱሳን ዘንድ አንዱ ብቻ ነው እንጂ ሌሎቹ የሉም የሚያስብል ታሪክም ድርጊትም የለም፤ ሊኖርም አይችልም፡፡ ልዩነት ያለ የሚመስለን መገለጦችን የምንረዳበት ሒደት አነስተኛ ሲኾን ብቻ ነው፡፡

‹‹ይህ ከኾነ ታዲያ በሠለስቱ ደቂቅ የድኅነት ታሪክ ውስጥ ቅዱስ ገብርኤል ጎልቶ ለምን ይወጣል? ዕለቱ (ታኅሣሥ ፲፱ ቀን) በዓል ኾኖ የሚከበረው ለቅዱስ ገብርኤል ለምን ሆነ?

ይህ የኾነበት ምክንያት ዝም ብሎ ወይም በአጋጣሚ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሥጋዌውን አስቀድሞ የገለጸው መላእክትንም በሰው አምሳል እንዲገለጹ በማድረግም ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ ለሙሴ መጀመሪያ የተገለጠለት በዚሁ መንገድ ነበረ፡፡

‹‹የእግዚአብሔርም መልአክ በእሳት ነበልባል በእሾኽ ቍጥቋጦ መካከል ታየው፤ እነሆም ቍጥቋጦው በእሳት ሲነድ፣ ቍጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ፤›› ተብሎ ተጽፏልና /ዘፀ.፫፥፪/፡፡ ይህም ነገረ ተዋሕዶን ወይም ምሥጢረ ሥጋዌን የሚያስረዳ መገለጥ ነው፡፡ እግዚአብሔር ራሱን በመላእክት አምሳል ሲገልጥ ደግሞ ቅድሚያውን ስፍራ የሚይዘው ቅዱስ ገብርኤል ነው፡፡ ምክንያቱም ገብርኤል ማለት ‹‹ቃለ እግዚአብሔር ›› እንደዚሁም ‹‹ሰውና አምላክ›› ማለት ስለ ኾነ ነው፡፡ እመቤታችንን ሊያበሥር የተላከውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡

ስለዚህ ‹‹አራተኛ ሰው አያለሁ›› እስኪል ድረስ እግዚአብሔር ለናቡከደነፆር ሥጋዌውን (ሰው መኾኑን) ገልጦ ያሳየው ከሦስቱ ሊቃነ መላእክት መካከል ይህን የተዋሕዶ ምሥጢር በስሙም በተልእኮውም ቅዱስ ገብርኤል የተሸከመው በመኾኑ ነው፡፡

✨ ቅዱስ ገብርኤል ሊቀ መላእክት ✨

ስለዚህም ሦስቱም ሊቃነ መላእክት በጠባቂ መላእክትነታቸውና ረቂቃን ኃይላት በመኾናቸው በአዳኝነት ቢጠቀሱም እግዚአብሔር ሊገልጠው ለፈለገው ታላቅ ምሥጢር ተስማሚ የኾነውን መልአክ (ራሱ ገብርኤል መኾኑ ትርጕምና መልእክት ያለው ነውና) የነገሥታትን ልጅ በሚመስል ጎልማሳ አምሳል የንጉሠ ሰማይ ወምድር የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ምሳሌ ኾኖ እንዲገለጽለት አድርጓል፡፡ በዓሉ ለገብርኤል የተሰጠውና ሥዕሉ የእርሱ የኾነበት ምክንያትም ይኸው ምሥጢር ነው፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን የተዋሕዶ ምሥጢር መሠረት አድርጋ በዓሉ በቅዱስ ገብርኤል ስም በታላቅ ሥርዓት እንዲከበር፣ በሥዕሉም ቅዱስ ገብርኤል ጐ

ጎልቶ እንዲታይ በማድረግ ነገረ ሥጋዌውንም፣ የሕፃናቱን ተጋድሎም፣ የመላእክቱን ጠባቂነትም ስትገልጽበትና ስታስረዳበት ትኖራለች፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በምልዓት መረዳት ያለውም በእውነተኛው የሐዋርያትና የሊቃውንት ትምህርት ትውፊትና ሥርዓተ አምልኮ ጸንታ በምትኖረው በዚህች ቅድስት ተዋሕዶ ሃይማኖት ነው፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት፤ የንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ልዩ አማላጅነት፣ የሊቃነ መላእክቱ ጥበቃና የቅዱሳን ዅሉ ምልጃ አይለየን፤ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ልዑል፥

ወለወላዲቱ ድንግል፥

ወለመስቀሉ ክቡር ዕፀ ሣህል፥

አሜን፨

መቅረዝ ዘተዋሕዶ 2005 ዓ.

Report Page