"መንግሥት አይወክለኝም ለሚሉ ወገኖች ምርጫ ምላሽ ይሰጣል" ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና

"መንግሥት አይወክለኝም ለሚሉ ወገኖች ምርጫ ምላሽ ይሰጣል" ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና


ከሁለት ሳምንት በፊት በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከፍተኛ አመራሮችና ጄነራሎች መገደላቸው "አገሪቷ ያለችበትን የፖለቲካ ችግር በግልጽ አሳይቷል" ሲሉ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ለቢቢሲ ተናገሩ።

ሕዝብ በመንግሥት ላይ ቅሬታ ካለው፣ መንግሥት እየበደለኝ ነው ወይም እያገለገለኝ አይደለም ብሎ ካመነ እንዲሁም በአገሪቱ ትልቅ ክፍተቶች ካሉ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ለማድረግ የሚነሳሳ ኃይል ሊኖር ይችላል ሲሉ ፕሮፌሰር መረራ ያስረዳሉ።

ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች ተከትሎ በሀይል ለሕዝብ ምላሽ እሰጣለሁ የሚል ቡድን ካለ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሊያደርግ ይችላል በማለትም ያክላሉ።

የሕዝብን ጥያቄ በመፈንቅለ መንግሥት አንመልሳለን ብለው የሚነሱ ሀይሎች ለሚወስዱት እርምጃ በቂ ምክንያት አላቸው ወይስ የላቸውም? የሚለውን መመለስ የሚኖርባቸው ራሳቸው ኃይሎቹ ናቸው ይላሉ።

"በአጠቃላይ የተፈጸመው ተግባር በአገሪቱ ውስጥ ችግር መኖሩን ነው ያሳየን" ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፤ መሰል ተግባር ከባድ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።

ምርጫ እንደ አማራጭ

መሰል ችግሮች መፍትሄ ከሚያገኙባቸው መንገዶች አንዱ ምርጫ ነው የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ፤ "ይህ መንግሥት አይወክለኝም ለሚሉ ወገኖችም ምርጫ ምላሽ ይሰጣል፤ ስለዚህ መፍትሄው ምርጫ ማካሄድ ነው" ይላሉ።

በቀጣይ ዓመት እንዲካሄድ ቀጠሮ የተያዘለት ምርጫ ይዘራም ወይስ ይካሄድ? የሚለው ሀሳብ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሀሳብ ልዩነት ፈጥሯል።

ገሚሱ ምርጫው በተያዘለት ጊዜ መካሄድ ይኖርበታል ያሉ ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ በአገሪቱ የሰላምና የደህንነት ስጋቶች እያሉ ምርጫ ማካሄዱ ትክክል አይደለም ይላሉ።

የደህንነት ስጋት እያለ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም የሚሉት አካላት፤ "ሕዝቡን ማን ያረጋጋ? ሥራዎችን ማን ያከናውን? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ የላቸውም" ይላሉ ፕሮፌሰር መረራ።

"ሕዝቡን አረጋግቶ ወደ ምርጫ የምንሄድበትን መንገድ ስርዓት ማስያዝ ነው እንጂ ፕሮፖጋንዳ መንዛት ብቻ መፍትሄ አይሆንም" ብለዋል።

"መሬት ላይ አለ የሚሉትን ችግር ማን እንዲያስተካክልላቸው ነው የሚጠብቁት?" ሲሉም ፕሮፌሰር መረራ ይጠይቃሉ።

መንግሥት እንደ መንግሥት የሚጠበቅበትን መፈጸም መቻል እንዳለበትና የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሁለት ጫፍ ረግጠው እርስ በእርስ ከመባላት ይልቅ መፍትሔ የሚሆን አጀንዳ ይዘው መሥራት እንዳለባቸውም ያስረዳሉ።

ፕሮፌስር መረራ፤ ከሁሉም በላይ መንግሥት አገራዊ መግባባት ለማምጣት ሕዝባዊ ድጋፍ ካላቸው ፓርቲዎች ጋር ተቀምጦ መወያየት አለበት ይላሉ።

"ሕዝቡ የመረጠው መንግሥት ስልጣን ላይ ሲወጣ ብቻ 'አትወክሉንም' የሚለው ጥያቄ ምላሽ ያገኛል'' የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ፤ በአሁኑ ወቅት እየታዩ ላሉት ችግሮች መፍትሄው ምርጫ ማካሄድ እንደሆነ ይናገራሉ።

ፕሮፌሰር መረራ በሚቀጥለው ዓመት ምርጫ የማይካሄድ ከሆነ አገሪቱ የባሰ ሰላምና መረጋጋት ሊርቃት እንደሚችል ይናገራሉ።

በምርጫ ቦርድ ውስጥ እየታዩ ያሉ ለውጦች እንዲሁም ጠቅላይ ሚንስትሩ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ቁጭ ብለው መነጋገራቸውን እንደ መልካም አጋጣሚ እንደሚመለከቱት የሚናገሩት ፕሮፌሰር መረራ፤ ከዚህ በላይ ግን ለሕዝቡ ተስፋ የሚሰንቁ ነገሮች መሬት ላይ መታየት አለባቸው ይላሉ።

ፕሮፌሰር መረራ ጨምረውም "በኢህአዴግ ውስጥ ያሉት አራቱ ፓርቲዎች ከመደማመጥና አብሮ ከመሥራት ይቅል እርስ በእርሳቸው መጠላለፍ ነው የያዙት ይህም በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው" ይላሉ።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

@tsegabwolde @tikvahethiopia

Report Page