ሜቴክ የሰወረው ሌላ ስምንት ቢሊየን ብር አልተገኘም

ሜቴክ የሰወረው ሌላ ስምንት ቢሊየን ብር አልተገኘም



ሜቴክ ለህዳሴው ግድብና ሌሎች ግንባታዎች 8 ቢሊየን ብር ለንግድ ባንክ ሳይከፍል በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ተያዥነት ሰውሮታል። ገንዘቡ የት ገባ? የሚለውን የሚመልስ አልተገኘም። በጉዳዩ ላይ ያለንን መረጃ አሰናድተናል

ዋዜማ ራዲዮ- ብዙው ነገር የተፈጸመው በ2008 ዓ.ም ነው።የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የህዳሴውን ግድብ ፕሮጀክትና ሌሎች የግንባታ ውል የወሰደባቸው ፕሮጀክቶች የክፍያ አካል የሆነውን ስምንት ቢሊየን ብር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይልና ከሌሎች ውል ሰጪ ተቋማት ይቀበላል።

ይህም ገንዘብ ጥቅም ላይ እንዲውል ከታሰበው ስራ ውስጥ ኮርፖሬሽኑ ለህዳሴ ግድብ የሚሰራቸው የኤሌክትሮ እና ሀይድሮ ሜካኒካል ስራዎች የሚያስፈልጉ ግብአቶች ከውጭ ማስገባት ይገኝበታል።ታድያ በዚህ የኢትዮጵያ ብር ከውጭ እቃ ለማስገባት ተመጣጣኙ የውጭ ምንዛሬ እንዲገኝ ገንዘቡ ለኤልሲ ወይንም ሌተር ኦፍ ክሬዲት መክፈቻ ባንክ መግባት አለበት።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነበር ሌተር ኦፍ ክሬዲት ከፍቶ የሜቴክ እቃዎች ከውጭ እንዲገቡ የውጭ ምንዛሬ የፈቀደው።ንግድ ባንክ ይህን ሲያደርግ ግን ሜቴክ የመንግስት ኮርፖሬሽን ነው ; ገንዘቡንም ስለሚከፍል አገኘዋለሁ በሚል እርግጠኝነት ሜቴክ ለውጭ ምንዛሬው ተመጣጣኙን ብር ማስገባቱን ሳይጠብቅ ኤልሲ ከፍቶ እቃውን ያስመጣለታል።

ነገር ግን ሜቴክ እቃዎቹ ከመጡም በሁዋላ የእቃዎቹን ዋጋ በኢትዮጵያ ብር ማለትም ስምንት ቢሊየን ብሩን ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አላስገባም ወይንም ለማስገባት ፍቃደኛ አልሆነም።

በዚህ ጊዜ ታድያ በበቃሉ ዘለቀ ፕሬዚዳንትነት ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘቤ አልተከፈለኝም በሚል እቃው ለሜቴክ እንዳይሰጥ ያደርጋል።በዚህ መሀል ከፍተኛ ንትርክ ተፈጥሮም እንደነበረ የባንክ ምንጮቻችን ነግረውናል። ገንዘቡ ለንግድ ባንክ መከፈል እንዳለበት በግልጽ እየታወቀ ፣ ሜቴክም ለንግድ ባንክ መከፈል ያለበትን ገንዘብ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል መቀበሉም ግልጽ ሆኖ ሳለ ክፍያው እንዲፈጸም የሚያስገድድ አካል መጥፋቱ ነበር።

Abdulaziz Mohamed

ከዚህ ይልቅ ጉዳዩ ውስጥ የቀድሞው የገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የአሁኑ የገንዘብ ሚኒስቴር እንዲገባበት ነው የተወሰነው ።የግድቡ እና የሌሎች ፕሮጀክቶች እቃዎች መጥተው ስራው ከሚጓተት ሜቴክ ላልከፈለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘብ የገንዘብና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ዋስትና ሆኖ ሜቴክ እቃዎቹን እንዲረከብ ነው የተደረገው።በወቅቱም የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዲኤታ የነበሩት አቶ አብዱልአዚዝ መሀመድ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጻፉት ደብዳቤም ላይ ይህን ብለዋል ;

ሜቴክ ከፍተኛ የሀይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችና የስኳር ማምረቻ ፋብሪካዎችን በመገንባት ሂደት ለኮርፖሬሽኑ የተከፈቱለት ኤሌሲዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሊወራረዱ ባለመቻላቸው ለጉዳዩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ያልተወራረዱ የስምንት ቢሊየን ብር ሰነዶች በኮርፖሬሽኑ ስም በብድር ተመዝግበው እንዲወራረዱ በመንግስት አቅጣጫ የተሰጠ በመሆኑ መስሪያ ቤታችን ዋስትና ሰጥቷል።

ይህም ሆኖ ግን የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የድሞ የሆነበትን ገንዘብ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አልመለሰም። ከባንክ አካባቢ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመውም ይህን ዘገባ እስከሰራንበት ጊዜ ድረስ የስምንት ቢሊየን ብሩ ብድር ተንጠልጥ አልተሰማም።

አቶ አብዱል አዚዝ መሀመድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ሀላፊነት ከመጡ በሁዋላ ለጥቂት ወራትለተያዥነት የፈረሙበትን ደብዳቤ የጻፉለትን ሜቴክን በምክትል ዋና ዳይሬክተርነት መርተዋል።

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እና ከሌሎች ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ የቀድሞው ሜቴክ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይልና ከሌሎች ተቋማት የተከፈለውና መድረሻው ያልታወቀው ስምንት ቢሊየን ብር በዚህ መሀል ተንጠልጥሎ የቆየው ሊሆን እንደሚችል ዋዜማ ራዲዮ መረዳት ችላለች።ነገር ግን መርማሪ ፓሊስ የቀድሞ የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘውን ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ የምርመራውን ውጤት ለፍርድ ቤት ሲያቀርብ በደፈናው ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ገንዘብ የደረሰበት አልታወቀም ከማለት ውጭ ያለው ነገር አልነበረም።

ምንጭ፦ ዋዜማ

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page